>
5:33 pm - Tuesday December 5, 1933

የሰኔ 23 2012 ዓ.ም. በባቱ፣ሻሸመኔ እና አካባቢው የነበሩ ጥቃቶችን ተከትሎ የተጠናቀረ ሪፖርት (አዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ)

የሰኔ 23 2012 ዓ.ም. በባቱ፣ሻሸመኔ እና አካባቢው የነበሩ ጥቃቶችን ተከትሎ የተጠናቀረ ሪፖርት

 
በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ 

መግቢያ
አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 22/2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሌሊቱን እና በማግስቱ 23/10/12 የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች ተከስተው በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡
ከኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞችና አርቲስቶች ሕብረት ጋር ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተርና ቡድናቸው በሐምሌ 27 እና 28 2012 ዓ.ም.በነበሩት ቀናት በባቱ እና ሻሸመኔ ከተሞች እና አካባቢ በተወሰነ መልኩ ተዘዋውረን የደረሰውን ጉዳት ለማየት ሙከራ አድርገናል፡፡
ባቱ ከተማ
አብነት ገለታው
እኛ አግኝተን ያናገርናችው ሶስት ወንድማማቾች ባቱ ከተማ ዘመድ ቤት ሀዘን ተቀምጠው ቢሆንም አምስት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ማለትም አባታቸውን፡ እናታቸውን፡ ወንድም፣ እህታቸውን እና የአጎታቸውን ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ ያሳጣቸው ድርጊት ግን የተፈጸመው ከባቱ 7ኪ.ሜ ርቃ በምትገኘው አዳሚ ቱሉ ከተማ እንደነበር ነግረውናል፡፡
የሟቾች ስም ዝርዝር
አቶ ገለታው አውላቸው   (አባት)  ዕድሜ 60
ወ/ሮ ፀሀይ መንግስቴ      (እናት)  ዕድሜ 47
ወጣት ሳሙኤል ገለታው   (ወንድም) ዕድሜ 24
ወጣት ነፃነት ገለታው      (እህት) እድሜዋ 22
ወጣት ዋሴ አግዜ        (የአጎት ልጅ) እድሜ 21 ናቸው
ተጎጂዎቹ ጥቃቱ የደረሰባቸው በእምነታቸውና በማንነታቸው እንደሆነ የሚያምኑ ሲሆን ቤተሰቦቻቸውን ያጡት በድብቅ ሳይሆን ፖሊስ ባለበት ሀገር በቀን ቤታቸው ተሰብሮ ተገንጥሎ መስኮት በመሰባበር ገብተው በግፍ በአሰቃቂ ሁኔታ ቆራርጠው ነው የገደሏቸው ብለውናል፡፡
“ መግደላቸው ሳያንስ ሙሉ ቀን ከጠዋት 3፡30 እስከ 10 ሰዓት ድረስ ሳይሸሹ ፤ ሌሎች ልጆችም አሉ ሲመጡ እንገድላለን ብለው እየጠበቁን ስለነበር እኛም ሄደን ሬሳ እንኳን ማንሳት አልቻልንም ነበር፡፡ አዱኛ ንጉሴ የተባለ ደግ የአባታችን ጓደኛ ነው ፡በዚያ አስቸጋሪ ሰዓት ሄዶ ሆስፒታል በመውሰድ የሬሣ ሣጥን በመግዛት ያነሳቸው፡፡ ቤተሰቦቻችን ስራ ከመስራትና ለአካባቢው መልካም ከማድረግ ውጪ ምንም ነገር ውስጥ የሌሉ ነበሩ፡፡ለተከራዮቻቸው እንኳ እንደ አባትና እናት ደግሰው የሚድሩ የሌሎችን ሰዎች ልጆች እንኳ ያሳደጉ ያስተማሩ ነበሩ፡፡ በማያውቁት ተገደሉብኝ ”  ብሏል ልጃቸው  አብነት ገለታው፡፡
