>
4:42 am - Tuesday January 31, 2023

የማለዳ ወግ ... በ2006 ዓም የመጨረሻ ሰአታት፣ የማይረሱኝ የተጨመቁ ትዝታዎች ..[ነቢዩ ሲራክ]

Nebiyu Sirak (2006 -2007 )አዲስ የነበረውና ዛሬ ገና 12 ወር ከ5 ቀኑ “ያረጀ ያፈጀ ” የምንለው 2006 ዓም ለመገባደድ ጥቂት ሰአታት ብቻ ነው የቀሩት ። 2006 ዓም በሳውዲ ለምንገኝ ኢትዮጵያውያን ልዩ የማይጠፉ ትዝታዎቸን አስተናግደንበታል ።
* ፍጹም የማይረሱኝ ትዝታዎች …
በ2006 ተከስተው የማይረሱኝ የተለያዩ ክስተቶች እና አስደሳችና መራራ ትዝታዎች ብዙ ቢሆኑም የተጨመቁትንና ፍጹም ከአዕምሮየ የማይጠፉት በአዲሱ አመት መግቢያና በአሮጌው አመት መሸኛ የመጨረሻ ሰአታት ላድታውሳቸው ግድ አለኝ …
* መስከረም ጠብቶ የሴት ልጅ በረከቴን ማህሌትን ከፈጣሪ ያገኘሁበት ቀን በውስጤ ሴት ልጅ ማግኘቴ እናቴን የመተካት ያህል የደስታ ስሜት …
* በጅዳ ቆንስልና ከኮሚኒቱ ግቢ ውስጥ ይተረማመሱ የነበሩ ራሳቸውን የሳቱ ፣ የነሆለሉ ፣ ያበዱና ያዙኝ ልቁኝ ይሉ የነበሩት የኮንትራት ሰራተኞች …
* በጅዳ ፣ በጣይፍ ፣ በሪያድ በደማም ከተሞች ለስራ ጉዳይ ስንቀሳቀስ በአውራ ጎዳናዎች ራሳቸውን ስተው ከራሳቸው ጋር እያወሩ ሲንከራተቱ ያገኘኋች እህቶች …
* በደረቁ ሌሊት ስልክ ተደውሎ መረጃ ደረሰኝ ፣ ወደ ቦታው አመራሁ ፣ በጅዳ ቆንስል በር የወደቀችውን እህት አገኘኋት! … ወደ መጠለያ ለማስገባት ከሃላፊዎች ጋር በስልክ ለማነጋገር ዘወር ስል እንቅልፍ ይዟት ኖሮ ስታንጎላች ከግድግዳ ጋር የተጋጨችው እህት የዚያ ምሽት እንባ …
* በሪያድ መንፉሃ ሁከት ቤት እየተሰበረ ሲበረበር፣ “ወጣቶች ከአዘረፋ አልፈው በሰሎቻችን እየደበደቡ እየደፈሩን ነው”ብለው ሲቃ እየተናነቃቸውና እያለቀሱ የደወሉልኝ ቀን እህቶች የምሬት ድምጽ.. !
