>

የጤና ነው ወይ...?!? (አሰፋ ሀይሉ)

የጤና ነው ወይ…?!?

አሰፋ ሀይሉ

 

*  ከ340 በላይ ዜጎች በገጀራ፤ በቆንጨራ፤ በስለርና በጥይት ፤ እንዲሁም በድብደባ ብዛት ሕይወታቸውን አጥተዋል!
‹‹1,022 የመኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ ተሰባብረዋል፡፡ 
227 ሆቴሎች ተቃጥለዋል፣ ተሰባብረዋል፡፡ 
104 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወድመዋል፡፡ 
ከ10,000 በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ 
ከ1,000 በላይ ዜጎች ለአካል ጉዳት፣ ድብደባ፣ እንግልት ተዳርገዋል፡፡ 
20 የመንግሥት እና 273 የግል መኪኖች ተቃጥለዋል!››  – ይሄ ሁሉ ውድመት የደረሰባት አገር ጠ/ምኒስትሯ  ከኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር ጋቢና ላይ ፊጥ ብሎ መሪ ጨብጦ ሲዝናና የተነሳውን ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ለቆ ማየት በሰለባዎቹ ቁስል ላይ ጨው የመነስነስ ያህል አሰቃቂ ነው!
ከብዙ ክፍለ ዘመናት በፊት የሮማው ንጉሥ ኔሮ ሮም በእሣት እየተቃጠለች እርሱ በደስታ ስሜት ተሞልቶ በመኖሪያ ቤቱ ጊታር ይጫወት እንደነበር በአሳዛኝ ቀለም የተጻፈው የግል ታሪኩ ያወሳል፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት ጉደኛውን የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕንም ብዙ ዜጋቸው እንደዚያ እንደ ኔሮ ነው የቆጠራቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዚህ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ዜጎችን ህይወት እንደቀጠፈና ሚሊዮኖችን እንደለከፈ በሚነገርለት በአስከፊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መሐል ሆነው አሜሪካውያን የጭንቀት ምጥ እያማጡ ባለበት የመከራ ወቅት ላይ ዶናልድ ትራምፕ ከሌላ ቢሊየነር ጓደኛቸው ጋር ሆነው በጎልፍ ሜዳ እየተጫወቱ የሚያሳይ ፎቷቸው በሚዲያ በመለቀቁ ነው፡፡
እውነትም ግን – ምሳ እንኳ ብዙ ጊዜ የሚያልፈኝ – ከአብርሃም ሊንከን በስተቀር ብዙ ሰዓት በመሥራት የሚስተካከለኝ የለም – እያሉ የሚደሰኩሩት የህዝብ ሰው ዶናልድ ትራምፕ – እንዴት ዜጎቻቸው በጭንቀት እያማጡ፣ ዕለት በዕለት እየሞቱና ዘመድ አዝማድ ያልተጠራበት የኮሮና ቀብራቸው ዕለት በዕለት እየተፈፀመ – እርሳቸው እንዴት ቢያስችላቸው ነው የጎልፍ ጨዋታ የሚያምራቸው? ይሁን ይመራቸው ጨዋታው፡፡ እንዴት ቢያስችላቸው ነው ፊታቸውን ለካሜራ ደቅነው የተነሱትን ፎቶ ለህዝባቸው የሚለቁት? ይሄ አዲሱ ህዝብን የማፅናናት መንገድ ነው ወይ? አሜሪካውያን ግን እንደዚያ አልወሰዱትም፡፡ ከትራምፕ ፎቶ ሥር ሚሊየን ዓይነት የቁጣ አስተያየቶች ናቸው የዘነቡት፡፡
