>

ወንጀልን በትክክለኛ በስሙ ሳንጠራ ፍትሕ አይገኝም፤ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ነው!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ወንጀልን በትክክለኛ በስሙ ሳንጠራ ፍትሕ አይገኝም፤ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ነው!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ሰሞኑን አርቲስት እና የመብት ተሟጋች ታማኝ በየነ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ስለተፈጸሙት በዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ውይይት አድርገን ነበር። በዛ አጭር ውይይት ላይ የአርቲስት አጫሉን ግድያ ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተፈጸፈው ጭፍጨፋ ዘር ተኮር (Genocide) ነው በሚል አስረግጠን ተናግረን ነበር። ለዛም ዝርዝር ማስረጃዎችን ከአርባ ጉጉ፣ በደኖ እና ወተር ጭፍጨፋዎች አንስቶ እስከ ትላንቱ ድረስ የተፈጸሙትን ጥቃቶች በምን ምክንያት ዘር ተኮር ወንጀል ሊፈረጁ እንደሚችሉ ለማስረዳት ሞክረናል።
ይህን ውይይት ተከትሎ አስገራሚ ሃሳቦች እና ወቀሳዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲሰነዘሩብን አድምጫለሁ። ገሚሱ ስለወንጀሎቹ ስያሜ፣ መስፈርቶቹ እና የሕግ ትርጓሚ ግንዛቤ ካለመኖር ይመስላል። ቀሪዎቹ ወቃሾች ደግሞ አስመሳይነት እና ፖለቲካዊ መሽኮርመም ብለው ይሻላል። የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ነገሮችን አዛብቶ መረዳት ይመስላል። በዛው ልክ አይናቸውን በጨው አጥበው የክህደት (denial) መከራከሪያ የሚያነሱም አይቻለሁ። ለማንኛውም እኔና ታማኝ በየነ ከሌሎች ሁለት እንግዶች ጋይ ያደረግነውን አጭር ውይይት ላልሰማችሁትም ሆነ ሰምታችሁ ነገሩ ብዥታ ለፈጠረባችሁ ሰዎች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተፈጸሙት ጭፍጨፋዎች ዘር ተኮር መሆናቸውን ባጭሩ ላስረዳ።
ከዛ በፊት ትንሽ ስለ ዘር ተኮር ጥቃት ወይም Genocide የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረን ትንሽ ልግለጽ። ይህ የዘር ተኮር ጭፍጨፋ አለም አቀፍ ወንጀል ነው። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በDecember 9, 1948, የተባበሩት መንግስታት አጽድቆ ባወጣው the Convention on the Prevention and Punishment of tGhe Crime of Genocide የስምምነት ሰነድ በዘር ላይ ያነጣጠረው ጥቃት አለም አቀፍ ወንጀል ተደርጎ ተደንግጓል። በዚህ ሰነድ ላይም በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል። በዚህ ሰነድ አንቀጽ ሁለት ላይ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ወይም genocide ማለት አንድን በብሔሩ፣ በኃይማኖቱ፣ በዘሩ፣ በቀለሙ ወይም በሌላ በማንነቱ ተለይቶ የታወቀን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ በዛ ማህበረሰብ አባላት ላይ ግድያ፣ ከፍተኛ የአካል ማጉደል፣ ወይም የአዕምሮ ጉዳት ማድረስ፣ ሆን ብሎ በዛ በተለየ ሕዝብ ሕይወት ላይ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ተግባራትን በመፈጸም፣ ያ ህዝብ እንዳይዋለድ እና ቁጥሩ እንዳይጨምር ታስቦ ወልደትን የሚገድብ እርምጃ ሲፈጸም እና የዛን ማህበረሰብ ሕጻናት ልጆች በጉልበት በመንጠቅ ለሌላ ማህበረሰብ አሳልፎ መስጠትን እንደሚጨምር ይገልጻል። ከእኔ የግርድፍ ትርጓሜ ባለፈ እንግሊዘኛውን ማንበብ ለምትፈልጉ እነሆ፤
Genocide means any of the following acts committed with intent to destroy, in whole or in part, a national, ethnical, racial or religious group, as such:
(a) Killing members of the group;
(b) Causing serious bodily or mental harm to members of the group;
(c) Deliberately inflicting on the group conditions of life calculated to bring about its physical destruction in whole or in part;
(d) Imposing measures intended to prevent births within the group;
(e) Forcibly transferring children of the group to another group.
