>
5:18 pm - Friday June 15, 4136

ለአክራሪ እስልምና እንቅፋት የሆነች ሀገር-ኢትዮጵያ!!! (እውነት ሚድያ አገልግሎት)

ለአክራሪ እስልምና እንቅፋት የሆነች ሀገር-ኢትዮጵያ!!!

እውነት ሚድያ አገልግሎት

* ‹‹በሌሎች የዓለም ሀገራት ያለ ምንም እንከን፣ በቀላሉና በፍጥነት የተስፋፋው እስልምና ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ ለምን አዘገመ?›› 
*     *       *
✍️ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ‹‹ጽዮናዊ›› ቅሪቶች የአክራሪ እስልምና ተግዳሮት ሆነዋል፤ የእነዚህ አሻራዎች መሠረትና ጠባቂ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ ‹‹ወላሂ፤ ካላጠፋናት አናርፍም!›› ብለው የተማማሉባት ይመስላል!
✍️ ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት›› የሚለው ዋናው የአክራሪ ሙስሊሞች አለርጂ ነው፤ አሁን ደግሞ በተራቸው ‹‹ኢትዮጵያ የእስልምና ሀገር!›› ለማሰኘት እየሠሩ ይገኛሉ!
✍️ አክራሪ እስልምና ኢትዮጵያን ለመውጋት የተቸገረባቸው ሦስት መሠረታዊ እውነቶች አሉ፡- ታሪካዊ (ድል አድራጊነት)፣ የነቢያቸው ትእዛዝ (ሀበሻን አትንኩ) እና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ‹‹ኦርቶዶክሳዊ ሙስሊሞች›› መሆናቸው (አረባዊ ጠባይ የሌላቸው፣ ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር በፍቅር ለመኖር የሚሞክሩ)፡፡
✍️ ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት የአክራሪ እስልምና ዋነኛ ጠላቶች ተብለው ተፈርጀዋል፡- ክርስትናን እና እሴቶቹን በማይነቃነቅ መሠረት ላይ ጥለው አልፈዋል ብለው ያምናሉና!
✍️ የሰዎችና የቦታ አሰያየም በኢትዮጵያ ውስጥ የክርስትናው አሻራ ያለባቸው ናቸው፤ የኢትዮጵያ ምድር ብትቆፈር እንኳን ኦርቶዶክሳዊነቷን ልትክድ አትችልም፤ እናም….ኢትዮጵያ ለአክራሪ እስልምና የማትመች ሀገር ሆናለች!
✍️ አክራሪነትና አረባዊነት ግን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጠባይ ባለመሆኑ በጥንቱ መከባበር መሠረት የሃይማኖታቸው መለየት የልባቸውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ሳይከፍለው በፍቅር ጸንተው መኖር ይጠበቅባቸዋል፤ ከአጥፊዎች ጋር የመተባበር አዝማሚያ ከታየ ግን ኦርቶዶክሳውያን ሞት የማይፈሩ የሰማዕታት ልጆች መሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል!!!
‹በሌሎች የዓለም ሀገራት ያለ ምንም እንከን፣ በቀላሉና በፍጥነት የተስፋፋው እስልምና ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ ለምን አዘገመ?›› :- የሚለው ጥያቄ እና ምላሹን መፈለግ በተለይ የአረብ ሀገራት የጥናት ትኩረት ሳይሆን አልቀረም፡፡ እውነትም እስልምና ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ታሪካዊ ጊዜና አሁን በደረሰበት ደረጃ ለመሆን እንኳን የወሰደበትን ጊዜ ሌሎች ሀገራት ውስጥ ገብቶ ሙሉ በሙሉ እስኪቆጣጠራቸው ከወሰደበት ጊዜ፣ ጉልበትና ፋይናንስ አንጻር ሲታይ እጅግ ረዝሞ መታየቱ እውነትም ጥያቄ ያስነሣል፡፡
እናም እንደ አንዳንዶቹ ሀገራት የነበሩትን እሴቶች ሙሉ በሙሉ አጥፍቶ ‹‹አረባዊ›› ማድረግ ያልተቻለበት፣ የሕዝቡንም የኖረ ባህልና ታሪክ እስላማዊ አድርጎ መቅረጽ  በኢትዮጵያ ፈተና የሆነ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ በፖለቲካዊ እሳቤም ቢሆን የሀገርን ነጻነትና የሕዝቡን አንድነት በማዳከም የሚፈለገውን አስተሳሰብ በቀላሉ መጫን ሲቻል ይህ እንዳይሆን እንቅፋት የሆነ ነገር አለ ማለት ነው፡፡
አሁን ‹‹በሁሉም አቅጣጫ›› በሚባል ደረጃ የሀገሪቱ ነጻነት ምሥጢር፣ የሕዝቦቿም አንድነት ድርና ማግ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኗ በግላጭ እየተረዳ መጥቷል፤ ታሪክም ያንኑ አረጋግጦላቸዋል፡፡ እናም ይህቺን ተቋም ቸል ብሎ እስልምናን ማክረር ብሎ ነገር የሚታሰብ እንዳልሆነ ጠንቅቀው የተገነዘቡ ይመስላሉ፡፡ ‹‹ወላሂ! የጉዞ መሥመራችን እንቅፋት የሆነችውን ይህቺን ተቋምማ  ‹ልክ ማስገባት አለብን›› ብለው አልተማማሉም ብሎ ለመገመትም አይቻልም፡፡ ግን ለምን? እንዴት? አንዳንድ ተያያዥ ነጥቦችን ዘርዘር አድርገን እንመልከታቸው፡-
1) ‹‹ጽዮናዊ›› ቅሪቶች፡-የአክራሪ እስልምና ተግዳሮት በኢትዮጵያ!
