>
5:13 pm - Saturday April 19, 2487

ታዋቂ ሰዎች ዕርምጃ እንዲወሰድባቸውና ንፁኃን እንዲታፈኑ አቶ ጃዋር መሐመድ ትዕዛዝ መስጠቱን ፖሊስ አስታወቀ (ታምሩ ጽጌ)

ታዋቂ ሰዎች ዕርምጃ እንዲወሰድባቸውና ንፁኃን እንዲታፈኑ አቶ ጃዋር መሐመድ ትዕዛዝ መስጠቱን ፖሊስ አስታወቀ

ታምሩ ጽጌ

‹‹ሰላም ለማውረድ መንግሥት በማይገባበት እየገባሁ ትጥቅ ሳስፈታ የነበርኩ እንጂ ነፍሰ ገዳይ አይደለሁም››

ተጠርጣሪ አቶ ጃዋር መሐመድ

‹‹ምርመራው በፖሊሶችና ዓቃቤ ሕግ የሚከናወን እንጂ የማንም ጣልቃ ገብነት የለበትም››

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን

ከአንድ ወር በፊት በድንገት ከተገደለው የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥሮ በእስር ላይ የሚገኘውና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) በቅርቡ የተቀላቀው አቶ ጃዋር መሐመድ፣ የታዋቂ ሰዎች አድራሻ ተለይቶ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸውና ንፁኃን እንዲታፈኑ ትዕዛዝ ማስተላለፉን በምርመራው እንዳረጋገጠ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት ተናገረ፡፡

አቶ ጃዋር በበኩሉ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹ሰላም ለመፍጠር መንግሥት መግባት በማይችልባቸው ቦታዎችና አካባቢዎች በመግባት፣ ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑ ታጣቂዎች ትጥቅ ያስፈታሁ እንጂ ነፍሰ ገዳይ አይደለሁም፤›› ብሏል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድንና አቶ ጃዋር ይህንን የተናገሩት፣ ሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ በልደታ ማስቻያ ችሎት ለሦስተኛ ጊዜ ቀርበው ነው፡፡

መርማሪ ቡድኑ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በነበረው ችሎት በተፈቀደለት 14 ቀናት የምርመራ ጊዜያት ውስጥ ባከናወነው የምርመራ ሥራ፣ አቶ ጃዋር ያደራጀውን ሕገወጥ ቡድን የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ ንፁኃን እንዲታፈኑ ሊያደርግ እንደነበር ማረጋገጡን አስረድቷል፡፡ የመኖሪያ ቤቱ በድጋሚ ሲፈተሽ ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ዘመናዊ የሳተላይት መሣሪያዎች ማግኝቱንና መሣሪያዎቹ ከኢትዮ ቴሌኮም ዕውቅና ውጪ የሚሠሩ ከመሆኑም በላይ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከኔትወርክ ውጭ ቢሆን እንኳን ከየትኛውም ዓለም ጋር ግንኙነት ማድረግና መረጃ መለዋወጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ማረጋገጡን ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪው በዚህ ዘመናዊ መሣሪያ የታዋቂ ሰዎችን ንግግር በመጥለፍ ያዳምጥ እንደነበርና አድራሻቸው ተለይቶ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ትዕዛዝ መስጠቱን፣ ምስክሮች መናገራቸውን መርማሪ ቡድኑ ጠቁሟል፡፡

አቶ ጃዋር የድምፃዊ ሃጫሉ አስከሬን ከቡራዩ ኬላ እንዲመለስ ያስደረገው ለአሥር ቀናት በማቆየት የዳግማዊ ምንሊክ ሐውልትን በማፍረስ በቦታው ለመቅበር፣ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ያለውን መንግሥት በማባረር ሥልጣን ለመያዝ በማለም መሆኑን በምስክሮች ማረጋገጡን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪው እንዴት እንዳስገባቸው የማይታወቁ ሕገወጥ የሳተላይት መሣሪያዎችን ያስገጠመው፣ ከውጭ አገር ባስመጣቸው ባለሙያዎች መሆኑንም አክሏል፡፡

