>

ሺ ጊዜ ሞተው አገር ከገደሉ ጎን አልቆምም!  (ውብሸት ታዬ)

ሺ ጊዜ ሞተው አገር ከገደሉ ጎን አልቆምም!

   ውብሸት ታዬ
 
*   ካልተደማመጥን ምን አጯጯኸን?!
1983 ዓ.ም ላይ በጥላቻ ተመርዘው፣ በሐሰተኛና አውዳሚ ትርክት ታጥቀው፣ አገር በመከፋፈልና በመሸጥ ተክነው ቅድስቲቷን ምድር ሲቆጣጠሩ መከተል የጀመሩት በአብዛኛው የኢጣሊያን የቅኝ ግዛት የአገዛዝ ስልት ነበር።
   እንደአንድ ቅኝ ገዥ ለ27 ዓመታት ዘረፉ፣ አሰሩ፣ ገደሉ፣ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ። በተለይ ከ1997 ዓ.ም በኋላ የነበሩት 15 ዓመታት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል የመከራ እንደነበሩ መናገርም ቀባሪውን ማርዳት ነው።
   የረገጡት ሁሉ ጨው የተዘራበት ይመስል ስለሚደርቀው የታሪክ ነውሮች የዴሞክራሲ ጠበቆች ናቸው እያሉ ለመመስከር መሞከር፣ ከእነሱ ጎን መቆም፣ የእነሱ ቅጥረኛ ሆኖ አገርንና ሕዝብን ለድርድር ማቅረብ አንድ ሞት ሳይሆን ሺህ ሞት ነው። ሺህ ጊዜ ሞተው አገር ከገደሉ ጎን ከመቆም ዝም ማለት ይሻላል።
ስለእነዚህ የታሪክ ነውሮች አደገኛ አካሄድ የገባንንና ያወቅነውን ያህል ጮህን፣ የሚከተሏቸውን የጥፋት ስልቶችና አማራጮች በዚሁ የfb. ሚዲያ ጭምር በየቀኑ ለማጋራት ሞከርን። ለማንምና ለምንም ሳይሆን ለህሊናችንና በመከራው የእስራችን ወቅት ፍቅርና አጋርነት ላሳዩን ውለታቸው መቼም ተከፍሎ ለማያልቀው የአገር ልጆች ክብር ስንል።
   በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ አገር መገንባት የሚችለው አብዛኛው ዜጋ በዝምታ ውስጥ ራሱን ሸብቦ፤ በአግባቡ ‘ተው!’ ቢባሉ የትም የማይደርሱ በጣት የሚቆጠሩ እኩያን፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቃችሁ ብሎ ካባረራቸው የታሪክ ነውሮች ጋር አብረው አገር ሊያፈርሱ ላይ ታች ሲሉ ሕሊናችን እየደማ ‘አይሆንም !’ ለማለት ሞክረናል።
   ለአገር የቆመው ሃይል በጋራ መቆምና መናበብ አቅቶት ሲተራመስ፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል…” ዓይነት ከንቱ የስልጣን ቅዠት ውስጥ የገባውና በተጠና ሁኔታ አገር ለመበተን የሚሠራው የጅብና የአህያ ጋብቻ መስርተው በአገራችን ላይ መአት አውርደውባታል።
   ቀድሞ በዚያ ባህሪ የማላውቃቸው አንዳንዶች ደግሞ የከረረ ጽንፍ ይዘው ሲጽፉና “ለምን?” ሲባሉ “ያኛው ወገን እንዲያ ስላደረገ ሚዛኑን ለማስጠበቅ” የሚል ከንቱ መከራከርያ ያቀርቡ ነበር። አውቀውም ይሁን ሳያውቁ አብረው አገር አቃጥለዋል። ሩቅ ሆነው የደሃ ጎጆ ሲነድ ሞቀዋል።
   በክፉዎች ብትር ሕይወታቸው ላለፈ፣ ለተጎሳቆሉና ለተሸማቀቁ፣ ለዘመናት ያፈሩት ሐብት በሰዓታት ለወደመባቸው፣ በአገራቸው ውስጥ ባይተዋርና ጠላት ለተደረጉ የኢትዮጵያ ልጆች ልቤ በሐዘን ተሰብሯል።
*እስካሁን ለነበረን ጊዜ እግዚአብሔር የከበረ ይሁን።*
ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን እግዚአብሔር ይጠብቅ !
Filed in: Amharic