>
5:18 pm - Friday June 14, 9811

ያልተነገረ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት የታላቁ ህዳሴ ግድብ !!! (ብስራት ወልደሚካኤል)

ያልተነገረ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት የታላቁ ህዳሴ ግድብ !!!

(ብስራት ወልደሚካኤል)

የዘመናት ህልምና ቁጭት የወለደው ልማት:: በጥንት ስሙ ግዮን የአሁኑ አባይ ወንዝ:: ከትናንት እስከ ዛሬ ለዘመናት በኢትዮጵያውያን በቁጭት ብዙ ተዚሞለታል ተሰፍሮ የማያልቅ ዋጋም ተከፍሎበታል:: የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ጅማሮ እውን መሆኑ በጣም ደስ የሚል መልካም ዜና ነው:: ከ62 ዓመታት ጉዞ በኋላ እውን የሆነ ትልቅ ድል ነው::
ይህ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጥናት በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በ1950 ዓ.ም.(እ.ጎ.አ. 1958) የመጀመሪያው ጥናት ተካሄደ:: ግድቡ እንደገና በ1956 ዓ.ም. (እ.ጎ.አ. በ1964) የሁለተኛውና የተሻሻለው የመጨረሻው ጥናት ከሌሎች አጠቃላይ የአባይ ወንዝና ተፋሰሱ ላይ የሚደረጉ የኤሌክትሪክና መስኖ ልማት ጥናቶች ተጠናቀቁ:: ጥናቶቹ በተጠናቀቁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፊንጫ መስኖ እና ኤሌክትሪክ እንዲሁም ጣና በለስ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ መደረግ ጀመሩ::
በርግጥ የአሁኑን የታላቁ የህዳሴ ግድብም ለመጀመር ሀገር ውስጥ በቂ አቅምና ገንዘብ ባለመኖሩ የዓለም ባንክን ጨምሮ አበዳሪ ተቋማትና ሀገሮች የገንዘብ ድጋፍ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀረ:: ከዛም እልህ የተናነቃት ግብፅ ከወዳጇ ሱዳን እና አጋር የአረብና ከፊል ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ከነበራቸው አውሮፓውያን ጋር በመሆን የአባይ ተፋሰስ ላይ የሚደረጉ የልማት መርሃ ግብሮችን ለማስተጓጎል ከቀጥታ ጦርነት በስተቀር አለን የሚሉትን ሁሉንም ኢትዮጵያን የማተራመስ ከተቻለም የመበታተን አማራጮችን ተጠቀሙ:: በተለይ ግብፅ በ1950 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአባይ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ጥናት እንዳጠናቀቀች በእንግሊዝ በኩል መረጃው ከደረሳት በኋላ ወዲያውኑ ሁለት ርምጃዎችን ወሰደች:: የመጀመሪያ በ1950 ዓ.ም. (እ.ጎ.አ. በ1958) በሃሚድ ኢድሪስ አዋቴ አማካኝነት አማካኝነት ዋና ጽህፈት ቤቱን በግብፅ ካይሮ ያደረገና ሙስሊሞችን ብቻ የያዘ ”የኤርትራ የነፃነት ንቅናቄ” የሚል እንቅስቃሴ አስጀመረች::
ግብፅ ተንኮሏን አጠናክራ በመቀጠል በታህሣሥ 6-10 ቀን በ1953 ዓ.ም. (እ.ጎ.አ.በ1960) በአዲስ አበባ መፈንቅለ መንግሥት አስተባበረች:: ቀጥሎም በነሐሴ 26 ቀን በ1954 ዓ.ም. በሃሚድ ኢድሪስ አዋቴ የሚመራው ጀበሃ ”የኤርትራ ነፃነት ግንባር) በይፋ ኤርትራ ውስጥ የመገንጠል ጥያቄ አንግቦ የትጥቅ ትግል ተኩስ ጀመረ:: ይሄ አካሄድ ያላማራቸውና በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ዳግም የተዋሃደችው ኤርትራ በአንድ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የፈለጉ የኤርትራ አንድነት አባላት ”የሀገር ፍቅር ማህበር” በመመስረት ጉዳዩን ለንጉሱ በማሳወቅ የኤርትራ ፌዴሬሽኑ በቶሎ ፈርሶ በአንድ ኢትዮጵያ እንድትጠቃለል ምክረ ሐሳብ አቀረቡ:: ይህ ”የሀገር ፍቅር ማህበር” ከሚታወቅባቸው አንዱ ”ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!” የሚለው መለያ መፈክራቸው ነው:: እዚህ ላይ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያውያን የምንጠቀመው ”ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!” የሚለው መፈክር ቀድሞ በማስተጋባት የኤርትራ ”ሀገር ፍቅር ማኀበር” አባላት መሆናቸውን ልብ ይሏል::
