>

ንጹህ ዜጋን በዉሸት ክስ ማሰር አንድ የኖቤል ተሸላሚን አይመጥንም  (ግርማ ካሳ)

ንጹህ ዜጋን በዉሸት ክስ ማሰር አንድ የኖቤል ተሸላሚን አይመጥንም

ግርማ ካሳ

እነ አዳነች አበቤ ይሄን ፎቶ አይተው “በአንድ ቢጫ ላስቲክ ቦምብ ይዞ ሲዞር ተገኝቷል” ብለው ደግሞ በእስክንድር ላይ ሌላ ክስ እንዳይመሰርቱ፡፡ይሄ እስክንደር ከ7 አመት እስር በኋላ ከቃሊቲ እስር ቤት ሲወጣ ነው፡፡
እስክንድር ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ዋጋ በመክፈል ፣  ወያኔን በድፍረትና በጀኝነት በመታገሉ፣ በሐሳብ ፣ በእስኪሪፕቶ  እርሱን መቋቋም ስላልቻሉ ነበር ያሰሩት፡፡ በዉሸት ክስ፡፡
አሁን ደግሞ  ኦህዴድ መራሹ መንግስት በሐሳብ ማሸነፍ ስላልቻለ፣ እነ እስክንድር ኦህዴድች የሚሰሩትን ዘረኛና አፓርታይዳዊ አሰራር በማጋለጣቸው፣ ከወያኔ ደብተር በመኮረዥ የፈጠራ ክስ መስርተዉባቸዋል፡፡
አላወቁም እንጂ እስክንድርንና ባልደራስን ወደ ላይ ከፍ እያደረጉ፣ እነርሱን ግን እያዋረዱ፣ ትንሾች መሆናቸውን እያሳዩ ነው፡፡  በመታሰራቸው እነ እስክንድር እያሸነፉ ነው፡፡እነ ዶር አብይ ደግሞ እየተሸነፉ ነው፡፡
ዶር አብይ እስክንድር ነጋን አስሮ በድፍረት ሕዝብ ፊት የመናገር የሞራል ብቃቱን ነው የሚያጣው፡፡ እንደ መለስ ዜናዊ የሰላማዊ ታጋዮች አሳሪ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡
የእስክንደርና የጃዋር ኬዞች  እጅግ በጣም ሃይ ፕሮፍይል ኬዞች ነው የሚሆኑት፡፡ እነ ጃዋር ላይ ከበቂ በላይ መረጃዎች አሉ፡፡ እነ እስክንድር ላይ ግን ከዉሸት መረጃ ውጭ ሌላ መረጃ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ እነርሱም ያውቁታል፤ እኛም እናውቀዋለን፡፡ የቀረቡ መረጃዎችን ውሸትነት ለማየት ከባድ አይሆንም፡፡  በዚህ መልኩ በዉሸት ክስ ሰላማዊ ዜጎች ለማፈን መሞከር ደግሞ  አንድን የኖቤል ተሸላሚ ሰውን የሚመጥን አይደለም፡፡
በመሆኑም ደግሜ እላለሁ፣ ዶር አብይ አህመድ  እጅግ በጣም ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍለውን የፖለቲካ ስህተት ከመስራት ቢቆጠብ ይሻለዋል፡፡ግብጾች በአንድ በኩል፣ ወያኔና ጽንፈኛ ኦነጎች በሌላ በኩል የዶር አብይን አይን ማየት አይፈለጉም፡፡ ለርሱ የተከፈተ ልብ ያለውን የአዲስ አበባ ሕዝብ ባያሳዝን፣ ባያስኮርፍ ይሻለዋል፡፡  እስክንደር ነጋና ባልደራሶች የአዲስ አበባ ልጆች ናቸው፡፡
እስክንድር ለ 7 አመት ታስሮም መንፈሱ አልተሰበረም፡፡ እርሱን  በማሰር እንሰብረዋለን ብለው ኦህዴዶች ካሰቡ መለስ ብለው ጌታቸው አሰፋ ጽ/ቤት ያለውን የእስክንደርን መዝገብ ሄደው ያንብቡ፡፡
ዛሬ እስክንድርን ቢያስሩ አስር ሚሊዮን እስክንደሮች አሉ፡፡ ይሄን የሚጽፈው ግርማ ካሳ  ሌላው ስሙ እስክንድር ነጋ ነው፡፡ እስክንደድር ነጋ በአካል ቢያስሩትም የእስክንድር አጀንዳዎችን፣ ሐሳቦቹን ግን ማስቆም አይችሉም፡፡ እስክንድርንና ባልደራሶችን በማሰር የአዲስ አበቤን ድምጽና የመብት ጥያቄ ማስቆም አይችሉም፡፡
መቼም አዲስ አበባ የአንድ ጎሳ ብቻ አይትሆንም !!!!! መቼም የኦህዴድ ስዉር አዲስ አበባ ኦሮማይዝድ የማድረግ፣ የፊንፌኔ ፕሮጀክት አይሳካም !!!!!!!! መቼም በአዲስ አበባ አፓርታይዳዊ አንድ ጎሳ ብቻ ልዩ ተጠቃሚ ይሁን የሚለው ነገር ተቀባይነት አይኖረውም !!!! አዲስ አበባ የነውሪዎቿ ናት፡፡
Filed in: Amharic