>

" ሊበሏት ያሰባትን አሞራ .... " እንዳይሆን ! (ደሴት ኢትዮፕ)

” ሊበሏት ያሰባትን አሞራ …. ” እንዳይሆን !

ደሴት ኢትዮፕ

ከአጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ በሕግ አካላት ” የሁከት ተጠርጣሪዎች ” የተባሉ መያዛቸውን ተገልፇል ። ፖሊስ ጀዋርን ጨምሮ ….ከጀዋር የፖለቲካ አስተሳሰብ እጅግ በረጅም ርቀት የሚገኘውን እስክንድርንም አስሯል ።
.
ግድያውንም ምክንያት አድርጎ በተለያዩ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ሁከት መፈጠሩም ይታወሳል ። አዲስ አበባም ጨምሮ ። በተለይም ፈረንሳይ ለጋሲዬን ፣ ቄራ ፣ ሰንጋ ተራ ፣ ልደታ ፣ ቃሊቲ ፣ ገላን ፣ አዲሱ ገበያ ፣ ፓስተር ፣ አስኮ ፣ አቃቂና ሌሎችም አካባቢ መኪናዎች ጋይተዋል ፤ ተሰባብረዋል ። የ11 ሰው ሕይወት ማለፉንም ፖሊስ ተናግሯል ። መኪናዎች ሲሰበሩና ሲወድሙ የነበሩት ታርጋቸው እየታየ ነው ። መዚህ ዘመን መኪናዎችም ጭምር ብሄር አላቸውና ፤ በለጠፉት ብሄራቸው ምክንያት ከወድመት ተርፈዋል ። በለጠፉት ብሄር ምክንያትም ተጠቅተዋል ።
.
ይህን ድርጊት ሲፈፅሙ የነበሩት ከሌላ አካባቢ የመጡና ጨፈቃ የተሸከሙ ወጣቶች ናቸው ። በጀዋርና “በጋሽ ” በቄ እንዲሁም ልሳናቸው በሆነው በOMN በተጨማሪም በተባባሪያቸው በትግራዩ DW ቴሌቪቪን በተላለፈ ጥሪ የነሱ አጀንዳ ተሸካ የሆኑ ቡድኖች ከየአቅጣጫው ከተማውን አጥለቅለቀዋል ። ድርጊቱ ያበሳጫቸውና የብሔር አስተሳሰብ ካባ ያልደረቡ የየአካባቢው የአዲስ አበባ ወጣቶች ” መንደራችንን አታውኩ ! ” በሚል ከየቤታቸው በመውጣት ከአዋኪዎቹ ጋር ግብ-ግብ ገጥመዋል ። ከፖሊስም በላይ የአካባቢያቸውን ሰላም አስጠብቀዋል ።
.
የአ/አበባ ወጣት የፖሊስን ዘገምተኝነትና ዳተኝነትን ወደ ጎን ትቶ ሰፈሩን ላለማስደፈር ባይነሳ ሌላኛዋ ሻሸመኔ … አዲስ አበባ ትሆን ነበር ። በተለይም የአቃቂ ከተማ ወጣቶች ከየአካባቢው በመንጋ ይመጡ የነበሩ ወጣቶችን በተገቢውና ስነስረአት ባለው መንገድ በመገሰፅ ፣ ከዚያም ያለፈውን በመከላከል ከተማቸውን ታድገዋል ። በዚህም ለጥቃት ተጋላጭ የሆነው አቃቂ ከተማን በመታደግ አንድም ጉዳት ሳይደርስ ችግሩን ተሻግረዋል ።
.
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የአዲስ አበባ ወጣት ራሱንና መንደሩን ለመጠበቅ ያደረገውን የመከላከል እርምጃ ከእስክንድር ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም ። የአዲስ አበባ ወጣት የፀጥታ አካሉ ችላ ባይነት አሳስቦት ከተማውን ተከላክሏል ። ይህ አዲስ አበቤ ለመብቱ ያደረገውን ተጋድሎን ለአንድ የፖለቲካ ቡድን አሳልፎ የመስጠት ተግባር ነው ። እስክንድር ይህንን የሚያስተባብርበት ሁኔታና አደረጃት ላይ አይገኝም ። አስተባብሮም ቢሆን የከፋ ችግርና ጥፋት እንዳይከሰት አስተዋፅኦ እንዳደረገ መታሰብ ይገባ ነበር ። አሁንም ደግሜ የምጠቅሰው የአ/አ ወጣት ከቤቱ ሊወጣ የቻለው የችግሩ አሳሳቢነትና ከየአቅጣጫው የሚፈሰው እንዲሁም ወደ ከተማው ለሁከት የሚገባው ወጣት ጥቃትና የንብረት ውድመት ለመከላከል ነው ። ከፖሊስ ያልተናነሰ የዚህ ወጣት አስተዋፅኦ አዲስ አበባን በመታደግ ረገድ የጎላ ነበር ። ፖሊስንም በማገዝ ሊመሰገን የሚገባው ነው ።
.
ይህ ሆኖ ሳለ እስክንድርን በዚህ ተጠያቂ ማድረግ አገር አዋኪውን የችግር አቅጣጫ ማሳት እንዳይሆንና እነ እስክንድርንም ማሰር ወደ ፖለቲካዊ ብቀላም እንያማራ ከፍትህ አካሉ ንፅህና ይጠበቃል ። የነ እስክንድር እስር ” ላም ባሏለበት …. ” ከሆነ የአጫሉን ግድያና ገዳዮች ለማድበስበስ በር ይከፍታል ። ገዳዮቹንም ማስደሰት ነው ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሞክሮ እንዲህ አይነት ችግሮች በአገር ላይ ሲከሰት ጥርስ የተነከሰባቸው ፖለቲከኞችና ታዋቂ ሰዎችን ከተጠርጣሪ ጎራ ጋ በጅምላ ማሰር የተለመደ ሆኖ ቆይቷል ። አሁንም ይህ እንዳይሆን በብዙዎች ዘንድ ስጋት አለ ። የተገኘን አጋጣሚ ለብቀላ መጠቀም የወያኔ ስራ ነው ። ሕወሓት በዚህ ተግባር አልተጠቀመም ። ይህ የለውጥ ቡድንም ሊጠቀም አይችልም ። የእስክንድር እስር ” ሊበሏት ያሰቧትን … ” አይነት እንዳይሆን !
Filed in: Amharic