>

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚደንት  የአቶ እስክንድር  ነጋ የፍ/ቤት ውሎ...!!! (ታምሩ ገዳ)

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚደንት  የአቶ እስክንድር  ነጋ የፍ/ቤት ውሎ…!!!

ታምሩ ገዳ

ከሁለት ሳምንት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ሰር የዋሉት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋን በተመለከተ ፖሊስ ምርመራውን ለማጠናቀቅ የጠየቀው ተጨማሪ ቀን ፍርድ ቤት ተፈቅዶለታል።
ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ እስክንድር ነጋ “የብሔርና የሐይማኖት ግጭት እንዲፈጠር ወጣቶችን በማደራጀት ገንዘብና የተለያዩ ድጋፎችን አድርገዋል “የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ጠበቃቸው አቶ ሄኖክ አክሊሉ  ገልጸዋል።
በዚህም” ከፍተኛ መጠን ያለው ውድመት በንብረት ላይ እንዲሁም በሰዎች ህይወትና በአካል ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል” የሚል ክስ በፖሊስ መቅረቡን ጠበቃው ጠቅሰዋል።
ጉዳያቸው በፌደራል የመጀመሪያ አራዳ ምድብ ችሎት የሚታይ ቢሆንም ለደህንነት ሲባል ችሎቱ ልደታ በሚገኘው ፍርድ ቤት እንደተሰየመ የተናገሩት አቶ ሄኖክ፤ ፖሊስ ሃያ ምስክሮችን ማድመጡን እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ማስረጃዎችን እየተመረመረ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ፖሊስ እስካሁን ያከናወናቸውን መረጃ የማሰባሰብና ምርመራ የማካሄድ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አመልክቶ ቀሩኝ የሚላቸው ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ከዚህ ሌላ አቶ እስክንድር ለፍርድ ቤቱ ተፈጽሞብኛል ያሉትን በደል ያቀረቡ ሲሆን፤ ይህም በቁጥጥር ሰር በዋሉበት ዕለት “በፌደራል ፖሊስ አባላት ድብደባ እንደተፈጻመባቸው” እራሳቸውና ጠበቃቸው ለችሎቱ አቤት ብለዋል።
ፍርድ ቤቱም በቀረበው አቤቱታ መሰረት በአቶ አስክንድር ላይ ድብደባ የፈጸሙት የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ ምርመራ እንዲካሄድና እንዲጣራ ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፖሊስ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ያቀረበውን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄን በተመለከተ የአቶ አስክንድር ጠበቆች ፖሊስ ማስረጃ እንዳለው ለችሎቱ መግለጹንና ጠቅላይ አቃቤ ህግም ተከሳሹን ወንጀለኛ የሚያስብላቸው ማስረጃ ማግኘቱን ማመልከታቸው አስረድተዋል።
ስለዚህም እነዚህ ማስረጃዎች ደግሞ በፖሊስ እጅ መኖራቸውን በመጥቀስ ተጨማሪ የጊዜ ገደብ መጠየቅ ተገቢ አይደለም ብለው ለፍርድ ቤቱ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ፍርድ ቤቱ በቀረበው ተቃውሞ ላይ በሰጠው ምላሽ “ምንም እንኳን ፖሊስ ማስረጃ አግኝቻለሁ ቢልም ምርመራው አልቋል ብሎ ስለማያምን ተጨማሪ 13 የምርመራ ቀናት መስጠቱ አስፈላጊ ነው “በማለት ለሐምሌ 22 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ጠበቆች ግን መረጃዎች በፖሊስ እጅ ያሉ በመሆናቸው ምርመራውን በራሱ ለማካሄድ የሚችል በመሆኑ ተጨማሪ ቀን መስጠት ተገቢ አይደለም ብለው ቢከራከሩም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል ሲሉ አቶ ሄኖክ  ተናግረዋል።
የአቶ እስክንድር ነጋ ጠበቃ ጨምረው እንደተናገሩት ደንበኛቸው ቀደም ሲል ታስረውበት ከነበረው የማረፊያ ቦታ ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወራቸውንም  ገልጸዋል።
Filed in: Amharic