>

“ግመል ሰርቆ አጎንብሶ መሄድ” አይቻልም - ለኦቦ ሽመልስ አብዲሣ (ይነጋል በላቸው)

“ግመል ሰርቆ አጎንብሶ መሄድ” አይቻልም – ለኦቦ ሽመልስ አብዲሣ

ይነጋል በላቸው

በፈጠራ ታሪክ አማራንና ኢትዮጵያን አምርሮ እንዲጠላ በወያኔና በኦነግ ተኮትኩቶ ያደገው ወጣቱ “የኦሮምያ ክልል” ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሣ ከሰባት ወራት በፊት ለኦሮሞ ምሁራን በምሥጢር እንዳደረገው የተነገረለት አስደናቂና አስገራሚ ንግግር ብዙ እያወዛገበና “እያስጨነቀን” ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ድብቅ ንግግር እምብዝም እንግዳ ባንሆንም የሀገራችንን ያለፈና  መፃኢ ዕድል ለማይረዱ የዋሃን ይህን መሰሉ የባለሥልጣንና የባለ ዱላ የዕብሪት ንግግር ብዙ ቢያሳስብ አይገርምም፡፡ በዚያ ላይ ዘመኑም የሽብር ነው፡፡

ሕወሓትም ኢትዮጵያንና አማራን ለማጥፋት በትግርኛ በሚደረጉ የሤረኝነት አባዜ የተጠናወታቸው ስብሰባዎች እጅግ በርካታ ሌሊቶችን ማባከኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የነዚያን ዝግ ስብሰባዎች ውጤትም በከፊል አይተናል – ዋናውን ግን በቅርቡ እናያለን (ወያኔዎችና መሰሎቻቸው ገና የዶግ ዐመድ ይሆናሉና! “ዕንባና ጸሎት ሲጥሉ እንጂ ሲወረወሩ አይታዩም” የምንለው ለቀልድ አይደለም)፡፡ የነሱ ዝግ ስብሰባዎች እምብዛም ወደ ውጪ አይወጡም ነበር፡፡ ውጤታቸው ግን በግልጽ ይታይ እንደነበር አጋንንታዊ የተቀበሩ ፈንጂዎቻቸው እዚያና እዚህ እየፈነዳዱ አሁን ድረስ ክፉኛ ሲያውኩን ይታያሉ፡፡ የነዚህኞቹ ከዚያኞቹ የተለዬ መሆኑ ነገርዬው በቶሎ ተዘርግፎ ቁርጣችንን ማወቃችንና የባለሥልጣናቱ ሱሴና ኢትዮጵያየ መዝሙር የፉገራ ጭምብል ስለመሆኑ ብዙም ሳይረፍድ ገና በጧቱ መረዳታችን ነው፡፡ ለማንኛውም ያኛውም ሆነ ይሄኛው ሤራ ከፍላጎት ሳያልፍ በምኞት የሚቀር መሆኑን የማበሥርላችሁ ኢትዮጵያችን ትንሣኤዋ ሊበሠር ጥቂት ጊዜ የቀራት መሆኑን በከፍተኛ መተማመን በመገንዘብ ጭምር ነው፡፡ ነፃነት ግን የቡና ቁርስ አይደለችምና እጅግ ታላቅ መስዋዕትነትን ትሻለች፡፡ ለዚያም የተዘጋጁ እውነተኛ ልጆች አሉ፡፡ ጊዜው ሲደርስና በፈጣሪ ሲታዘዙ ከየበዓታቸው ወጥተው ይህችን ምሥኪን ሀገር በደማቸው ይዋጇታል፡፡ አለመሆኛ ጊዜ እንዳለው ሁሉ መሆኛም ጊዜ አለው፤ ለመረገዝ ጊዜ እንዳለው ለመወለድም ሆነ ለመጨንገፍ ጊዜ አለው፡፡ እያስቸኮለን ያለው ያሳለፍነውና እያሳላፍነው የምንገኘው ሊናገሩት የሚዘገንን መከራና ግፍ “በርግጥ ይወገድልን ይሆን?” የሚለው አጠራጣሪ ጥያቄ ነው፡፡  ከያንዳንዱ ድቅድቅ ጨለማ በስተመጨረሻ ብርሃን መኖሩን አንርሣ፡፡ … 

ሤራና ተንኮል ለጊዜው ማስደንገጡ አይቀርም፡፡ አልዋሽም – እኔ ራሴ ያን ንግግር ስሰማ ራሴን ታምሜ ለብዙ ጊዜ ሽብር በሽብር ሆኜ ነበር፡፡ እውነቱን እያወቅሁት የዕብሪት ንግግሩ ግን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን አስበርግጎኛል፡፡ ዕብድና ሕጻናትም ያስደነግጣሉ፡፡