እኔም ሁኔታውን ተመልክቼ የትራምፕ ነገር ከጥንቱ የሮማ ንጉሥ ኔሮ ጋር ተመሳስሎብኝ ስገረም ነበር፡፡ መሪዎች ህዝቡን ሳይመስሉ ሲቀሩ የሚከሰተው ይሄው ነው፡፡ እያልኩም ነበር በልቤ፡፡ አንድ በ14ኛው ክፍለዘመን በምድረ እንግሊዝ በተከሰተ የባሮች አመጽን ተከትሎ ለብሪቲሽ ባሮኖች የተጻፈ የሥሞታ ደብዳቤ ላይ እንዲህ የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩበት፡- ‹‹ዜጎች ተከፍተው፣ ንጉሡ እንዴት በደስታ ሊሰክር ይችላል? ዜጎች አጥተው፣ ንጉሡ እንዴት ሊትረፈረፈው ይችላል? ዜጎች ተርበው፣ ንጉሡ እንዴት ጠግቦ ሊያድር ይችላል? ዜጎች ጠግበውስ፣ ንጉሡ እንዴት ተርቦ ሊያድር ይችላል?…›› እውነተኛ የህሊና ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ከዘመነ ኔሮ እስከ ዘመነ ትራምፕ ትክክለኛ መልስ ያላገኙ እውነተኛ የህሊና ጥያቄዎች፡፡
እና ሰሞኑን ከትራምፕ የጎልፍ መዝናኛ ፎቶ ጋር እነዚህን የቆዩ ታሪኮች እያሰብኩና እየከለስኩ ስገረምና ስብሰከሰክም ቆይቼ … ቀና እላለሁ – የኛው የራሳችን ጉድ ደግሞ ጉብ ብሎልኛል፡፡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አልኩኝ፡፡ የኛው ‹የአፍሪካው ዘመናይ ባለራዕይ ወጣት መሪ› አብይ አህመድ አሊ ደግሞ ከሚሊየነሩ ሯጭ ከኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር ጋቢና ላይ ፊጥ ብሎ መሪ ጨብጦ የተነሳውን ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ለቋል፡፡ በኢትዮጵያ የተገጣጠመችውን የመጀመሪያዋን የኤሌክትሪክ መኪና ከኃይሌ ሃዩንዳይ ካምፓኒ በሥጦታ ተሰጥታኝ ይኸው እያሽከረከርኳት ነው – ብሎ ነው የለጠፋት፡፡ የሥጦታ (የመኪና ቁልፍ ርክክብ) ሥነሥርዓቱን የሚያሳይ ሌላ አጃቢ ፎቶም አለ፡፡ ምን ጉድ ነው ግን ያመጣብን ዘንድሮ?
አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሞኑ ብቻ የተከሰተው አሰቃቂ የሰው ልጆች እልቂትና የንብረት ውድመት፣ እጅግ የበረታ ሀገራዊ ተቃውሞና የተቀሰቀሰው ቁጣ፣ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች እስርና የደጋፊዎቻቸው ዓለማቀፍ ጩኸት ባየለበት በዚህ ሰዓት፣ በዚህ በክረምት የሚፈናቀሉ ወገኖች በሜዳ ላይ ጎጆ እንደሌላቸው ወፎች ተበትነው ‹‹የፍትህ ያለህ፣ የመንግሥት ያለህ›› እያሉ አምርረው በሚጮኹበት በዚህ ሰዓት፣ ከ340 በላይ ዜጎች በቁጣ በነደዱ ቄሮዎች ታርደውና ተቀጥቅጠው ሕይወታቸውን በግፍ በተነጠቁበት በዚህ ሰዓት፣ የታሠሩ ፖለቲከኞቻችን ካልተፈቱ መንገዶችን ሁሉ እንዘጋለን ብለው ብዙ ዜጎች ለአመፅ በተነሳሱበት በዚህ አስከፊና አሳሳቢ ሰዓት፣ ገና የሟቾች ድንኳን እንኳን ሳይፈርስ… የስንት ሚሊየን ዜጎች ኃላፊነት የተጣለበት የሀገሪቱ መሪ… እንዴት እንዲህ አዲስ መኪና በነጻ ተሰጠኝ – እያለ የደስ-ደስ ፎቶዎቹን ለህዝብ በመልቀቅ ላይ ይሰማራል? የጤንነት ነው ወይ ይሄ? ይሄን የኛኑ እብደት ምን ዓይነቱ ኔሮነት፣ ወይ ምን ዓይነቱ ትራምፕነት እንበለው? ወይስ ምን ያለ ህጻንነት፣ ምን ያለ ጮርቃነት ነው? ወይስ እንደምን ያለ ሰው-ጤፉነት?
