>
2:20 pm - Tuesday June 6, 2023

"አጥፊዎች እንዲጠየቁ፣ የተጎዱ  እንዲቋቋሙ እንሰራለን!!!"  ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

“አጥፊዎች እንዲጠየቁ፣ የተጎዱ  እንዲቋቋሙ እንሰራለን!!!” 

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በተፈጠረ ሁከትንና በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ200 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙ ይታወቃል።
በዚህም ሳቢያ በድርጊቱ ውስጥ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ 5 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕረስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ከእነዚህ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ኃላፊዎችና የፀጥታ አካላት ይገኙበታል።
ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ ስለደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና አያያዝን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል።
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነሩ ዳንኤል (ዶ/ር) ከሁለት ሳምንት በፊት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተከሰተውን ለሰዎች ሞትና ለንብረት ውድመት የሆነውን ክስትት “በጣም አሳዛኝ ነው” በማለት የገለጹት ሲሆን፤ ይህንንም ተከትሎ ኮሚሽኑ የደረሱ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ገልፀዋል።
በመሆኑም የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዓይነት እና የጉዳት መጠን ለይቶ ለማወቅ እንዲሁም አጥፊዎቹ በሕግ እንዲጠየቁ፣ የተጎዱ ሰዎች ደግሞ እንዲካሱና መልሰው እንዲቋቋሙ ለማስቻል የሚረዳ ጥናት ለማካሄድ አንድ ቡድን መቋቋሙን አመልክተዋል።
ከዚህም ባሻገር አሁንም ሙሉ ፀጥታና መረጋጋት ያልሰፈነባቸው አካባቢዎች ላይ ወይም ጉዳቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ፤ ከተፈጠረው ችግር ጋር ምን ያህል ተመጣጣኝ እንደሆነ ለማረጋገጥና ከሁከቱ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች አያያዝ ሕጋዊነትን ለማወቅ ክትትል እያደረጉ እንደሆነ ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር) ለቢቢሲ አብራርተዋል።
ኮሚሽነሩ ከሁከቱ ጋር ተያይዞ መንግሥት የሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ጥናት እያደረጉ እንደሆነ እስካሁን ባላቸው ቅድመ ምልከታና መረጃ መሠረት በአብዛኛው የፀጥታ አስከባሪዎች ሚና ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን፤ የፀጥታ አካላት ባይደርሱ ኖሮ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
የሚቀርበው አብዛኛው ቅሬታም “የፀጥታ አካላት ሕብረሰተቡን ለመጠበቅ በወቅቱ አልደረሱም” የሚሉ እንጂ በፀጥታ አስከባሪዎቹ ጉዳት ደረሰብን የሚሉ አይደሉም ብለዋል።
ይሁን እንጅ አልፎ አልፎ የፀጥታ ኃይሎች ሕግ በማስከበር ሂደት ከሚጠበቀው መስመር በመውጣት የተወሰዱ እርምጃዎች እንደሚኖሩ ግምት መውሰዳቸውን ኮሚሽነር ዳንኤል ተናግረዋል።
የእስረኞች አያያዝ
ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር) ታሳሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማየት ከአንዴም ሁለት ጊዜ ሄደው እንደተመለከቱና እንዳነጋገሩ አስታውሰዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ታሳሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ጀምሮ ድብደባ ማሰቃየት ተፈፅሞባቸዋል የሚል የተሳሳተ መረጃ በስፋት ይሰራጭ ነበር ብለዋል።
በተለይ ወሬው አቶ እስክንድር፣ አቶ ጀዋር እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 35 ሰዎች መታሰራቸው ይፋ መሆኑ ከታወቀ በኋላ በነበረው ጊዜ በስፋት ይናፈስ እንደነበር ያስረዳሉ።
ሁሉም ታስረው የነበሩት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስር ቤት ውስጥ እንደነበር የሚገልፁት ኮሚሽነሩ፤ ከአቶ እስክንድር ነጋ እና ኦኤምኤን ድረ ገፅ ላይ እንደሚሰሩ ከገለፁላቸው አቶ አህመድ ጠሃ በስተቀር ሁሉም እንዲህ ዓይነት አቤቱታ እንዳላሰሙ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ታሳሪዎቹን በጎበኟቸው ወቅትም “አቶ ጀዋር መሐመድንና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ አንዳንድ ታሳሪዎች የእስር አያያዛቸው ደህና እንደሆነ አረጋግጠውልናል” ብለዋል።
“አቶ እስክንድር ነጋና አቶ አህመድ ጣሃ የተባሉት ታሳሪ ግን በእስር ወቅት ድብደባ እንደደረሰባቸው ገልፀውልናል” የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ በጎበኟቸው ጊዜ በመልካም አካላዊ ጤንነት ላይ ነበሩ ብለዋል።