ኢትዮጵያ በዚህን መሰል ዝግ ስብሰባዎች በሚደረጉ ድንፋታዎች የምትጠፋ ሀገር ብትሆን ኖሮ ከመለስ ዜናዊ የበለጠ ክፉና ሤረኛ በምድር እንዳለመኖሩ ይሄኔ ጠፍተን ነበር፡፡ “አሁን አልጠፋንም እንዴ? አለን ማለት ነው?” የሚል አሽሙረኛ ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ አልጠፋንም፡፡ ያልጠፋነውም በአንድዬ ፈቃድ ነው፡፡ መገነዣ ክሩ ተፈትሎ የሚድን ሰው አላያችሁም? እንነሣለን!!

የሽመልስ አብዲሣ ንግግር የሁሉም ኦሮሞዎች እምነት ነው ለማለት አይቻልም፡፡ የወያኔ ንግግርና እምነት የሁሉም ትግሬዎች እምነትና አቋም እንዳልነበርና እንዳልሆነም ሁሉ ይሄኛውም ልክ እንደዚያው የአክራሪዎች ዕቅድና ፍላጎት ነው፡፡ ይሁንና ብዙ ተከታይ የላቸውም ብሎ መዘናጋት ሞኝነት ነው፡፡ በዚህን ዓይነቱ ግርግር በሥልጣንም ሆነ በሀብት ተጠቃሚው በርካታ የየጎሣው አባል እንደመሆኑ ጥቅም የማያታልለው የለምና፣ በዚያም ላይ ከልጓም ዘር መሳቡ የሚጠበቅ ነውና “ሁሉም ኦሮሞና ትግሬ ኦነግንና ወያኔን አይደግፍም!” ብሎ መዘናጋት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ዘረኞች ስቶ የሚያሳስት ልዩ መግነጢሳዊ ኃይል አላቸው፡፡ በደምብ አየነው፡፡

ሽመልስ ያለውን ብሏል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱም የሽመልስን ንግግር ደግፎ ወይም ተቃውሞ መግለጫ ባያወጣም በተግባር የሚታዬው ግን የሽሜን ንግግር በተግባር ላይ የሚያውል ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ጉንጭአልፋነቱ እየታወቀም ቢሆን በዚህ መከራከር ይቻላል፡፡ የጦሩን ስብጥር፣ የፌዴራል ሥልጣኑን ኦሮሞኣዊ ይዞታ፣ የልዩ ኃይል ግንባታውን፣ የባለሥልጣናትን ሃይማኖታዊ ማንነት፣ የኬኛና ፊንፊኔ ፖለቲካ፣ የመሬት ቅርምት፣ የአዲስ አበባን የሕዝብ አሰፋፈር (ዴሞግራፊ) በኦሮሞ የመለወጥ ጥድፊያ፣ ለአማሮችና ለኦርቶዶክሶች ዕልቂት መንግሥት ያለውን “ገደብ የጣሰ ርህራሄ”፤ ወዘተ.  ማየት ይቻላል፡፡ ለምሣሌ በገዛ ሀገሩ ከ300 በላይ ሕዝብ በእምነቱና በዘሩ ተጨፍጭፎ ሳለ ባንዲራ ዝቅ ተደርጎ እንዲውለበለብና የሀዘን ቀን እንዲታወጅ መመርያ መስጠት ቀርቶ በአንዲት መስመር ደብዳቤ ሀዘኑን ለሚዲያ ፍጆታ እንኳን መግለጽ ያቃተው ጠ/ሚኒስትር ለአንድ ክልል አንድ ታዋቂ አርቲስት ሞት በሀዘን በመንጨርጨር ስንትና ስንት የስም ማስጠሪያ የመታሰቢያ ሀውልትና የጎዳና፣ የትምህርት ቤትና የመናፈሻ ስያሜዎችን በስሙ ሲያስጠራና ቀጥሎም በውጭ ሀገር በደረሰ አደጋ ለሞቱ 100 ሰዎች ማንም ሳይቀድመው የሀዘን መግለጫ መላኩን በተገነዘብንበት ወቅት … ያን ነገር ለታሪክ ፍርድ ከመተው ባለፈ ያኔም ሆነ አሁን ምንም ማለት አልተቻለንም፡፡ የዳዊት ልጅ ሶሎሞን ጨርሶታል – ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡  ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ሀገር እየተገነባች አይደለችም ብሎ ራስን ማሞኘት የማንችልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡

በመሠረቱ አንድ ግዛት ከአንድ ነባርም ይሁን አዲስ አካባቢ ተገንጥሎ ራሱን እንደሀገር ለመመሥረት እስካልጣረ ድረስ አንድ ነባር ሀገር በየ50 እና 100 ዓመቱ ሀገር እየፈረሰ ከዜሮ ተጀምሮ አይገነባም፡፡ ለሽዎችና ለመቶዎች ዓመታት ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ተስማምተውና ወደው በአንድ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ መኖር ከጀመሩ በኋላ ሊፈጠሩ የሚችሉ የአስተዳደር ችግሮችን ከማረምና ከማስተካከል ባለፈ እያንዳንዱ ጎሣና ነገድ ሙቀቱ በጨመረ ቁጥር በየጊዜው እየተነሣ ሀገርን አፍርሼ ልገንባ ቢል ሁከትና ትርምስ ይፈጥራል እንጂ ፍላጎቱ እውን የሚሆንበት ዕድል እጅግ ጠባብ ነው – በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከ80 በላይ ቋንቋዎችና ብሔር ብሔረሰቦች ባሉባት ጥንታዊት ሀገር፡፡ የነዚህ በቁማቸው የጠፉ ልጆች ዓላማና ፍላጎት ከዚህ አኳያ ሲታይ ከማሳቅና ለጊዜው ከማሳዘን ባለፈ ሚዛን የማይደፋው ለዚህ ነው፡፡ ከትናንትናው ከሕወሓት እንኳን መማር አለመቻል በትንሹ አለመታደል ነው፤ ከፍ ሲልም መረገም፡፡ ኃይልና ዕብሪት ሲሰማህ ተቆጣጠረው ወንድሜ – አለበለዚያ ማጣፊያው ለሚያጥር ችግር ይዳርግሃል፡፡ በጠላትነት የፈረጅከው ወገን የሞተ ከመሰለህም ግዴለህም እንደተኛም ቁጠርና ጠንቀቅ በል፡፡ የእውነትን ዘገር ደግሞ አጥብቀህ ያዝ፡፡ 

ስለዚህ የሽመልስ አብዲሣ ንግግር ራስን በጊዜ ከማሳወቅ በዘለለ ትርጉም እንደሌለው መረዳት ተገቢ ነው፡፡ እንደሽሮ ድንፋታ ዓይነት ውሰዱት፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መታየቱ በርግጥ አሳዛኝ ነው፡፡ የዚህ ሰውዬ ቅድመ አያቶችና ምንጅላቶች የኢትዮጵያ ነገሥታት ነበሩ – በየጁም በጎንደርና በሸዋም፡፡ አፄ ገላውዴዎስ ኦሮሞ ነበሩ፣ አፄ ምኒልክ ኦሮሞ ነበሩ፤ አፄ ኃይለ ሥላሤ ኦሮሞ ነበሩ፤ ፊታውራሪ ዲነግዴ (አባ መላ) ኦሮሞ ነበሩ፤ ጓድ ሊ/መንበር መንግሥቱ ኃ/ማርያም ኦሮሞ ነበሩ፤ ጓዶች ሌ/ጄ ተስፋየ ገ/ኪዳንና ተስፋየ ዲንቃ ኦሮሞዎች ነበሩ፤ …. ድንቁርና መጥፎ ነውና – አራትና አምስት መቶ ዓመታትን ወደ ኋላ ወስዶም በጋሪዮሻዊ የ“አሳደህ በለው” የመንጋ አስተሳሰብም ያሣውራልና እነዚህ ሁሉ አማራ ያልነበሩ ወይም በከፊል አማራ የነበሩ ነገሥታትና የጦር መሪዎች የሀገሪቱን የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ኦሮምኛ ማድረግ ጠፍቷቸው እንዳልነበረ እነገመቹና ጫልቱ አያውቁም፡፡ ትግሬው ሀፄ ዮሐንስም በአማርኛ የገዙት ትግርኛን ብሔራዊ ቋንቋ ማድረግ ከብዷቸው አልነበረም፡፡ ግን እነዚያኞቹ ኢትዮጵያውያን ከዚህኛው ደንቆሮ ትውልድ በበለጠና ሊወዳደርም በማይችል ሁኔታ ሰውና ቋንቋ ባሕርያዊ ግንኙነት እንደሌላቸው ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር እንደነዚህኞቹ አልዘቀጡም፡፡ ቋንቋና ባህል የሰው ናቸው እንጂ ሰው የቋንቋና ባህል እስረኛ አይደለም፡፡ እንደድንቁርና ያለ ፈውስ የለሽ በሽታ መቼም የለም፤ አያድርስ ነው፡፡ አማርኛ አማራ ለሚባሉ ወገኖች ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ በትረ መንግሥቱን ለያዙት ኦሮሞዎች ይበልጥ እንደሚጠቅም የሥነ ልሣን ምሁራን ያውቃሉ፡፡ ሰማንያ ስድስቱን የኢትዮጵያ ነገዶች ያስተሳሰረውን አማርኛን ማጥፋት ደግሞ በቀን 86 ንጹሓን ዜጎችን እንደማረድና ማሳረድ ቀላል አለመሆኑን ደናቁርቱ አይረዱም፡፡ ተዘጋጅቶ ማዕድ ላይ የቀረበን ምግብ ብላ ሲሉት ገና ጫካ መንጥሬ፣ መሬት አለስልሼ፣ ዘር ዘርቼ፣ የዘራሁት በቅሎና ተወቅቶ፣ ተፈጭቶና ተቦክቶ ተጋግሮ ነው የምበላው ካለ ሰውዬው በሽተኛ ነው፡፡ በተሠራ ድልድይ ተሻግረህ ጉዳይህን አከናውን ሲሉት “የለም! ጠላት በሠራው ድልድይ ከምሻገር ጠላቴ የሠራውን ድልድይ አፍርሼ፣ አዲስ ድልድይ ራሴው ገምብቼ በራሴው ድልድይ ነው የምሻገረው” የሚል ደደብ ከገጠመህ ችግሩ የማንም ሣይሆን አሳዳጊ የበደለው የዚያ ዘገምተኛ ሰውዬ ነው፡፡ አምልኮተ ተቃርኖ የሚያጠቃቸው ሰዎች ያሳዝናሉ፡፡ ወደው አይደለም፡፡