ከጥንት ጀምሮ ሀገራችን ኢትዮጵያ ‹‹ሀገረ እግዚአብሔር››፣ ሕዝቦቿም ‹‹ሕዝበ እግዚአብሔር›› ተብለው በቅዱሳት መጻሕፍት ጭምር ሲመሰከርላቸው መቆየታቸው የጠላቶቻችንን ዐይን ደም ሲያለብስ እንደቆየ ይታመናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንኳን ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው ስም ከ#40 ጊዜያት በላይ ተደጋግሞ መጠቀሱ በተለይ የአረብ ሀገራትንና የአክራሪ እስልምናን አስተሳሰብ ሊጭኑባት የሚዳክሩ መሰል አካላትን ሊያስደስት አይችልም፡፡ ይልቁንም ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ ከእስራኤል ቀጥላ የክርስትና መሠረት›› መሆኗ በታሪክ ሲጠቀስ ከመስማት በላይ ራስ ምታት የሚሆንባቸው፣ ጨጓራቸውንም የሚልጥ ነገር ያለ አይመስልም፡፡  እናም ይህንን ታሪክ ለመቀልበስ እንቅልፍ ቢያጡ፣ ቁልቁለት ቢሮጡ፣ ዳገት ቢቧጥጡ ሊገርመን አይገባም፡፡
ኢትዮጵያ ያኔ ከብሉዩ ዘመን ጀምራ ከእስራኤልና እስራኤላዊነት ጋር የጠበቀ ቁርኝት የነበራት ከመሆኗም ባሻገር ዛሬም ድረስ እነዚያኑ አሻራዎች አጠናክራ መቀጠሏም ሌላው የአረብ ሀገራት ሆድ ቁርጠት ምንጭ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የአረብ ሀገራት እስራኤል የምትባል ሀገር ከገጸ ምድር ብትጠፋ በወደዱ ነበር፤ በዓለም ካርታ ላይ እንኳን ሊያዩአት የማይፈልጉ  እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሌሎች የዓለም ሀገራትን ሲዘረዝሩ የእርሷን ግን ‹‹ስሟን ቄስ ይጥራው›› በሚመስል አኳኃን ሆን ብለው የሚዘልሏት ዜጎቻቸውም አይጠፉም፡፡
እናም እንዲህ በግዘፍ ለምትታወቀዋ እስራኤል በዚህ ደረጃ ጥላቻ እያላቸው ሌላ ‹‹አማናዊ እስራኤልነት›› ብላ በሃይማኖቷ የምትመካ ሀገር ማየትና መስማት ምንኛ ይቀፍፋቸው! በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ጉርብትናዋን የጠሏት እስራኤል ከዚያም መልክዓ ምድር ተሻግራ አፍሪካ ውስጥ ሥርዓተ አምልኮዋን መነሻ አድርጎ በተሻለ ሃይማኖትና ሥርዓት እውን ሆኖ ሲያገኙት የተጠናወታቸው መንፈስ ባይጮህ ይገርም ነበር፡፡ ይህንን ‹‹እስራኤላዊነት›› መስተጋብር የፈጠረችው፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውንም ሃይማኖታዊና ባህላዊ መስተጋብሮች አመቻችታ ሳይቋረጥ በዘመናት ቀመር ውስጥ አልፎ ለትውልድ እንዲሸጋገር ያደረገችው ደግሞ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ናትና በእርሷ ላይ አለማተኮር አይቻላቸውም!
