>
5:16 pm - Sunday May 23, 2647

ለማ መገርሳ የሀገርና የህዝብ ባለውለታ ነው ! (አበጋዝ ወንድሙ)

ለማ መገርሳ የሀገርና የህዝብ ባለውለታ ነው !

 አበጋዝ ወንድሙ


ባለፈው ሳምንት፣ የኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ለሁለት ቀናት በክልሉ ውስጥ ስላለው ሁኔታና በፓርቲው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስብሰባ ተቀምጦ ነበር። ስብሰባው ሲጠናቀቅ በክልሉ ውስጥ ስላለው የጸጥታ ሁኔታ፣ በዜጎች ላይ ብሄር ወይንም ሃይማኖት ተኮር የሆኑ እጅግ አሳዛኝ ግድያዎችና አካላዊ ጥቃቶች፣መፈናቀሎች ፣ የግለሰቦች ንብረት ውድመትና፣ እጅግ የከፋ የከተሞች ውድመትን አስመልክቶ ስላደረገው ውይይትም ሆነ  ችግሩንም በጊዜያውነትም ሆነ በዘላቂነት ለመቅረፍ ያሳለፈው ይሄ ነው የሚባል ውሳኔ አልሰማንም።

ይልቁንም በስብሰባው መጨረሻና ከዛ በዃላ በኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲም ሆነ በዜና አውታሮች የመወያያ ርዕስ ሆኖ የከረመው፣ በሶስት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የብልጽግና ፓርቲ ወሰድኩ ያለው፣ ከድርጅቱ አመራርነት የማገድ ተግባር  ነው።

እግድ ከተጣለባቸው ሶስት የአመራር አባላት አንዱ ለማ  መገርሳ ነው። ለማ የዛሬ ዘጠኝ ወር ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ  በሰጠው ቃለ መጠይቅ መደመርየሚለው እሳቤ ብዙም እንዳልገባው፣ኦዴፓን በአሁኑ ጊዜ አፍርሶ ብልጽግና የሚባል ፓርቲ መመስረትን እንደማይደግፍ ቢደግፍም አንኳን አሁን ወቅቱ እንዳልሆነና የቸኮለ ውሳኔ ነው ብሎ እንደሚያስብ  ሃሳቡን አጋርቶ ነበር።

ይሄ የለማ ቃለ መጠይቅ አነጋጋሪ እንደነበርና፣ እናት ድርጅቱ ኦህዴድንም ባልጠበቀው ወቅትና ሁናቴ መከወኑ ስላሳሰበው ነባርና የአሁን አመራሮችን ያካተተ መደበኛ ስብሰባ አካሂዶ ለማ ላይ ጫና በማድረግ እርቅ ወርዷል የሚል መግለጫ በጊዜው ሰጥቶ ነበር።

ወርዶ የነበረው እርቅ ምን እንደነበር ድርጅቱ በጊዜው ባለመግለጹ፣ በርግጠኝነት ይሄ ነበር ለማለት ባይቻልም ለማን (መመስረት፣ ቢያንስ ጊዜው አይደለም ብሎ የሚያስበው ፓርቲን ) ከስም ያለፈ የድርጅቱ አመራር አካል ነበር ብሎ ማሰብ ይከብዳል። የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱም  ለማ የታገደበትን ምክንያት ሲያቀርብ  መሰረታዊ ብሎ  ያለው በልዩ ልዩ የፓርቲው  የአመራርና ሌሎችም ስብሰባዎች አለመገኘትን ነው።

 ከዚህ በመነሳት ምናልባትም ለማ ቃለ መጠይቁን በሰጠበት ወቅት እንዳለው፣ ገፍተው (እስኪያስወጡኝ ድርጅቱ ውስጥ ሆኜ እታገላለሁ ያለው) መንግስታዊ ሃላፊነቱን እያካሄደ ፓርቲውን ግን በሚመለከት ውስጣዊ ትግል ሲያካሂድ ቆይቶ ውጤት ለማምጣት ባለመቻሉና ፓርቲው ደግሞ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በእርቅ አስታግሶ አመቺ ባለው ሰዓት የእገዳው ሰለባ አድርጎታል ማለት ይቻላል።  

በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው ውዝግብ ምንም ይሁን ምን ክስተቱ፣ ለጊዜውም ቢሆን ለማ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበረውን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ያከሰመ ነው ብለን ለመውሰድ እንችላለን።

ያም ቢሆን ግን የአበው ብሂል እንደሚለው፣  ለማ ሰው የጠፋ እለት ሰው ሆኖ የተገኘ ነበርና በድርጅት ውስጥ አሁን የተፈጠረው ሁናቴ የለማን የሀገር ባለውለታነት በምንም አይነት ሊያሳንሰው አይችልም ፣ አይገባማምም !!

