>

አፄ ምኒልክንና አማራን መሳደብና ማዋረድ - የዘመናችን ፖለቲካ የይለፍ ቃል! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

አፄ ምኒልክንና አማራን መሳደብና ማዋረድ – የዘመናችን ፖለቲካ የይለፍ ቃል!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


በተለይ ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ ያለውን የሀገራችንን ፖለቲካ በጥልቀትም ሆነ በግርድፉ ለሚመለከት ታዛቢ በዚሁ በተግማማው ፖለቲካችን ውስጥ ለይስሙላም ቢሆን “ኢትዮጵያ” እየተባለች በምትጠራው ሀገራችን ግዘፍ ነስቶ የምናየው ትልቅ ነገር በፓርቲዎችና ድርጅቶች ማኒፌስቶና በአቋም ደረጃም ጭምር አማራን ከኢትዮጵያ ጋር ደርቦ መጥላት፣ መሳደብና ማንቋሸሽ ነው፡፡ ይህን ፋሽን ያልተከተለ ፖለቲከኛ የሀገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ አድባር አትቀበለውም (ይመስለኛል)፡፡

ይህን እንድል በሩን ወለል አድርጎ የከፈተልኝ አንድ በፍጹም ያልጠበቅሁት ሰሞነኛ ጉዳይ ነው – በጣም እወደውና እንዲቀናው እመኝለት እጸልይለትም ከነበረ ብላቴና የወጣ አስጸያፊ ቃል ፖለቲካን በጥቅሉ ይበልጥ አምርሬ እንድጠየፈው ማድረጉን የምገልጽላችሁ በከፍኛ ሀዘን ነው፡፡ 

መሬት ትቅለለውና ፀረ-ኢትዮጵያው መለስ ዜናዊ አንድ ወቅት “የአማራ ተረትና የሶማሌ በጀት ነው የበጠበጠኝ” ብሎ እንደቀለደ በወቅቱ ሰምተናል፡፡ ያሻችሁን በሉኝ እንጂ እኔም  ልተርት ነው፡፡ “ ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ” እንላለን፡፡ “መቼ መጣሽ ሙሽራ፣ መቼ ቆረጠምሽ ሽምብራ”ም እንላለን፡፡ ነገር በሦስት ይጸናልና “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” ብዬ ልሰልስና ወደመነሻየ ልግባ፡፡

የፈንቀል ተብዬው እንቅስቃሴ መሪ የተባለ ከወያኔ ኮረጆ የወጣ ደቀ-ሕወሓት አንድ የሚዘገንን ነገር ሲናገር በዐይኔ በብረቱ እየሰማሁ በጆሮየ በታምቡሩ አዳመጥኩት፡፡ ዲጂታል ወያኔ አመሳስለው ያን መልእክት አስተላልፈውት እንደሆነ ብዬም ደጋግሜ በመስማትና በማየት ለማጣራት ሞከርኩ፡፡ የልጁ የራሱ ነው፡፡ በከንፈር እንቅስቃሴና በድምፁ መለየት ይቻላል፡፡

ይህ ልጅ የሚለው አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ለባዕዳን የሸጡና ሀገርን የከፋፈሉ ባንዳ ናቸው ነው – በአንተታ እየዘረጠጠ ለዚያውም  – የስሜት ሕዋሳቴን ተጠራጠርኳቸው፡፡ በርግጥም በዚህች ሀገራችን የገባ ሾተላይ ሥር የሰደደ መሆኑ ገባኝ፡፡ ይሄ አንድ መስከረም ሳይጠባ ስንቱን ጉዳጉድ እያሰማን እንደሆነ እንግዲህ ልብ በሉ፡፡ እነዚህን የየብሔር ብሔረሰቡን ልጆች ምን እየጋቱና እየቀለቡ እንዳሳደጓቸው ግልጽ ሆነልኝ፡፡ የዚህች ሀገር በሽታዎች መፍትሔ በእግዜር እጅ ብቻ መሆኑንም ተገነዘብኩ፡፡ 