በመልክዓ ምድር ደረጃ (Geographically) በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ተጨባጭና አካላዊ እስራኤላዊነትን ሲያሻቻው በፖለቲካዊ እሳቤ፣ አልያም በአብዛኛው እንደሚያደርጉት ፊት ለፊት ጦርነት  ገጥመው ይገዳደሩታል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ያለውን ‹‹አማናዊ እስራኤላዊነት›› ተዋግተው ሙሉ በሙሉ የእስልምና ቀጠና ለማድረግ ግን ሌላ ስልት መቀየስ እንደሚያስፈልጋቸው የነቁ ይመስላሉ፡- የጽዮናዊ አስተሳሰቡ መሠረትና ባለቤት የሆነችውን ተቋም [ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን] አነጣጥረው መምታት፡፡
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እነርሱ ‹‹የአልነጃሺና የቢላል ሀገር›› የሚሏትን ኢትዮጵያን ‹‹እስራኤላዊ››፣ የሕዝቦቿንም አስተሳሰብ  ‹‹ጽዮናዊ›› ያደረገችው እንዴት ነው? በማሳያነት የሚቀርቡትስ ነጥቦች ምን ምን ናቸው? ጥቂቶቹን ብቻ እንመልከት፡፡
• የእስራኤላውያን ባህል (አመጋገብ፣ አለባበስ፣ የበዓላት አከባበር፣ የሐዘንና ደስታ ሥርዓቶች፣ ወዘተ.) እስካሁንም ተጠብቆና ወደ ትውልድ ተሸጋግሮ የኢትዮጵያውያን መደበኛ ባህል ሆኗል፡፡
• ኢትዮጵያ ታቦተ ጽዮንን ከእስራኤላውያን ወስዳ የራሷ ቅርስና የሃይማኖቷ ሥርዓት መፈጸሚያ ማእከል አድርጋለች፡፡ (ምንም እንኳን አክራሪ ሙስሊሞቹ በዚህ ባያምኑም) በዚህ ምክንያት ለእስራኤል ተሰጥቶ የነበረው ልዩ የእግዚአብሔር ጸጋ እና የታላቅነት ምሥጢር ከታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ጋር አብሮ ተላልፏል፡፡ ይህንንም እውነታ ጥበበኛው ንጉሥ ሰሎሞን በህልሙ ከምድር እስከ ሰማይ የብርሃን ዓምድ ተተክሎ ከእስራኤል ተነስቶ ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዝ ተመልክቷል (ደሴ ቀለብ፤ ታሪከ ነገሥት፤ ከምኒልክ ፩ይ እስከ ምኒልክ ፪ይ፣ 2007፡103)፡፡ ለዚህም ነው “መጽሐፍ ቅዱስ የእስራኤል ክብርና ግርማ ምንጩ ታቦተ ጽዮን መሆንዋን ሲያስረዳ በነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ታቦቷ በፍልስጤማውያን ስትማረክ  ኢካቦድ – ‘የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለችና ክብር ከእስራ ኤል ለቀቀ’ ብሎ የገለጸው (1ሳሙ.4፡21-22)፡፡
• የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀሳብና ልቡናም ከዚህች ታቦተ ጽዮን ተነጥሎ ሊኖር አልቻለምና ትክክለኛው ‹‹ጽዮናዊነት›› (Zionistic Ideology) በተጨባጭ እየተንጸባረቀ የሚገኘው በኢትዮጵያ ነው፡፡
• ምዕመናኑ በአካል ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው በመንፈስ ከሚረዱት ‹‹እስራኤል ዘነፍስነታቸው›› እና የያዕቆብ መባረክ ጸጋ የተነሣ ‹‹የእስራኤል አምላክ ሆይ…›› ብለው መማጸናቸው የተለመደ ነው፡፡
• እስከ ቅርብ ጊዜ [ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት] ድረስ  የእስራኤላውያንን ቅብዐ ነገሥት አካሄድ ስትከተልም ኖራለች፡፡ እነርሱም ሀገሪቱን በዚሁ የእሳቤ ማሕቀፍና አቅጣጫ ስለመሯት ክርስትና በሕዝቡ የአኗኗር ዘይቤና የፖለቲካ አመለካከት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ እንዲቀጥል ወሳኝ ሚና ተጫውታለች ይላሉ፡፡ አንድ ጸሐፊ፡- “Due to its link with the ‘divinely ordained’ Solomonic monarchy, Christianity inevitably was the core world-view of the political elite and a defining element of nationhood in a historical sense” ብሎ እንደተናገረው (Jon Abbink, An Historical-Anthropological Approach to Islam in Ethiopia: Issues of Identity and Politics. In: Journal of African Cultural Studies, Vol. 11, No. 2 (Dec., 1998; P.113). በግራኝ አህመድ ጊዜም በኢትዮጵያ ላይ የጂሃድ ጦርነት የታወጀው ይህንኑ አመለካከት የሚመራውን ክርስትናን እና የሰሎሞናዊውን ሥርወ መንግሥት መሥመር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅሎ ከሀገሪቱ ለማስወገድ እንደሆነ፡- “The stated aim of this war was to root out and destroy Christianity in the area and to end the Solomonic monarchy” ሲሉ ገልጸዋል (Jon Abbink, 1998:114)፡፡
በአጠቃላይ በእነዚህና በመሰል ምክንያቶች የተነሣ በእስራኤላውያን ዘንድ ብቻ ይታወቅ የነበረው ‹‹ጽዮናዊ›› አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታሰበው አክራሪ እስልምና አካሄዶች እንደ ትልቅ ተግዳሮት መታየቱ አልቀረም፡፡ ከክብረ ነገሥትና መሰል የታሪክ መጻሕፍት ጋር ያላቸው ጥላቻ መሠረትም ይኸው እውነት ብቻ ነው፡፡
2) ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት››፡-የአክራሪ ሙስሊሞች አለርጂ!