በዚሁ ድንጋጌ አንቀጽ ፫ ላይም በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቁት ተግባራትን ይዘረዝራል። እነሱም ከላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወይም genocide ድርጊት የፈጸመ፣ ወንጀሉ እንዲፈጸም የዶለተ (Conspiracy to commit genocide)፣ በቀጥታ እና በአደባባይ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዲፈጸም ያነሳሳ እና ቅስቀሳ ያደረገ (Direct and public incitement to commit genocide); የዘር ማጥፋቱን ወንጀል ለመፈጸም ሙከራ ያደረገ (Attempt to commit genocide); የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም በማናቸውም መልኩ ተሳትፎ ያደረገ (Complicity in genocide).
እነዚህ መነሻ ሃሳቦች ይዘን እስኪ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሩቁን ጊዜ ትተን ትላንት ከአጫሉ ግድያ ማግስት የተፈጸሙትን ጥቃቶች እንፈትሽ።
፩ኛ/ በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉም ሰው እንዲረዳው የሚያስፈልገው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲባል ብሔርን ወይም ጎሳን ብቻ መሰረት ያደረገ አይደልም። በኃይማኖት ወይም በሌሎች የልዩነት መሰረቶችም ላይ ያተኮረ ሊሆን ይችላል። የግድ የአንድ ብሔረሰብ ሰዎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ መሆን የለበትም። ከዚህ አንጻር ሰሞኑን በኦሮሚያ የተፈጸመው ጥቃት በአንዳንድ አካባቢዎች በአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ ብቻ አነጣጥሯል። በሌላ አካባቢዎች ኦሮሞ ባልሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች (አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ሌሎችም) ላይ አነጣጥሯል። በተወሰኑ ስፍራዎች ደግሞ ክርስቲያን (የኦሮሞ ክርቲያኖችን ጨምሮ) በሆኑ ሰዎች ላይ አነጣጥሯል። ስለዚህ ጥቃቱ የብሔር እና የኃይማኖት ይዘት ነበረው።
፪ኛ/ የአጥቂዎቹ ማንነት በተመለከተ የሚነሳ ክርክር አለ። በዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ የሚታየው የተጠቂው ዘር እና የአጥቂው ሃሳብ እንጂ የአጥቂው ማንነት አይደለም። ጥቃቱን የሚፈጽመው ማንም ሊሆን ይችላል። የአንድ ዘር ወይም ብሔር ወይም ኃይማኖት አባል ወይም ከተለያየ ዘር እና ኃይማኖት የተወጣጡ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ዋናው ነገር አጥቂው ጥቃቱን ሲፈጽም ዋና መነሻ ሃሳቡ እና አላማው ምንድን ነው የሚለው ነው። የአጥቂው ቡድን ማንነቱ ሳይሆን ሃሳቡ ነው የሚታየው። በተጨማሪም የዘር እልቂት ጥቃት ተፈጽሟል ሲባል የግድ አንድ ዘር በሙሉ ተነስቶ ሌላን ዘር አጠፋ ማለት አይደለም። ይህንን ብዙ ሰዎች ካለማወቅም ይሁን ሆን ብለው ሲያምታቱት ይስተዋላል። በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ በተፈጸሙትም ሆነ አሁን በተፈጸመው ጥቃት ተሳታፊዎቹ፣ አቀነባባሪዎቹ እና ዋናውን ድርጊት የፈጸሙት ሰዎች የኦሮሞ አክራሪ ብሔረተኞች መሆናቸው ግልጽ እና የሚያከራክር አይደለም። እነዚህ ሰዎች የተደራጁ ቡድኖች ናቸው እንጂ የኦሮሞን ሕዝብ ወይም አንድን ኃይማኖት የሚወክሉ ሰዎች አይደሉም። ስለዚህ ድርጊቱ የዘር ጥቃት ለመባል የአጥቂ ወገኖች የአንድ ብሔር አባላት ሰዎች በጠቅላላ ተሰባስበው የፈጸሙት ነው ወይም አንድ ብሔር ነው ሌላውን ያጠቃው ለማለት አይደለም ወይም እንዲህ ያለ ትርጓሜ አይሰጥም። ዋናው ነገር ፈጻሚዎቹ አንድን ዘር ወይም ኃይማንት ለማጥቃት አስበው የተደራጁ ቡድኖች መሆናቸው ነው። ይሄ ደግሞ በአደባባይ ጭምር ነፍጠኛን ግደሉ፣ ክልሉን ከሌሎች ብሄሮች አጽዱ፣ ክርስቲያኖችን አስወግዱ የሚሉ ቅስቀሳዎች በአደባባይ፣ በመገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ድህረ ገጾች ይካሄዱ እንደነበር እና ድርጊቱም በዚሁ አግባብ መፈጸሙ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው። በመንግስትም ተደጋግሞ ተገልጿል።
፫ኛ/ ሌላው በክልሉ ውስጥ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ዘር ተኮር መሆኑን የሚያሳዩት ከቅድመ ዝግጅት አንስቶ ድርጊቱ በተፈጸመባቸው ወቅቶች የታዩና በበቂ ማስረጃ የሚደገጉ ተጨባጭ ኩነቶች ናቸው። እነዚህም፤
+ ክፍፍል እና ፈረጃ (classification and symbolization) አገሪቷ ውስጥ ለሰላሳ አመታት የቆየው የዘር ተኮር ፖለቲካ ሕዝቡን በማንነቱ እንዲከፋፈል አድርጎታል። በተጨማሪም በተለያዩ ሚዲያዎችም ሆነ በተደጋጋሚ በመንግስት አካላትም አንድን ማህበረሰብ ነፍጠኛ፣ መጤ፣ ወራሪ፣ ጡት ቆራጭ የሚሉ እና ሌሎች ስያሜዎችን እየሰጡ ጥላቻ በዛ ማህበረሰብ ላይ እንዲፈጠር ተደርጓል። ይህንን ኦቦ ለማ መገርሳ በአንድ መድረክ ንግግራቸው ላይ በደንብ አድርገው ከነስጋታቸው ገልጸውታል፤
+  ከሰውነት ተራ ማውጣት ወይም ማበደን (dehumanization)፤ ይህ ነገር በሁለት መልኩ ተፈጽሟል። አንደኛው ለታዳጊ ወጣቶች እና ተማሪዎች አንድን ማህበረሰብ እንደ ሰው  እንዳይቆጥሩ እና ጭራቅ አድርገው እንዲስሉ ብዙ ሥራ ተሰርቷል። ነፍጠጫ የሚሉትን የአማራውን ሕዝብ በታሪክ አገሪቱን ካስተዳደሩ ገዢዎች ጋር በማቆራኘት እራፊ ልብስ እና ቁራጭ ዳቦ የጠረረበትን ድሃ የአማራ ገበሬ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ በዝባዥ፣ ጡት ቆራጭ፣ መሬት ወራሪ፣ ዘራፊ እና አፈናቃይ አድርገው እንዲያስቡ በመንግስት ደረጃ በተዋቀሩ ሚዲያዎችና ሹማምንት ሳይቀር ብዙ ቅስቀሳ እና ጥላቻ ሲሰበክ ቆይቷል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እነዚህን በጥላቻ ያነጿቸውን ወጣቶች ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል እንደ ጠላት አድርገው እንዲቆጥሩ እና የጭካኔ እርምጃ በሌሎች ላይ እንዲወስዱ ወደ አውሬነት ባህሪ ቀይረዋቸዋል። በዚህም ሳቢያ በዚሁ ሰሞን በእኛው ዘመን ወጣቶች ጡት ቆርጠዋል፣ ቆዳ ገፈዋል፣ ሰውነት ቆራርጠው ገድለዋል፣ ሙሉ ቤተሰብ አርደው ከነቤታቸው በእሳት አጋይተዋል።