ሚክያስ ገለታው 
ሚክያስ እሱም አምስት ቤተሰቦችን የተነጠቀ የአብነት ወንድም ሲሆን ሁኔታውን እንዲህ ገልጾልናል፡፡
“ ቤተሰቦቼን በቀን በፋስ በቆንጨራ ቁርጥርጥ አድርገው ነው የገደሉብኝ ሬሳ እንኳ ማንሳት አልተቻለም፡፡ ምንድነው ፖሊስ የለውም እንዴ ሀገሩ? ፖሊስ ምንድን ነው የሚሰራው? አባታችን የሀገር ሽማግሌ ነበር፡፡ በማግስቱ የኛ ቤተሰቦች የቀብር ቦታ አዳሚ ቱሉ ማርያም ቤ/ክርስትያን ያዘጋጁት ቦታ ነበር ለመቅበር ስንሄድ አልተቻለም፡፡ ከዚያ ጊዮርጊስ ቤ/ክርስትያን ስንሄድ ደግሞ ጭራሽ ነፍጠኛ እዚህ አይቀበርም ብለው ከለከሉ ከዚያ መከላከያ መጥቶ ነው የአባታችን ወዳጅ የቤተሰቡን የመቃብር ቦታ ሰጥቶን ለመቅበር እንኳን የቻልነው፡፡ የኔስ ቤተሰቦች አልቀዋል፡፡የሌላውስ የመኖር ዋስትና ምንድን ነው? እነዚህ ገዳዮች የኛን ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ክርስትያን ሳይሉ የመላውን ኢትዮጵያውያን እናት አባት እህት ወንድም ና ዘመድ ነው የገደሉት፡፡ መንግስት እነዚህን ገዳዮች በአደባባይ ያውጣልን፡፡ እኛም ቤተሰቦቻችን ጀምረውት የነበረውን በጎ ስራ ሁሉ እናስቀጥላለን፡፡ማረድ የፈለገ መጥቶ ማረድ ይችላል ” ብሎናል፡፡
መምህር አስናቀ ደቻሳ
በባቱ ከተማ በቤ/ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሰባሰቡትን ንብረታቸው የተጠቃባቸውን ወገኖች በጎበኘንበት ወቅት ስለሁኔታው አጠር ያለ መግለጫ የሰጡን በሙያቸው መምህር የሆኑት አቶ አስናቀ ደቻሳ እንደገለፁልን፡
“ወደ 218 ገደማ ሆቴሎች የንግድ ቦታዎች ዝቅተኛ ተዳዳሪ ንብረቶች ፋርማሲ ሳይቀር ተቃጥለዋል ወድሟል፡፡ ወደ 30 የሚሆኑ የንግድና የቤት ተሸከርካሪዎች ተቃጥለዋል፡፡ ወደ 52 የሚሆኑ የንግድ ስፍራዎች ንብረታቸው ወድሟል፡፡ ተጎጂዎችንም ማህበረሰቡ ተቀብሎ በየሰው ቤት ይገኛሉ፡፡የችግራቸው መጠን ቢለያይም የሚቀምሱት የሚለብሱት የሌላቸው ወገኖችም ግን አሉበት፡፡ የምግብ፣የአልባሳት እና መልሶ መቋቋም የሚያስፈልጋቸው ናቸው” ብለውናል፡፡
አቶ መንበሩ አድገህ
የ 80 ዓመቱ አቶ መንበሩ ፡በባቱ ፣መቂና ሞጆ ከተሞች ላይ በመንግስት መ/ቤት ለ42 ዓመታት አገልግለው  ጡረታ ከወጡ 20 ዓመት እንደሞላቸው የሚናገሩት የዕድሜ ባለፀጋ በ23/10/12 በባቱ መኖርያ ቤታቸው ስለተፈጠረው ሁኔታ ሲናገሩ
“ብዙ ሆነው መጡ ግባ ብለው አስገብተው አንድ ሁለቱ ጭንቅላቴን መቱኝ ሌሎቹ ተው ብለው ሌላ ሰው ቤት አስገብተው ዘጉብኝ ከዚያ ቤቴና ንብረቴን እሳት አነደዱበት፡፡ሳገለግል የኖርኩት ሁሉንም ህዝብ ነበር፡፡ እኔም አብሬ እሞታለሁ ምን ቀረኝ ብዬ እሳት ልገባ፡መከላከያዎች ናቸው ያተረፉኝ፡፡”
 ሻሸመኔ
ሻሸመኔ ከተማዋን ተዘዋውረን እንደተመለከትናት መጠነ ሰፊ የንብረት ጉዳት ደርሶባታል፡፡ህይወታቸውንም ያጡ ወገኖች አሉ፡፡
አቶ እንዳልካቸው ጥጋቡ
አቶ እንዳልካቸው መኖርያ ቤት ስንደርስ ሀዘን ላይ ነው ያገኘናቸው፡፡ ከሟች ባለቤታቸው ጋር በኦርቶዶክስ ክርስትና መሰረት ቆርበው እንደነበር እና ለ22 ዓመታት በትዳር ቆይተው እንደነበር ነግረውናል፡፡ በትዳራቸውም ኤፍራታ የተባለች የ13 ዓመት ሴት ልጅ እና ሶፎንያስ የተባለ የ11 ዓመት ወንድ ልጅ አፍርተዋል፡፡