የድምፃዊ ሃጫሉን ሞት ምክንያት በማድረግ ተጠርጣሪው በኦሮሚያ ክልል በሻሸመኔ፣ በአርሲ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በባቱ፣ በባሌና በተለያዩ አካባቢዎች ባስተላለፈው ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የብሔር ግጭትና የአመፅ ጥሪ፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና በርካታ ንብረቶች መውደማቸውን ተናግሯል፡፡ ይህንን የሚያጣራ 17 የምርመራ ቡድን ወደ ሥፍራው መላኩንና እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባደረገው ምርመራ 109 ሰዎች መሞታቸውን፣ በ187 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን፣ 44 ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች መቃጠላቸውን፣ ሁለት ሐውልቶች መፍረሳቸውን፣ 328 የግል መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ 199 የንግድ ድርጅቶችና ሁለት  ፋብሪካዎች መቃጠላቸውን፣ 70 የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት መሰባበራቸውን፣ መዘረፋቸውንና መቃጠላቸውን፣ 26 የግል ተቋማት፣ አንድ የእምነት ተቋምና 53 ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን፣ መሰባበራቸውንና መውደማቸውን ከመርማሪ ቡድኑ ከተላከለት ሪፖርት ማወቁን ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ የምርምራ ቡድን በተሰጠው የ14 ቀናት የምርምራ ጊዜ ውስጥ ለቴክኒክ ምርመራ የላካቸውን ሰባት ሽጉጦች ምርመራ ውጤት መቀበሉን፣ ተጠርጣሪው የኦኤምኤን ሚዲያ አመራር እንደነበርና ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ የአመፅ ጥሪ በቀጥታ ሥርጭት ያስተላለፈውን ትዕዛዝ የሚያረጋግጥ ማስረጃ መሰብሰቡንም አሳውቋል፡፡ የአሥር ተጠርጣሪዎችንና የ25 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ ከላይ በተጠቀሰውና ገና በምርመራ ላይ በሚገኘው በአዲስ አበባ በተፈጠረ ቀውስ ከ166 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን ማወቁንም፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ አቶ ጃዋር የጦር መሣሪያ በመግዛትና ወጣቶችን በማደራጀት ያስታጥቅ እንደነበር፣ እነዚህ ታጣቂዎች የድምፃዊ ሃጫሉ አስከሬን ከቡራዩ ኬላ እንዲመለስ ሲያደርጉ ቡራዩ ላይ በፈጠሩት ተኩስ አራት ሰዎች መገደላቸውን፣ አራት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉድለት መድረሱንና ከሰባት ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ንብረት መውደሙን የቡራዩ ከተማ አስተዳደር በማስረጃ እንዳረጋገጠለት፣ የተለያዩ ግብረ አበሮቹን በቁጥጥር ሥር እያዋለ መሆኑንና ይህንን ሥራውን የሚያረጋግጥ የሰነድ ማስረጃ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ማያያዙንም መርማሪ ቡድኑ አብራርቷል፡፡

ተጨማሪ የምስክሮች ቃል መቀበል፣ በንፁኃን ላይ የተፈጸመውን ጉዳት የሚያረጋግጥ የሕክምና ማስረጃ ሰነድ መሰብሰብ፣ ለቴክኒክ ምርመራና ለባለሙያ ትንተና የተሰጡ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ምርመራ ውጤት መሰብሰብ፣ በተፈጠረው ቀውስ በመንግሥትና በግል ተቋማት ላይ የደረሰውን የንብረት ውድመት ግምት ለማወቅ የተጻፈ ደብዳቤ ምላሽ መቀበል፣ ለምርመራ ከተላከው ቡድን የሚመጣ የምርመራ ውጤት ለመቀበልና ሌሎች ቀሪ የምርመራ ሥራዎችን ለመፈጸም ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ዘጠኝ ጠበቆች የቆሙለት አቶ ጃዋር ጠበቆቹ መርማሪ ቡድኑ ላቀረበው የምርመራ ሥራ ሪፖርት መከራከሪያ ሐሳብ ከማቅረባቸው በፊት፣ የሚያመለክተው ነገር እንዳለ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ አቶ ጃዋር ፍርድ ቤት መቅረብ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የሚገኙት የመንግሥት ሚዲያዎች ብቻ ናቸው ብሏል፡፡ እነሱ ደግሞ ሪፖርት የሚያደርጉት መንግሥት የሚያቀርበውን ክስ ብቻ መሆኑን፣ በዚህም ስሙ እየጠፋ በመሆኑ የግልም፣ የመንግሥትም ሁሉም ሚዲያዎች እንዲገቡ እንዲፈቀድ ወይም ሁሉም እንዲከለከሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡ ጠበቆቹም ተመሳሳይ አቤቱታ በማቅረብ የአቶ ጃዋርን አቤቱታ አጠናክረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ወዲያውኑ በሰጠው ምላሽ በፍርድ ቤት ተገኝቶ ችሎት እንዳይገባ የተከለከለ ሚዲያ እንደሌለ አስታውቆ፣ ችሎቱ ግልጽ መሆኑንና እንዳይገባ የተከለከለ ሚዲያ ካለ አቤቱታ አቅርቦ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ከተያያዘ ትዕዛዝ ከሚሰጥበት በስተቀር፣ ‹‹ይህኛው ሚዲያ ይግባ፣ ያኛው ሚዲያ ይከልከል›› የሚል ሥራው ውስጥ እንደማይገባ አስታውቋል፡፡ ሚዲያዎች የችሎት ውሎን ከመዘገብ ባለፈ ሌላ ነገር ሪፖርት ያደረጉት ካለ በግልጽ ጠቅሰው እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ በጥቅሉ ሚዲያው አቋም ይዟል ማለት ተገቢ እንዳልሆነም አስታውቋል፡፡