* 3000 ተማሪዎች የሚማሪበት የጅዳ የኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ ትምህርት ቤት አደጋ ላይ መውደቅ ፣ የመምህራን የስራ ማቆም አድማ ፣ የሙስናው ጣጣ ፣ የኮሚኒቲው መዳከምና የቆንስል መስሪያ ቤቱ ዳር ቆሞ መመልከት አሳዛኝ ሂደት
* የታሰርኩባት ቀንና ለሁለት ሳምንታት ያሳለፍኩት አበሳ … በጊዜያዊው ማቆያ እስር ቤት ያየሁት ህይዎት …
* የአንድ ወር ተኩሉ የብሪማን ማዕከላዊ እስር ቤት ቆይታ …የሞት ፍርዱን እንደ ቀላል ነገር ተቀብሎ እየኖረ ካለ ነፍሰ ገዳይ ጋር ባንድ ማዕድ ቀርቦ መብላት …ከአእምሮ ህመምተኛ ጋር እጅና እግር ታስሮ ወደ ክሊኒክ በጠራራው ጸሃይ እየተጓተቱ የመጓዙ ስቃይ …
* በብሬማን ማዕከላዊ እስር ቤት ከኢትዮጵያን ታሳሪዎች ጋር ያሳለፍኩት አስደሳች አስገራሚና አሳዛኝ ጊዜ …ስለ ባህሩ ጉዞ ፣ ስለ እረኝነቱ ፣ ስለመጠጥ ዝግጅት አሻሻጡ ፣ ስለተደራጀው ስርቆት ከባለቤቶቹ የሰማሁት ታሪክ …
* በብሪማን ማዕከላዊ አስር ቤት የፍርድ ጊዜያቸውን ጨርሰው ለአመታት ወደ ሃገራቸው ለመግባት መንገዱ ተጠፍቶባቸው የተማረሩትን ጨምሮ ፣ ምንም ወንጀል ሳይፈጽሙ ለአመታት በእስር ስለሚንገላቱት ወንድሞች የሰማሁ ያየሁት ታሪክ…
* በብሪማን ማዕከላዊ እስር ቤት ከ500 የተለያዩ ሃገር ታሳሪዎች መካከል ከ50 በላይ ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች ፋሲካን ያከበርንበት የትንሳኤ ደማቅ ዓውደ አመት …
* በብሪማን ማዕከላዊ እስር ቤት በራሱ ወገን ተደብድቦ አይኑ የጠፋው ፣ ጥርሱና መንጋገው የረገፈ ፣ መላ ፊቱ የተበለሻሸ ፣ አጅ እግሩ የተሰባበረና የፈራረሰ፣ አካሉ እንደነገሩ የተጠገነውን ወንድም እሱም እኔም በሰንሰለት ታስረን በክሊኒክ ቤቱ የተገኘንበት ቀን …እና እኔ ከእስር ነጻ ወጥቸ እሱ ለተጎዳው ፍትህ ሳያገኝ ሊሴ ፖሴ ተሰርቶለት መሸኘቱን የሰማሁበት ክፉ ቀን …
* በእሰር ቤቱ መጸዳጃ በረንዳ ከፕላስቶክ ባልዲ ላይ ጺሜን በቴዲ እየተስተካከልኩ ነው ፣ ጸጉር ማስተካከያዋ በብልሃት የተገጣጠመች ናት። ኮረንቲውም ስለማይፈቀድ ከጣራው መብራት ተፈልቅቆ ከወጣው ገመድ እንደነገሩ የተያያዘ ነው፣ ብቻ ጸጉር ያጸዳል … በቀኝ በኩል ግማሽ ጺሜን ተላጭቸ ልጨርስ ስል ስሜ በማይክራፎን የተጠራ መሆኑን ሰምቻለሁ .. . እኔን መሆኑ አልገባኝም …ወዳለሁበት እየተንደረደሩ የመጡት ታሳሪ ጓደኞቸ ” ሰሓፊ መብሩክ ፣ መብሩክ !” “ጸሃፊ እንኳን ደስ ያለህ ! ” እያሉ ነጻ መውጣቴንን ልፈታ ስሜ መላኩን ከበው አበሰሩኝ … ግራ ተጋባሁ ፣ ተደናገጥኩ …የሆነውን ማመን እንደተቸገርኩ የማደርገው ግራ ገብቶኝ ስቅበዘበዝ የከበቡኝን ወዳጆቸን ወንድሞቸን በውል ሳልሰናበታቸው በሆታ ጭፈራ በደስታ ተለያየሁ …የደስታ የእልህ ስሜት ልቤን ሰቅዞት ፣ የለመድኩትን ህይዎት ፣ የለመድኳቸውን ታሳሪዎች መለየቱ ሌላ መከራ ሆነብኝ …በሰንሰለት ታስሬ እግሬን እየጎተትኩ የገባሁ የወጣሁበትን ወህኒ ድብልቅልቅ ባለ ስሜት ተውጨ ለቅቄ ወጣሁ …
