>
8:27 pm - Wednesday June 7, 2023

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ የስድስት ወር የእቅድ አፈፃፀም...!!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ የስድስት ወር የእቅድ አፈፃፀም…!!!

ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ
                   መግቢያ
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት እና የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ መሪ ክቡር  አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከስድስት ወር በፊት በቀጣይ ክልላዊ መንግስታቸውና ፓርቲያቸው ሊፈጽም ያሰበውን እቅድ ማቅረባቸው ይታወሳል። በዚህም መሰረት በሶስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የነበረው እቅድና አፈፃፀም እንደሚከተለው ቀርቧል። እነዚህ ቁልፍ ጉዳዬች የብልጽግና ፓርቲ አመሰራረት እና አመራር ውክልና ፣የኦሮምኛ ቋንቋና የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳዬች ናቸው። በክፍል አራት ቁልፍ እቅዶቹ የተፈፀመበት አቅጣጫዎች ተመላክተዋል።
                    ***
                 ክፍል አንድ፣
የብልጽግና ፓርቲ አመሰራረት እና አመራር ውክልና በተመለከተ፣
1.1. ቁልፍ ተግባር የብልጽግና ፓርቲን መራሽ” በማድረግ የስልጣን የበላይነትን ማረጋገጥ። ኢትዮጵያን የኦሮሞ ብልጽግና በሚፈልጋት መልኩ መፍጠር።
1.2. ዝርዝር ተግባራት
  1.2.1. የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንትና ምክትሉ በምርጫ ጉባኤ ይካሄዳል።
    1.2.2. የፓርቲው የአመራር ውክልና በህዝብ ቁጥር ፕሮፓርሽን ይሆናል። አርባ ፐርሰንት የኦሮሞ ብልጽግና ይወስዳል።
                1.2. የእቅድ አፈፃፀም፣
   1.2.1. በእቅዱ መሰረት የብልጽግና ፓርቲ ምስረታ እውን ሆኗል።
  1.2.2. በእቅዱ መሰረት የአመራር ውክልናም በህዝብ ብዛት እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ብልጽግና የአመራሩን አርባ ፐርሰንት በመያዝ የፍጹም የበላይነት መያዙን አረጋግጧል።
  1.2.3. ብልፅግና ፓርቲ ካሁን በኋላ የሚመራው ኦሮሞ መሆን አለበት ካልሆነ ደግሞ የኦሮሞ ብልጽግና ሊፈቅድለት የሚገባበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
              ***
           ክፍል ሁለት፣
 
