>

ኮከብ የሌለውን ሰንደቅአላማ ከሰዎች እጅ መንጠቅ ይቻል ይሆናል፤ ከዜጎች ልብ ግን መፋቅ አይቻልም!!! (ቢቢ ሽጉጤ)

ኮከብ ቆጣሪ ፖሊሶች !

 ቢቢ ሽጉጤ

ኮከብ የሌለውን ሰንደቅአላማ ከሰዎች እጅ መንጠቅ ይቻል ይሆናል።፤ ከዜጎች ልብ ግን መፋቅ አይቻልም!!!

  ” ድምፃችን ለግድባችን” በሚል ህዝቡ አጋርነቱን እንዲያሳይ መንግስት በጠራው መሰረት፤ ትላንት ህዝቡ ምንም እንኳን ኮረናን ችላ ማለቱ ቢያሳስብም ፤በአንድነት መንፈስ በያለበት ወጥቶ “ግድቡ የእኔ ነው” እያለ አጋርነቱን ሲገልፅ ውሏል።
  ይሁን እንጂ በአዲስአባ አንዳንድ አካባቢዎች እና በድሬዳዋ ዜጎች  “ለምን ኮከብ የሌለው ባንድራ ያዛችሁ'” ተብለው በፖሊስ ተንገላተዋል።
  በተለይ በድሬዳዋ ባጃጅ ላይ እና መኪና ላይ ኮከብ የሌለው ባንድራ ያውለበለቡ ሰዎች ከነተሽከርካሪያቸው ወደፖሊስ ጣቢያ እየተወሰዱ ከ15ሺ እስከ 50ሺ የቅጣት ወረቀት እንደተሰጣቸው ለሚዲያ ገልፀዋል። ኮመንት መስጫው ላይ ያለውን የቅጣት ወረቀት ተመልከቱ።
  እኔ የምለው እነዚህ ኮከብ ቆጣሪ የሆኑ ፖሊሶች ፡ሰሞኑን በሃገሪቷ ውስጥ ዜጎች ሲታረዱ እና ንብረት ሲወድም ፡ “ድረሱልን” እያለ ህዝቡ ሲደውል ፡ “ትዕዛዝ አልተሰጠንም፣ስብሰባ ላይ ነን” እያሉ ህዝቡን አስጨርሰው፤ ኮከብ የሌለው ባንድራ የያዘን ሰው ለማደን ግን እንዴት ነው ፈጣን ትዕዛዝ የሚሰጣቸው?
  ባሳለፍነው ሁለት አመት ኮከብ የሌለውን የኢትዮጵያ ባንድራ ይዘው የተገኙ ዜጎች ብዙዎቹ በፖሊስ ተነጥቀዋል ፣ተደብድበዋል ፤ የኦነግን አርማ ይዞ ሲንቀሳቀስ የተቀማ ወይም የታሰረ አንድ ሰው አለ?
  በኢትዮጵያ የሰንደቅአላማ ታሪክ የቆየ ቢሆንም በነገስታቱ ዘመን በቤተመንግስት ፣ በዘውድ በአል ላይ ወይም በዘውድ ም/ቤት አካባቢ የሚውለበለበው ባንድራ የአንበሳ ምስል (የዘውድ አርማ) አለበት። ዜጎች ግን አርማ የሌለው ሰንደቅ አላማ ያውለበልባሉ ። “ለምን” ብሎ ግን መንግስት አያስራቸውም።
  አምባገነን የተባለው ወይም የነበረው ደርግ እንኳን፤  የደርግ ኢሰፓ መ/ቤት ፣የፓርቲ ጽ/ቤት ወይም የፖለቲካ ስብሰባዎች ላይ የኢህድሪ አርማ ያለበትን ባንድራ ይሰቅላል። ዜጎችን ግን “ለምን አርማ የሌለው አረንጓዴ፣ቢጫ፣ቀይ ሰንደቅ አላማ ያዛችሁ” ብሎ አይነጥቅም፣ አያስርም።
  ተረኞች ሆይ ! ወላጃችሁ ህወሃት 27 ዓመት  ኮከብ የሌለው ባንድራን ከሰዎች እጅ ላይ ስትነጥቅ ብትኖርም ፤ከዜጎች ልብ ላይ ግን መፋቅ ሳትችል፤ እራሷ ከአራት ኪሎ ተፋቀች።  እናንተም አትችሉም አትልፉ።
 አረንጓዴ፣ቢጫ፣ቀዩ አርማ ከኢትዮጵያ አልፎ በጥቁር ህዝብ ልብ ላይ የታተመ ታሪክ ነው።
Filed in: Amharic