ሽመልስ ያለውን ለመስማት በየዩቲዩቡ ግቡና ፈትሹ፡፡ ደግሞም ስሙት፡፡ ጥሩ ነው፡፡ የሀገሬ ባላገር “ሽልም ከሆነ ይገፋል፤ እህልም ከሆነ ይጠፋል” የሚለው አለነገር አይደለም፡፡ በእጅ የገባን የሀገር አስተዳደር ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ ይዞ በፍትህ እንደማስተዳደር እንዲህ ያለ ቅሌት ውስጥ ከገቡ ዋጋ ከፋዮቹ እነሱ እንጂ ሌላ አይሆንም፡፡ ኦሮምያ በሚባለው አካባቢ የጠፋው ያ ሁሉ የሰው ሕይወትና የወደመው ሀብትና ንብረት ምክንያቱ እንደሚባለው ኦነግ ሸኔና ወያኔ ሳይሆኑ እዚሁ ማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል – የተጠቀሱት ኃይሎች ሚና ቀላል ነው ባይባልም፡፡ አባይን ተሻግረው በማሳመንም በማደናገርም (ሽሜ convince and confuse ሲል የገለጸው) የሠሩትን “ጀብድ”ም ዘግይቶም ቢሆን አንዳንድ የዋሃን እንዲገነዘቡ መደረጉ አይከፋም፡፡ የሽመልስ መረጃ በገንዘብ ቢተመን ቢሊዮኖችም ያንሱታል፡፡ መረጃ ደግሞ አይናቅም፤ አይካበድምም፡፡ ኦሮምያ ያሰለጠናቸው በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የልዩ ኃይል አባላት፣ ምሥኪን አማሮች ሲታረዱና ለዘመናት የለፉበት አንጡራ ሀብታቸው በእሳት ሲጋይ እንዲያድኗቸው ሲለምኗቸው “ትዕዛዝ አልደረሰንም!” የማለታቸውን ምሥጢር መረዳት የሚቻለው የሽመልስን ንግግርና የነአዳነች አቤቤን በህግ ስም ንጹሓን ዜጎችን በመናጆነት አስሮ ማሰቃየት ስንታዘብ ነው፡፡ ስለዚህ መረጃው እንደመረጃ ወርቅ ነው፡፡ አሁን ሁሉም ግልጽ ነው – ሰበቢን እንጂሩ፡፡