አክራሪ ሙስሊሞች ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት›› ከሚለው ንግግር በላይ የሚነስራቸው የለም፤ እነርሱ ኢትዮጵያ እንድትሆን ለሚያስቡት የእስልምና ቀጠና (Islamic State) የማድረግ ቅዥት ትልቅ እንቅፋት ይሆንባቸዋልና፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሙስሊሞችም ቢሆን ከዚህን በፊት በቅንነት ይገነዘቡት የነበሩትን ይህንን አገላለጽ ከተነገራቸው የተዛባ ትርጉም የተነሣ መጸየፍ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡
ይባስ ብሎ እጇን ዘርግታ በእግድነት ተቀብላ የፍቅርን መዓድ ያቋደሰቻቸውን፣ ለበርካታ ዘመናትም የአብሮነት ታሪክ የተጋራቻቸውን ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖትን እንደ ‹‹ያለፈበት ሥርዓት አቀንቃኝ›› እና ‹‹ጨቋኝ መደብ›› ማሰብ መጀመራቸው አሳዛኝ ነው፡፡ “From the Muslim side…in relation to the Orthodox understanding of Ethiopia as a ‘‘Christian Island’’, seen as continuation of past discriminatory sentiments…” እንዲል ጸሐፊው (Jörg Haustein & Terje Østebø (2011) EPRDF’s revolutionary democracy and religious plurality: Islam and Christianity in post-Derg Ethiopia, Journal of Eastern African Studies, 5:4, PP.767-68)፡፡
ከዚህም የተነሣ በቀደሙት ጊዜያት ይደረግ እንደነበረው ጥምቀትና መስቀልን በመሳሰሉ የአደባባይ ክብረ በዓላት ላይ ኦርቶዶክሳውያን ለበዓላቱ ማድመቂያ በሚለብሷቸው አልባሳት (T-Shirt) ላይ፡- ‹‹ኢትዮጵያ፥ የክርስቲያን ደሴት!›› የሚል ጽፈው ከለበሱ እንደ ትልቅ ወንጀል መቆጠር ተጀምሯል፡፡ በርካቶችም እንደድሮው በበጎ ሕሊና መረዳዳት ያለ መስሏቸው፣ ያን ያህልም የጠብ አጫሪነት መልእክት መስሎ ስለማይታያቸው በቅንነት ለብሰው ወደ አደባባይ ከወጡ በኋላ በፖሊስ ክፉኛ ከመደብደብም አልፈው ለእስር ተዳርገዋል፡፡
3) አክራሪ እስልምና ኢትዮጵያን ለመውጋት የተቸገረባቸው ሦስት መሠረታዊ እውነቶች
እስልምና አስተምሮ ከማሳመን ይልቅ በንግድ ሰበብና በጦርነት ኃይል የመስፋፋት ታሪካዊ አመጣጥ እንደነበረው በርካታ የታሪክ ድርሳናት የሚመሰክሩት ነው፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን ተመሳሳይ ጠባይና አካሄድ እንዳለው  “Islam in Ethiopia” የሚለውን የ Trimingham, J. Spencer  መጽሐፍ ያነበበ ሰው የሚረዳው ነው (Oxford University Press, 1952)፡፡ ነገር ግን አክራሪ እልምና በሌሎች ክፍለ ዓለማት በተለመደው አካሄዱ ኢትዮጵያን ለመውጋትና በቀላሉ ለመውረር የተቸገረባቸው ሦስት መሠረታዊ እውነታዎች ያሉ ይመስላሉ፡- ታሪካዊ ተሞክሮ (Historical Experience)፣ እምነታዊ ትእዛዝ (Religious Order) እና እሳቤያዊ ማሕቀፍ (Ideological Framework)፡፡
የመጀመርያው ታሪካዊ ተሞክሮ ነው፡- ይህቺን ሀገር በጦርነት ጥበብና በቴክኖሎጂ ዝማኔ ማሸነፍ ቀላል እንዳልሆነ፣ እንኳንስ ለእነርሱ በወቅቱ የሥልጣኔ ቁንጮ ላይ ለነበሩት ለአውሮፓውያን እንኳን ያልተንበረከከች፣ ጥቁሮች እንኳንስ ነጮችን ሊወጉ ቀርቶ ቀና ብለው እንኳን ለማየት በሚሳቀቁበት ዘመን እዚህ ግባ በማይባል መሣርያ ብቻ መግቢያና መውጫ አሳጥታ ያርበደበደች ሀገር መሆኗን ከአድዋ ታሪክ ጠንቅቀው ተረድተዋል፤ በዚህ ታሪክ አዋቂነታቸው ሊደነቁ ይገባል፡፡ በዚያውም ላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የተጠቁና ነጻነታቸውን በኃይል የተነጠቁ ሲመስላቸው የበለጠ የሚጠነክር ሰብእና እንዳላቸው ተገንዝበዋል፡፡ የዚህ ሥነ ልቦናዊ እሴት መሠረት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች የታሪክ ድርሳናት ተባብረው ይመሰክራሉ፤ እነርሱም አይክዱም፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ያኔ የገዛ ወገኖቼ እንኳን ባሳደዱኝ ዘመን ከነቤተሰቦቼ በፍቅር ተቀብለው በሰላም አስተናግደውኛልና ኢትዮጵያን አትንኩ!