+ ለጥቃት መደራጀት (organization)፤ ይህ የዘር ተኮር ጭፍጨፋ ለመፈጸም የተደራጀ ቅስቀሳ እና ዝግጅት ተካሂዷል። በዚህም ላይ የክልል የመንግስት አካላት፣ የታጠቁ አማጺያን እንደ ኦነግ ሽኔ አይነት፣ በቄሮ ስም የተደራጁ ወጣቶች፣ እንደ OMN ያሉ ሚዲያዎች እና ሌሎች አካላትም በተቀናጀ እና በተደራጀ መልኩ ተሳትፎ አድርገዋል። ለዚህም በመንግስት ከተገለጹት ማስረጃዎች ባለፈ እጅግ በርካታ መረጃዎች ተገኝተዋል።
+ ሌላው አብሮ መታየት ያለበት ፍሬ ጉዳይ ለሰላሳ አመት የተዘራው የዘር ተኮር ልዩነት ባለፉት ሁሉት እና ሦስት አመታት አፍጦ ወጥቶ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይቀር በግልጽ መነጣጠል እና መፈራረጅ (ethnic polarization) ሲካሄድ ቆይቷል። በአንዳንድ ቦታዎችም ዘር ተኮር ግጭቶች ከመከሰትም አልፎ ዘር ተኮር አፈናዎች ተካሂደዋል። የደንቢዶሎ ተማሪዎች አፈና ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ከዛም አልፎ ቀደም ሲል ከቡሬ ሆራ ዩንቨርሲቲ ከሁለት መቶ በላይ የአማራ ተማሪዎች በተለየ ሁኔታ ተነጥለው የተባረሩበት እና ባርዳር ሜዳ ላይ የፈሰሱበት ክስተት፣ በአማራ ክልልም ባሉ ዩንቨርሲቲዎች እንዲሁ የኦሮሞ ብሔር ተማሪዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መፈጸማቸው የዚህ ማሳያ ነው።
+ ይህ ዘር ተኮር ጥቃት ድንገት የፈነዳ ክስተት ሳይሆን ብዙ ዝግጅት የተደረገበት እና በአካባቢው ባሉ የመንግስት አካላትም ጭምር የተደገፈ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ባለሥልጣናቱ አንዳንድ ቦታ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበሩ። አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ በዝምታ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። ይህ አይነቱ ነገር በመንግስት አካላት መፈጸሙ አይገርምም። ምክንያቱም የክልሉ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ሽመልስም ሆኑ ሌሎች ባለስልጣናት በየመድረኩ ነፍጠኛን ሰብረናል ሲሉ ከታች ያለው ካድሬ እና ወጣቱ ነገሩን የሚረዳበት መንጋድ ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። እነሱ ሰብረነዋል ያሉትን ነፍጠኛ በOMN  እና በአንዳንድ የኦሮሞ አክራሪ ፖለቲከኞች ገና ያልተሰበረ ነፍጠኛ ከጎረቤትህ አለ ሲሉት ወጣቱ ያንን የተፈረጀ ሰው ሊሰብር፣ ሊያጠፋ እና ሊገድል ቢነሳ ምን ይደንቃል? ብዙ ወጣቶች በመንግስት ተሿሚዎች እና በሚከተሏቸው የፖለቲካ መሪዎች የተፈረጀን እና የተኮነን ሰው መግደል እና ንብረቱን ማቃጠል እንደ ተፈቀደና ትክክለኛ እርምጃ (legitimate action) አድርገው ቆጥረውታል።