“ በ23/10/12ዓ.ም. ብዙ የማናውቃቸው ሰዎች ወደ ቤታችን በመምጣት ክፈት አንተ ነፍጠኛ አማራ፡ የነፍጠኛ ቤት እያሉ በሩን መደብደብ ጀመሩ በሩ ጠንካራ ስለነበር በገጀራ 3 ቦታ ቀደዱ ከዛም ሰው የሚገባበትን አነስተኛ ተካፋች በመፍለጫ ላሜራውን ቀደዱ ዋናውን በር ቤንዚን አርከፍክፈው በሩን እያቃጠሉ ገንጥለው ገቡ፡፡ ባለቤቴ የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር የነበረችው ወ/ሮ ሜሮን ተስፋዬ፤ እንዲሁም ሁለት ልጆቻቸው የ11 ዓመቱ ሶፎንያስ እንዳልካቸው እና እህቱ የ13 ዓመቷ ኤፍራታ እንዳልካቸው በቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ እኔ ላይ ጌጀራ ደግነው ባለቤቴን መሬት ላይ ጣሏት እግሯን ይዘው ጎተቷት፡፡ ልብሷን አስወልቀው እንገልሻለን የአማራ ልጅ አይወለድም የክርስቲያን ልጅ አይወለድም እያሉ ወደ አንገቷ እና ሆዷ አስጠግተው እየሳሉ ሲያስፈራሯት ስለእናት ብላችሁ እናት የላችሁም እያለች እየጮኸች  ለመነቻቸው፡፡
 አብረው ከነበሩት ሴቶች መካከል ግደላት ሰንጥቅና አሳየኝ የምትልም ነበረች፡፡ ይህ አሰቃቂ ሁኔታ  ሲሆን ሁለት ልጆቿን ግራና ቀኝ አንበርክከው እነሱ ፊት ነበር፡፡ ይህ ድርጊት በግምት ከ40 ደቂቃ እስከ 1ሰዓት ያህል ቆይቷል በዚህ መሃከል ግን ባለቤቴ ሜሮን ራሷን ስታ ነበር፡፡ ልጆቼም እያለቀሱ ሶፎንያስም እናቴን እያለ ይጮህ ነበር እኔን ግደሉኝ እያለ ያለቅስ ነበር፡፡ በዚህ መሐል ከእነርሱ መካከል አንዱ በቃ በቃ እረፉ ይህን ማድረግ የለብንም ብሎ መናገር ጀመረ እርስ በራስ በኃይል ለመናቸው፡፡ ከውጭም ሌላ ሴት ቀሬ መጥታ እንዴት እንዲህ ታደርጋላችሁ ብላ ተናገረቻቸው፡፡ በዚህም ባለቤቴን ራስዋን በሳተችበት ትተው እኔን መሳርያ አምጣ አሉኝ፤ እንደሌለኝ ነገርኳቸው፡፡ ገንዘብ አምጣ አሉኝ እሺ ብዬ ወደ ካዝና ወስጃቸው ቁልፍ እስከማወጣ ድረስ መትተው ጣሉኝ ፡፡በመጥረብያና በብረት ካዝናውን ገንጥለው 480000(አራት መቶ ሰማንያ ሺህ ) ብር ወሰዱ፡፡ወርቅ አምጣ አሉኝ የቤቱን እቃ በሙሉ አውድመው  ሄዱ” ብሎናል፡፡
ከዚያም ባለቤቱንና ልጆቹን ይዞ ወደ ሀዋሳ ለመሄድ መንገድ ዝግ ስለነበር ጎረቤት ለሁለት ቀን እንደቆየ  መንገድ ሲከፈትም ሀዋሳ ሄዶ ጓደኛው ቤት አድረው በማግስቱ ታቦር የእናቶችና ሕፃናት ሆስፒታል እንደወሰዳትና ሀኪሟ በዚህ ሁኔታ ሊረዷትና ኦፕራስዮንም ማድረግ እንደማይቻል ምክንያቱም በመጀመርያ በጣም መረጋጋትና ከጭንቀት መውጣት እንዳለባት ነግሮን ነበር፡፡
“ እሷ ግን እንቅልፍም የላት እንደጮኸች መጡብኝ አረዱኝ ልጄን ልጄን እንዳለች እንደባነነች፡ በ13/11/12 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7  ላይ ሕይወቷ ሊያልፍ ችሏል፡፡ “ብሎናል፡፡