›› የሚለው የነቢያቸው መሐመድ ኑዛዜና እምነታዊ ትእዛዝ ነው፡፡ ምንም ቢሆን ትእዛዙን ያስተላለፈው ታላቁ ነቢያችን ብለው የሚመኩበት ነውና ከልባቸው ባይሆንም ሊያምኑበት ግድ ይላቸዋል፤ ክፉ ሊያስቡባት ሲሉም ይፈታተናቸዋል፡፡ እናም በግልጽ ጅሃድ ሊያውጁባት ይቸግራቸዋል፡፡ “…no jihad was directed against [Ethiopia]” እንደተባለው (Trimingham, J.S. Islam in Ethiopia. Oxford University Press, 1952:46)፡፡
ሦስተኛው ደግሞ ‹‹ኦርቶዶክሳዊ እስልምና›› የሚለው የአስተሳሰብ ማሕቀፍ በኢትዮጵያ ውስጥ መሠረት የያዘ መሆኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው እስልምናና ሙስሊሞች ዙርያ በርካታ ጥናቶችን ያጠኑ ምሁራን ሃይማኖቱን ‹‹ኦርቶዶክስ እስላም››፣ በኢትዮጵያውያ ያሉትን ሙስሊሞችን ደግሞ ‹‹ኦርቶዶክስ ሙስሊም›› ሲሉ ይገልጹአቸዋል (Trimingham, 1952:225)፡፡ ይህን ያስባላቸው ዋናው ምክንያቱ ደግሞ እስልምናው ዋናውን የጭካኔ አስተምህሮና አረባዊ ባህሉን ትቶ ኢትዮጵያዊ ባህልን ወርሶ፣ የክርስትናውን የጨዋነት ደንብ ተላብሶ የሚኖር ስለሆነ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም፡- ‹‹እስልምና ሰላም ነው›› የሚለውን ንግግር በተግባር እያስመሰከሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በሰላምና በፍቅር የሚኖሩ፣ በሀገራቸው ሕልውና ላይ የጠላት አደጋ ሲጋረጥም የሃይማኖታቸውን ልዩነት ሳያጎሉ  ለአንድነቷና ነጻነቷ በጋራ የሚፋለሙ ስለሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሂደቶችና እሴቶች ተደማምረው አክራሪ እስልምና ያሰበውን ያህል የክፋት እርምጃ በኢትዮጵያ ለማሳካት እንቅፋት እንደሆኑበት ለመገመት አያዳግትም፡፡
4) የኢትዮጵያ ነገሥታትና እስልምና
======================
በሀገሪቱ ቀደምት ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ ነገሥታት ቅብዓ ነገሥትን ቀብታ (Anointing Kings)፣ የበትረ ሥልጣኑን እውቅና ሰጥታ (Authorize) በንግሥና መንበሩ ላይ እንዲቀመጡ የማይተካ ሚና የነበራት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደነበረች ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ይህ የመቀባት፣ እውቅና የመስጠትና የማንበር ሥልጣኗ ደግሞ ቀድሞም በቅዱሳት መጻሕፍት የነበረ ሥርዓት ከመሆኑም ባሻገር በነገሥታቱ ዘንድ አንጻራዊ ተሰሚነት እንዲኖራት አድርጓታል (ደሴ ቀለብ፤ 2007፡133)፡፡
ከዚህም የተነሣ እነዚህ ነገሥታት ለእስልምናው መስፋፋት ‹‹በቂ ትኩረት አልሰጡም፣ ምቹ ሁኔታም አልፈጠሩም›› ተብለው በአክራሪዎቹ ይታማሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ‹‹የነገሥታቱ ችግር›› ተብለው ከሚጠቅሷቸው ነጥቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል [እነርሱ ‹‹ችግር›› ብለው ስለጠቀሱ ጉዳዮቹ በዚያው ደረጃ ብቻ መታየት አለባቸው የሚል ድምዳሜ ባይኖርም]፡-
