>
5:18 pm - Sunday June 15, 3947

ዘረኛ ነኝ !!! (እንየው ደቻሳ)

ዘረኛ ነኝ !!!

(እንየው ደቻሳ)
ከረጅም ጊዜ በፊት ‘ማቭሪክ /Maverick/’ የሚባል ከብት አርቢ በአሜሪካ ይኖር ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ጥቂት የመንግስት ሠራተኞች ወደ ግቢው ዘው አሉ። ከብቶቹ ሁሉ ተለይተው እንዲታወቁ ምልክት ለማድረግ መምጣታቸውን ነገሩት። ቀለም እና ጆሮ መብሻ ይዘዋል። “መለየታቸው ለምን አስፈለገ?” አለ ማቭሪክ በጥርጣሬ። “ከብቶቹ ለገበያ ሲወጡ ከየት አካባቢ እንደመጡ ለማወቅ እና ጎሣቸውንም /Breed/ ለመወሰን እንዲቻል ነው” አሉት ሰዎቹ።
ማቭሪክ በስጨት ብሎ ተናገረ፦ ” ከብቶቹ ጎሣቸውም ሆነ አድራሻቸው እንዲበየን አይፈልጉም፤ የከብቶቹ ፍላጎት ፍየሉም እንደ ፍየል፣ በሬውም እንደበሬ መታየት ብቻ ነው። የ’መንዝ በግ፣ የመራቤቴ ፍየል’ እየተባሉ መጠራታቸው ፋይዳ የለውም።” … በዚህ ምክንያት ከብቶቹ የጎሣ ባጅ ሳይታሰርላቸው ቀረ።
እንሆ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ቅጽል እና ምልክት ሳይፈልጉ የሰው ልጅ ብቻ መሆናቸውን አምነው የሚኖሩ ሰዎች ‘ማቭሪክ’ ይባላሉ። እኔስ ማን ነኝ?
እናቴ አማራ ናት ይላሉ፤ ያም ሆኖ እኔ አማራ አይደለሁም። አባቴ ኦሮሞ ነው ይላሉ፣ ይሄም ሆኖ እኔ ኦሮሞ አይደለሁም። ከሥሩ ቢጣራ የእናቴም አማራነት፣ የአባቴም ኦሮሞነት ውስጥ የማንነት ቅልቅል አለ። ይሄንን በቅልቅል ተጋብቶና ተፋቅሮ የመኖር ጥበባቸውን ታድያ ፖለቲካ የሚባል ጥርስ ነከሰው፤ ከንክሻው ለመዳን የሚያስችለውን ‘ቲታነስ’ መርፌ ከመንግስታት እጅ መፈልቀቅ አልቻል አለ። የሐበሻ ዘር በብሔር ተቧድኖ እንዲጠብ ተደረገ። ይህን ሲስቴም ‘ከፋፍለህ ግዛ’ ይሉታል ፖለቲከኞቹ በድል አድራጊነት።
እኔ ከዚህ ብሔረተኛ ‘ባጅ’ ማምለጥ እፈልጋለው። ወጥመድ ላለመግባትም ስል ቀበሌ መሄድን አላዘወትርም። እንደቀበሌ ያለ የብሔር ጥያቄ የሚያፈቅር የመንግስት ቢሮ ገጥሞኝ አያውቅም።
እኔ ብሔረተኛ አይደለሁም፤ ነገር ግን ዘረኛ ነኝ። ሁለቱ ሐሳቦች ‘የአብራሪና የዋናተኛ’ ያህል ይራራቃሉ። ብሔረተኛ ስትሆን እንደ ኮንደምንየም መጸዳጃ ቤት ትጠባለህ። ዘረኛ ስትሆን ግን ሃገር አይበቃህም።
ሰው መሆንህን ብቻ እንደ መመዘኛ ይዘህ ከሰው ጋር የምትቀላቀልበት ፀጋ ነው፣ ዘረኛ መሆን። ዘርህ ከዱር እንስሳት ወይም ከጓሮ አትክልት ሳይሆን ከሰው እንደሚነሳ ማመን ነው፣ ዘረኛ መሆን።
እኔ ዘሬ ከሰው ልጅ ሁሉ የሚገጥም በመሆኑ ሰውን ሁሉ ዘመዴ የምል ዘረኛ ነኝ። ብሔረተኛ ብሆን ግን ዘመዴ እንደ መንደር ዕቁብተኞች ውስን ነው።
ዘረኛ ነኝ!!! ከትግራይ እስከ አፋር፣ ከቦረና እስከ ሐመር ሁሉም የኔ ብጤ ሐበሻ በመሆኑ ቤተሰቤ ነው። ከ80 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ጋር በአንድነት እና በመመሣሰል የምኖር ዘረኛ ነኝ። ሁሉም ዘሬ ነው፤ ሁሉም ከአንድ ዘር የተከፈለ ነው።
ዘረኛ ነኝ!!! ያም ሆኖ ግን ዘረኛነቴ በኢትዮጵያነት ብቻ አይቆልፈኝም። እውነተኛ ዘረኛ ስትሆን ከሱዳን እስከ ሞሮኮ፣ ከሞዛምቢክ እስከ ጋና ድረስ ዝምድናህ ይሰፋል። አፍሪካዊያን ሁሉ ያንተ ዘር ከተነሣበት ኩሬ የተቀዱ ወንድሞችህ ናቸው። ዘረኛ ስትሆን አፍሪካዊያን እናቶች ሁሉ እኩል ትሁቶች ሆነው ይታዩሃል። የአፍሪካ ሽማግሌዎች ሁሉ ብልህ ወላጆችህ ይሆናሉ።
እዚህ ድረስ ዘረኛ ነኝ!!!
ያም ቢሆን በቀለም ልዩነት የማምን ጠባብ አፍሪካዊ አይደለሁም። ዘሬ ጥቁር ብቻ አይደለም። ዓለም ሊቃወም ይችል ይሆናል፤ ቢሆንም 7 ቢሊየን የዓለም ሕዝብ ዘሩ አንድ ነው። ከሕንድ እስከ ጃማይካ ያሉት ሁሉ እህቶቼ ናቸው፤ ከሊባኖስ እስከ ፔሩ ያሉት ሁሉ ወንድሞቼ ናቸው። የሰው ልጅ የሆነ ሁሉ ዘሬ ነው።
የሰው ልጅ ከአንዱ ሃገር ተነስቶ ወደሌላው ሃገር ሲሄድ ምን ዓይነት ዕምነት ይዞ ነው? የትኛውም ሃገር ያለ ሰው ዘሩ እንደሆነ ስለሚያምን ነው። እንደ ፖለቲካው ፍላጎት ቢሆን የሰው ልጅ ሁሉ እንኳን ሀገሩን፣ ቤቱን ቆልፎ በፍራቻ ውስጥ በኖረ ነበር። ሰዎች ከብሔረትኝነትም በታች እጅግ በጠበቡ ነበር። ነገር ግን ዘረኞች በምድር ላይ ስለሚበዙ እነሆ ዓለም ዛሬም አልጠፋችም። ሃገርም በሠላም እና በአንድነት የመቀጠሏ ምስጢር ይሄው ነው። ዘረኛ መሆን! ሰውን በሰውነቱ ብቻ መቅረብ እና ማቅረብ።
ዘረኛ መሆን ማለት ‘ማቭሪክ’ መሆን ማለት ነው።
Filed in: Amharic