ነገሩ ‹‹ሁሉም ነገር አማን ነው፣ ተረጋግታችሁ ህይወታችሁን ምሩ፣ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም›› ብሎ ህዝብን ለማረጋጋት የታለመ ፕሮፓጋንዳ ብቻ ቢሆን እኮ – መቂያቂያሉ እንደተጠበቀ ሆኖ – ምንም አልነበረም እኮ፡፡ ነገሩ ግን ከዚያም በላይ ነው፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ ህዝብ በደረሰበት መከራ እያለቀሰ ባለበት በዚህ አሳዛኝ ወቅት – የሀገሪቱ መሪ – ዓይን ያወጣ የታሪክና የዝና ሽሚያ ላይ ራሱን አሰማርቶ መገኘቱ እኮ ነው የሚገርመው፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው እንግዲህ ዳግማዊ ምኒልክ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን መኪና ያሽከረከሩ መሪ ናቸው፡፡ እንዲያውም የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የተነዳችው መኪና ብሎ በሚያምር መከዳ ላይ አስውቦ – አዋሳ ኃይሌ ሪዞርት ሆቴል ውስጥ ተቀምጣ ያየኋት ታሪካዊ መኪና ትዝ አለችኝ፡፡ እስከማውቀው – የምኒልክ መኪና በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ዲስፕሌይ ተደርጋ ከቆየች ዘመን የላትም፡፡ እና የኃይሌ ገብረሥላሴ የታሪክ ሽሚያም የራሱን ትዝብት የሚያጭር ነገር ቢኖረውም – ቢያንስ ግን ወደ ሆቴሉ ለሚመጡ የውጭ ሰዎች ቀደምት የዘመናዊ ቱሩፋት ታሪካችንን ለማውሳት የሚሞክር ነው ብለን እንውሰደውና እንለፈው ይሁን፡፡ አሁንስ? አሁንስ ኃይሌንና ጠቅላዩን በመኪና ጋቢና ውስጥ ምን አገናኛቸው?
ሀገሪቱ በያቅጣጫው በተለኮሱ እሳቶችና ስጋቶች ታምሳለች፡፡ ግን ያው የመኪናው ጉዳይ ደግሞ ቀጥሏል! የአብይ-ኃይሌጥምረቱ ሲታይ ሰሞኑን ሆቴሎቼ ተቃጠሉብኝ ብሎ በየሚዲያው እሪ ሲል የሰነበተው ኃይሌ ከመቼው ከጉዳቱ አገግሞ ለአብይ አህመድ ስጦታ ወደመስጠት እንደተሸጋገረ ለሰሚው ግራ ቢመስልም – ያው ለጉዳቱ ማካካሻ እየተደረገለት መሆኑ ነው፡፡ ሃዩንዳይ ካምፓኒ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን የኤሌክትሪክ መኪና ለገበያ ሲያቀርብ የኖቤል ሽልማት በተቀበለው በአብይ አህመድ እየተነዳለት ለዓለም አስተዋወቀ ማለት ነው፡፡ አሪፍ አድቨርት ነው፡፡ አሪፍ የቢዝነስ ፕሮሞሽን ነው ለኃይሌ፡፡
መኪናዋን የነዳው መሪስ? መኪናዋን የነዳው መሪ ደግሞ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን የኤሌክትሪክ መኪና የነዳው መሪ እየተባለ ለመጠራት የታሪክና የዝና ሽሚያ ላይ ነው፡፡ አንዱ ምርቱን እያሻሻጠ፣ ሌላው ደሞ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪነቱንና ከምኒልክ ያልተናነሰ ታሪክ ሠሪነቱን እያሻሻጠ ነው፡፡
‹‹ሀብታም ለሀብታም ይጎራረሱ፣ ደሀ ለደሀ ይለቃቀሱ›› ይላል ያገራችን ሰው፡፡ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ፣ ጉልት ወጥተው ቃሪያና ቲማቲም፣ ከሰልና ድንች መቸርቸር ያቃታቸው፣ ልጅ-አባት-እናት-ወንድም-እህት የሞተባቸው፣ የሚይዙትን የሚጨብጡትን ያጡ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን በዚህች ሰዓት በጭንቅ ተይዘው ያለቅሳሉ፡፡ ሚሊየነሩ አትሌትና ሚሊየነሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ የነጻ መኪና ስጦታ ሲሰጣጡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ፎቶ ይለቀቅለታል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሚዲያና በኢትዮጵያ ህዝብ ሥልጣን ላይ ቁጭ ተብሎ ቁስና ዝና ይነገድበታል፡፡
ይሄም በደህና ጊዜ ቢሆን ባልከፋ፡፡ ግን የብዙ መቶዎች ኢትዮጵያውያን ደም እንደ ጅረት በሚፈስበት በዚህ ወቅት፣ ገና የብዙ ንጹሃን ወገኖች ደም ሳይደርቅ እኮ ነው – የሀገሪቱ መሪ ዓይኑን በጨው አጥቦ አደባባይ ወጥቶ ይሄን የዲታ ሾው የሚተውነው! ሀገር በጭንቅ እያማጠች – የኢትዮጵያን ህዝብ እግዜር ያፅናችሁ ያላለ መሪ – ዝናና ምርት ለማሻሻጥ – ባደባባይ መኪና ላይ ፊጥ ብሎ – ‹‹እዩልን-ስሙልን›› ላይ ተሰማርቶ መገኘት – እውነት ህሊና ላለው ሰው፣ ህሊና ላለው መሪ.. አያሳፍርም ወይ? እውነት የጤናስ ነው ወይ?