• አስቀድሞ እንደተገለጸው የሀገሪቱ የእምነትና የባህል ይዘት ‹‹እስራኤላዊ›› ነጸብራቅ ስላለበት በተመሳሳይ መልኩ ነገሥታቱም ‹‹ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ…›› ብለው ራሳቸውን ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ሰሎሞናዊ መሥመር ጋር ማገናኘታቸው የተለመደ ነው፡፡ ይህ ሰሎሞናዊ የንግሥና መሥመርና ቅብብሎሽ እክል የገጠመው (በተለምዶ ‹‹ሕገ ወጥ›› የሚባለው) በአጼ ድል ነአድ እና በአጼ ይኵኖ አምላክ መካከል በትረ ሥልጣኑ በዛጔዎች እጅ በገባ ጊዜ ነበር (ደሴ ቀለብ፤ 2007፡212)፡፡ ስለዚህም ባለችበት ሀገር ላይ የጠሏትን እስራኤል ንግሥና መሥመርና ሥርዓት ኢትዮጵያ ድረስ አምጥታ የምታስቀጥል ቤተ ክርስቲያንና ነገሥታቱ ሁለቱም በእነርሱ ዘንድ ‹‹የተጠሉ›› ናቸው፡፡
• በሚደፉት አክሊል፣ በሚለብሷቸው የንግሥና አልባሳት፣ በሚይዙት በትረ ሥልጣን፣ በየማህተሞቻቸውና በሣንቲሞቻቸው ላይ ጭምር የመስቀል ቅርጽን ጨምሮ ሌሎች የክርስትና ሃይማኖት መለያ ምልክቶችን ሲያስቀምጡበት ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ የዛሬው ትውልድ እውነቱን ማስተባበል በማይችልበት ደረጃ ዛሬም ድረስ የቁፋሮ ጥናት (Archaeological Research) እና ጽሑፋዊ ድርሳናት (Scriptural History) ጭምር ከክርስትና አሻራ ንክኪ ነጻ ሊሆኑላቸው አልቻሉም፡፡ እናም ለሚያስቡት ‹‹ከክርስትና የጸዳች እስላማዊ መንግሥት›› ቅዥት የትውልዱን አእምሮ በውድም ሆነ በግድ ቢያጥቡ እንኳን ምድሪቱ አፏን ከፍታ ትመሰክርባቸዋለችና ይበሳጫሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በተለይም ኦሮምያ ላይ የትኩረቱ መጀመርያ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው አክራሪ እስልምና ‹‹የኢትዮጵያ ነገሥታት የኦሮሞ ሕዝብ ጠላቶች ናቸው›› የሚል የሀሰት ትርክት ለመፈብረክ የተገደደውም ከዚሁ አንጻር ነው፡፡ ከዚሁ ጋር አዳብለው ደግሞ ኦርቶዶክስንም ‹‹የነገሥታቱ ሃይማኖት›› ስለሚሏት ‹‹ከኑግ የተገኘሽ ሰሊጥ…›› ሊያደርጓት ያሤራሉ፡፡
እነርሱ ኦርቶዶክስን ‹‹ከነገሥታቱ ጋር ሆና እስልምናን ስትገፋ ኖራለች›› ብለው ይከሷታል እንጂ ራሳቸውም በግራኝ አህመድ 15 ዓመታት የመከራ ዘመናት እንዲሁም በልጅ ኢያሱ (ጥቂት ዓመታትም ቢሆን) ቤተ ክርስቲያኒቱን ምን ያህል እንዳሰቃዩአት የዘነጉ ይመስላሉ፡፡ ዛሬ በሀገራችን የተለያዩ አከባቢዎች የሚስተዋሉ የተዛነፉና የተነቀፉ ባህሎች (ከአንድ ሚስት በላይ ማግባትና የሱሰኝነት ችግሮችን ጨምሮ) የሙስሊሞቹ አገዛዝ ትርፍና አሻራ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ በወጉ ሥልጣን ላይ ባልነበሩባቸው በእነዚያ ጥቂት ጊዜያት ይህንን ያህል ጥፋት ካስመዘገቡ ከዚያን በኋላ በነበሩ ረጅም ዘመናት የንግሥና ዙፋኑ ላይ ቢወጡ ኖሮ ሀገሪቱን ምን ያህል ያከስሩአት እንደነበር ለመገመት አያዳግትም፡፡ ነገርዬው፡- ‹‹ተንኮሉን አውቆ እባብን እግር ነሳው›› እንደሚሉት ሆኖ ሀገራችን ከነ አኩሪ እሴቷና ቱባ ባህሏ ለዛሬ በቃች እንጂ ከጣልያን የግፍ አገዛዝ በአድዋ ብንድንም በአረቦች እጅ አዙር አገዛዝ ሥር መውደቃችን ግን አይቀሬ ነበር፡፡
እስልምና ለመስፋፋት ሲያስብ ዛሬ ከተወሰኑ ብሔሮች ጋር ተለጥፎ የነገሥታቱን ፖለቲካ እያራገበ ትርፍ ለማጋበስ ማሰቡ የሚደንቅ፣ አዲስ ስልትም አይደለም፡፡ ድሮም ቢሆን የወቅቱን ፖለቲካ አጥንቶ በዚያ እየታከከ የሚፈልገው ደረጃ ላይ ለመፈናጠጥ ሲጥር ቆይቷል፤ እንዳሰበው አልተሳካለትም እንጂ፡፡  እስልምና በተለይ ለሰሜኑ የሀገራችን ሕዝብ ጥላቻ ካላቸው ጋር ተጣብቆ ዒላማውን ከግብ ለማድረስ ሲጥር እንደነበር ‹‹እስልምና በኢትዮጵያ›› በሚል ሰፊ ጥናት አካሂደው ቱባ መጽሐፍ የጻፉት ምሁር እንዲህ ይገልጹታል፡-
 “Islam’s force of expansion amongst pagans in Ethiopia was helped by the fact that it was the religion hostile to that of the Amharic race who lorded it over them” (Trimingham, 1952:101).