ዝርዝሩን ለመመልከት ዩቲዩብ ወይም ፌስቡክ ገብታችሁ እዩት፡፡ የማነ የሚሉት ሣልሣዊ ወያኔ አፄ ምኒልክን  ቂጣ በቆረጠ  ስድ አፉ ሙልጭ አድርጎ ይሳደባል፡፡ 

የማያድግ ልጅ በአባቱ ብልት ይጫወታል ይባላል – መግቢያየ አካባቢ ዘንግቼያት ነበር አንተዬ! እኔ ስጠረጥር “ወደ ሀገር እንድትገባና ትግሉ እንዲሰምርልህ ከፈለግህ በአማራ ታርጋ የሚታወቀውን ምኒልክን አጥረግርገህ ስደብ፤ አማራንም በእግረ መንገድ ፈሪና ቦቅቧቃ እያልክ ሞልጨው፡፡ ከዚያ በኋላ እኛ እንደግፍሃለን…” ያለው ወገን ሳይኖር ልክ እንደዚህ ደረቱን ነፍቶ የጥቁሮችን አባት ባልተሳደበ ነበር፡፡ የሚገርመኝ ሌላው ቢቀር አማራን እወክለዋለሁ የሚለው በቁልምጫ ስሙ አዴፓ የሚባለው ነፈዝ የሆዳሞች ጥርቅም አንድም ነገር ትንፍሽ አለማለቱ ነው፡፡ በስማም እንደተባለበት ሰይጣን አፉ ተለጉሞ ከጡት አባቶቹ የሚጣልለትን ፉርሽካና ‹አልፋ-አልፋ› በማሞስካት ሥራ ላይ ተጠምዷል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ስድ አፎችን ከአለቃው ጋር በመመካከር ጭምር – ለራሱ ፖለቲካዊ ቅቡልነትም ሲል ቢያንስ አነስተኛ መግለጫ ቢያወጣና “አለሁ ወንዱ! ማናባቱ ነው አማራን የሚነካ!” ቢል ከዘመኑ የዘረኝነት ቅኝት አኳያ መልካም ነበር፡፡ ዳሩ የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም – ሞኝነቴ፡፡

ሀጫሉና የማነ ኦነግንና ሕወሓትን በመወከል እንዲህ እያሳቁን ነው፡፡ ተራው የትግራይና የኦሮሞ ሕዝብ ግን ይህን መሰሉን ቅዠትና የባለጌዎች ዘለፋ እያዬ ጉድ ከማለት ውጪ የአብዛኛውን ድጋፍ ይሰጣል ተብሎ አይገመትም፡፡ የሞተ ሰው ዕረፍት በሚያጣባትና ዐፅም እንኳን በመቃብሩ አርፎ እንዳይተኛ በሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር ደጋግሞ በሚገደልባት ሀገር መኖር አሳፋሪም፣ አስደንጋጭም ነው፡፡ አክራሪ ኦሮሞዎችንና ብልጣብልጥ ወያኔዎችን ለማስደሰት ሲሉ አፄ ምኒልክ አንዴ ተነስተው ለሁለተኛ ጊዜ ቢሞቱ እንዴት በተገላገልን ነበር! 

ለማንኛውም የማነ ንጉሱ የተባልክ የወያኔ ጥርብ ድንጋይ ይቅናህ፡፡ በርታ፡፡ ቃላትን እየተበዳደርክና እየተዋስክም ቢሆን በጀመርከው መንገድ ንጉሥ ምኒልክንም ሆነ አማራን ሞልጫቸው፡፡ ምን ያመጣሉ? ለጊዜው ሁሉም አልጋ ባልጋ ነው፡፡ ከቤተ መንግሥት እስከ ደደቢት ያንተን ሃሳብ የሚጋራና አይዞህ የሚል ነው፡፡ ቀን እስኪዘምብህ በርታልን፡፡ ወፌ ቆመች ስንልህ ባንዴ ዘጭ በማለትህ ግን አሁንም ልተርትልህ “የማያድግ ልጅ ካካው ብዙ ነው” እንዲሉ ሆነሃልና ለፓምፐርሱ ኦነግንና ሕወሓትን በደምብ ጠጋ በል – ያምበሸብሹሃል፡፡ 

