>

ባሕርዳርን በማሻማት ጎንደርንና ጎጃምን የማጋጨት የፀረ አማራው ብአዴን ሴራ!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ባሕርዳርን በማሻማት ጎንደርንና ጎጃምን የማጋጨት የፀረ አማራው ብአዴን ሴራ!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ባሕርዳር ከተማ የማን ናት??? የጎጃም ወይስ የጎንደር???
ፀረ አማራው ብአዴን በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በኩል በጣም የተለጠጠና ፈጽሞ አቅምን ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ የባሕርዳር ማስተር ፕላን ማስጠናቱን በብዙኃን መገናኛው በኩል አስታውቋል!!! ዓላማው በማይሆን ነገር ሕዝብን በማስጎምጀት ከሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት መሆኑ ነው!!!
እንደምታስታውሱት ከዓመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባሕርዳር ያላትን ተፈጥሯዊ ጸጋ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ባሕርዳርን “ወደፊት ከሚወጡት የዓለማችን 10 ውብ ከተሞች አንዷ ትሆናለች!” ብሎ ተንብዮ ነበር፡፡ በኋላም ባሕርዳር “የዓለም የትምህርት ከተማ!” ተብላ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ተቋም (UNESCO) መሠየሟ የሚታወስ ነው!!!
ይሄ ነገር ብአዴንን አስቃዠው መሰለኝ ፈጽሞ አቅምን ያላገናዘበ ማስተር ፕላን “አስጠናሁ!” በማለት እየተቦተረፈብን ይገኛል!!! ሀገራችን ያላትን አቅምና የማደግ ዕድል ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ባሕርዳርን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደተነበየላት ዓይነት ከተማ ሆና ለማየት ግን ቢያንስ ከ70-100 ዓመታት ይጠይቃል እንዲህ በቀላል የሚደረስበት ነገር አይደለም!!!
ከሰኔ 15ቱ የፀረ የአማራ የህልውና ትግል የአገዛዙ ዘመቻ በኋላ ካድሬዎቹን የእነ አምባቸው መኮንን ደጋፊ እና የእነ ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ደጋፊ ብሎ ለሁለት ከፍሎ ጎንደርንና ጎጃምን ለማባላት ከፍተኛ ጥረት  ሲያደርግ የቆየውና የሕዝቡን አንድነት በመፈረካከስ ብዙ ኪሳራ ያደረሰብን ፀረ አማራው የጥፋት ኃይል ብአዴን አሁን ደግሞ የባሕርዳርን ወደ ጎንደር የተለጠጠ ማስተር ፕላን ምክንያት አድርጎ ጎንደርንና ጎጃምን ለማባላት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል!!!
ለውጥ ከሚለው የወያኔ/ኢሕአዴግ ድራማ በኋላ እንኳ ፀረ አማራው የጥፋት ኃይል ብአዴን የአማራ ትግል ዋነኛ ተዋናይ የሆኑትን ጎንደርንና ጎጃምን በማጋጨት የአማራን ትግል ለማክሰም ከፖለቲካዊ እስከ ሃይማኖታዊ ያሉ ጉዳዮችን በመጠቀም ሴራ የተሞላ የማጋጨት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል!!!
ከለውጡ ድራማ በፊትም አማራ አንድ እንዳይሆንና ለመከፋፈል ጎንደርና ጎጃምን ለማጋጨት ብዙ ሲጥር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ አንዱም የማጣያ ምክንያቱ የነበረችው ይህችው ባሕርዳር ከተማ ነበረች፡፡ ፀረ አማራው ብአዴን በባሕርዳር ምክንያት ጎንደርንና ጎጃምን የማጋጨት ጥረቱን አሁንም አጠናክሮ ቀጥሎበት ይገኛል!!!
ይሄንን ተከትሎም እነ አምባቸው መኮንንን እያነሣ ሲነፈርቅ የከረመው የፀረ አማራው ብአዴን የፋርጦች ቡድን ተቆርቋሪ መስሎ በመቅረብ ማስተር ፕላኑን በመቃወም “ጎንደር እራሷን ችላ ክልል መሆን አለባት!” በማለት የአማራን አንድነት የመክፈል ሸፍጠኛ ሐሳብ እያራገበ ይገኛል!!! በወዲያኛው በኩል ያለው ማለትም ከጎንደር ተቆርሶ ወደጎጃም መከለሉን የሚደግፈው ሌላኛው የፀረ አማራው የብአዴን ቡድን ደግሞ እንዲህ በመደረጉ በደስታ እየቦረቀና “ግፋ በለው!” እያለ ይገኛል!!!