አቶ ጃዋር በመቀጠል ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው በአንድ ወር የእስር ጊዜው እንዳረጋገጠው፣ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪዎች ፕሮፌሽናል መሆናቸውን ነው፡፡ ‹‹ለዚህም ለፖሊሶቹ ክብር አለኝ፣ ነገር ግን የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለ፡፡ የምርመራ ሒደቱን ለፖለቲካ ፍጆታ እያዋሉት ነው፤›› ብሏል፡፡ ከሃጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ አስከሬን እንዲመለስ ተደርጎ ኦሮሚያ ብልፅግና ጽሕፈት ቤት ሲገባ በር ላይ አንድ ፖሊስ እንደተገደለ ሲነገር ከርሞ ቆይቶ፣ አሁን ደግሞ ውስጥ በተተኮሰ ጥይት እንደተገደለ እየተገለጸ መሆኑንና የጦር መሣሪያ ቁጥርም እየጨመረ የእሱም ጠባቂዎች በሕገወጥ መንገድ የተደራጁ እንደሆነ እየተገለጸ ያለው፣ ከዋናው ምርመራ ያፈነገጠና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መኖሩን የሚያሳይ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

እንደ አቶ ጃዋር ገለጻ፣ ዘጠኝና አሥር ክላሽንኮቭ የሚባለው በሕገወጥ መንገድ የተገኙ ሳይሆን፣ ከመንግሥት ተፈቅዶ የተሰጡት መሣሪያዎች ናቸው፡፡ አራት ጠባቂዎቹም የፌዴራል ፖሊስ አባል የነበሩና መንግሥት መድቦለት በስምምነት እሱ ዞን የቀሩ እንጂ፣ ከጫካ ያሰባሰባቸው ወንበዴዎች አይደሉም ብሏል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት አባላቱም የመንግሥት ግዴታን በአግባቡ ፈጽመው መልቀቂያ (ክሊራንስ) ተሰጥቷቸው፣ ለእሱም ሕይወትና ለመንግሥትም ጥንቃቄ ሲባል በደኅንነት ማንነታቸው ተረጋግጦ አጃቢዎቹ እንዲሆኑ የተደረጉ መሆናቸውን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከፕሬዚዳንቱ ጋር ሲንቀሳቀስ አብረውት የሚንቀሳቀሱ ታማኝ ሰዎች እንጂ ከየትም ዝም ብለው የመጡ እንዳልሆኑ አስረድቷል፡፡

መንግሥት ሊደርስባቸው በማይቸሉ ቦታዎች በምዕራብና በደቡብ የተለያዩ አካባቢዎች ከአባ ገዳዎች ጋር በመሄድ ሰላም እንዲሰፍን ከአንድ ሺሕ በላይ የጦር መሣሪያዎችን ያስፈታ እንጂ፣ ነፍሰ ገዳይ አለመሆኑንም ተናግሯል፡፡

በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለመፍታት ከሞያሌ እስከ ቦርደዴ ድረስ በመጓዝ በአካባቢዎቹ ያሉ የአገር ሽማግሌዎችን በማምጣት የማስታረቅና የማስማማት ሥራ ሲሠራ የነበረው፣ ሰላም እንዲሰፍንና ሽግግሩ እንዲሳካ እንጂ ለሌላ ጉዳይ አለመሆኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በአማራና በኦሮሞ መካከል የነበረው ልዩነት እንዲፈታ ውይይት መደረግ እንዳለበት ያቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት በተደጋጋሚ ጊዜ ውይይት እንዲደረግ ማድረጉንም አክሏል፡፡ በብሔርና በሃይማኖት ግጭት እንዲነሳ አድርጓል የሚለውም ትክክል እንዳልሆነና እናቱ አማራና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ፣ ባለቤቱ ፕሮቴስታንት መሆናቸውን ጠቁሞ ጉዳዩ የወንጀል ሳይሆን የፖለቲካ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ይህም ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረ የፖለቲካ ችግር መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ፖለቲከኛ በመሆኑና ከምርጫ ውጪ ለማድረግ የተሠራ የፖለቲካ ጨዋታ በመሆኑ፣ ሊፈታ የሚችለው በውይይት ብቻ እንደሆነም አስረድቷል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ፍርድ ቤቱን፣ ፖሊስንና ዓቃቤ ሕግንም ማንገላታት ስለማያስፈልግ፣ ‹‹መንግሥት በእስር እንድቆይ የሚፈልገውን ያህል ጊዜ ይንገረኝና የሚጠቅም ከሆነ እቆያለሁ፡፡ እኔና እስክንድር ነጋ ያለን መስመር የተለያየ መሆኑ እየታወቀ በተመሳሳይ ጉዳይ ተጠርጥረን መታሰራችን የሚያሳየው ጉዳዩ ፖለቲካ መሆኑን ብቻ ነው፤›› ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ የአቶ ጃዋርን ንግግር በማስቆም፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ የመንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ አይደለም፡፡ የመናገር ነፃነትዎን ልጠብቅልዎ ብዬ ነው፡፡ በዚህ ችሎት መናገር የሚችሉት ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ወይም ፍርድ ቤቱ የሚያስተናግደው የሕግ ጉዳዮችን ብቻ ነው፤›› በማለት አስቁሞታል፡፡

ጠበቆቹ በመቀጠል የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ‹‹ሠርቻለሁ›› ያላቸው የምርመራ ሒደቶች፣ ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት ያቀረበውን በድጋሚ በማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተሰጠው ጊዜ በትጋትና በስፋት እየሠራ አለመሆኑን የሚያሳይ የምርመራ ሒደት መሆኑንና በአንድ ወር ውስጥ የሰነድም ሆነ የሰው ማስረጃ መሰብሰብና ማጠናቀቅ ሲገባው ይህንን ባለማድረጉ፣ ምርመራው መቼ እንደሚያበቃ እንደማይታወቅና የምርመራውን ፋይዳም እያሳየ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ወደ ክልል ተልኳል ስለተባለው የምርመራ ቡድንም ጥርጣሬ እንዳላቸውና ሆን ተብሎ ደንበኛቸውን (አቶ ጃዋርን) የማጉላላት ሥራ እንደተያዘ ጠቁመዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ምስክር ያደረጋቸው ሰዎች በአቶ ጃዋር ላይ ምን እንደመሰከሩና ምን እንደሚቀረው በግልጽ ለይቶ አለመናገሩን፣ በኦኤምኤን ሚዲያ ተናግሯል ስለተባለው ጉዳይም የአንድና የሁለት ቀን ሥራ በመሆኑ መጠናቀቅ እንደነበረበት ለፍርድ ቤቱ አስረድተው፣ መርማሪ ቡድኑ ያቀረባቸው ምክንያቶች ከደንበኛቸው ነፃነትና ሕገ መንግሥታዊ መብት አንፃር ሲመዝኑት ሚዛን የማይደፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምርመራው ከውስብስብ ወደ ቀላልና የቱ ጋ እንደሚቆም ከመገመት ይልቅ እየተወሳሰበ መሄዱን ጠቁመው፣ መርማሪ ቡድኑ የወደሙ ንብረቶችን ዝርዝር ካወቀ ‹‹ግምቱን አላወቅሁም›› ማለት እንደማይችልና ምን ያህሉን ንብረት ግምት አውቆ የምን ያህሉ ንብረት ግምት እንደቀረው ከማሳወቅ ይልቅ፣ በጥቅሉ በመናገር እያወሳሰበው መሄዱን ጠበቆቹ ብለዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የሰነድ ማረጃዎችን የሚሰበስበው ከመንግሥት ተቋማት መሆኑን ጠቁመው፣ ቀሩኝ ያላቸውን የዓይን ምስክሮች አድራሻ እያፈላለገ መሆኑን ከመግለጽ አኳያ የማግኘት ዕድሉ አጠራጣሪ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሰው አስሮ ማስረጃ የሚፈለገው ማስረጃውን ለማግኘት አስፈላጊ ሲሆን ብቻ እንደሆነ የሚደነግገውን መርህ የሚጥስ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ቡድኑ የተወሰኑ ምርምራዎችን ማጠናቀቁን ገልጾ በመንግሥትና በግል ተቋማት የደረሰውን የንብረት ውድመት ሪፖርት በደብዳቤ ጠይቆ እየተጠባበቀ መሆኑን አስታውሰው፣ የንብረቱ ዓይነት፣ መጠንና እስከ መቼ እንደሚጠብቅና ከተጠርጣሪው ጋር የሚያያይዘውን በግልጽ ማሳየት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ጉዳዩ ወንጀልና ከባድ በመሆኑ ከአቶ ጃዋር ጋር የሚያገናኛቸውን ነገሮች መርማሪ ቡድኑ በግልጽ ማሳየት እንዳለበትም አክለዋል፡፡ በመርህ ደረጃ በቂና አሳማኝ ምክንያት ስለሌ የአቶ ጃዋር መታሰር ለምርምራ የሚረዳ ባለመሆኑ፣ የተጠየቀው የ14 ቀናት የምርምራ ጊዜ ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ በዋስ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡

