>

በማወቅም ሆነ ባለማወቅ መንግስት እራሱን ጠልፎ ሊጥል እየሰራ ነው !!!! (ሻለቃ አጥናፉ በቀለ)

በማወቅም ሆነ ባለማወቅ መንግስት እራሱን ጠልፎ ሊጥል እየሰራ ነው !!!!

ሻለቃ አጥናፉ በቀለ

ከወደደ መውደቁ ባላስከፋ የሚያሳስበን አገር ይዞ መውደቁ እንጅ !!!
የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ አሳቦ በኦሮሚያ ክልል በበርካታ ወገኖቻችን ላይ የዘር ፍጅትና ማጽዳት በአሰቃቂ መንገድ ተፈጽሟል ።
   በዚህ ፍጅት እጃቸው አለበት ወይንም ተሳትፎ ነበራቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችና የፓለቲካ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ፍርድ ቤት በመመላለስ ላይ ናቸው ። በተለይም የጀዋርና የበቀለ ገርባ ደጋፊ ነን የሚሉ የኦሮሞ ጽንፈኞች ሲያሻቸው በብሔር ፣ አንዳንዴም በሀይማኖት እየተሰባሰቡ በውጭ አገር አብይ ስልጣን ይልቀቅ ! አቢይ የነፍጠኛ አገልጋይና የኦሮሞ ጠላት ነው !!!
ወዘተ እያሉ አገር እያመሱ ይገኛሉ ።
     በሌላ በኩል አገር እንዳይፈርስ፣  ወደ ለየለት የእርስ በእርስ መጠፋፋት እንዳንሄድ መንግስት ህግና የህዝባችንን ደህንነት የማስጠበቅ መንግስታዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ  የሚፈልገው ኢትዮጵያዊ መንግስትን በማበረታታትና በማገዝም ጭምር ሰላምን ለማስፈን አጋርነቱን በይፋ ሲገልጽ ቆይቷል ።
      ይሁን እንጅ ችግሩ በተከሰተባቸው ቀናቶች ተጠርጥረዋል በሚል ለእስር ከተዳረጉት ውስጥ ከሃጫሉ ግድያ ጋር ምንም የሚያገናኝ ጉዳይ የሌላቸው እንዲያውም ሰላማዊው ህዝብ በሻሽመኔ፣ በአርሲ፣ በአጋርፋ ፣ በጭሮ፣ ጅማና ሌሎች በርካታ ከተሞች የደረሰው አይነት ፍጅትና የንብረት ውድመት እንዳይደርስ ህዝብ ተደራጅቶ ህይወቱንና ንብረቱን እንዲጠብቅ በማሳሰባቸው ሊመሰገኑ የሚገባቸው ለምን እልቂቱን ገታችሁ በሚያስመስል መልኩ የእስር ሰለባ መሆን ብቻ ሳይሆን ድብደባና እንግልት እንደተፈጸመ መንግሥት አረጋግጧል።
        እልቂቱ ከተፈጸመ ከወር በኋላም ከኦሮሞ ጽንፈኞች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የጥላቻና የዘር እልቂት በአደባባይ ሲያደርጉ የነበሩ የሚዲያ ዘጋቢወች  ከእስር እየተፈቱ በተቃራኒው ከኦሮሞ ጽንፈኞች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ሰወች እየታሰሩ ነው ።
        በሌላ በኩል የፌደራልም ፣ የኦሮሚያም ክልላዊ መንግሥት በግፍ በማንነታቸውና በእምነታቸው የተጨፈጨፉ ቤተሰቦችን ሲያጽናና፣ እርዳታ ሲያቀርብም ሆነ ለወደፊቱ ተመሳሳይ እልቂት  እንዳይኖር በቂ እርምጃ እንዳልወሰደ ከተጎጅወች እየሰማን ነው ። በከፍተኛ የመንግስት ሹሞች በአንዳቸውም ስለተጨፈጨፉት ወገኖች ቁጭት፣ ጸጸት፣ ሃዘን ህዝባችን አለማየቱ ግርምትን ፈጥሮብናል ፣ እንኳን ክቡር የሰው ፍጡር እንስሳ ያላግባብ ህይወቱ ሲያልፍ የሚሰማውን ስሜት ያክል ከመሪወቹ ህዝባችን አላየም፣ አልሰማም ። ለምን ? ለምን ????
         ቢያውቅበት ኖሮ ፣ ለአገርና ህዝብ ደህንነት ቢታሰብ ኖሮ ፣ የመንግስት ማህበራዊ መሰረቱና አጋሩ ከኦሮሞ ጽንፈኞችና ከትህነግ ውጭ ያለው ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የሚፈልገው መላው አገሩንና ህዝቡን የሚያፈቅረው ህዝብ ነበር ። ይህ ሐቅ ገና ጠ/ሚ አብይና ሌሎችንም እንደ ለውጥ ሃዋርያ አድርጎ ህዝብ በነቂስ ዳር እስከዳር ድጋፉን በመስጠት አሳይቶ ነበር ።
