>

ዘመኑን ሁሉ ፍትህ፣ እርቅና ብሄራዊ መግባባትን ሲሰብክ የኖረን ሰው "በአስር ሰዎች ሞት መክሰስ" አሳፋሪ ድርጊት ነው!!! (መአዛ መሀመድ)

ዘመኑን ሁሉ ፍትህ፣ እርቅና ብሄራዊ መግባባትን ሲሰብክ የኖረን ሰው “በአስር ሰዎች ሞት መክሰስ” አሳፋሪ ድርጊት ነው!!!

መአዛ መሀመድ
የኢትዮጵያን ፖለቲካ በሴራ በሚያቦኩ ሰዎች መካከል እውነቷን ፊት ለፊት ተናግረው ከሚጋፈጡ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ይልቃል ጌትነት ነው። ይህ ሰው በጨለማው ዘመን አደባባዩን እየሞሉ ከሕወሓት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ የሚተናነቁትና አገዛዙን ራቁቱን ያስቀሩት የሰማያዊ አናብስት ወጣቶች መሪ ነው። መሪነትን ሱፍ ለባሽና ቢሮክራሲ ወዳድ የሊቃነ መናብርት ሲይዙትና ይልቃል ሲይዘው ልዩነት አለው።
በዚያ በጨለማው ዘመን እርሱ የሚመራቸው ወጣቶች ቅዳሜ ከሰአት  በወጣቶች ውይይት እሁድ ጠዋት በምሁራን ትምህርት ግቢውን ሲያደምቁት መሀላቸው አይታጣም። በአስፈሪዎቹ ሰላማዊ ሰልፎች ከቅስቀሳ እስከ ሰልፉ ፍፃሜ ድረስ እንደ አንድ አባል ያስተባብራል ይሰራል፤ወጣቶቹ ሲታሰሩ አብሮ ይታሰራል፤ሲደበደቡም እንዲሁ፤ከእለታት በአንዱ ቀን ወታደሮች ከመኪና ላይ ወርውረው ሊገድሉት ሞክረው ተርፏል፤በሌላም ጊዜ መነፅር  አይኑ ላይ ሰብረውበታል፤ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምድር ቤት እስከ ፖሊስ ጣቢያዎች እስር ድረስ ተፈራርቀውበታል።
ከውጪ የህወሓት ማሳደድ፣ከውስጥ የ”አንጋፋ ነን” ባይ የፓርቲ አባሎች ፍረጃና ጠለፋ እየተፈራረቀበት ሀገሩን አስቀድሞ በየክፍለሀገሩ እየዞረ ፓርቲውን አደራጅቷል። የማይደፈረውን የደፈረውን ሰማያዊን ይዞ ጭቆናን ተጋፍጧል። ከዚህ ሁሉ በኋላም ለሽሽሽሽ ብሎ የነበረው ከእንቅልፉ ባኖ ስለለውጥ ሲዘምር በቀዳሚነት “ይህን ነገር ታግሰን እንየው ከተራ ወዳሴና ጭብጨባ ወጥተን ጉዟችንን መነሻና መድረሻ እናብጅለት የሽግግር ጊዜ ፍትህ የሚሰጥ ገለልተኛ ኮሚሽን ይቋቋም በማለት በተደጋጋሚ ተናግሯል።”በዚህም ከጠሚሩ ጀምሮ በተደማሪ ተቃዋሚዎች እና አሸርጋጅ ምሁራን ውግዘት ደርሶበታል።”
ያለማሽሞንሞንና ይሉኝታ እውነቱን እየተናገረ ለአፍታም ከሰላማዊነቱ ሳያፈነግጥ ተረኞችን ተጋፍጧል።
በእኛ ዘመን አሳዳጅና ተሳዳጅ የለም ያሉት መሪዎች አፍታም ሳይቆዩ ይልቃልን አንድ ጊዜ በትግሉ አቁስሎ መቀሌ ካስገባቸው የህወሓት ሽማግሌዎች ጋር ሌላ ጊዜ ደግሞ እውነት እውነቷን ነግሮ ቀንዳቸውን ካላቸው የኦሮሞ ፅንፈኞች ጋር ፈርጀው እስር ቤት ጥለውታል።
ኢትዮጵያም ስለ ሽግግር፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ ሃገር አንድነት፣ እርቅና ብሄራዊ መግባባት ሲሰብክ የነበረውን ይልቃልን በአስር ሰዎች ሞት በመክሰስ ጉደኛ ታሪኳን ቀጥላለች።
Filed in: Amharic