+ የመጨረሻው ሃሳብ እውነታን መካድ ወይም አለመቀበል ወይም እውነታውን ላለማየት እና ላለመናገር እራስን ማታለል (denial) ነው። ይሄንን አይነት ነገር በመንግስት እካላት፣ በድርግት ፈጻሚዎቹ ወገን በቆሙ ሰዎች እና አብሮ ለመኖር፣ ለመቻላል፣ ቂም እና በቀልን ለማስቀረት እውነታውን ከመናገር መቆጠብ ወይም እንዳላዩ ሆኖ ማለፍ ወይም ወንጀሉን በሌላ ስም ብንጠራው ይሻላሉ በሚሉ ሰዎች የሚንጸባረቅ ሙግት ነው። አጥቂው ማን እንደሆነ ይታወቃል፣ የአጥቂው ቡድን አላማ (intention) ግልጽ እና በዘር ላይ ያነጣጠረ መሆኑ እራሱ አድራጊው ሳያፈር በአደባባይ ይናገራል፣ መሬት ላይ የተፈጸመውን ድርጊት በዘር ላይ ያነጣጠረ መሆኑ በበቂ ማስረጃ ይገለጻል፣ አንዳንድ ለህሊናቸው ያደሩ የመንግስት ተሿሚዎችም እውነታውን ይናገራሉ ነገር ግን ድርጊቱን እና ወንጀሉን የዘር ማጥፋት ብሎ መሰየም በአገሪቱ ፖለቲካ እና የወደፊት መስተጋብሮች ውስጥ የሚያሳድረውን ነገር ከወዲሁ በማስላት አይ ሌላ የዳሞ ስም እንስጠው የሚል እጅግ ደካማ የሆነ መሟገቻ ይቀርባል። ይሄ አይነቱ አካሄድ ኢትዮጵያን ከዘር ተኮር ጥቃት የሚታደጋቢ ቢሆን ኖሮ ከአርባ ጉጉ፣ ከበደኖ እና ከአርሲው ጭፍጨፋ በኋላ የተከሰቱት ተመሳሳይ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች ባልተፈጸሙ ነበር።
ሃሳቤን ለማጠቃለል ያህል አዎ ደግሜ ደጋግሜ እናገራለሁ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እኩይ እና በብሔር ፖለቲካ በሰከሩ ጥቂት አክራሪ ቡድኖች በተቀነባበረ መልኩ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ተደጋግሞ የዘር ተኮር ጭፍጨፋ ተፈጽሟል። ጭፍጨፋው የዘር ተኮር ነው ለመባል በሺዎች ወይም በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው መታረድ የለበትም። ሕጉም ይህን እንደ መስፈርት አያስቀምጥም። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ባይታረዱም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ከቂያቸው ተፈናቅለው እና ይሄ የእናንተ ክልል አይደለም ተብለው ተባረዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ለዚህም ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ።
መፍትሔ፤ መንግስት በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ያላቸውን ሰዎች ለፍርድ የማቅረቡ ሥራ የሚበረታታ እና የሚደገፍ ነው፡፡ ይሁንና ይህ ድርጊት በየስድስት ወሩ እየተቀሰቀሰ የንጹሃን ዜጎች ደም በየሜዳው የሚፈስበት ክስተት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊባበቃ ይገባዋል። በመሆኑም ከችግሩ ስፋት፣ ጥልቀት እና ውስብስብነት አንጻር ይህ ዘር ላይ ያተኮረ ጥቃት ለአቃቤ ሕግ እና ለፖሊስ ምርመራ ብቻ የሚተው መሆን የለበትም። እነዚህ ጥቃቶች ትኩረት ሰጥቶ የሚያጠራ፣ የሚመረምር እና የመፍትሄ ሃሳብ የሚያመነጭ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ሊቋቋም እና ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከሚመሩት የሰብአዊ መብት ተቋም ጋር አብሮ በጋራ እንዲሰራ መደረግ አለበት። የችግሩ ምንጭ እና የአደጋውን መጠን በቅጡ አጥንቶ አጥፊዎቹንም ለፍርድ የማቅረቡ ሥራ ለይምሰል ሳይሆን በማያዳግም መልኩ ማስተማሪያም እንዲሆን ይረዳል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ጥቃት በስሙ ጠርተን እናውግዝ!

Filed in: Amharic