የኦሮምኛ ቋንቋ በተመለከተ፣
         2.1. ቁልፍ ተግባር
ከምርጫ በፊት የአማርኛን ቋንቋ በሚገድል አቅጣጫ የኦሮምኛ ቋንቋን የፌዴራል የስራ ቋንቋ ማድረግ።
         2.2. ዝርዝር ተግባራት
2.2.1. በብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ የኦሮምኛ ቋንቋን ጨምሮ አምስት ቋንቋዎች የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ መወሰን።
2.2.2.  የፓርቲውን ውሳኔ ተከትሎ በፌዴራል መንግስት የሚኒስትሮች ምክርቤት የቋንቋ ፖሊሲ ከሁለት ወይም ከሶስት ሳምንት በኋላ ለካቢኔ ይቀርባል። ተጠናቅቋል። ለፌዴራል ካቢኔ ማለት ነው። ስድስት ክልሎች ነው እንዲወስኑ የምንፈልገው።
2.2.3. የአማርኛ ቋንቋ እንዲዳከም በማድረግ አሟሟቱን ማፋጠን።
             2.2. የእቅድ አፈፃፀም
2.2.1. በእቅዱ መሰረት ብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ የኦሮምኛ ቋንቋን ጨምሮ አምስት ቋንቋዎች የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ በመወሰን ለሚኒስትሮች ምክርቤት ተልኳል።
2.2.2. የፓርቲውን ውሳኔ ተከትሎ በፌዴራል መንግስት የሚኒስትሮች ምክርቤት የቋንቋ ፖሊሲ ከሁለት ወይም ከሶስት ሳምንት በኋላ ለካቢኔ ይቀርባል። ተጠናቅቋል።
2.2.3.  በ1987 ዓ.ም. ኦሮምኛ በ13 % ከአማርኛ በታች የነበረውን በመቀየር አሁን አፋን ኦሮሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አማርኛን ከ10% በላይ እንዲበልጠው ተደርጓል።
 2.2.4. ከደቡብ ተገንጥሎ የወጣው ሲዳማ (ሐዋሳን ጨምሮ) የስራ ቋንቋ ከአማርኛ ወደ ሲዳምኛ ተቀይሯል። በቀጣይም እየፈራረሱ ያሉት የደቡብ ክልሎች ሲጠናቀቅ በደቡብ አማርኛ የቁልቁለት ጉዞውን ይቀጥላል።
 2.2.5. ቤንሻንጉል 37% አፋን ኦሮሞ የሚናገሩባት ሁኔታ ተፈጥሯል። በጋምቤላ፣ ሃረሪ፣ ሶማሌ ውስጥ አማርኛ እየሞተ በመምጣት ወደታች እየሄደ ነው።
2.2.6. በአዲስ አበባ ባስገባናቸው 5,700 የኦሮምኛ አስተማሪዎች ምክንያት ከ56,000 በላይ ተማሪዎች በኦሮምኛ መማር ችለዋል።
                      ***
                ክፍል ሶስት
     አዲስ አበባን በተመለከተ
3.1. ቁልፍ ተግባር፣
የአዲስ አበባ ባለቤትነት ማረጋገጥ።
3.2. ዝርዝር ተግባራት
    3.2.1. በአዲስ አበባ ህጋዊና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሰፈራ በመፈፀም ዲሞግራፊውን መለወጥ።
    3.2.2. አዲስ አበባን የማትፈለግና ትርጉም አልባ ከተማ ማድረግ
    3.2.3. የኦሮሚያ ብልጽግና የሚመራው ማህበራዊና የኢኮኖሚ አውታሮችን መገንባት
     3.2.4. የወሰን መስመር በኦሮሞ ብልጽግና መራሽነት ማጠናቀቅ።
            3.3. የእቅድ አፈፃፀም፣
  3.3.1. የኦሮሚያ የትግል ማዕከል መሆኗን የተገነዘበና ይህንንም በአደባባይ የሚያስተጋባና ወደ ተግባር የሚቀይር ከንቲባ ተመድቧል። የመሬት አስተዳደርን ጨምሮ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን እንዲሁም አምስቱን የማስፋፊያ ክፍለ-ከተሞች ከንቲባነት በኦሮሙማ እንዲያዝ ተደርጓል።
  3.3.2. የወሰን መስመሩ ልክ አዳማን ከአጐራባች ወረዳዎች እንደሚሰመረው፤ እምብርታችን የሆነችው አዲስ አበባም ተመሳሳይ ወሰን ተሰምሮላት ተጠናቋል።
 3.3.3. የኢሬቻ በአል የከተማው ባለቤትነትን በሚያሳይ መልኩ በድምቀት እንዲከበር ተደርጓል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአምቦ ህዝብ ጋር በነበራቸው ውይይት የኢሬቻ በአል አዲስ አበባ እንዲከበር የተደረገበት ምክንያት የነፃነት ምልክት መሆኑን ገልፀዋል።
3.3.4. የአዲስ አበባ ዴሞግራፊ ከመቀየር አኳያ ከ10ሺህ በላይ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉትን በመዲናዋ ሰፍሯል።
3.3.5. ከ5,700 በላይ የኦሮምኛ አስተማሪ መምህራን ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡና እንዲሰፍሩ ተደርጓል።
  3.3.6.  በአዲስ አበባ ውስጥ 2ሺህ የኦሮምኛ ተማሪዎች ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ  56,000 የኦሮምኛ ተማሪዎች መፍጠር ተችሏል።
    3.3.7. በ10ሩም ክፍለ ከተማ 10 የኦሮሞ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የገበያ ማዕከል በመገንባት ላይ ይገኛል።
   3.3.8. በአዲስ አበባ የተገነቡና እጣ የወጣላቸውን ኮንደሚኒየም ለነዋሪው እንዳይከፋፈል አድርገናል። የጨፌ ኦሮሚያ ሰራተኞች፣ የኦቢኤን ጋዜጠኞችና ወደ አዲስ አበባ የገቡ መምህራን በምደባ ኮንደሚኒየም እንዲያገኙ ተደርጓል።
3.3.9. ቄሮዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ ባዶ ቦታዎችን ለከተማ ግብርና በሚል ሰበብ መሬቶችን እንዲቆጣጠር ተደርጓል።
3.3.10. የኦሮሙማ አባላት የቄሮ አባላት መታወቂያ በጅምላ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።
                   ***
               ክፍል አራት
        የአፈፃፀም አቅጣጫ ፣
4.1. ለውጥ ማምጫ መንገድ ሪፎርም እንዲሆን ተደርጓል። ሪፎርሙ መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ጥያቄዎቻችንን በሚፈታ መንገድ ተፈጽሟል።
4.2.  የአፈፃፀም አቅጣጫው ኦሮሙማን የምትመስል ኢትዮጵያ መልሰን reconstruct በማድረግ ፣ superstructure ውስጥ  ኦሮሞነትን በመትከል የሚፈፀም ይሆናል።
4.3. የአፈፃፀም አቅጣጫው በተቻለ መጠን በማሳመን ፤ ካልተቻለ ደግሞ ግራ በማጋባት እንዲተገበር ተደርጓል። የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የሰው ሃይል ማሳመን ተችሏል። ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑት ግራ ቢጋቡም ድጋፋቸው የኦሮሙማ እንዲሆን ማስቻል ተችሏል።
               ***
          ማስታወሻ : –
ይሄ የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርተር የተዘጋጀው አንዳንድ “ተደጋፊ ተደማሪዎች” ለሚያቀርቡት “አልሞት ባይ” መከራከሪያዎች ምላሽ እንዲሆን በማሰብ ነው። እነዚህ “ተደጋፊ ተደማሪዎች” በአንድ በኩል የአቶ ሽመልስ አብዲሳ እቅድና ሪፓርት ክልላዊ መንግስቱንና ፓርቲውን አይመለከትም የሚል ” የፓለቲካ ድህነታቸውን” የሚገልጥ መከራከሪያ እያቀረቡ ነው። በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንቱ እቅድ ወደ ተግባር አልተለወጠም የሚል ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ የሆነ አድርባይ መከራከሪያቸውን ይዘው ብቅ ብለዋል። ይህ ምናባዊ ሪፓርት ለዚህ የውሸት መከራከሪያ መጠነኛ ምላሽ እንዲሆን የተዘጋጀ ነው። አንባቢያን በዚህ መጣጥፍ ያልተገለጹ ጐላ ያሉ እቅዶችና አፈፃፀሞች በእጃችሁ ካለ በአስተያየቱ ላይ በማስፈር ሪፓርቱን እንድናዳብረው ፍቃዳችሁ ይሁን።
Filed in: Amharic