እስክንድር ነጋ-ለእኛ ብዙ ነው!
ወንድምአገኝ እጅጉ
እንዴት ማለት ጥሩ፦
– ከ40 ምናምን አመታት በላይ ፖለቲካ ውስጥ ተዘፍዝፈው ያረጁት ቧልተኛ ፖለቲከኞች ፓርቲ ከመቀያየርና ከማለቃቀስ ባለፈ ምን የፈጠሩትና ያሳዩን ነገር አለ??
እውነት ለመናገር መልሱ ምንም ነው!
– 40 ምናምን አመታት ፖለቲካ ውስጥ ተዘፍዝፈው እስካሁንም የሚጮሁ ፖለቲከኞች-እነሱም ካልገባቸው የግራ ዘመም ፖለቲካ እና ከፈረደበት የአልባንያ “ብሔር-ተኮር” ጉንጭ አልፋ ዲስኩር ባለፈ ምን የፈየዱት ነገር አለ?
እውነት ለመናገር መልሱ ምንም ነው!
ስማ! እስኬው በጋዜጠኝነቱ ሕወሐት መራሹን መንግሥት በብእሩ ብቻ ሰቅዞ በማስጨነቁ-ዘጠኝ ጊዜ ታስሯል፣ አምባገነኖች ሊያደርሱት የሚችሉትን መከራና ስቃይ ዋጥ አድርጓ ተቀብሏል! በዚህም 5 አለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘ ነገር ግን መታበይ ፈጽሞ የሌለበት- ትሁት የሰላማዊ ትግል icon ነው እስክንድር!
– እስኬው “ለውጥ” ተብዬው መጣ ብሎ እንደ ሌሎቹ ሕሊናውና መርሁን አላመቻመቸም! እስኬው አሁንም ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የሚተጋ፣ የሰላማዊ ትግል ቀንዲል ነው!
– ኦዲፒ የሕወሐትን መንገድ ተውሶ፣ ለየት ባለ ዜማና ቀለም ሲተገብር “አይሆንም!” “ትክክል አይደለም!” ብሎ ከማንም ቀድሞ ፊትለፊት ወጥቷ የሞገተ፣ያጋለጠና የታገለው እስኬው ነው።
♦ የሚረባ ፖለቲከኛ ሲጠፋም በፈጠረው የሕዝብ ንቅናቄ አባላት ግፊት – ወደ ፖለቲካ የገባው እስኬው እንደሌሎች ፖለቲከኞች ሳይርመጠመጥ፣ መርሁን ጠብቆ የአገሪቷን ፖለቲካ ማርሽ ቀይሮታል። ከቀየራቸው ብዙ ነገሮች ጥቂቶቹ፦
1. ከ40 አመታት በላይ በግራ ዘመም አመለካከት የተጠመደውን ፖለቲካ- ወደ መሐል ፖለቲካ(center-right politics/moderate right politics) ለማምጣት እየሰራ ነው። በዚህም ሕዝቡ የተለየ አማራጭ እንዲያይ ያደረገ ፖለቲከኛ ነው እስኬው።
2- Grass root የሚሉትን የፖለቲካ አካሄድ- ለአገራችን ጡረተኛ ፖለቲከኞች “በቀጥታ ስርጭት” እና በተግባር ያስተማረው እስኬው ነው! በአጭሩ የእኛ ፖለቲከኞች አካሄዳቸው “ችግራቹህ ይሄ ነው!” እና “እኛ እናውቅላችኃለን” የሚል ነው። የስኬው ግን ሕዝብ ውስጥ ገብቶ፣ ከሕዝቡ ጋር ኖሮ ነው ከሕዝቡ ጋር ቁጭ ብሎ ችግራችንን በአብሮነት ነቅሶ ያወጣው። እስኬው ለዚህ ነው ለሕዝቡ የቀረቡ አጀንዳዎችን አንድ፣ሁለት ብሎ ቀርጾ ሕዝብ ሲያታግል የነበረው። ለዚህ ነው አምባገነኑ ገዢና ጡረተኛ ፖለቲከኞች እስኬው ላይ በግልፅም በስውርም ጦርነት የከፈቱት።
3- ሐላፊነት እና ተጠያቂነት ያለው የፖለቲካ አካሄድ- እስኬው ደጋግሞ ሲል እንደሰማችሁት “እኛ ሀላፊነትና ተጠያቂነትን ይዘን ነው ወደ ምርጫ የምንገባው፣ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ወረዳ ካሸነፈ ተጠያቂ ነን!” ይል ነበር እስኬው ደጋግሞ! እንደምታውቁቱ ሌሎች ጡረተኛ ፖለቲከኞች የፖርቲ አይነት እና ስም ይቀያይራሉ እንጂ- እንደ እስኬው ጀግነው በዚህ መልኩ ሐላፊነት እና ተጠያቂነት ሲወስዱ ታይተው አይታወቅም!
ለዚህ ነው እስኬው ለእኛ ብዙ ነው የምንለው!
ታዲያ እንዲህ ያለውን ታጋይ- በአካል ስላሰሩ የሚገላገሉ የመሰላቸው ተረኛ ቁማርተኛ ካድሬዎች በእጅጉ ተሳስተዋል!!