እንዴ? የእውነት ግን… ምን ነክቶናል እኛ ኢትዮጵያውያን? አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤሌክትሪክ መኪና ሥጦታዬን እዩልኝ ስሙልኝ የሚልበት ሰዓት ነው ወይ?  ኢትዮጵያ አሁን ምን ዓይነት ጭንቅ ውስጥ ነች? በሰሞኑ ብቻ በያቅጣጫው የተረጨው የስንት መቶ ኢትዮጵያውያን ደም ገና ከፈሰሰበት መሬት ላይ ሳይደርቅ ተራ የዝናና የታሪክ ሽሚያ ላይ ተሰማርቶ መገኘት እንደ ሀገር መሪ የህዝብ ትዝብት ላይ አይጥልም ወይ? አሁን በሰሞኑ ብቻ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የወደቀበት መከራ ስንት ነው? ከጥቂት ቀናት በፊት በቁጣ በነደዱ የኦሮሞ ቄሮዎች የነደደው ንብረት ምን ያህል ነው? … ቆይ ድጋሚ አይቶ ጉድ ለማለት ለሚሻ ከሁለት ቀን በፊት ‹‹የኦሮሚያ ክልል›› በይፋ አምኖ ለህዝብ ይፋ ያደረገውን የጉዳት አሃዝ አሁን ልድገመው፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት በሀገራችን ይሄ ሁሉ ሆኗል፡-
‹‹1,022 የመኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ ተሰባብረዋል፡፡
227 ሆቴሎች ተቃጥለዋል፣ ተሰባብረዋል፡፡
104 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወድመዋል፡፡
ከ10,000 በላይ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ከ340 በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ከ1,000 በላይ ዜጎች ለአካል ጉዳት፣ ድብደባ፣ እንግልት ተዳርገዋል፡፡
20 የመንግሥት እና 273 የግል መኪኖች ተቃጥለዋል፡፡››
ይሄ አልበቃ ብሎ ‹‹በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል›› እንዲሁ በዘራቸው እየተለዩ በቀስትና በጥይት የተገደሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዜጎች እንዳሉ የመንግሥት ዜና ይናገራል፡፡ ሀገር እንዲህ በጭንቅ ተውጣለች፡፡ ብዙ ህዝብ በሀዘንና በቁጣ ስሜት አንጀቱ እየተቃጠለ፣ ውስጡ እየነደደ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ ትኩስ መከራ በወረደበት ህዝብ መሐል ሆኖ ነው ጠቅላዩ ያለምንም ምንተ እፍረት፣ ያለምንም የህሊና ወቀሳ፣… ያለምንም ምንም…. በአደባባይ ወጥቶ .. ‹‹አዲሷን የኤሌክትሪክ መኪናዬን እዩልኝ ስሙልኝ›› ብሎ ፎቶዎቹን የሚለቀው፡፡
በበኩሌ ይሄ ሕዝብና ሀገር የጣለብህን ከባድ ኃላፊነት መዘንጋት ብቻም አይመስለኝም፡፡ ብሽሽቅም አለበት፡፡ ግን ሕዝብ በመከራ ላይ ተጥዶ እጅህን አጣጥፈህ እያየህ እየሰማህ… ከማን ጋር ነው ብሽሽቅ ውስጥ የምትገባው? ማን ሆነህ… ከማንስ አብራክ ወጥተህ ነው በህዝብ መከራ መሐል ሆነህ የህዝብ መከራ የማይሰማህ? የማይታይህ? የማይሸትህ? እንዴት ከህዝቡ መከራ መሐል ተገኝተህ የችግሩ፣ የሀዘኑ፣ የጭንቁና የምጡ ተካፋይ የመሆን የጨዋ ወጉ ቢቀርብህ… እንዲህ በህዝብ መከራና ደም ላይ ለመዘባበት የሚያስችል ሥልጣን ማን ሰጠህ? የምትዘባበትበት በሺኅዎች የሚቆጠር ፍጡር የሰው ልጅ፣ ያገር ዜጋ አይደለም ወይ? የፈሰሰው በመቶዎች የሚቆጠር ፍጡራን ደም – የሰው ልጅ ደም አይደለም ወይ?