ፀረ አማራው ብአዴን ሲፈልግ ደግሞ በአማራ ትግል ወቅት የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ “ባሕርዳር የአማራ አይደለችም የወይጦዎች ናት!” የሚል አስቂኝ አጀንዳ በማራገብ አማራን ለማናደድ ጥረት ያደርግ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ፀረ አማራው ብአዴን ጎንደርንና ጎጃምን በባሕርዳር ምክንያት ለማጋጨት ማሴር የጀመረው ከተማዋ ዓባይን ወይም ድልድዩን ተሻግራ ወደ ጎንደር መስፋቷን ተከትሎ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እስከ ዘንዘልማ ድረስ ሔዶ ጎንደር ደራ ወረዳን ቆርሶ ወደ ባሕር ዳር በመከለል ቦታውን ካርታ ላይ የጎጃም ክፍል አድርጎ ካወጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው!!!
ሕዝቡም ይሄንን የወያኔ/ብአዴን የክፋት ሴራ መቃወሙን ለመግለጥ የተለያዩ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ ታክሲዎች ከዓባይ ወንዝ ወይም ከድልድዩ ማዶ ወዳለው አዲሱ የከተማዋ ክፍል ሲጭኑ “ጎንደር ጎንደር!” እያሉ ነበር ይጠሩና ይጭኑ የነበሩት፡፡ ብአዴን ታክሲዎችን በመቅጣትና የሥራ ፈቃድ በመሰረዝ ነበር ታክሲዎችን “ጎንደር ጎንደር!” እያሉ መጫንን ያስቆማቸውና “ዓባይ ማዶ!” እያሉ እንዲጠሩና እንዲጭኑ ያደረጋቸው፡፡ ሌላው ደግሞ ከድልድዩ ማዶ ባለው በዚሁ አዲሱ የከተማዋ ክፍል ቤት የሚሠራውና የሚገዛው ከሞላ ጎደል የጎንደር ሰው ሆኖ መገኘቱ ሌላኛው የሕዝቡ ተቃውሞን የመግለጫ መንገድ ይመስለኛል!!!
እንዲህ ዓይነት አንድ ከተማ በሁለት ክፍላተ ሀገር መሀል የመገኘቱ አጋጣሚ በባሕርዳር ብቻ የተከሰተ አይደለም፡፡ በዓለማችን በርካታ ተመሳሳይ ዕጣ ያላቸው ከተሞች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከዓመታት በፊት የወያኔን ጎሳ ተኮር ፌዴራላዊ የክልል አወቃቀር ስሕተትነትን ለመግለጥ በጻፍኩት ጽሑፍ ላይ በሜሪላንድና በቨርጂኒያ መሀከል ያለችውን የአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲን ምሳሌ አድርጌ ማቅረቤ ይታወሳል!!!
ዋሽንግተን ዲሲ ከሜሪላንድ ወደ ቨርጂኒያ እየሰፋች ሔዳ ከአንዱ ወደሌላው ፌዴራላዊ ግዛት ስትሻገር እንደ ባሕርዳር የተሻገረችበትን ግዛት መሬት ቆርሳ በማምጣት አልነበረም የሰፋችው፡፡ የቨርጅኒያ ዲሲ ክፍል፣ የሜሪላንድ ዲሲ ክፍል ተብላ እንጅ!!! ይሁንና ግን ከተማዋን የሚያሥተዳድረውና የከተማዋ ግብር የሚሰበሰበው ከሜሪላንድም ከቨርጅኒያ እጅ ወጥቶ ለፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ ይሄንን ሁኔታ የፈጠረው ከተማዋ በሁለቱ መሀል በመገኘቷ ነው!!!
