>
5:13 pm - Sunday April 19, 1265

እንደሁኔታው ማንነት የሚለዋውጡት የጃዋር መሐመድና የዐቢይ አሕመድ እናቶች ...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

እንደሁኔታው ማንነት የሚለዋውጡት የጃዋር መሐመድና የዐቢይ አሕመድ እናቶች …!!!

አቻምየለህ ታምሩ

ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በሚያቆበቁብበት ወቅት እንዳየሩ ጸባይ የዊኬፔዲያ ፕሮፋይሉን በየቀኑ ያርመው [edit ያደርገው] ነበር። እንደየሁኔታው ከሚቀያይራቸው ታሪኮቹ መካከል የእናቱ ማንነት ዋናው ነበር። የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ እንደተሰየመ ሙሉ ታሪኩን በዊኬፔዲያ ሲጽፍ እናቱ አማራ እንደሆነች ጻፈ። ይህን ተከትሎ የኦሮሞ ብሔርተኞች በጃዋር ቴለቭዥን ቀርበው “ዲቃላ” እያሉ ሲዘምቱበት አማራ እንደሆኑ የጻፈውን የእናቱን ማንነት ኦሮሞ አደረገው።
ከዚያ ከአንድ ዓመት በኋላ የኖቤል ሽልማት ሲቀበል በፊቱ ከተነበበው የሕይዎት ታሪኩ ኦሮሞ አድርጓቸው የነበሩት እናቱ አማራ መሆናቸውን አሳወጀ።  ከወራት በኋላ የሓጫሉን ግድያ ተከትሎ  በጥላቻ ያበዱት ኦነጋውያን “ዐቢይ ነፍጠኛ ነው” እያሉ ሲዘምቱበት ናዝሬት በሚገኘው የኦ.ቢ.ኤን. ስቱዲዮ በመገኘት በሰጠው ቃለምልልስ ኖርዌይ ኦስሎ የኖቤል ሽልማት ሲቀበል አማራ ያደረጋቸውን  እናቱን ማንነት ቀይሮ ንጹሕ ኦሮሞ አድረጋቸው። በዚህ ቃለምልልሱ የኦሮሞነት ጥራቱን ለማብራራት የሄደበት ርቀት ገራሚ ነው። የአባቱን ንጹህ ኦሮሞነት ሲያብራራ “ከሰላምታ ያለፈ አማርኛ መናገር የማይችል” ሲል ነበር የገለጻቸው።
ጃዋር መሐመድም እንደ ዐቢይ አሕመድ ሁሉ የእናቱን ማንነት በየጊዜው ሲቀያይር የኖረ ሰው ነው። ወደ አሜሪካ እንደመጣ እናውቀዋለን የሚሉ ሰዎች [ለምሳሌ አበበ ገላው] እናቱን የመንዝ አማራ እና ክርስቲያን እንደሆኑ ጃዋር እንደነገረው ጽፎ አንብቤያለሁ። በቅርብ እናውቀዋለን የሚሉ ሌሎች ሰዎችም  ስለ እናቱ ማንነት ተመሳሳይ ነገር እንደነገራቸው ሲናገሩ ሰምቻለሁ።  የሰዎችን አስተያየት ሳላጣራ አለመቀበልን/አለመድገምም እንድ መርኅ ስለያዝሁት የአማራና የኦሮሞ ወጣቶችን ትግል በምናስተባብርበት ወቅት ስለእናቱ ማንነት የሚወራውን ወሬ በሚመለከት ጠይቄው ነበር። በሰጠኝም መልስ እናቱ ኦሮሞ እንደሆኑ፤ ክርስቲያን የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን ሙስሊም መሆናቸውን ነግሮኛል። ይህ ውይይታችም  በመዝገብ የተያዘ ነው።
እናቱ ኦሮሞ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲናገር የኖረው ጃዋር ባለፈው ሳምንት ግን ፍርድ ቤት ተብዮው ፊት ቀርቦ “የብሔርና በሃይማኖት ግጭት እንዲነሳ አድርገኻል” ተብሎ ለቀረበበት ክስ ሲመልስ ክሱ ትክክል እንዳልሆነና እናቱ አማራና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መሆናቸውን ጠቁሞ ጉዳዩ የወንጀል ሳይሆን የፖለቲካ መሆኑን ማስረዳቱን ሪፖርተር ዘግቧል። ፍርድ ቤት ፊት የቀረበ ተጠርጣሪ መዋሸት እንደሌለበት የሕግ ቀዳሚ መርኅ ነው። ጃዋር ግን እናቱ የአብቹ ኦሮሞ [የራስ ጎበና ዘመድ] ስለመሆናቸው ባሕር ዳር አቫንቲ ሆኔታ ከንጉሱ ጥላሁን ጎን ተቀምጦ  የተናጋረው  በስምልና በድምጽ በሚገኝበት ሁኔታ “የብሔርና በሃይማኖት ግጭት እንዲነሳ አድርገኻል”  ተብሎ የቀረበበትን ክስ ለማስተባበል ሲል ከዚህ በፊት ስለ እናቱ  ማንነት ሲናገረው የነበረውን በመካድ በፍርድ ቤት ተብዮው ፊት ነጭ ውሸት ዋሸ። እንደ ዐቢይ ሁሉ የእናቱን ማንነት እንዳስፈላጊነቱ እየለዋወጠ በሁለት ቢላዋ ሲበላና ሲያጭበር የኖረውን ጃዋር መሐመድን  ፍርድ ቤት ተብዮው  እጅ ከፈንጅ  እንዲህ ሲዋሽ ፍርድ ቤቱን በመዋሸት ተጠያቂ ያደርገው ይሆን?
ከታች የታተመው የጃዋር ንግግር እናቱ የአብቹ ኦሮሞ መሆናቸውን ባሕር ዳርን በጎበኘበት ወቅት የተናገረውን ነው።  ከጎኑ የተቀመጠው የዐቢይ አሕመድ ፕሬስ ሴክሬታሪያቱ  ንጉሡ ጥላሁን ነው። ጃዋር ፍርድ ቤት ተብዮው ፊት  ቀርቦ አቃቢ ሕግ ተብዮው  “የብሔርና በሃይማኖት ግጭት እንዲነሳ አድርገኻል” ሲል  ላቀረበበት ክስ መልስ ሲሰጥ  ክሱ ትክክል እንዳልሆነና እናቱ አማራና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መሆናቸውን  ለፍርድ ቤት ተብዮው የዋሸው  እናቱ የአብቹ ኦሮሞ መሆናቸውን በአደባባይ የተናገረውን እንዲህ በምስልና በድምጽ ተመርጆ በሚገኝበት ሁኔታ ነው።
___________
ጃዋር ፍርድ ቤት ተብዮው ፊት ቀርቦ እናቱ አማራና ኦርቶዶክስ እንደሆኑ የተናገረውን ይህን የሪፖርተር ትር በመጫን ማንበብ ይቻላል።
Filed in: Amharic