አቶ ጃዋር የመናገር መብቱን ተጠቅሞ በኦኤምኤን ሚዲያ ባስተላለፈው ንግግር ጉዳት ደርሷል ከተባለ ጉዳቱንና ንግግሩን አገናኝቶ ምን ውጤት እንዳስገኘ መርማሪ ቡድኑ ባላስረዳበት ሁኔታ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ ተገቢ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ ምን ያህል የጦር መሣሪያዎች የቴክኒክ ምርመራ ተደርጎላቸው ምን ያህል እንደቀሩ መታወቅ እንዳለበትም ጠይቀዋል፡፡

አቶ ጃዋር መጀመርያ የተጠረጠረበት ወንጀልና አሁን እየቀረበበት ያለው የምርመራ ውጤት እንደማይገናኝ ጠቁመው፣ በአጭር ጊዜ ተጣርቶ መጠናቀቅ ያለበትን ምርመራ ከአንድ ወር በላይ እንዲወስድ ማድረግ ተጠርጣሪው በፍርድ ቤቱ ላይ መጥፎ አንድምታ እንዲኖው የሚያደርግ መሆኑንም ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡ በመርማሪ ቡድኑ የምርመራ ሪፖርት ላይም ጥርጥሬ ስላላቸው ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ወስዶ እንዲመለከትላቸውም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን አቶ ጃዋርና ጠበቆቻቸው ላቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ ባቀረበው የመቃወሚያ ሐሳብ እንዳስረዳው፣ እያከናወነ ያለው ምርመራ አንድ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ አይደለም፡፡ የምርምራ ሒደቱ እየሰፋ የሚሄድና ውስብስብ መሆኑን፣ በሰውም ላይ ሆነ በንብረት ላይ የደረሰን ጉዳት በደንብ መመርመርና ውጤቱን ማወቅ ተገቢ እንደሆነ፣ የወደመ ንብረትና መጠኑን ማወቅም የተለያየ ነገር መሆኑን፣ የጉዳቱን መጠን ለማወቅ የባለሙያዎች ትንተና ስለሚያስፈልግ ጊዜ እንደሚወስድና መጠኑን እንደማወቅ ቀላል እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

