>
11:57 am - Tuesday June 6, 2023

ዐቢይ አሕመድ በባሕር ዳር የአሊ ቢራን የጭካኔ አስተያየት ደግሞታል!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ዐቢይ አሕመድ በባሕር ዳር የአሊ ቢራን የጭካኔ አስተያየት ደግሞታል!    

አቻምየለህ ታምሩ

* ለብአዴኖች በሰጠው መመሪያም በቄሮ የተካሄደው ፍጅት “በሓጫሉ ግድያ የተበሳጨ ኦሮሞ ያደረገው” መሆኑንና  በድርጊቱ የተገደለው አብዛኛው ኦሮሞ ስለሆነ  “ዘር ተኮር” የሆነ ጥቃት አድርገው እንዳያቀርቡት ትዕዛዝ አስተላልፏል!!!
 
አዛውንቱ ድምጻዊ አሊ  ቢራ ባለፈው ሰሞን  ከፕራይም ሜዲያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ዘር እና ሃይማኖት ላይ ስላነጣጠረው የሰኔ 23 ፍጅት  በሰጠው አስተያየት   “የኦሮሞ ሕዝብ ያጣው ውዱን እና እንቁ ልጁን ነው። በዚያ ስሜት ውስጥ ያደረገው ነገር  ልክ ነው። አንድ ሰው ዘሎ ኪስህ ገብቶ ቦርሳህን ሲወስድብህ ዝም ብለህ ቆመህ አታይም። React ታደርጋለህ፤ ስለዚህ ችግሩ የሚሆነው እንቁህን ሲነጥቁህ ዝም ብለህ ካየህ ነው። ያጣነው እኮ ሀጫሉን ነው። መንግሥትም ከዛ በኋላ ሕዝቡ እንዲህ አጠፋ፣ እንዲያ አደረገ ብሎ የሚያወራው ነገር ስህተት ነው” ብሎ ነበር። በአሊ ቢራ አስተያየት የዘጠኝ ወር እርጉዝ መታረድ፣  በግፍ ተፈጅተው ለጅብ የተጣሉ አማሮች በዘራቸው እና ሃይማኖታቸው ብቻ መወንጀላቸው ትክክል ነው።
ይህን የአሊ ቢራን የጭካኔ አስተያየት  ኢትዮጵያ ውስጥ የቆመው የአፓርታይድና የዘር ማጥፋትን ፖለቲካው ያደረገው አገዛዝ ቁንጮ የሆነው ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ወደ ባሕር ዳር አቅንቶ በእንደራሴዎቹ በብአዴኖች አውጫጭኝ በመገኘት አሊ ቢራ የተናገረውን  ደግሞታል።  ለብአዴኖች በሰጠው መመሪያም በቄሮ የተካሄደው ፍጅት “በሓጫሉ ግድያ የተበሳጨ ኦሮሞ ያደረገው” መሆኑንና  በድርጊቱ የተገደለው አብዛኛው ኦሮሞ ስለሆነ  “ዘር ተኮር” የሆነ ጥቃት አድርገው እንዳያቀርቡት ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ቄሮ ባካሄደው ፍጅት የተገደሉ የኦሮሞ ተወላጅነት ያላቸው ሰዎች መኖራቸው ፍጅቱን የዘር ማጥፋት ከመሆን ያሳንሳዋልን? ናዚዎች ባካሄዱት የእብራውያን የዘር ማጥፋት ለዘብተኛ ጀርመኖች መገደላቸው፤ ኢንተርሃሚዮች ባካሄዱት የቱትሲዎች የዘር ማጥፋት ለዘብተኛ ሁቱዎች መገደላቸው ፍጅቱን የዘር ማጥፋት ከመሆን ያሳንሰዋልን? የዘር ማጥፋት ወይም ጅኖሳይድ የመጀመሪያው እርምጃ ጅምላ ፍረጃ እና ጅምላ ስያሜ መስጠት አይደለምን? የኦሮሞ ተወላጆች ሆነው በአማራነት ወይም ነፍጠኛነት ተፈርጀው ከተገደሉ  የሞቱት የኦሮሞ ተወላጆች መሆናቸው ፍጅቱን ከዘር ማጥፋት አያሳንሰውም።
