>
5:18 pm - Friday June 16, 7217

"አንዳንድ ባለሥልጣናት ስልክ እየደወሉ ያስፈራሩናል” (ማህበረ ቅዱሳን)

“አንዳንድ ባለሥልጣናት ስልክ እየደወሉ ያስፈራሩናል”

ማህበረ ቅዱሳን


የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያውያን በብሔራቸው እና በሃይማኖታቸው ምክንያት ጭፍጨፋ እንደተፈጸመባቸው ዕውቅና መስጠቱ መንግሥትን ያስመሰግነዋል። ይህን የምንለው ያልተለመደ በመሆኑ እንጂ መፈጸም ከነበረበት በላይ ፈጽሞ አይደለም። ባለሥልጣናት እንደ ከዚህ ቀደሙ ለማድበስበስ ከመሞከር ይልቅ በሚዲያ እየቀረቡ እውነቱን መናገራቸው በጎ ጅምር ነው። ችግሩን አምኖ በክርስቲያኖች ላይ ለደረሰው ጥቃት ዕውቅና መስጠቱ ተገቢ ቢሆንም የማያዳግም የእርምት ግምጃ መውሰድ ይኖርበታል። ከዚሁ ጎን ለጎን ያዘኑትን ማጽናናት፣ መልሶ ማቋቋም እና ዳግም ለጥቃት እንዳይጋለጡ አስተማማኝ ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል። ፍርሃታቸውን እና ስጋታቸውን መጋራትም ይገባል። አጥፊዎች ከአድሎ የጸዳ ፍርድ እንዲያገኙ ማድረግም ለአገር አስተማማኝ ሰላም ያመጣል። በዘረኝነት እየተገፋፋ የሰው ሕይወት እና ንብረት ለማጥፋት የሚነሣሣውንም አደብ ያስገዛል።

አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን እንደ ጻፈው በጦርነት የወደሙ የመሰሉትን አዳባ፣ አጋርፋ፣ ባሌ፣ አርሲ ነገሌ፣ ሻሸመኔ እና ዝዋይ ከተሞች ትናንት ማታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማሳየቱ መልካም ቢሆንም ከዚህ ባለፈ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ተጎጂዎች ሲናገሩ የሰማናቸው ሁለት ነገሮች አሳዛኝም አሳሳቢም መሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል። “እስካሁን በመንግሥት በኩል የተደረገልን ዕርዳታ የለም” የሚለው የመጀመሪያው ሲሆን ሁለተኛውና በጣም አሳዛኝም አሳፋሪም የሆነው ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ “አንዳንድ የየአካባቢው ባለሥልጣናት በየግል ስልኮቻችን እየደወሉ እያስፈራሩን እና እየዛቱብን ነው” የሚለው ነው።

የፈጸሙት እና ያስፈጸሙት ጥቃት አላረካ ብሏቸው ደግመው በሰው ደም ለመታጠብ ጊዜ የሚጠብቁትንና ሰው በማሰቃየት ደስታ የሚያገኙ የሚመስላቸውን ባለሥልጣናት በቍጥጥር ሥር ማዋል ካልተቻለ ተጨማሪ ጥፋት እንዲያደርሱ ዕድል መስጠት ነው። ጥፋትህን አውቄብሃለሁ ሲባል ካለፈው ስሕተቱ መማር የማይችል ባለሥልጣን ጤነኛነቱ የሚያጠራጥር በመሆኑ ወንበር ላይ ሆኖ የራቀውን ዕውቀት ከፍትሕ ማግኘት ይኖርበታል። በጥፋታቸው ተጸጽተው የተጎዱትን ማጽናናት ሲገባቸው በስልክ ማስፈራራት መቀጠላቸው ማናለብኝነታቸውን ያሳያል። እነማን ይህን ድርጊት እንደሚፈጽሙ ከኢንሳ ዕውቅና ውጭ ሊሆን እንደማይችል ይታወቃልና። ይህን እኩይ ድርጊት የሚፈጽሙ ባለሥልጣናት በዘመናቸው ታሪክ ተቀይሮ አይተው ያልተማሩ በመሆናቸው መንግሥት ተከታትሎ ከአሸባሪ ድርጊታቸው ማስቆም ይኖርበታል። እንዲህ ዓይነቶቹ አረመኔዎች ሰዎችን በመግደል ደስታን ያገኝ የነበረው አጋግ በሰዎች ላይ ይፈጽም የነበረው በራሱ ላይ ሲደርስ “ሞት እንዲህ አስጨናቂ ናትን” የሚሉ ናቸው።

ያሉበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ እና አሳሳቢ በመሆኑ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ተጠልለው የሚገኙ ወገኖቻችንን ለዘለቄታው ከማቋቋም እና ከማደራጀት አስቀድሞ ጊዜያዊ እርዳታ ማድረግ ይገባል።

Filed in: Amharic