አቶ እስክንድር በፖሊስ ድብደባ እንደፈፀመበት መግለፁን ተናገረው፤ ጉዳዩን ከፖሊስም ለማጣራት በሞከሩበት ወቅት በእስር ወቅት ‘ፍጥጫ’ ተፈጥሮ እንደነበር መስማታቸውን ገልፀዋል። ጉዳዩ እንዲጣራና ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ ምክረ ሃሳብ መስጠታቸውንም ኮሚሽነር ዳንኤል ( ዶ/ር) አክለዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ ታሳሪዎችን ለመጎብኘት በሄዱበት ወቅትም ከዚያ በኋላ አቶ እስክንድር ምንም አይነት ድብደባ እንዳልደረሰባቸው እንዳረጋገጡላቸው አስረድተዋል።
የቀረቡ ሌሎች ቅሬታዎች ምንድን ናቸው?
ከቤተሰብ ጋር ለመገናኘት አለማቻል ቀዳሚው ቅሬታ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነር ዳንኤል ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ ከቤተሰብ ጋር መገናኘትና ምግብና ልብስ መቀበል ታግዶ ስለነበር እስረኞቹ ይህንን እንደ ቅሬታ አቅርበዋል ብለዋል።
ይህንን በሚመለከትም ከእስር ቤቱ አስተዳደር ጋር መነጋገራቸውንና በተወሰነ መጠን መሻሻሉን እንደሚያውቁ ገልፀዋል።
ነገር ግን ይህ ችግሩ በአዲሶቹ እስረኞች ላይ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለው የታሰሩት ላይም ተግባራዊ የተደረገና ከወረርሽኙ መከላከል ጋር ተያይዞ የተወሰደው እርምጃ ያስከተለው ውጤት ነው ብለዋል።
ያሉበት የማይታወቁ እስረኞች ስለመኖራቸው በተመለከተም፤ በተለይ በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ስር የታሰሩ የኦፌኮ አባላት፣ የኦነግ አመራሮች እና ሌሎች አንዳንድ እስረኞች ከቤተሰባቸው ጋር ቶሎ የሚገናኙበት እድል ባለመፈጠሩ “የታሰሩበትን አናውቅም” የሚል አቤቱታ እንደቀረበላቸው የገለፁት ኮሚሽነሩ፤ በጉዳዩ ላይ ክትትል እያደረጉ እንደሆነና በአፋጣኝ መስተካከል እንደሚገባው አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨመሪም “አቃቤ ሕግና ፖሊስ እስረኞችን በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት መልካም ቢሆንም፤ አሁንም በ48 ሰዓታት ያልቀረቡ እስረኞች አሉ” ብለዋል ኮሚሽነር ዳንኤል ።
ሁሉንም እስር ቤቶችና እስረኞችን ጎብኝተው ያልጨረሱ ቢሆንም በፌደራልና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ያሉ ታሳሪዎችን ግን ማየታቸውን ገልፀዋል።
ጭሮ፣ ቡራዩ እና አርሲ ነገሌ እንዲሁም ዴራ በርካታ እስረኞች ስለመኖራቸው መረጃ እንደደረሳቸው የገለፁት ኮሚሽነር ዳንኤል፤ ክትትል ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ኮቪድ-19 እና የእስረኞች ቁጥር መበራከት
በሺህ የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ባሉበት ሁኔታ የወቅቱ አሳሳቢ የጤና ችግርን ጉዳይ አብሮ የሚነሳ ነገር ነው። ይህንንም ስጋት በተመለከተ ኮሚሽነሩ “ፖሊስና አቃቤ ሕግ እንዳስታወቀው ምርመራው እየተፋጠነ ሲሄድ የሚለቀቁ ታሳሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ” የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ።
ከዚህም ባሻገር በእስር ቤቶች ውስጥ አቅም በፈቀደ መጠን ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን መመልከታቸውን አክለዋል።
ከእነዚህም ጥንቃቄዎች መካከልም፤ አልፎ አልፎ በሚደረግ የናሙና መረጣም ቢሆን የኮሮናቫይረስ ምርመራ፤ አዲስ ታሳሪዎች ከእስረኞች ጋር ከመቀላቀላቸው በፊት የሙቀት ልኬት፤ ምልክት አለባቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ካሉም ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እንደሚደረግ መታዘባቸውን ተናግረዋል።
“የምግብና የልብስ አለመግባቱ ዓላማም የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት ከተወሰዱ እርምጃዎች አንዱ ነው፤ የአቅም ውስንነት ስላለ በሚፈለገው መልኩ የተሟላ ነው ማለት ግን አይቻልም ” ብለዋል።
የመገናኛ ብዙሃን መዘጋትና የጋዜጠኞች መታሰር
ይህንን በተመለከተ መንግሥት “ሕግ ጥሰዋል” በሚል በእነዚህ አካላት ላይ ክስ ማቅረቡ በማስታወስ፤ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት የምርመራውን ውጤት መጠበቅ ግድ ይላል ብለዋል ኮሚሽነሩ።
“በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ቀውስ ሚዲያ ሚና አልነበረውም ማለት አይቻልም፤ ሚዲያ በዚህ ውስጥ ሚና የነበረው መሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም” የሚሉት ኮሚሽነር ዳንኤል፤ የትኞቹ ሚዲያዎች ምን ዓይነት ሚና ነበራቸው የሚለው በማስረጃ የሚረጋገጥ መሆኑን ገልፀዋል።
ነገር ግን “በምርመራው ሂደት ጣልቃ ባንገባም ሂደቱ ምን ያህል ሕጋዊና ፍትሃዊ መሆኑን ለማረጋጋጥ መታዘባችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
Filed in: Amharic