ዐቢይ ኦሮሞ አድርጎ ሊያቀርባቸው የሚፈልጋቸውን ግፉአን ቄሮ ምን ብሎ በመፈረጅ ነው  ነው በዱልዱም ያረዳቸው? አማራ ወይም ነፍጠኛ ብሎ በመፈረጅ አይደለምን? ነፍጠኛ ወይም አማራ እየተባሉ በአማራነት ወይም በነፍጠኛነት ተፈርጀው የአማራን የሰማዕትነትን ጽዋ አማራን ለማጥቃት በሰለጠኑ ቄሮዎች እጅ እንዲጨልጡ የተደረጉ ኦሮሞዎች መገደላቸው በምን ስሌት ነው ሰኔ 23 የተጀመረው ፍጅት  የዘር ማጥፋት የማይሆነው? ቄሮ በግፍ ያረዳቸው የኦሮሞ ተወላጅነት ያላቸው ግፉአን ስለተፈጸመባቸው ግፍ እየሰጡት ያለው ምስክርነት ምንድን ነው? በኦሮሞነታቸው እንደተገደሉ ነው እየተናገሩ ያሉት?  <<ኦሮሞ ነን እያልናቸው  ነፍጠኛ፣ አማራ ናችሁ እያሉ ነው ያረዱን>> በማለት አይደለም ምስክርነታቸውን እየሰጡ ያሉት?
ዐቢይ አሕመድ  በሻሽመኔ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሐረርጌና በዝዋይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት የዘር ማጥፋት አይደለም፤ የቀቀለውን ቁጥር በደስኮር በብዛት የተገደለው ኦሮሞ ነው እያለ የዘር ማጥፋቱን ለማድበስበስ ታትሮ እየሰራ ያለው  የአማራ እጣ ፈንታ የደረሳቸው የኦሮሞ ተወላጅነት ያላቸው ግፉዓን <<ኦሮሞ ነን እያልናቸው  ነፍጠኛ፣ አማራ ናችሁ እያሉ ነው ያረዱን>>  በማለት ምስክርነታቸውን እየሰጡ ባሉበት ሁኔታ ነው።
ብአዴንም ማምሻውን ዐቢይ አሕመድ የሚፈልገውንና በአማሮች ላይ የተካሄደውን የዘር ማጥፋት የሚያድበሰብስ መግለጫ አውጥቷል። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ አያትና ቅድመ አያቶቻቸው ጭምር በሻሽመኔ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሐረርጌና በዝዋይ ተወልደው ባደጉበት ምድር የተፈጁ  አማሮችን ነውረኛው ብአዴን በመግለጫው  የአማራ ክልል ተወላጆች  አድርጎ አቅርቧቸዋል።
ሽመልስ አብዲሳ በአማርኛ መቃብር ኦሮምኛን እያስፋፋን ነው፤ በሕግም በሕገ ወጥም አዲስ አበባን ኦሮሞን እንድትመስል እናደርጋታለን፤ ኢትዮጵያን አዳክመን ለኦሮሞ እናስገብራታለን፣  ወዘተ እያለ  የተናገረውንም  በሚመለከት የአማራ ጠላቶች ጉዳይ አስፈጻሚው ብአዴን  በመግለጫው የአንድ ግሰለብ የአፍ ወለምታ አድርጎ አልፎታል። ሽመልስ አብዲሳ ግን ጃዋር ባሾለከው ንግግሩ ያቀረበው ዐቢይ አሕመድ የሚመራውን  ፓርቲ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት እና ቀጣይ እቅድ እንጂ ተራ የአፍ ወለምታውን አልነበረም።
አማራ በግፍ እየተፈጀ ያለው፤ ኢትዮጵያም እየተዳከመው ያለችው ብአዴን የሚባለው የነውረኞች ስብስብ መንገዱ ላይ ቆሞ ነው። በመሆኑም የመጀመሪያው የለውጥ እርምጃ  መንገዱ ላይ የቆመውን ብአዴንን መጥረግ ነው።  አሁንም እንደግመዋለን! ብአዴን የሚባል የአማራ ጠላቶች እንደራሴ እስካለ ድረስ የአማራ ውርደት ይቀጥላል። ብአዴን የሚባለው ስብስብ በአማራ ሕዝብ ላይ ተጭኖ እስከቀጠለ ድረስ አማራ ወደፊትም ገና ብዙ ውርደት ይጠብቀዋል።
በአማራ ተወላጆች ላይ እየተካሄደ ላለው የዘር ማጥፋት  ዋነኛዎቹ ተጠያቂዎች ከአማራ ሕዝብ ባሕል፣ ታሪክ እና እሴት የተፋቱ፣ እንጥፍጣፊ ኢትዮጵያዊነት፣ ኅሊና እና ወገናዊነት የሌላቸው ወያኔዎች “ገ’ለን ቀብረነዋል” ያሉት አማራ መቃብሩን ፈንቅሎ እንዳይወጣ መቃብር ጠባቂ እንዲሆኑ ተደርገው የተፈጠሩት ነውረኞቹ ብአዴኖች ናቸው።
Filed in: Amharic