    ቀስ በቀስ ግን በኢትዮጵያ የማሉ ፣ ከማፍቀር አልፈው ሱሴ ናት ያሉን ሲክዱን ፣ በተቃራኒው ሲሰሩ ህዝባችን አስተውሏል ። እያደር እየጠራ ይሄዳል ፣ በውስጣቸው  ባሉ ጽንፈኞች ተውጠው እንጅ እሳቸው ለቃላቸውና ለኢትዮጵያ ታማኝ ናቸው ብሎ የሚያስበው ህዝብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ  ጊዜ እንስጣቸው በሚል ስሌት ሲደግፋቸው ነበር ። በተለይም አሁን የኦሮሞ ጽንፈኞችና ህወሃት በቅንጅት  መንግስትን በሃይልና በአመጽ ለመገልበጥ  እንቅስቃሴ ሲያደርጉና ቀንደኞች ቢታሰሩም አሁንም ደጋፊወቻቸው ከህውሃት ጋር ተባብረው አገሪቱን ወደ አጠቃላይ ጦርነት እየገፏት ባለችበት ወቅት  አገርን ከጥፋት ለመታደግ ዋነኛ አጋር መሆን የሚጠበቅበት በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት የማይደራደረው የህብረተሰብ ክፍል ነበር ። ይህ የማህበረሰብ ክፍል ግን መንግሥት በህግ የበላይነት ስም በሚወስዳቸው ተገቢ ያልሆኑ በፍትህ የመቀለድ እርምጃወችና ፣ አሁንም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚያሳየው ቸልተኝነት ፣ ግልጽ አድሎአዊነት ተቆጥቶና ተስፋ ቆርጦ  ወደ ኋላ እያፈገፈገ ነው ።
      መንግስት የዚህን ሃይል ድጋፍ በአግባቡ ሊጠቀምበት ሲገባ በራሱ ጥፋት ብቻውን ቁሞ ለጠላት እራሱን በማመቻቸት እራሱን ለውድቀት አገራችንንም አደጋ ላይ እየጣላት ነው።
         ሰሚ ከተገኘ ብዙ ጊዜ ባይኖርም አሁንም እድሉ አልተሟጠጠምና መንግስት ለአራችንም ለራሱም የሚያስብ ከሆነ የሚከተሉትን ማድረግ ቢችል ይመከራል
       ፩ኛ ፣  አገራችንን ለመታደግ ተወደደም  ተጠላም ማህበራዊ መሰረትህ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት የማይደራደረው ሰፊ የህብረተሰብ ክፍል ብቻ እንደሆነ አምነህ ተቀበልና ተመካክረህ ስራ፣
     ፪ኛ ፣ የኦሮሞ ጽንፈኞችና ህውሃት ሊታረቁ በማይችሉ አላማወችና ግቦች የሚያራምዱ ስለሆነ ለአገርም ላንተም ስለማይጠቅሙ አምርረህ ከመታገል ውጭ አታባብላቸው ፣እነሱን ለማለዘብ ብለህ የምትሰራው ሁሉ ያንተን መጥፊያ ጊዜ ያፋጥነዋል እንጅ አይጠቅሙህም ፣
     ፫ኛ ፣  ለቃልህ የምትታመን ከሆነ በፍትህ መቀለድ አቁም ፣ ያላግባብ ያሰርካቸውን በአስቸኳይ መፍታት ብቻ ሳይሆን ፣ ብዙወቹ የአንተ አጋር የሚሆኑ ናቸውና ተጠቀምባቸው ፣
     ፬ኛ፣ የታረዱና ሃብት ንብረታቸውን ያጡ ቤተሰቦችን ጎብኛቸው ፣ ተስፋ ስጣቸው ፣ መልሰህ አቋቁማቸው፣ በስማቸው መታሰቢያ አቁምላቸው ፣ ይህን ስታደርግ ጀርባህ ይሞቃል ፣ ሰፊው ህዝብም ከጎንህ ይቆማል፣
      ፭ኛ ፣ በንጹሃን ፍጅትና ውድመት ላይ እጃቸው ያለባቸውን ሁሉ ያለ ምህረት ለፍርድ አቅርብ ፣ የጸጥታ ተቋማትን አቋም እንደገና ፈትሺ  እስካሁን ተሰራ የተባለው ሪፎርም ሁሉ እንዳልሰራ በተግባር አይተሃልና አዲስ ነገር ሞክር ፣ ሙያተኞች እንዲያማክሩህ አድርግ ፣ ኢትዮጵያ የመሪ እንጅ የሰው ድሃ አይደለችምና ።
           መንግሥት ሆይ እራስህንም አገራችንንም እንዳታጣ መስመርህን ፈትሽ !!! አጋሮችህን ተስፋ አታስቆርጥ !!!!

https://www.facebook.com/461427310545569/posts/3488699271151676/

Filed in: Amharic