“ ልጆቼም ጤናቸውን አጥተዋል እየባነኑ ነው ከፍተኛ ጭንቀት ላይ ይገኛሉ፡፡ መንግስት ይፍረደኝ! የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ!የሐይማኖት አባቶች ፍረዱኝ! ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ፣የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈርያት፣ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት ወ/ሮ መዓዛ፡ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ እናት ናችሁ፤ ነፍሰ ጡር ላይ ጎራዴ? ይደረጋል? ስሜቱ እንዴት ነው? ስሜቱ ምን እንደሚመስል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረዱ “ ብሏል፡፡
*  አቶ እንዳልካቸው ከሻሸመኔ ከተመለስን በኋላ በስልክ ባነጋገርነው ወቅት በከፍተኛ ሀዘን ተውጦ “እውነቱን ለህዝብ አሳውቁልኝ በተለያየ መንገድ ያላልኩት ነገር እየተባለ እየተነገረ እንደሆነ ሰማሁ፡፡ ይህም በሐዘን ላይ ሐዘን ሆኖብኛል፡፡ ባለቤቴ ላይ የደረሰባት ነገር በራሱ አሰቃቂ ግፍ ነው፡፡ የ9ወር ነፍሰ ጡር መሬት ላይ ጥለው እግሯን ይዘው ጎትተው ልብሷን አስወልቀው አንገቷና ሆዷላይ አስጠግተው እየሳሉ እናርዳለን፡ እንገላለን የአማራ ልጅ አይወለድም ፡የክርስትያን ልጅ አይወለድም እያሉ ሁለት ልጆቿ ፊት ነው ይህ የተደረገው ብያለሁ፡፡ አረዷት በገጀራ ሰነጠቋት አላልኩም፡፡ ሀዋሳ ታቦር የእናቶች እና ሕፃናት ሆስፒታል  ወስጃት ነበር፡፡ያረፈችው በ13/11/12 ነው፡፡ከዚህ በፊትም የኢሳት ጣብያ ጠይቀውኝ ይህንኑአስረድቻለሁ፡ በሀዘን ላይ ሀዘን አይጨምሩብኝ፡፡ ይህንን ለህዝብ አሳውቁልኝ፡፡ለራሴ ልጆቼ ከፍተኛ ጭንቀትና መባነን ላይ ናቸው፤ ነፍጠኛ ምን ማለት ነው? አማራ ምን ማለት ነው? እያሉኝ ግራ ተጋብቻለሁ፡ ቤት ውስጥ መተኛት አልቻሉም“ ብሎናል፡፡
 
አቶ ብዙአየሁ ጥጋቡ
የሶስት ወንድ ልጆች አባት ሲሆን የአቶ እንዳልካቸው ወንድም ነው፡፡ እሱም በቤቱ ከቤተሰቡ ጋር እያለ
“ ሀጫሉ መገደሉን ሌሊት ሰምተን ደነገጥን ከዛ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እየጮሁ ነፍጠኛ ነፍጠኛ ኦርቶዶክስ ኦርቶዶክስ እየተባለ ነፍጠኛን ግደል ነፍጠኛ አይኖርም እያሉ በሞተር እየጮሁ ነበር፡፡ ሌሊት 10 ሰዓት ጀምሮ ዝርፍያ ተጀመረ፡፡የኔንም ቤት ጠዋት 12፡05 ላይ መደብደብ ጀመሩ፡፡ በመሬት በቀዳዳ እያየኋቸው ነበር በበር ስር ዝቅ ብዬ እያየኋቸው ነበር በግምት መቶ ይሆናሉ ገጀራ፣መፍቻ፣ባለንቲኖ፣ነጭ ጋዝ ቤንዚን ይዘዋል፡፡ ከቤቴ ፊት ለፊት ያለው ውብሸት ሆቴል ገቡ፡፡የዚህን ጊዜ እኔ ልጆቼን ይዤ በጎረቤት አጥር ዘልዬ አመለጥን፡፡ ጓሮ ነገር ነበር፡ የእንሰት ተክል ያለበት እሱ ውስጥ ተደበኩኝ፡፡ ወደ 4፡25 ሲሆን ኮፍያ ሹራብ አድርጌ ወጣሁና ወደ ስራ ቦታዬ ጋ ለማየት ሔድኩ ብዙ ልጆች ቆመዋል፤ ፈርቼ ተመልሼ ገባሁ፡፡ ለ4፡40 አካባቢ ቤቴን የሚወስዱትን ወስደው እንዳለ በእሳት አነደዱት፡፡ ካዝና ውስጥ የነበረ 413000(አራት መቶ አስራ ሶስት ሺህ ) ብር እና 20 ግራም ወርቅ ወሰዱ፡፡  ለስራም ቅዳሜ በ 19/10/12 ብቻ የ1050000 (አንድ ሚልየን ሀምሳ ሺህ ) ብር ጎማ ነበር የገዛሁት ያ ሁሉ ንብረት ወደመ፡፡ቅድሚያ ልጆቼንና ቤተሰቤን ማትረፍ ስለነበረብኝ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር፡፡ እኔንም ሊገድሉ እየፈለጉኝ ነበር፡፡ ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት እያቀያየርን ተደበቅን መከላከያ ከገባ በኋላ ፍለጋውም ረገበ በሌላ ቀን ልጆቼን እና ባለቤቴን ወደ ሃዋሳ ላኩዋቸው”  ብሎናል፡፡