ሁለተኛው የግብፅ ርምጃ በ1951 ዓ.ም. (እ.ጎ.አ. በ1959) የቀድሞ ቅኝ ገዥዋ እንግሊዛ ድጋፍ ከሱዳን ጋር ብቸኛ ባለቤትና ተጠቃሚ ያደርገኛል ያለችውን የአባይ ውሃ ድርሻ ውል ተፈራርማ በሀገራዋ ህጋዊ ሰነድ አደረገች:: በውል ስምምነቱም ግብፅ ከፍተኛውን ድርሻ ለራሷ ባደረገችው ውል ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳቸውም የውሃ አመንጪ ሀገሮች አልተሳተፉበትም:: ኢትዮጵያም በንጉሱ አማካኝነት ያን ውል ውድቅ በማድረግ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትና ያልመከረችበት የትኛውንም የናይል ወንዝ ውል እንደማትቀበልና እንደማትገዛም በይፋ አሳወቀች:: በመቀጠልም ኢትዮጵያ ከራሷ በሚፈሰው የአባይ ወንዝ ላይ ለምታደርገው ልማት የማንም ይሁንታና ፈቃድ እንደማያስፈልጋት አረጋገጠች:: ኢትዮጵያ ከሁለተኛው እ.ጎ.አ.1964 የተሻሻለው የአባይ ወንዝና ተፋሰሱ ልማት ጥናት በኋላ ተግባራዊ እንቅስቃሴዋን ቀጠለች::
ግብፅም ኢትዮጵያን የማወክ ተንኮሏን ቀጠለች:: በተለይ በግብፅ የተመሰረተውና ሙሉ ድጋፍ ሲደረግለት የነበረው ”ጀበሃ” በይፋ ”የኤርትራ ነፃነት ግንባር” ብሎ ኤርትራ ውስጥ የትጥቅ  ትግል በጀመረ በዓመቱ በ1954 ዓ.ም. (እ.ጎ.አ.በ1962) የኤርትራ ፌዴሬሽን ፈርሶ ዳግም በአንድ ኢትዮጵያ እንድትጠቃለል ተደረገ::
ይሁን ግብፅ ኢትዮጵያን የማበጣበጥ ተንኮሏን አጠናክራ ከሱዳን:ሱማሊያ እና ወዳጅ አረብ ሀገራትን እና የወቅቱ ጥብቅ ወዳጆቿን ጣሊያንና ራሽያን በማስተባበር የተማሪዎች አመፅና እንቅስቃሴን ጨምሮ የተለያዩ ታጣቂ የ”ፖለቲካ” ድርጅቶችንና ንቅናቄዎችን በማደራጀት አዲስ አበባን ጨምሮ ሀገሪቱን በአራቱም አቅጣጫ መበጥበጥ ጀመረች:: ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው መጀመሪያ የኤርትራ ”ጀበሃ”ን መስርታ  ማስታጠቅ የጀመረች ሲሆን በመቀጠልም በቅርብ ከተመሰረቱት የፖለቲካ ድርጅቶች በስቀር ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና ንቅናቄዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በግብፅ የተደራጁና የሚደገፉ ነበሩ ናቸውምም::
ግብፅ ከወዳጇ ሱዳን ጋር በመሆን የአባይ ተፋሰስ ልማት ጥናቶች መካከል አንዱ የሆነውን እና ወለጋ ውስጥ ያለውን የፊንጫ መስኖና ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት ለማደናቀፍ ብዙ ጥረት አደረገች:: ነገር ግን አልተሳካላትም:: ይሄም አንዱ የአባይ ግድብ ተግዳሮት አካል ነው:: በመቀጠልም የ1965/66 ”አብዮት” ፈነዳ ተባለና በነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ንጉሱ ከሥልጣን ተወገዱ:: ከዚያም በንጉሱ ምትክ ሥልጣን የያዙት ፕሬዘዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የአባይ ግድብ ጥናት ፕሮጀክትን እውን ለማድረግ በ1970ዎቹ መጨረሻና በ1980ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀመሩ:: ልክ እንደ አጼ ኃይለሥላሴ ኮሎኔል መንግሥቱም ብድር ተከለከሉ:: በነበረው  የገንዘብ  እጦት   ግድቡን እውን ሳያደርጉ በ1983 ዓ ም ከሥልጣን ተወገዱ::
በምትካቸውም አቶ መለስ ዜናዊ የሀገሪቱን መሪነት ተረከቡ:: ብዙም ሳይቆዩ በ1985 ዓ ም (እ.ጎ.አ. 1993) በትጥቅ ትግል ምሥረታና ጦርነት ጊዜ ዋነኛ አጋራቸው የነበረችው ግብፅ ተፕሬዘዳንት ሁስኒ ሙባረክ ከቀድሞው የሽግግር ፕሬዘዳንት ከነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ጋር የአባይ ተፋሰስ ልማት ዙሪያ ከግብፅ ጋር ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ እንዳታለማ የሚያስር መንደርደሪያ የሆነውን የሁለትዮሽ ውል ተፈራረሙ::