ለማጠቃለል ያህል – ይህን በጠራራ ፀሐይ በግልጽ የተነገረን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዕቅድ የምታስተባብሉ እንዳላችሁ ለመረዳት ችለናል፡፡ ለምሣሌ አክቲቪስት ሥዩም ተሾመ የተባለው ሰው ለሀገሩ ብዙ እንዳልደከመ አሁን አሁን ሚናውን ከሀገር አፍራሾች ጋር በመወገን የዚህን ልጅ ንግግር ሲያስተባብል ሰምቻለሁ (ይህን ንገሩልኝማ – ሽመልስ የተናገረውን ነገር የዛሬ ሰባት ወርም ተናገረው የዛሬ ሰባ ዓመት በመረጃው ዋጋ ላይ ልዩነት የለውም፡፡ ልዩነት ሊኖር ይችል የነበረው ለምሣሌ ፍሬኑ የማይሠራን መኪና ፍሬኑ እንደማይሠራ አንድ ሰው ተናግሮ ሳለ ነገር ግን ያን መረጃ ያላወቀ ሰው መኪናውን ነድቶ በራሱም ሆነ በሌላ ወገን ላይ ጉዳት ቢያደርስ ነው … ስለዚህ ይህን መረጃ ከጊዜ አንጻር ለማስተባበል መሞከር ‹የእናቴ መቀነት አሰናከለኝ› ከሚለው የጦጢት ፉርሽ አመክንዮ ጋር የሚመሳሰል ነው)፡፡ በዶ/ር አቢይ የሚያማልል ንግግር የተንበረከኩና ለፍርፋሪ ሥልጣን ደጅ የሚጠኑ ወይም በካፈርኩ አይመልሰኝ “አንዴውኑ ደግፌዋለሁና የመጣው ቢመጣ ወደኋላ አላፈገፍግም” የሚሉ ግትሮች ሁሉ ከአሁን በኋላ ምን አፍ እንዳላቸው አላውቅም፡፡ ከዚህ አንጻር የኢሳት ቴሌቪዥን፣ የኢዜማ ፓርቲና ጥቂት የማይባሉ ዕውቅናና ዝና ያላቸው ግለሰቦች በሕዝብና በሀገር ስቃይ ነግዶ ለማትረፍ የሚያደርጉትን ሽር ጉድ ቢያቆሙ የመጀመሪያ ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው ናቸው፡፡ የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ጠባሳ ትቶ እንዳያልፍ እያንዳንዳችን ራሳችንን ብንፈትሽ ጥሩ ነው፡፡ ይህ ጨለማ በርግጠኝነት ይነጋል፤ ትዝብቱና በታሪካችን መዝገብ ላይ የምናሳርፈው ቁስል ግን መቼም ሲጠዘጥዘን ይኖራልና ያን ነው መጠንቀቅ፡፡ እናም እባካችሁን ወንድም እህቶቼ! ሆድ መጥፎ ነውና የሆዳችንን ልክ በእውነተኛ ገቢያችን መጠን እናድርግ፤ የሥልጣን ሱስ ያለብንም ቆም ብን እናስብ – ሥልጣን ከሀገርና ከወገን ጉስቁልና አይበልጥምና፡፡ የዓለምና የሥጋ ፍላጎት ወሰን የለውም፡፡ ዝም ብለን ከተከተልነው ገደል ይከተናል – ሣሩን አይቶ ገደሉን ሳያይ ዥው ወዳለው ገደል ገብቶ እንደተንኮታኮተው በሬ፡፡ ለዚህች ትንሽ ቀሪ ሕይወት ብለን የኅሊና ኪሣራ ውስጥ አንግባ፡፡ ሽመልስን ለማስተባበል ስንንደፋደፍ ራሱም ሊታዘበንና “መቼ እንደሱ እንደምትሉት ወጣኝ!” ብሎ ሊያዋርደንም ይችላል፡፡ ለዚህ ሰውዬ ሽፋን ለመስጠት መሞከር የፍየል ጅራት መሆን ነው – ምንም ገመና የማይሸፍን ብጣቂ ነገር፡፡ የልጁ ንግግር በጣም ግልጽ ነውና የአንድምታ ፍቺ መምህራን አያስፈልጉትም፡፡ ግመል ሰርቆ አጎንብሶ መሄድ እንደማይቻል ወግቶ ይማርህም አያዋጣምና ሰውዬውን ይቅርታ ማስጠየቅም ሆነ ከኃላፊነቱ ማስነሳት መፍትሔ አይሆንም፡፡ መፍትሔውን ጊዜ እንደሚያመጣው በልበ ሙሉነት በግሌ ባውቅም ለአሁኑ ግን ጥጋብን በረድ አድርጎ አካባቢያዊ ኹነቶችን ማጤን ነው፡፡ በቃ – ወደ ኅሊና ተመልሶ ሰው መሆን፡፡ ጠላት ባጠመደው ፈንጅ ከመረማመድ ተቆጥቦ የጤናማ አስተሳሰብ ባለቤት መሆን፡፡

Filed in: Amharic