>
11:14 am - Thursday August 18, 2022

አገዛዝን መደገፍ ማለት ምን ማለት ነው? (ከይኄይስ እውነቱ)

አገዛዝን መደገፍ ማለት ምን ማለት ነው?

ከይኄይስ እውነቱ


መቼሽ ልማድ ሆኖብን መንግሥት እንላለን እንጂ ራሱን በጉልበት ሰይሞ በቆመጥና በመጨቆኛ ሕግ የሚገዛ ቡድን ዋኖቻችን እንዳስተማሩን ትክክለኛ መጠሪያው አገዛዝ ነው፡፡ በዚህ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እየተለመደ የመጣና ካለማስተዋል የገነነ ንግግር ‹‹መንግሥትን ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን መደገፍ›› የሚለው ነው፡፡ 

አገዛዙን ለምንድን ነው የምንደግፈው? አገዛዝ እኮ ነው፤ሕዝብ ሳይወድና ሳይፈቅድ በጉልበቱ ሥልጣን የያዘ አካል፡፡ ያውም ዘረኝነት የነገሠበት፤ ንቅዘትና ቅጥፈት የሠለጠነበት፤ ሽብርና ሥርዓተ አልበኝነት የሰፈነበት፤ የሕዝብን መሥዋዕትነት ከንቱ ያደረገ፤ ለመንግሥትነት ያልበቃና ክሽፈትን ገንዘቡ ያደረገ፡፡ 

አገር በእውነት፣ በዕውቀት፣ በቅንነት፣ በሕግ የበላይነት፣ ዜጎችን በእኩል ዓይን በማየት፣ ከሁሉም በላይ በሥራ እንጂ ከአገር ቤት እስከ ውጩ ዓለም በሚያሠማሩት አድር ባይ ቲፎዞ አማካይነት አይመራም፡፡

መንግሥት በትክክለኛው ትርጕሙ ቢኖረን እንኳ የቆመበትን መደበኛ ተግባር በማከናወኑና ህልው የሆነበትን ዓላማ በመፈጸሙ ማወደስ አይጠበቅብንም፡፡ ሥራው ነዋ!!! የየትኛው አገር ሕዝብ ነው እንዲህ ዓይነት ገልቱነት የሚነካካው፡፡ ይህን÷ይህን አከናውናለሁ ብሎ ቃል ገብቶ ምሎ ተገዝቶ ቧግቶ ለምኖ ነው እኮ ወደ ሥልጣን የመጣው/የሚመጣው በትክክለኛው የዴሞክራሲ መንገድ ከመጣ፡፡ ይሄ ንፍገት አይደለም፡፡ በዓለማችን ዴሞክራሲን በአንፃራዊነት አስፍነዋል የሚባሉ መንግሥታት እንኳን መደበኛ ሥራቸውን ባንፃራዊነት እንጂ በተሟላ ሁናቴ የሚወጡ የሉም፡፡ ሊኖሩም አይችሉም፡፡ በመንግሥታት ዘንድ እንኳን ትሩፋት (ከታዘዘው ወይ በሕግ ከሚጠበቅበት አልፎ የላቀ በጎ ተግባራት ማከናውን) የትእዛዙን/የሕጉን በቅጡ አይወጡም፡፡ 

በጭፍን ስሜታዊነት (በጐሣና በእምነት መመሳሰል፤ ያልተገባ ጥቅም/ፍርፋሪ በማግኘት፤ ከነውር/ወንጀላቸው ከለላ ለማግኘት) ሲያጠፋ ሲበድል ጭምር መደገፍ አለብን የሚሉ ከንቱዎችን ትተን ከቅንነት በመነጨ እንደግፈው እናመስግነው የሚሉ አንዳንድ ወገኖችን ምክንያት ስመረምር አገዛዝ በመሆኑና ባሕርይው ለጥፋት ቅርብ በመሆኑ ከብልግናው እንታደገው እንደሆነ እና በጎ ተግባራትንም ካከናወነ ለማበረታታት በሚል ተስፋ ይመስለኛል፡፡ አንድም በማያቋርጥ የአገዛዞች ጭቆና ውስጥ የኖርን ማኅበረሰቦች በመሆናችን ከፍራቻ በመነጨ ወይም የማባበልም መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡

የሉዐላዊነት፣ ብሔራዊ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት ባጠቃላይ የዜጎችን በሙሉ ትብብር የሚጠይቅ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ለአገዛዞች ሥልጣን ማራዘሚያና ለፕሮፓጋንዳቸው መሣሪያ ለመሆን በትንሹም በትልቁም የራስ ሳያንስ ሌሎችንም አገዛዙን ካልደገፋችሁ ማለት ከንቱነትና የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ በተለይም የጐሣ ፖለቲካ የአገር ህልውናን እየተፈታተነ ባለበት አገር ‹ድጋፍ› የሚባለው ዋና መሠረቱ ጐሣ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

አንዳንዶች አገዛዙን ወይም የአገዛዙን አለቃ አለማወደስ ‹ለውጡን› የማደናቀፍ ተግባር አድርገው ይወስዳሉ፡፡ የትኛው ለውጥ? ስድስት ወራት ሳይሞላው በጅምር የቀረውን? ሽብርተኞችን ያነገሠውን? ዜጋውን ባገሩ ባይተዋር ያደረገውን? ዜጎችን በጐሣና በሃይማኖት ማንነታቸው ያስጨፈጨፈውን? ንጹሐንን የሚያሳድደውን? አገር አጥፊውን የወያኔ ‹ሰነድ› አትንኩብኝ የሚለውን? በአገዛዙ አለቃ ጭምር ለዘር ፍጅት ምክንያት የሆነው የተሳሳተ የጐሣ ጭቆና ትርክት የተያዘበትን? ኧረ ወዲያ!!!

መጀመሪያውም መጨረሻውም አንተ ነህ፤ ያለአንተ አገር ውላ አታድርም የሚለው ግብዝነት ለአገርም ለአገዛዙም አይጠቅምም፡፡ የአገዛዙ አለቃ በዚህ ደዌ የተያዘ ይመስለኛል፡፡ ውዳሴ ከንቱ እንጂ ተገቢ ምስጋናም አይደለም፡፡ ሰሞኑን በውጩ ዓለም በተጠሩ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ዜጎች በጐሣ ማንነታቸውና በሃይማኖታቸው የደረሰባቸውን የጅምላ ፍጅት ወደጎን አድርጎ አገዛዙን ማወደሻ እናድርገው በሚል የታየው መከፋፈል እጅግ አሳፋሪና አንዳንድ የዳያስጶራው አባላትን አድሮ ቃሪያነትና አድርባይነት ገሃድ ያወጣ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ወያኔ ትግሬን የተቃወሙበት መሠረታዊ ምክንያት ምን ይሆን? በጐሣ ከተደራጁት አሸባሪዎች ልዩነታቸው ምንድን ነው?

በተቃራኒው (የሚያዳምጥ ከሆነ) ለመንግሥትም ሆነ ለአገዛዝ የሚጠቅመው የአገርን አንድነትና ሉዐላዊነት፣ የሕዝብን ደኅንነትና ዕድገት ማዕከል ያደረገ ትችት፣ ነቀፌታና ምክር ነው፡፡ በተለይም ዕውቀትና የሕይወት ልምድ ከጠገቡቱ፣ የአገራቸውና የሕዝባቸው ጉዳይ እንቅልፍ ከሚነሳቸው፡፡ ምክርና ትችቱ ለማረም ለማሻሻል ስለሚረዳ እኔ ድጋፍ የምለው ይህንን ነው፡፡ ይልቁንስ ድጋፋችንን የዘር ፍጅት ለደረሰበት፣ ቤት ንብረቱ በሽብርተኞች ለጠፋበት ወገናችን እናድርግ፡፡ ይህ ውዳሴ ከንቱ የሌለበት በምድርም ለአብሮነታችን መሠረት÷ በሰማይም የጽድቅ መንገድ እንደሆነ አምናለሁ፡፡

Filed in: Amharic