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስር አቶ መለስ ሥልጣናቸው እስኪረጋጋ በሚመስል የተፈራረሙትን ያንን መሰሪ ውል አሽቀንጥረው በመጣል ታህሣሥ 2 ቀን 2003 ዓ.ም. (እ.ጎ.አ. December 10,2010) የዛሬውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ አስጀመሩ:: ከዚያም ግድቡ ከተጀመረ ከ5 ወራት በኋላ ሚያዚያ 2003 ዓ.ም. ግድቡ በይፋ መጀመሩን አበሰሩ:: ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ህልፈት በኋላም በቦታቸው የተተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተጀመረው ግድብ ከግብ እንዲደርስ የቻሉትን ያህል ጣሩ:: ከዚያም በነበረው ህዝባዊ አመፅ ሥልጣናቸውን ለዶ/ር አብይ አስረከቡ::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ሥልጣን ከተረከቡ ጀምሮ ግድብ በቶሎ እንዲሳካና አገልግሎት እንዲበቃ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሥራው እንዲፋጠን የተለያዩ በጎ ማሻሻዎችን አደረጉ::
በሂደትም ግድቡ የመጀመሪያው ጥናት ከተጠናቀቀበት ከ1950 ዓ.ም.(እ.ጎ.አ. 1958) ከ62 ዓመታት በኋላ በትውልድ ቅብብሎሽ እውን በመሆን እነሆ በያዝነው ወር ሐምሌ 2012 ዓ.ም. ዶ/ር አብይ አህመድ ዘመን የግድቡን የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ተጀመረ:: ላለፉት 62 ዓመታት እንዲህ እውን እንዲሆን ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ታላቅ ፕሮጀከት::
የግድቡ ፕሮጀክት ጀምሮ አሁን ያለበት እንዲደርስ የቻሉትን ያህል የደከሙትን ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ: ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም: አቶ መለስ ዜናዊ: አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ዶ/ር አብይ አህመድ እንዲሁም መንግሥታቸውና በስራው የተሳተፉና በሚችሉት አቅም ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል:: ግድቡ የታሪካችሁ አካል ሆኖ ይቀጥላል:: እናመሰግናለን!!
ይህ የታላቁ የህዳሴ ግድብ አጼ ኃይለሥላሴ ካስጠኑት 27 የአባይ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል ፊንጫ: ጣና በለስ እና ርብ ግድብ ቀጥሎ ይሄ አራተኛው የተሳካ ፕሮጀክት ይሆናል ማለት ነው::
ግድቡ በገንዘብና ቴክኒካል አቅም እጦት ቢዘገይም በኛ ዘመን እውን መሆኑ ደስ ይላል:: ይህም የያው የተጀመረ መጠናቀቁ አይቀርምና:: አጠቃላይ ግድቡ ተጠናቆ በሙሉ ኃይሉ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ሲጀመር በኢትዮጵያ ከ1953 ጀምሮ ሰላም ሲነሳን የነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እስከወዲያኛው ያከትማል:: ምክንያቱም ከእንግዲህ ላለቀ ነገር ግብፃውያን ሀገር ውስጥ ለማተራመስ የምትሰጠው የገንዘብ እና የቁሳቁስ አቅርቦትም ሆነ ማንኛውም የጥፋት ተልዕኮና ድጋፍ ምንም እንደማይጠቅማት ትረዳለች የሚል እምነት አለኝ:: በከንቱ ገንዘቧንም ቆሻሻዋንም ማራገፏን እስከመጨረሻው ታቆማለች:: በአንፃሩ እማማ ኢትዮጵያ ከነበራት ሌላ ተጨማሪ አቅም ይሆናታል::
ስለዚህ ግድቡ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ባልተናነሰ ትልቅ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አለው:: በቀጣይ በአባይ ወንዝና በሌሎች ተፋሰሶች ላይ ሌሎች ግድቦችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ:: ከእንግዲህ ወደ ኋላ ማለት የለም:: ወደፊት እንጂ!!
Filed in: Amharic