የአቶ ጃዋርን የተከሳሽነት ቃል አለመቀበሉን አረጋግጦ ምክንያቱ ደግሞ ማስረጃዎቹን ሰብስቦ ከጨረሰና እሱን የሚመለከተውን ጉዳይ ከለየ በኋላ፣ ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎችን በማንሳት ለመቀበል መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ተናግሯል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ኃላፊነት ወስዶ በታማኝነት የሚሠራ እንጂ፣ ለፍርድ ቤቱ የሐሰት ሪፖርት እንደማያቀርብ በመግለጽ ጠበቆቹ ወደ ክልል ተልኳል ስለተባለው የምርመራ ቡድን እምነት እንደሌላቸው ለገለጹት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ስለኦኤምኤን ሚዲያ የገለጸው ዝም ብሎ ሳይሆን፣ ብዙ ሕይወት የጠፋው ተጠርጣሪው በቀጥታ ባስተላለፈው የአመፅ ጥሪ መሆኑን በማስረጃ ስላረጋገጠ መሆኑንም አክሏል፡፡ በኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የተገደለው የኦሮሚያ ፖሊስ አባል፣ የተጠርጣሪውን አጃቢዎች ትጥቅ ለማስፈታት በተደረገ ጥረት ውስጥ በተደረገ ተኩስ መሆኑንና እነሱ ከታጠቁት ክላሽኒኮቭ ጠብመንጃ የተተኮሰ መሆኑንም በፎረንሲክ ምርመራ ማረጋገጡን መርማሪ ቡድኑ አስታውቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ የሚጠይቀው ወንጀሉ ከባድ ስለሆነ፣ የሰው ሕይወት የጠፋበትና በርካታ ንብረት የወደመበት በመሆኑና ውስብስብና ሰፊ ምርመራ ማድረግ ስለሚያስፈልግ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በቁጥጥር ሥር ሲውሉ የተያዙት ጠብመንጃዎች ዘጠኝ መሆናቸውን፣ አንዱ ጠብመንጃ ከአቶ ጃዋር ቤት በፍተሻ የተገኘና ሕገወጥ ትጥቅ መሆኑንም አስረድቷል፡፡ አምስት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከመንግሥት ጋር ተስማምቶ እንደተፈቀደለት ቢገልጽም፣ የጦር መሣሪያው የተፈቀደው ኦኤምኤን ለሚባለው ሚዲያ ለድርጅት ጥበቃ እንጂ ለእሱ አጃቢዎች አለመሆኑን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ መሣሪያውን ይዘውት በመገኘታቸው ባልተፈቀደ ቦታ ከዓላማው ውጪ በመገኘቱ ሕገወጥ ትጥቅ መሆኑን አክሏል፡፡ አራቱ ክላሽኒኮቭ ጠብመንጃዎች ደግሞ ከየት እንደመጡና ምንጫቸው እንደማይታወቅም ጠቁሟል፡፡

‹‹እኛ ፕሮፌሽናል መርማሪዎች ነን፤› ያለው መርማሪ ቡድኑ የፖለቲካ አቅጣጫ ሊመራው እንደማይችል፣ ምርመራው በፖሊስና በዓቃቤ ሕግ ብቻ ከመመራቱ ውጪ  የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንደሌለበት ተናግሯል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ቡድኑ ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ፣ ተጠርጣሪው ከተጠረጠሩበት ጉዳይ ውጪ የሚያነሱትን ክርክር ፍርድ ቤቱ እንዲያስቆምለት ጠይቋል፡፡ ምንም እንኳን አቶ ጃዋር ጠባቂዎቹ በተለያዩ ተቋማት ይሠሩ የነበሩና በስምምነት እንደወሰዳቸው ቢናገርም፣ ፌዴራል ፖሊስንና መከላከያን ጠይቆ እንደተረዳው የአገልግሎት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ከድተው የኮበለሉ መሆናቸውን እንዳረጋገጠ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የመርማሪ ቡድኑን የምርመራ መዝገብ ወስዶ ለ15 ደቂቃ ያህል በጽሕፈት ቤት ከተመለከተው በኋላ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የምርመራ መዝገቡን እንዳየው የምርመራ ቡድኑ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ውስጥ በርካታ ሥራዎችን እንዳከናወነ መረዳቱን፣ አንድ የወንጀል ምርመራ ሥራ ሲከናወን ብዙ ውጤቶች ሊገኙ እንደሚችሉና  መርማሪ ቡድኑም ሰፊ ሥራዎችን መሥራቱን ፍርድ ቤቱ እንደተረዳ ገልጿል፡፡ ቡድኑ ስለኦኤምኤን ሚዲያ ያቀረበው የሚነቀፍ ሆኖ እንዳላገኘው ገልጾ፣ ከምርመራው ስፋት አንፃር መርማሪ ቡድኑ በቀጣይ 12 ቀናት ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ በማዘዝ፣ ለነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Filed in: Amharic