* በብሪማን ማዕከላዊ እስር ቤት በራሱ ወገን ተደብድቦ አይኑ የጠፋው ፣ ጥርሱና መንጋገው የረገፈ ፣ መላ ፊቱ የተበለሻሸ ፣ አጅ እግሩ የተሰባበረና የፈራረሰ …ያልኳችሁን ወንድም ታሪክ ከእስር ቤት ወጥቸ ፈራ ተባ እያልኩ ጻፍኩት ፣ በቀናት ልዩነት ይህ ወንድም በጅዳ ቆንስል አማካኝነት ፍትህ ሳያገኝ ሊሴ ፖሴ ተሰርቶለት መሸኘቱንና ካጡ ከነጡ ድሃ ገበሬ ቤተሰቦች ጋር መቀላቀሉን ሰማሁ …ያ ክፉ ቀን …
* በዘንድሮው ክረምት በጅዳና አካባቢው የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች እረፍታቸውን በአልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ ከአመታት በፊት በሰላም ስፖርት የተጀመረውን አመታዊ ውድድር በማስቀጠሉ ረገድ የመዋደድ ያብባል ማህበር ያሳየው አበረታች ትጋት …
* የ2006 ዓም የምስል መረጃዎች …
በ2006 ዓም በስደተኛው ወገን ዙሪያ በርካታ የምስል መረጃዎች አቅርቤያለሁ ። ካቀረብኳቸው መረጃዎች መካከል አልፎ አልፎ “ሊያዩዋቸው የሚሰቀጥጡ ምስሎች ” እንደነበሩ አንዳንድ ወዳጆቸ ሳይቀር አጫውተውኛል ። በእኔ እይታ ደግሞ የቀረቡት ምስሎች እጅግ የማያስፉ
ከፉትን መርጨ መሆኑን ነው። ነገሩ እንዲህ ነው … መርጨ መራርጨ ያወጣኋቸው ምስሎችም ቢሆኑ ሊረብሹ ይችሉ ይሆናል ፣ በአካል ተጎጅዎችን አግኝቶ ህመማቸውን ከአንደበታቸው መስማት ፣ ከጉዳታቸው አሸራ ሰቆቃቸውን ማየት ብቻ የሃጢያት ያህል ይከብዳልና ተገፊውን በአካል ላየሁት ወንድማችሁ ከምስሎቹ በላይ የሚያመው የዜጋ በደልና መከራ አስረጅ መግለጫ አጣለሁ … በላዩ ላይ ” የተጻፈው መረጃ ሃሰት ነው!” የሚሉ የሚክዱት ሞልተዋል ። ኩነቶችን በጽሁፍና በንግግር ለማስረዳት አመኔታን ሳጣ ለማየት የማይመቹ የወገን ጉዳት ያረፈባቸውን አሻራ ገላጭ መረጃዎችን ለማቅረብ እገደዳለሁ ። ምስሉን የወገኔን መከራ ለቀረው እንዲያስተምር ፣ ህግ አስፈጻሚዎች የችግሩን ጥልቀት እንዲረዱት ለማድረግ ሙከራም እድጌያለሁ ። በ2006 ዓም የመጨረሻ ሰአታት እና ነገ በሚገባው አዲሱ የ2007 ዓም ሁኔታዎች ካላስገደዱኝ በቀር ተመሳሳይ “የሚረብሹ” የሚባሉ ምስሎችን ላለማውጣት ውሳኔ ላይ መድረሴን መግለጽ እወዳለሁ !
ይህች የመጨረሻ የማለዳ ወግ አጭር የግል ትዝታ ዳሰሳየ ናት … ደግሞ አዲሱ አመት ሊገባ ነው ፣ መልካም መልካሙን የምንሰማ የምናሰማበት ቀን ይሁንልን ብየ አሮጌውን 2006 ዓም ልሰናበት !
ነቢዩ ሲራክ
2007 ዋዜማ የመጨረሻ ሰአታት

Filed in: Amharic