ይሄንን ተሞክሮ ወደ እኛ ዐውድ ስናመጣው ባሕርዳር ወደጎንደርም ሆነ ወደ ጎጃም የምትሰፋውን ያህል ብትሰፋ ከተማዋ የጎጃምም የጎንደርም ሳትሆን አገዛዙ “የአማራ ክልል መንግሥት!” ለሚለው ንብረት ሆና የሚያሥተዳድራትና ግብሯን የሚሰበስበው እሱ ይሆናል እንደማለት ነው፡፡ ባሕርዳር በሁለት የተለያዩ ክልሎች መሀል ብትሆን ኖሮ ደግሞ በዋሽንግተን ዲሲ ዐውድ ንብረትነቷ ለፌዴራሉ መንግሥት ትሆን ነበር!!!
ወደፊት ይሄ ትግል እየተኪያሔደበት ያለው ፀረ ኢትዮጵያ የጎሳ ተኮር ፌዴራላዊ ሥርዓት ሲገረሰስና የአማራ ክልል መንግሥት የሚባለው ሲጠፋ ደግሞ በጎንደር በኩል ያለውን የከተማዋን ክፍል ጎንደር እንዲያሥተዳድር በጎጃም በኩል ያለውን የከተማዋን ክፍል ደግሞ ጎጃም እንዲያሥተዳድር መደረግ ይኖርበታል!!!
ለአሁኑ ግን ከላይ የተጠቀሰውን የአሜሪካ ተሞክሮ በመውሰድና ከዚህ ተሞክሮ በመማር ብአዴን ጎንደርንና ጎጃምን ለማጋጨት የፈጸመው ስሕተት መታረም ይኖርበታል፡፡ ካልሆነ ግን የከተማ መስፋፋት ተፈጥሯዊ በመሆኑና ገናም የሚቀጥል በመሆኑ ዛሬ እስከ ዘንዘልማ ድረስ ወደ ባሕርዳርና ጎጃም እንዲከለል የተደረገው መስፋፋት ነገ ደግሞ እስከ ሐሙሲት ከነገ ወዲያ እስከ ወሮታ እያለ እያለ የጎንደርን አብዛኛ ክፍል ጎጃም ወደማድረግ ሊኬድ ነው ማለት ነው!!!
በውጤቱም ታሪክ ይጠፋል፣ የታሪካዊ መቸት (Setting) ይምታታል ወይም ይፋለሳል፣ ሕዝብን ለግጭት ይዳርጋል ወዘተረፈ. በነገራችን ላይ የጎንደር ግዛት እየሸሸ እየሸሸ መጥቶ የዓባይን ወንዝ ተፈጥሯዊ ድንበር አድርጎ ቆመ እንጅ ጎንደር በጌምድር ትባል በነበረበት ዘመን አዴት ድረስ የጎንደር ግዛት ነበረ፡፡ የጎጃም ዋና ከተማውም ደብረማርቆስ ነው የነበረው!!!
አዲሱ ማስተር ፕላንም እራሱ የጣና ዙሪያን በሙሉ የከተማዋ አካል ማድረግ መሆኑን እዚያው ላይ ተገልጿል፡፡ ልብ በሉ የጣና ሐይቅ ከ90% በላይ ጎንደር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ካርታ ላይ እንደምታዩት ጣና ዙሪያውን በጎንደር ተከቦ በባሕርዳር በኩል ያለው የጣና ጫፍ ክፍል ብቻ ነው ዳጋን ይይዝና ወደ ጎጃም የሚሔደው፡፡ እና እንግዲህ እንደ ማስተር ፕላኑ ሐሳብ ከሆነ ብአዴን ከሦስት ሚሊዮን በላይ የጎንደር ገበሬ ሰፍሮ ያለበትን የጣና ዳርቻ ወደ ባሕርዳር ቀላቅሎ ለሪዞርት፣ ለሎጂና ለባለሃብቶች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ሊቸበችብ ነው ፍላጎቱ!!!
ወያኔ/ብአዴን እንቦጭን አምጥተው የረጩበት ዓላማስ ገበሬውን በእንቦጭ አማሮ ለማፈናቀል አይደል??? አሁን ተንገፍግፎ ተማረረላቸው መሰለኝ “ለውጥ ቦታ እንስጥህ!” ሲሉት ዓይኑን ሳያሽ “እሽ!” እያለ እንዲነሣላቸውና ገበሬውን አንሥተው ዓይነ ግቡውንና ውቡን የጣናን ዳርቻ ለባለሃብት ለመቸብቸብ ተዘጋጅተዋል ማለት ነው!!!