እንደ አፍሪካም ቢሆን እስልምና የተስፋፋው በተመሳሳይ ስልት፣ ዘረኝነትን መነሻና ከለላ በማድረግ፣ በብሔር ፖለቲካም ተደግፎ እንደሆነ አጥኚው ምሁር ፡- “An important element in the spread of Islam in Africa has been Arab pride of race” ሲሉ አጋልጠዋል (Trimingham, 1952:141)፡፡ ከረጅም ዓመታትም በኋላ፣ ዛሬም ድረስ እስልምና በዚሁ የፖለቲካ ዘይቤ ለመስፋፋት ማሰቡ ያሳዝናል፤ ይደንቃልም፡፡
5) የሰዎችና የቦታ አሰያየም በኢትዮጵያ ውስጥ
=============================
 አክራሪ እስልምና ኦርቶዶክሳዊነትን በሰዎች ዘንድ ለማጥላላት ከሚጠበቅባቸው ፖለቲካዊ አካሄዶቹ መካከል ሌላኛው የስመ ክርስትና አሰያየም ጉዳይ ነው፡፡ በእነርሱ የተንሻፈፈ ትርክት መሠረት ‹‹ገብረ እግዚአብሔር›› የሚል ስም ለውሉደ ጥምቀት የሚሰጠው በክርስትና አስተምህሮው መሠረት ሳይሆን ‹‹ሆን ተብሎ ኦሮሞዎችን ወደ አማራነት ለመቀየር በማለም›› ነው፡፡  በዚህችው ማደናገርያ ብቻ በርካቶችን ከኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት አስወጥተዋል፡፡ እጅግ የሚገርመው ግን ‹‹ኦሮሞ ‹ገብረ እግዚአብሔር› መባል የለበትም›› ብሎ የሚከራከረው ራሱ ‹‹አብደላ›› የሚል ስም የያዘው ሙስሊም መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ቀመር መሠረት እግዚአብሔርና አላህ አንድ ከሆኑ (አይደሉም እንጂ) ‹‹ገብረ እግዚአብሔር›› ማለት የእግዚአብሔር አገልጋይ፣ ‹‹አብደላ›› (አብዱ-አላህ) ደግሞ የአላህ አገልጋይ ማለት ስለሆነ ሁለቱም አንድ ዓይነት መልእክት ያላቸው ስያሜዎች መሆናቸው ነው፡፡ በእነርሱ አመክንዮ እንሂድ ቢባል እንኳን ሁለቱም ‹‹የኦሮሞ ስሞች›› አይደሉም፡፡
ባይሆን ‹‹የትኛው ለኦሮሞ ይቀርባል?›› ብሎ መጠየቅ ሳይሻል አይቀርም፤ መልሱ ደግሞ ያለ ጥርጥር በኢትዮያዊው ግእዝ የተሰየመው ‹‹ገብረ እግዚአብሔር›› እንጂ አረባዊው ስያሜ ‹‹አብደላ›› ሊሆን ከቶ አይችልም!
ኢትዮጵያ ጥንቱን ክርስቲያናዊት ሀገር እንደነበረችና በሀገሪቱ ውስጥ አክራሪ እስልምና በቀላሉ መሠረት እንዳይይዝ ያደረገው ሌላኛው ነጥብ ደግሞ ምድሪቱ ራሷ የምትሰጣቸው ምስክርነቶች ናቸው፡፡ አሁንም ድረስ ለእነርሱ ራስ ምታት የሚሆኑባቸው ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃዎች በሀገሪቱ ምድር እምብርት ውስጥ አሉ፤ በየጊዜውም በሚደረጉት የቁፋሮ ጥናቶች አማካይነት እየወጡ አፍ አውጥተው ኦርቶዶክሳዊነትን ይመሰክሩላቸዋል፡፡  እናም እነዚህን ተጨባጭ ማስረጃዎች ላለማየት ሲሉ ከተቀበሩበት የሚያወጣቸው ምርምር ባይደረግ፣ ከወጡ ደግሞ ጠርገው ቢያስወግዷቸው፣ ፍቀው ቢያደበዝዟቸው ደስ ባላቸው ነበር፡፡
እነዚህ ‹‹ክርስቲያናዊ አሻራዎች›› የቦታዎችና  የሕዝብ ተቋማት ስያሜዎች፣ በቤተ መንግሥቱ ውስጥና ዙርያ ያሉ እሴቶች፣ ዓለም አቀፋዊ መዝገቦች ላይ የሰፈሩ ታሪካዊ የቱሪዝም መስህቦች፣ ወዘተ. የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡  ጥቂቶቹን ብቻ ለመዘርዘር ያህል፡-
• የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት (Palace) ዛሬም ድረስ ‹‹ሦስት መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉት›› አክራሪ ሙስሊሞቹ ይሞግታሉ፡- በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን መከበቡ፣ ዙርያውን የከበበው የብረት አጥር በመስቀል ምልክት የተሞላ መሆኑ እና የነገሥታቱን ክርስቲያዊ እምነት የሚገልጹ ቁሳቁሶች ጭምር ከፍተኛ ክብር ተሰጥቶአቸው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ መቀመጣቸው፡፡