በመጨረሻም፡-

ከመቼው ነግቶልኝ ይህችን ማስታወሻ ጽፌ በላክሁ ብዬ አሥሬ ሰዓቴን ሳይ እንደተለመደው ድረ ገፆችን መጎብኘት ጀመርኩ፡፡ ዘሀበሻ ላይ ስደርስ ባየሁት አንድ ዜና ፈገግ አልኩና እንደመሳቅ ሲቃጣኝ ባልተቤቴ “ምን ሆንክ?” አለችኝ፡፡ እኔም “ባለቤትሽ ሞቶ አንቺ እዚህ ተጋድመሽ እንቅልፍሽን ትለጥጫለሽ!” ስል አፌዝኩባት፡፡ አልገባትም፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- በአባቴ ስም በ“ጉዱ ካሣ” የብዕር ስም ይጠራ የነበረ አለማየሁ በላይነህ የሚባል ወንድማችን ሰሞኑን ከዚህች ዓለም ተሰናብቷል፤ ያም ዜና በኢካድፍ ወጥቷል፡፡ ያንን ዜና ቀደም ሲል ከኢካድፎረም አንብቤ በአስተያየት መስጫውም የተሰማኝን ገልጬ አልፌያለሁ፡፡ ዛሬ ግን የዘሀበሻ ድረ ገፅ አዘጋጆች ያ ሰው እኔ መስያቸው የሀዘን መግለጫ አውጥተው አየሁ – ያቀንየለይ፤ ገለቶማ፤ አመሰግናለሁ – ብሞትም እንዲሁ ነበርና ሳልሞት “ዓለሜን አየሁ”፡፡ አንድ ሰው ሳይሞት የሀዘን መግለጫዎችን የማየት ዕድል ካለው አንዱ እኔ መሆን አለብኝ፡፡ በአንድ በኩል ደስ አለኝ፡፡ በሌላ በኩል … የምን በሌላ በኩል ነው … ኧረ ምንም አልተሰማኝም በሌላ በኩል፡፡

ወንድሞቼ እነ አባዊርቱና ገብረ ሕይወት እነኩኒ ያደረሱኝን የሀዘን መግለጫ አንብቤያለሁ፤ በገነት ወይም በገሃነም ሆኜ ሳይሆን እዚችው ጉደኛዋ አዲስ አበባና ፊንፊኔ ውስጥ ሆኜ፡፡ ምሥጋናየ እጅግ ላቅ ያለ ነው፡፡

ለፈገግታ ያህል፡- አንድ ክፉ ፊታውራሪ ይሁኑ ደጃዝማች ነበሩ አሉ፡፡ ከክፋታቸው የተነሣ ቀብራቸው እንደማያምር ይጠራጠሩ ነበር አሉ፡፡ አንድ ወቅት ታዲያ “ማን እቀብሬ ላይ እንደሚገኝ፣ ማን እንደማይገኝ፣ ማን ከልቡ እንደሚያለቅስ… ለማወቅ እፈልጋለሁና አሁን ሞቻለሁ አሉ … እንደሞትኩ ቁጠሩና አልቅሱ፤ ከፍኑኝናም ወደ መቃብር ውሰዱኝ፡፡ በደምብ መመልከት እንድችል ታዲያ ለዐይኖቼ ቀዳዳ ነገር አብጁልኝ፡፡ ሳትቀብሩኝ ግን የውሸት መሆኑን ነግረን ለቀስተኛውን እናሰናብታለን፡፡” ብለው ለቤተሰባቸው ነገሩ አሉ፡፡ እንዳሉት ሁሉ ሆነ፡፡ ሰውዬው እንደጠረጠሩት የተገኘው ለቀስተኛ በጣት የሚቆጠር ሆነና የራሳቸውን ዕርም አወጡ ይባላል – የቁም ሞቸታውን፡፡ 