“ ይህ ሁሉ የሆነው ፖሊስም ልዩ ሀይልም እያለ ነው፡፡ ከሌሊት ጀምሮ እንደገና በቀን ሲፈጸም ፖሊስ ምን ያደርጋል? ካሁን በኋላስ ዋስትናችን ምንድን ነው? አልታዘዝንም ነበር የሚሉት፡፡ እኛ ምን አደረግን?  “ ብሏል፡፡
ብዙአየሁ ቀጥሎ “ ሃሙስ በ25/10/12 ዓ.ም. ጎረቤት ፖሊስ ነበር የተቃጠለብህን ንብረት አስመዝግብ ብሎ ጠራኝ፡፡ አልመጣም ይቅርብኝ ስሜቴ ጥሩ አይደለም ስል፤ ግድ የለም ስትደርስ ደውልልኝ አለኝ፡፡ ስደርስ ወዴት ነህ አሉኝ ፖሊሶች አይ ተደውሎልኝ ነው አስመዝግብ ተብዬ ነው አልኳቸው፡፡ አንዱ አትገባም አለኝ፡፡ አሁን  ተደውሎልኝ ነው ለምን አልገባም ስለው አንተ …(ስድብ)………ነፍጠኛ ብሎ በጥፊ መታኝ፡፡ሌሎችም ፖሊሶች መጡ በዱላ ቀጠቀጡኝ፡፡ አዛዡም እያየ ነው የተመታሁት ብሏል፡፡ ያስጣሉትም እንዴት ትመቱታላችሁ ንብረቱንም አጥቶ ብለው ሁለት በስም የጠቀሰልን ፖሊሶች እንደሆኑ ነግሮናል፡፡ ስወጣም የመታኝ ፖሊስ እዚች ሀገር ሰርተህ ትበላታለህ! ብሎ ዛተብኝ፡፡ ፖሊሶቹ ስምንት ወንዶች እና አንድ ሴት ነበሩ ብሎናል፡፡ይህ ሲሆን ጓደኞቼም ወንድሜም አይተዋል”  ብሏል፡፡
ወ/ሮ ቆንጂት በላይ
የሟች ባለቤታቸው ስም አቶ ወንደሰን መኮንን
ወ/ሮ ቆንጂት ቤት ስንደርስ ሌላ አሳዛኝ ድርጊት እንደተፈፀመ ሰማን፡፡ ሟች ባለቤታቸው አቶ ወንድወሰን መኮንን
የ79 ዓመት ባለፀጋ እንደነበሩና በሻሸመኔ ከተማም ከ40 ዓመታት በላይ እንደኖሩ በ23/10/12 ዓ.ም. በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ ነግረውናል፡፡
“ታማሚ ነን፤ ስኳር፣ ግፊትና የነርቭም ችግር አለበት፡፡እኔም እንደዛው የልብ ሕመም እና ግፊት አለብኝ፡፡ በዕለቱ በራችን መደብደብ ጀመረ፤ ከዛ ዘለው ገቡ፡፡ ነይ ውጪ፡ ድርጅትሽን አቃጥለን ነው የመጣነው፡ ቤትሽንም እናቃጥላለን ሲሉኝ፡ ምን አደረኩ ብላቸው ሀጫሉ ሞቷል አሉኝ፡፡ ነፍሱን ይማረው፡ ታድያ እኔ ምን አደረኩ ብላቸው፡ ያንቺ ዘመዶች ናቸው የገደሉት አሉኝ፡፡ የትኛው ዘመዴ፡ ኧረ እኛ ሽማግሌዎች ነን ብዬ ለመንኳቸው፡፡ ጩቤ ፣አካፋ፣ ቆንጨራና ግንድ መፍለጫ ይዘዋል፡፡እግራቸው ላይ ወድቄ እየለመንኳቸው ውጪ ብለው አስወጡኝ፡፡ ሰዎች ጎረቤት አስገቡኝ፡፡ ባለቤቴን ይዘው አስረው አየጎተቱ አሰቃይተውት ኪሱን እየበረበሩ አንገቱ ላይ ገመድ አስገብተው እየጎተቱ ከቆዩ በኋላ አንገቱን አረዱት፡፡
አስከሬንም አንሰጥም ብለው ስንት ሰዓት ሙሉ ቆይተው ልጆቼንም ሊገድሉ ሲያባርሩ ዋሉ፡፡ እሱም በስቃይ ተቀበረ፡፡ “ ብለውናል፡፡