በል ደሞ የጎንደር ገበሬ “ለውጥ ቦታ እንስጥህ!” ወይም የማይረባ ገንዘብ “ካሳ እንስጥህ!” ስትባል እየተቀበልክ ከቅምቅማት ምንጅላትህ የወረስከውን እርስትህን አስረክበህ ውጣና ከንቱ የከተማ ኩሊ ሆነህ ቅር አሉህ ደሞ እሽ???
“ከተማ አይደግ፣ የጣናን ውብ ተፈጥሯዊ ገጽታም ተጠቅመን ኢኮኖሚያችንን አንደግፍ!” እያልኩ አይደለም ያለሁት፡፡ ነገር ግን ይሄንን የጣና ዳርቻ ውብ ተፈጥሯዊ ገጽታ ለዚህ አገልግሎት ከማዋላችን በፊት የአገዛዙ የመሬት ፖሊሲ መቀየርና ገበሬው የመሬት ባለቤት መሆን፣ መሬቱንም የመሸጥ የመለወጥ መብት ባለቤት መሆን ይኖርበታል!!!
ከዚያ ይሄንን የጣና ዳርቻ መሬት ገበሬው በገበያ ዋጋ ለፈለገው ባለሀብት መሸጥ ይችላል፡፡ ሀብት የሚፈጠረው ግብርናውም ሊዘምን የሚችለውና ከአቅሙ በላይ 85% የሀገሪቱን ሕዝብ የተሸከመው ግብርናው ቀንሶ 15% የሆነው የከተማው ሕዝብ ቁጥርም ከፍ ሊል ሀብትም በከተማ ሊፈጠር የሚችለውና የከተማውና የገጠሩ ነዋሪ ቁጥርም እንደየችሎታው በራሱ መንገድ እራሱን ሊያመጣጥን የሚችለው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በአሜሪካ ገበሬው ከሀገሪቱ ሕዝብ 2% ብቻ ነው፡፡ በአብዛኞቹ ያደጉ ሀገራት ገበሬው 3% በላይ አይደለም፡፡ ግብርናቸው ግን ዘመናዊ ስለሆነ ይሄ በጣም አነስተኛ የገበሬ ቁጥር ሕዝባቸውን ከመመገብ አልፎ ወደ ውጭ ገበያ ይልካሉ!!!
ይሄ መሬትን የገበሬው የአራሹ ወይም የግል በማድረግ ሀብት የመፍጠሪያ የኢኮኖሚ አቅጣጫ የምዕራቡ ዓለም ኢኮኖሚ የበለጸገበት የኢኮኖሚ አቅጣጫ እንጅ የሌለና ያልተሞከረ አቅጣጫ አይደለም፡፡ መሬት የመንግሥት ከሆነ የሙስና ሲሳይ ሆኖ ሀገር የምትመዘበርበትን በር ይከፍታል እንጅ አንዳችም ነገር ሀገርንም ሆነ ሕዝብን ሲጠቅም ታይቶ አይታወቅም፡፡ በሀገራችንም ሆኖ ያየነው ይሄንን ነው!!!
ወያኔ የገበሬውን መሬት በመያዣነት በመያዝ ገበሬው “መሬቴን እቀማለሁ!” እያለ በመፍራት ሳይወድ በግዱ ወያኔ/ኢሕአዴግን እንዲመርጥ ለማስገደድ ነው መሬትን የመንግሥት ያደረገው እንጅ ይሄ የመሬት ፖሊሲ ለሀገር ዕድገት ስለሚጠቅም አይደለም!!! ባደጉ ሀገሮች ወይም በምዕራቡ ዓለም መሬት የመንግሥት የሆነበት አንድ ሀገር ብትፈልጉ አታገኙም!!!
እናም እንግዲህ የጎንደርም ሆነ የጎጃም አማራ በፀረ አማራው የጥፋት ኃይል ብአዴን የተሸረበብህን ይሄንን ሴራ በዚህ መንገድ አንድ ሆነህ ታከሽፈውና ትዋጋው ዘንድ አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ!!!
Filed in: Amharic