 መስከረም 2008 ዓ. ም. ኦህዴድ አካሂዶ በነበረው አስቸኳይ ስብሰባ ከዚህ ቀደም በኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ ባልተለመደ መልኩ (እህት የሚባሉ ድርጅቶችን በዋናነትም ህወሃትን ሳያማክር! ) ሙክታር ከድርና አስቴር ማሞን ከክልልና ከድርጅት አመራር (በወቅቱ ሁለቱም በም/ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የመንግስት ኃላፊዎችም ነበሩ!) አንስቶ ለማንና ወርቅነህን ሲሾም፣ ለማ ነባር የኦህዴድ አባል የነበረ ቢሆንም፣ ከሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የተዋወቀበት ወቅት ነበር።

የክልል ፕሬዘዳንትነቱን ሲረከብህወሃት አምላክ አይደለችምየሚለውን መርሆውን ተከትሎ የክልሉ ፕሬዘዳንት ከሆነ ማግስት ጀምሮ፣ በተጠና መንገድ በክልሉ ውስጥ የነበረውን የህወሃት ጣልቃ ገብነት መከርከም በመጀመሩ፣ በክልሉ ህዝብ ዘንድ ተሰሚነትንና ትብብርን በማግኘት፣ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በአንጻራዊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ  ማረጋጋት ቻለ። 

ይሄንን የህዝብ ተቀባይነት አጉልቶ ያሳየውም፣ 2007 .ም.  እሬቻ ክብረ በዓል ላይ የብዙ መቶ ሰዎችን ህይወት የቀጨው ድርጊት እንዳይደገም በማሰብ፣ በ 2008 ዓ. ም.  ህዝብ  የፌደራል ፖሊሶችና ወታደሮች  በስፍራው እንዳይገኙ ያቀረበውን ጥያቄ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ተደራድሮ ማሳካት መቻሉና፣ ይሄም በመሆኑ በዓሉ ያለአንዳች ችግር በስኬት መጠናቀቁ ነበር።

በዚህ ወቅት እሱ ያዋቀረውናየለማ ቡድንተብሎ መታወቅ የጀመረው ስብስብ ከክልሉ አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ መፍጠር ጀምሮ ፣በኔ ግምት ሁለት ዋና የምላቸው ተግባራትን አከናውኗል።

 በመጀመሪያ ደረጃ ህወሃት 26 ዓመት የበላይነቱን ማስጠበቂያ ዋና መሳሪያ አድርጎ ይጠቀምበት የነበረውን፣ በኦሮሞና አማራ ማህበረሰብ መሃል ጥርጣሬና አለመተማመን፣ ከፍ ሲልም ጥላቻ በመዝራት የገነባውን የክፍፍል አጥር፣ ጎንደር በተካሄደው ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ህዝብ ‘የሚፈሰው የኦሮሞ ደም ደማችን ነው’ በሚል ያበሰረውን የትግል አጋርነት በማጠናከር ፣ ባህርዳር ድረስ በመሄድ ባደረጉት ታሪካዊ ጉዞ መስበር መቻላቸው ነበር ።

ሁለተኛው የነለማ ቡድን ትልቁ አስተዋጽኦ በሻእቢያ የተጎነጎነውን፣ ሀውሃትም ሆነ ሌሎች የብሄር ድርጅቶችን ጨምድዶ ይዞ ብዙ እዳ ያስከፈለንን ታሪካዊ ትርክት ድባቅ በመምታት፣ የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር፣በኢትዮጵያ ሃገራዊ ግንባታም ሆነ እድገት ፣እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ነጻነቷን ጠብቃ እንድትኖር ያደረገውን አኩሪ ተጋድሎ ትክክለኛ ስፍራውን እንዲይዝ ማድረጋቸው ነው ።

የለማ ቡድን’ እነዚህን ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ተግባራዊ በማድረጉም በልዩ ልዩ ተቃውሞዎች ለስድስት ዓመት ስትናጥ የነበረችው ሀገራችን ውስጥ ሰፍኖ የነበረውን የሀገር መበታተን ፍራቻ በእጅጉ ለማቃለል በመቻሉና የሀገር ባለውለታነቱን በማስመስከሩ ክብርና ምስጋና ይገባዋል።

ለማ መገርሳ በአንድ ወቅት ይሄንን ብሎ ነበር 

ለዚች አገር ለአንድ ዓመትና ለአንድ ቀን አይደለም ለአንድ ሰዓትም ቢሆን ዋጋ የከፈለ ሰው ክብር ሊኖረው ይገባል!! እኛ አገር ዕድሜውን በሙሉ መስዋዕት ያደረገ ሰው ክብር ይሰጠዋል?.. ስንዞርበት ለውለታው ክብር ሳንሰጥ ኑሮውን፣ህይወቱን ሁለመናውን እናመሳቃቅላለን፤ ይህ ነው የእኛ አገር የፖለቲካ ባህል፤ ይህ ነው ከውስጣችን መውጣት ያልቻለው መርዝ !! 

ይሄ ክፉ የፖለቲካ ባህል በሱ ላይ መደገም የለበትም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ 

Filed in: Amharic