አንድ ልጨምር፤ በኮሮና ጊዜ የት ትሄዳለህ ዐርፈህ አንብብ፡፡ … አንድ መንደር ውስጥ እንደዚሁ አንድ እጅግ ክፉ ሰው ነበር፡፡ መንደርተኛው ሁሉ አደመበትና ሳይሞት እንደሞተ ተቆጥሮ ተከፍኖ እንዲቀበር ተወሰነ፡፡ ልቅሶው ተጀመረ፡፡ የሌላ መንደር ሰው ወደ አስከሬን ዝር እንዳይል ሠፈርተኛው ቃል ተገባብቶ እየጠበቀ ነው፡፡ መንደርተኛው ብቻ አስከሬኑን እየተቀባበለ ይዞት ወደ ቤተ ክርስቲያን ነጎደ፡፡ ሰውዬው ሣጥኑ ውስጥ ሆኖ እንዳልሞተ ቢጮህ ቢያጓራ ማን ሰምቶት፡፡ ተስፋ ቆርጦ ዝም ብሎ ሳለ በምክክሩ ያልበሩ አንድ የሕግ ጠበቃ አስከሬን ሸክሙን ለማገዝ ሲቀበሉ ይሰማል፡፡ ያኔ እርሳቸው ቢረዱኝ ብሎ ስማቸውን በመጥራት “ኧረ አያ እንቶኔ፣ መንደሩ አድሞብኝ በቁሜ ሊቀብረኝ ነው፤ ውሸታቸውን ነው አልትሞኩም…” ቢላቸው ሬሣውን ለሌላ ሰው ቀበል ያደርጉና የሕግ ማስታወሻና ብዕር ከኪሳቸው በማውጣት “ምሥክር አለህ?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ ማንን ያምጣ! ተቀበረና ዐረፈው፡፡ …

እንዲህ ያለ ነገር ያጋጥማል፡፡ ከመዝነኛነት ግን አያልፍም፡፡ ላዘናችሁልኝ እግዜር ይስጥልኝ – ክስተቱ “ውለታ መላሽ ያድርገኝ” የማያስብል በመሆኑ “በደስታ ልመልሰው” ልበል፡፡ ለተደሰታችሁ ግን ምንም ማድረግ አልችልም፤ አልሞትኩም፡፡ ሞት ደግሞ የሁላችንም ርስት ናትና መቼ እንደምትመጣ ሳታሳውቀን አንድ ቀን ላፍ ታደርገናለች፡፡ መጽሐፉም “በጧት አመጣ፣ በቀትር እመጣ፣ በማታ እመጣ አታውቁምና ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ” ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ የኛ ፋንታ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ነው፡፡ በሰው ሞትም መደሰት ከንቱነት ነው፡፡ ማንም ለማይቀርበት ነገር ትርፉ ትዝብት ነውና በቁም እያለን ለመማማር መትጋት ጥሩ ነው፡፡

 

ከዚህ በታ ያስቀመጥኩት አስተያየት ኢካድፍ ላይ ያስቀመጥኩትና በድረገፁ አዘጋጆች ከፀደቀ በኋላ የተለጠፈ ነው፡፡

 

    ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

 

July 21, 2020 at 1:14 am

 

ነፍሱን በገነት ያኑርልን፤ የልፋቱን ውጤት ሳያይ መሰናበቱ ቢያሥከፋም ሁላችንም ወደማንቀርበት ቀድሞን መሄዱ እንግዳ ነገር ባለመሆኑ ለቤተሰብና ዘመድ አዝማድ እንዲሁም ጓደኞቹና የሙያ አጋሮቹ መጽናናትን እመኛለሁ።

https://www.facebook.com/permalink.php?story_fbid=709175919904763&id=100024370830840&comment_id=709792459843109&notif_id=1595354155010199&notif_t=feedback_reaction_generic&ref=notif

Filed in: Amharic