• በመላው ሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ቦታዎች፣ ከተሞች እና አፍላጋት ሁሉ ‹‹እስራኤላዊነትን›› የሚያስታዉሱ ስያሜዎችን እንዲይዙ ተደርገዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ደብረ-ታቦር፣ ደብረ-ዘይት፣ ናዝሬት፣ ቀራንዮ፣ ሆሳዕና፣ ዮርዳኖስ፣ ወዘተ. የሚባሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
• የአንዳንዶች ከተሞችና ወረዳዎች አሰያየም ደግሞ ምንም እንኳን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ጋር የተዛመደ ባይሆንም ክርስትና በጥንቱ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምን ያህል የደመቀ አሻራውን አሳርፎ እንዳለፈ የሚያሳብቁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ደብረ-ብርሃን ከተማ ስያሜዋን ያገኘችው የዚያችው ከተማ ግርማ ሞገስ ከሆነው የቅ/ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነው (ብርሃን የወረደበት ስለሆነ)፤ የደብረ ጽጌ ከተማም ስያሜዋን የወረሰችው በዚያው ከምትገኘው የእመቤታችን ገዳም ነው፤ የደብረ ሊባኖስ ወረዳም እንደዚሁ የታላቁን አቡነ ተ/ሃይማኖት ገዳም ስያሜ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ታዲያ ዙርያችንን ሁሉ የሞሉ እነዚህ ሁሉ ምስክሮች እያሉ አክራሪ እስልምና እንዴት ይህቺን ሀገር ‹‹እስላማዊ መንግሥት›› ሊመሠርትባት ይቀለዋል?!
• በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ እንኳን የመንግሥትን እውቅና ያገኙ፣ የክርስትናን አሻራ የሚገልጹ የቀበሌዎችና ሰፈሮች፣ የጎዳናዎችና ማኅበራዊ ተቋማት ስያሜዎች በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ቀራንዮ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ…የሚባሉ ክፍለ ከተሞች አሉ፡፡ በሰፈር ደረጃ 41-ኢየሱስ፣ ቁስቋም ማርያም፣ ሳሪስ አቦ የሚባሉ ስያሜዎች አሉ፡፡
• ታክሲዎች እንኳን መዳረሻ ቦታዎችን ሲጣሩ፡- የአምስት ኪሎው ‹‹ማርያም፣ ማርያም››፣ የሃያ ሁለቱ ‹‹ዑራኤል፣ ዑራኤል››፣ የሰሜኑ አቅጣጫው ‹‹ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም›› እያለ ሲጣራ የአክራሪ ሙስሊሞቹን ጆሮ ጭው ያደርጋል፤ አልሆነላቸውም እንጂ እነዚህን የአክራሪ እስልምና ቀጣይ ዕቅድ እንቅፋቶች ባይሰሟቸው እጅግ ደስ ይላቸው ነበር፡፡
•  የክርስትና አሻራን የሚጠቃቅሱ የማኅበራዊ ተቋማት ስያሜዎችም እንደዚሁ በአክራሪዎቹ አይወደዱም፡፡ ለምሳሌ፡- ሆስፒታሎች (ቅዱስ ጳውሎስ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ አማኑኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ተክለ ሃይማኖት፣ ወዘተ.)፤ የባንክ ቅርንጫፎችም ቅ/ሥላሴ፣ ልደታ፣ አራዳ ጊዮርጊስ፣…ቅርንጫፍ ማለታቸውን ትተው አንዋር መስጊድ፣ ድሬ ሼክ ሁሴን፣ ዘምዘም፣ ወዘተ. ቅርንጫፍ ብቻ ቢባሉ በወደዱ፡፡
የእነዚህ ሁሉ ጸረ-አክራሪ እስልምና አሻራዎች ታሪካዊ መነሻ፣ ነባራዊ ጠባቂና መጻዒ አውራሽ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች በእነርሱ ዘንድ ምንኛ ትጠላ! ይህቺን ተቋም ሲሆን ለማጥፋት፣ ባይሆን አንድነቷን እየተፈታተኑ ለማዳከም እንቅልፍ አጥተው መሥራታቸውስ ለምን ይገርማል!? ቁልፉ መልእክት ግን አክራሪ እስልምና አረባዊ ጠባይ እንጂ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጠባይ አለመሆኑን መገንዘቡ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንስ ጥንቱን በመቻቻል ብቻ ሣይሆን በፍቅርና በመከባበር አብረው ኑረዋል፤ አሁንም እየኖሩ ናቸው፤ ወደፊትም የሃይማኖታቸው መለያየት የልባቸውን አንድነት ሳይከፍለው በአንድነት ጸንተው ይኖራሉ፡፡
Filed in: Amharic