ይንጋልኝ ወንደሰን የሟች አቶ ወንደሰን እና ወ/ሮ ቆንጂት ልጅ ሲሆን እሱም “ ቤታችን ላይ ጥቃት እንደደረሰ ሰምተን ስንመጣ እኛንም ሊገድሉን በጌጀራና በቆንጨራ ነው ያሳደዱን ሮጠን በየጎረቤቱ እየተደበቅን ነው የተረፍነው፡፡ የአካባቢው እናቶች ሳይቀር ለምነዋቸዋል እነርሱንም እያነቁ እየገፈተሩ ነው የመለሷቸው፡፡ከ2-3 ለሚሆን ሰዓት ከተደበቅን በኋላ ፌደራል ፖሊስ አግኝተን ብንለምናቸው ራሱ እኛ አንገባም ራሳችሁን አስመልጡ ነበር ያሉን፡፡ ከዚያም የከተማው ፖሊስ መምርያ ሄደን ስንለምናቸው የተወሰኑት አንገራገሩ የተወሰኑት ደግሞ እያወቅናቸው እንዴት እንዲህ እናደርጋለን ብለው ወደ 30 የሚሆኑ ፖሊሶች ጋር ሄደን አስከሬን አንስተን ሆስፒታል አስገባን፡፡
አባቴ የታረደው  ጠዋት 3፡30 አካባቢ ሳለ ሆኖ አስከሬን ማንሳት እንኳን ተከልክለን፡ አስከ 11፡30 ዝናብ ሁሉ እየዘነበበት ነው የቆየው፡ በጥቆማ ቅድመ ዝግጅት የነበረ በሚመስል መልኩ ቀጥታ እኛ ቤት ሲመጡ ለእናቴም ድርጅትሽን አቃጥለን ነው የመጣነው ብለዋታል፡፡ ሉሲ መኝታና ግሮሰሪ የሚባል ድርጅት ነበራት በእሳት ነዶ ወድሟል፡፡ ”
ወ/ሮ ስላስ አባዲ
ወ/ሮ ስላስ አባዲ ለ32 አመታት በሻሸመኔ ከተማ እንደኖሩና ከሶስት አመታት ወደዚህ የአይን ብርሀናቸውን እንዳጡ በ23/10/12 በነበረው ችግር ምክንያት ቤት ንብረታቸው እንደወደመ፣ የለበስኳትንም ልብስ ሰው ነው ያለበሰኝ ብለውናል፡፡
“ ክርስትያን ከሆናችሁ በክርስትያን አምላክ ሙስሊም ከሆናችሁ በሙስሊም አምላክ እያልኩ ለመንኳቸው እነርሱ ግን ቤቴን አቃጠሉት፡፡ “
ወ/ሮ መብሪት አያሌው
የማየት የተሳናቸው የወ/ሮ ስላስ አባዲ ልጅ ስትሆን ከ3ወር ልጇ ጋር በቤተክርስትያን ውስጥ ተጠልላ ነው ያገኘናት፡፡
“ በዕለቱ በ23/10/12 ማለት ነው፡ ቤታችን እያለን ብዙ ሆነው መጡ ብረታ ብረት ገጀራ ቆንጨራ ይዘዋል፡፡ መስኮቱን መሰባበር ጀመሩ መስታወት ሲሰብሩ ልጄን እና እኔን እንዳጋጣሚ መቱን፤ ባለቤቴም በነፍስ ነበር  ሲፈልጉት የነበረው አምልጦ ወጣ እኔም በበቆሎ ውስጥ ለውስጥ ሄጄ ነው የጠፋነው፡፡ ሕይወታችን ተርፏል በቢጃማ ብቻ ነው የቀረነው፡፡ የእኔም የበሽተኛ እናቴም ሙሉ ንብረት ነው የወደመው” ብላናለች፡፡
ወ/ሮ አስናቀች ዘውዴ
“ ከ50 ዓመት በላይ በሻሸመኔ ከተማ ኖሬአለሁ፡፡ ባለቤቴ እና ልጄ በፊት ሞተውብኛል፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያፈራሁት ንብረቴ ተቃጠለ ድንገት ባዶዬን ቀረሁ፡፡ የኔም የልጄም ቤት ባዶ አደረጉት፡፡አሮጊቷ የታለች ትውጣ እንረዳት ነፍጠኛ ናት እያሉ ጎረቤቶቼ እግዚአብሔር ይስጣቸው ደብቀው ነፍሴን አተረፉልኝ ብለዋል፡፡ እኔ ጡረተኛ ነኝ ሌላ ሀገርም የለኝ ብሞትም የምቀበረው እዚሁ ነው፡፡” ብለውናል፡፡
 አቶ ጌቱ ተመለሰው
አቶ ጌቱ ሻሸመኔ ከተማ ከ20 ዓመታት በላይ እንደኖሩ ይናገራሉ፡፡ ከባለቤታቸውና ከ3 ልጆቻቸው ጋር ይኖራሉ፡፡ ከመኖርያ ቤታቸው ጋር የተያያዞ ሱቅ የነበራቸው ሲሆን የሸማቾች ሸቀጥ ያከፋፍሉ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሻሸመኔ ተ/ሐይማኖት ቤተክርስትያን ተጠልለው ላሉት ኮሚቴ ሆነው እያስተባበሩ ያሉ ሲሆን
