>

ሃገራችንን እንደዋዛ አጥተን የሙት ልጅ እንዳንሆን የምንሰጋ ብዙዎች ነን...!!! (መስከረም አበራ)

ሃገራችንን እንደዋዛ አጥተን የሙት ልጅ እንዳንሆን የምንሰጋ ብዙዎች ነን…!!!

መስከረም አበራ

ኢትዮጵያችን በፅኑ ህሙማን ክፍል ያለ ታካሚን ትመስላለች። ህመሟ ብርቱና ለዘመናት የተጠራቀመ ነው።ሁነኛ ሃኪም (ከመሪም ከተመሪም)ሳታገኝ በመኖሯ የቆየው በሽታዋ እየደረደረ፣በላዩ ላይ ሌላው እየተጨመረ በፅኑ ታማሚ አድርጓታል።
 ህመምን ማግኘት የመፍትሄው ዋነኛ አካል ነው። ማናቸውም ሃኪም ደግሞ አብሮ የኖረ ፅኑ ህመምን ላያገኝ ይችላል። ቀንቶት ህመሙን ያገኘ ሁሉም መፍትሄው ላይከሰትለት ይችላል።
 የሃገራችን ነገርም እንዲሁ ነው።ህመሟን እፈውሳለሁ የሚል ገዥ ቢፈራረቅባትም እድገቷን ቀርቶ ህልውናዋን ማስተማመኑ አልሆነም እያለ ነው።ሃገራችንን እንደዋዛ አጥተን የሙት ልጅ እንዳንሆን የምንሰጋ ብዙ ነን።
ይህ ስጋታችን የገባቸው ታላቁ ሰው ዶ/ር ሃይሉ ዓርአያ”ኢትዮጵያና አምስቱ ህልመኞች” በሚል ርዕስ ድንቅ መፅሃፍ ፅፈዋል።የሃገራችንን ዋነኛ የህመም ስፍራዎች፣በታሪክ የተጀመረ የለውጥ ጥንስስ ሁሉ ያልሰመረበትን ምክንያት እጥር ምጥን ባለ ሁኔታ አስቀምጠዋል። አሁን ያለውን ሃገር የማዳን ልፋትም በደንብ አድርገው ዳሰዋል። ነገሩ በጅምር እንዳይቀር ምን መደረግ እንዳለበት የአዋቂ ምክር በጨዋ ብዕር ከትበዋል።
አሁን ሃገራችንን የሚመሩ ወገኖች በተለይ ደሞ ጠ/ሚ አብይ መፅሃፉን ቢያነቡ በጣም ብዙ ይጠቀማሉ። እናንተም ብታነቡት ብዙ ታተርፋላችሁ።ሌላው ቀርቶ የአፃፃፍ ጨዋነታቸው፣ማንንም ለማብጠልጠል አለመሞከራቸው ይልቅስ ለሃገር ሊሰራ የሞከረውን ሁሉ በጎ ምኞቱን ለመረዳት መሞከራቸው ትልቅ ትምህርት ሰጪ ነው።
በዘመናዊው የሃገራችን ታሪክ ብቅ ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችን ቅን ምኞት ከመርዳቱ ጎን ለጎን ክፍተቱንም በጨዋ ብዕር አስቀምጠዋል፤ያጠፋው ሁሉ ያጠፋውም ሲሰራ እንደሆነ  አበክረው ገልፀዋል፤  ማንንም ከማብጠልጠል ተቆጥበዋል። ይልቅስ ያጠፋው ሁሉ ያጠፋው ምን ቢጎድለው ነው? ሲሉ የጎደለውን በግልፅ አስቀምጠው ትናንት ከፖለቲካችን ሰፌድ የጎደለውን እየሞላን ሃገራችንን ከማስቀጠል እንጅ ያለፈውን ከመርገም የሚመጣ ነገር እንደሌለ ጠቁመዋል። በሃገራችን በተለያየ ወቅት የተነሱ የፖለቲካ ሃይሎችንና ምሁራንን  ድርጊቶች ሁሉ ከፍርድ ርቀው ለመረዳት የሞከሩበት መንገድ አስደንቆኛል፣ድሮም አክባሪያቸው ነኝ ይበልጥ ገዘፉብኝ! ምነው በርከት አድርገው በፃፉ?!
 ያላነበበ ቀረበት
Filed in: Amharic