በዚህ አስከፊ የክረምት ዝናብ ከቤቱ ተፈናቅሎ የሚጠለልበት ጣራ ያጣ ህዝብ መሐል ሆነህ… የዚህ ህዝብ መሪ ሆነህ… እንዴት የህዝቡ ጭንቅና መከራ ውል ሳይልህ ቀረ? በዚህ ሁሉ የመከራ ዶፍ መሀል – በዚህ ሰዓት – አሁን ላይ – ሚሊየነር ሆነህ እያለ – በነፃ መኪና ተሰጠኝ ብለህ ፎቶህን ለህዝብ ስትለቅ ትንሽ እንኳ እፍረት አዕምሮህን በጨረፍታ እንዴት አይዳስሰውም? ታትሮ ሠርቶ፣ በልቶ፣ ጠግቦ፣ ልጆቹን በሠላም አስተምሮ፣ ያለ እንባ ማደር በተሳነው መዓት የተቸገረ ህዝብ መሐል… የህዝብ መሪ ተብለህ… የአንተ የቅንጦትና የዝና ሽሚያ ግፍ አይሆንብህም ወይ? … አንዳንዴ ይህ ነገር… የጤና አይመስለኝም፡፡ እውነትም ኢንጂነር ይልቃል እንዳለው ነገረ-ሥራውን ሁሉ አስተውሎ ላየው – የጠቅላዩ የአዕምሮ ጤንነት በትክክልም ያጠራጥራል፡፡
ግን እንዲህ ማሰቢያችንን የሚደፍንብን፣ እንዲህ ህሊናችን ላይ እንደሞራ ተጋግሮ ህሊናችንን የሚደፍንብን፣ ሕዝባችንን የሚያስረሳን፣ በተስፋ አንጋጦ ሰማይ በሰቀለን ህዝብ ላይ፣ ቁልቁል አዘንብለን እንድንሸና የሚገፋፋን የህሊና መድፈኛችን ግን ከየትና በምን የሚመጣ ይሆን? ያለማሰባችን ምስጢሩ ምንድነው? አላውቅም፡፡ አንድዬ ይወቅ፡፡ እና አንድዬ ከዚህ ዓይነቱ ጥጋብም፣ ልክፍትም፣ ህመምም ይሰውረን ማለት ብቻ ነው፡፡ ሌላ ምን ይባላል?
ለነገሩ ምን ያድርግ መሪው? ህዝቡ የመከራ ዶፍ እየወረደበት ‹‹አሜን! ሺህ ዓመት ንገሥልን!›› ብሎ ከተቀበለ መሪው ምን ያድርግ? ህዝቡ ቢጭኑት አህያ፣ ቢረግጡት መሬት፣ ቢጋልቡት ፈረስ… ሆኖለት… መሪው ምን ያድርግ? ዋ ግና! ዋ! ዋ ለናንተ! ዋ ለናንተ የህዝብ እንባና ደም እንደ ወፍ ላባ ለቀለለባችሁ ባለጊዜዎች! ዋ ለናንተ! የግፉ ፅዋ ሞልቶ እየፈሰሰባችሁ ነው! ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ነበር እንዲያ ያለው…፡- ‹‹ዋ ለናንተ! ዋ ለናንተ.. የኢትዮጵያ ህዝብ እኔ የተነሳሁለት ዓላማ ገብቶት.. መከራው መርሮት የተነሳባችሁ ለታ! ዋ ለናንተ!››፡፡
እንደዚያ ነበር ያለው መንግሥቱ ነዋይ፡፡ መንግሥቱ ነዋይና ግርማሜ ነዋይ የተሰዉለት ሕዝብ የተነሳ ለታ – ያለችሎት፣ ያለፍርድ፣ ያለይግባኝ፣ ያለአማላጅ… ብስል ከጥሬ፣ ሽበት ጎፈሬ.. ሳይል… ሁሉንም ባንድ ሰብስቦ ነው መቃብር የጨመራቸው! ዋ… ለእናንተ! ዋ ለናንተ! የኢትዮጵያ ህዝብ… መከራው መርሮት የተነሳባችሁ ለታ! ዋ ለናንተ! እርሱ ይሁናችሁ!! በጊዜ ጤናውን ይመልስላችሁ!!!!
ፈጣሪ ቅድስት ምድሩን ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ! 
Filed in: Amharic