“በ 23/10/12 ዓ.ም. ከጠዋት 1 ሰዓት ጀምሮ በአካባቢያችን ችግር ነበር፡፡ የኔም ቤት ከነንብረቱ ከነሱቁ ጨምሮ፡ በአካባቢያችን 8 ቤቶች 6 ባጃጆች እና 2 መኪናዎች ተቃጥለዋል፡፡ ዕድሜ ልክ ለፍተን ያፈራነው ንብረት በደቂቃዎች ውስጥ ሲጋይ ከባድ የአእምሮ ህመም ነው ያለው፡፡ ድርጊቱን ሲፈጽሙ የነበረውም ነፍጠኛ የምኒሊክ አሽከር እያሉ ነበር፡፡ ነፍሳችን የተረፈውም በአካባቢው ተወላጆች ነው፡፡ አሁን ተጠልለን ያለነው በቤተክርስትያን ውስጥ ነው” ብለውናል፡፡ ”
 መሳፍንት ተስፋዬ
መሳፍንት በ ደብረ ፅጌ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስትያን ውስጥ ተጠልለው ስለሚገኙት ወገኖች በዚህ መልኩ ገልፆልናል፡፡
“ በአባወራ ደረጃ 44 ሲሆኑ አጠቃላይ 185 ግለሰቦች ሕፃናትን ጨምሮ ይገኛሉ፡፡ ቤት ንብረታቸው በሙሉ በእሳት ቃጠሎ የወደመ፡ በርና መስኮታቸው የተሰባበረ እና የተወሰኑም በስጋትና በዛቻ ወደ ግቢው ሸሽተው የመጡም አሉ ”  ብሎናል፡፡
ሳብር ሀምዛ
“ ሻሸመኔ ተወልጄ፣ ወልጄ፣የልጅ ልጅ ያየሁባት ናት፡፡እናት አባቶቻችንን እዚሁ ነው የቀበርነው፡፡ የት እንሄዳለን ቤቱን ከሰራሁት አራት አመቴ ነው፡፡ በዝርፍያም በቃጠሎም ንብረታችን ወደመ እኛ ያለነው ገበሬ ማህበር ነው፡፡ እንዳለ ሆ ብለው መጥተው ሲወሩን  በካነቴራ ነው ሸሽተን ያመለጥነው መስኪድ ቅርባችን ነበር ጎረቤት ቀበሌ ነው ቀበሌያችን፤ ራቁታችንን ስለነበርን የመስኪዱ አስተዳዳሪ ሸህ ጀማል አልባሳትን ረዱን ከኛ አካባቢ 10 እንሆናለን ስልጤዎች ከአንዷ በስተቀር፡ ተባረን የመጣነው ቤታችን የተቃጠለው ማለት ነው፡፡ ለ18 ቀናት ያህል እዛው መስኪድ ነው የቆየነው፡፡ አስተዳደሮች የሀገር ሽማግሌዎች ይዘው መጥተው ለበሽታውም እዚህ ከምትሆኑ ብለው ዋናው ቤት ሙሉ በሙሉ ቢነድም ሰርቪስ ተሰባብሮ ተገነጣጥሎ ተዘርፎ የተረፈ አንድ ክፍል ጠጋግነው አሁን እዛ ገብቻለው፡፡ ከኛ ትንሽ ራቅ ብሎም የተቃጠሉትን ጨምሬ 15 የስልጤ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ አራት የሚሆኑ ባጃጆች ፡ 5 Lሚኒ ባስ ታክሲን ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ተሽከርካሪ ተቃጥሎብናል፡፡መስኪዱ ነው እኛን ጠብቆ ለዚህ ያደረሰን፡፡ ካገሩ ወጥተን እንዳንጠፋ ለ18 ቀን አቅፈው ይዘውን ከጎረቤታቸውም፡ ከየትም እያሉ ምግብም እያቀረበልን ነበር፡፡ ወረዳው፡ በቆሎ ከዛም ፓስታ አምጥተው ሰተውናል፡፡ በአጠቃላይ ሙስሊሞች ብቻ መስኪድ የተጠለልነው 53 እንሆናለን፡፡ከክርስትያኖቹ ጋር ከዚያ በላይ ነን፡፡ እኔ ብቻ 8 ቤተሰብ አለኝ፡፡ ይህን ሁሉ ሰው የረዱት ሼህ ጀማል የኑር መስኪድ አስተዳዳሪ ናቸው፡፡”
ሳብር ሀምዛ ይህ አሳዛኝ ድርጊት ለመፈጸሙ ስለምክንያቱ የራሱን አስተያየት ሲያስረዳ
“ እኛ ምን እናውቃለን ምንአልባት በብሄር ከሆነ እንጂ በሐይማኖት ቢሆንማ እኛስ ሙስሊም አይደለን፤ ሙስሊም አይነኩም ከተባለ እኛን ለምን ነኩን” ሲል ይጠይቃል፡፡
ፋሪስ ሲራጅ
የአርባ አመቱ ፋሪስ ተወልዶ ያደገው ሻሸመኔ እንደሆነና የስድስት ልጆች አባት እንደሆነ፣ ወደ ስልጤ ልሂድ ብል እንኳ የሚያውቀኝ የለም፡፡ አባቶቻችን እንኳ ሞተው ሞተው እዚሁ ነው የተቀበሩት ሲል ይናገራል፡፡
“ በ23/10/12 ዓ.ም. የደረሰብን ግን እኛ ከዚህ እንድንወጣ ያለመ ይመስላል፡፡ ሌላ የምናውቀው ሀገር የለንም፡፡ ስድስት ልጆች ወልጃለሁ ስራም ዕድርም ሁሉም ነገሬ እዚሁ ነው፡፡ የመንግስት የመኪና ሚዛን ዘመናዊ ድርጅት ካቃጠሉ በኋላ ወደ እኛ ቤት መጡ ለሚዛኑ ይቀርባል ቤታችን በነፍስ አምልጠን መስኪድ ተጠለልን፡፡መልካም ሰዎች ናቸው ህይወታችንን ያተረፏት፡፡
ወ/ሮ ፀሐይ እልፋይ
ወ/ሮ ፀሐይ ዕድሜአቸው 50 የደረሰ ሲሆን በሻሸመኔ ከተማ ተወልደው አድገው እዚህ እንደደረሱ ይናገራሉ፡፡
“ መኖርያ ቤቴ ሙሉ በሙሉ፤ ሰርቪስ ቤት የነበረኝ ሙሉ እቃ ባዶ ሆኖ በርና መስኮት ሳይቀር ነው የጠፋው፡፡እኔ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነኝ ነገር ግን በቅርቤ የነበረው ለመኖርያ ቤቴ የሚቀርበውም መስኪድ ነውና እዛ ነው የተጠለልኩት የነበረው፡፡ ከቤቴ ፊት ለፊት  የእስልምና እምነት ተከታዮች የስልጤ ብሔረሰብ ተወላጆች ነበሩ፡፡ የነሱም ንብረታቸው ከነቤታቸው መኪኖችና ባጃጆች ወድሞባቸዋል፡፡መስኪድ አብረን ነበር ተጠልለን የነበርነው፡፡ እኔ ከ14 ዓመት ልጄ እና ከማሳድገው የ4ዓመት የወንድሜ ልጅ ልጅ ጋር ወደ 15 ቀን በመስኪድ ተቀምጫለሁ፡፡ ሼክ ጀማል ነው የሰበሰበን፡፡ ከነቤተሰቡ ሰብስቦናል ልጆቹም ጭምር አይዞዋችሁ እያሉ እየመጡም ያዩናል፤ በረታችሁ ይሉናል፡፡ ት/ቤት አለ መስኪድ ውስጥ እዛ ነበርን፡፡ “
አቶ መኮንን ወ/ገብርዔል
የ ሀምሳ አንድ አመቱ አቶ መኮንን ተወልደው ባደጉበት ከተማ ሻሸመኔ ከባለቤታቸው እና አራት ልጆቻቸው ጋር የኖሩ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ወላጅ አባቴ እንኳን በ1928ዓ.ም. ነበር የመጣው፡፡ ቀደም ብሎ በሞት የተለየን ሰባ ዓመት የሚሆነው ወንድሜ እንኳን የተወለደው እዚህ ነው ብለውናል፡፡
“ እኔ የደረሰብኝ ጉዳት ብዙም አይደለም አጥር ለማፍረስ እንደሞከሩ ሕዝቡ ተባብሮ አትርፎታል ሁሉን ንብረቴን ሳይቀር ከብቶች ሳይቀር ወደ መስኪድ አስገብተው ነው ያተረፉልኝ የመስኪዱ አስተዳዳሪም የአካባቢው ነዋሪም በትብብር ው ያተረፉልኝ እንጁ አጥሩን መቅደድ ጀምረው ነበር፡፡ እንዳይነካ የኛ ነው በማለት ሳይገቡ ተቆጣጠሯቸው፡፡ እነሱን አባረው ትንሽ በረድ ካለ በኋላ ዕቃዬን አውጥተው በየቤቱ አደረጉልኝ፡፡
ለእኔና ቤተሰቦቼ አንድ ክፍል ለአንድአንድ ዕቃዎች ሌላ ክፍል ፡ ከብቶቹንም ለብቻ አድርገውልኝ ወደ 14 ቀን የሚጠጋ መስኪድ ውስጥ ያለ ት/ቤት ውስጥ ተቀምጠናል፡፡ ለኔም ብዙ ነገር የተባበሩኝ ሼህ ጀማል ናቸው” ብለውናል፡፡
አቶ ሰለሞን መኮንን
አቶ ሰለሞን ትውልዴም ዕድገቴም ኦሮምያ ላይ ነው ይላሉ፡፡ የ ስድስት ልጆች አባት እና የዜድ.ኤስ የግንድና ጣውላ መሰንጠቅያና ፈርኒቸር ባለቤት ናቸው፡፡
“ በ23/10/12 በከተማችን ሻሸመኔ ችግር ነበር፡፡ ጠዋት፡ ሰራተኛ ወደ ስራ ሊገባ ሲል ነው፡፡ ብዙ ሆነው ወጣቶች ለጥፋት ሲመጡ የአካባቢያችን ነዋሪዎችና ሸህ ጀማል  ሌሎችም ኢማሞች ወጥተው ብዙ ታግለው ነው ያተረፉን፡፡ የኔን ብቻ ሳይሆን እዛ አካባቢ ያለውን በሙሉ ያተረፉት እነርሱ ናቸው፡፡ለምሳሌ አርሲ ነገሌ ያለው አንድ ዓይነት ድርጅቴ ተቃጥሎብኛል፡፡ ማን እንዳቃጠለው አላውቅም፡፡ሙሉ በሙሉ ነው የወደመው፡፡ ሻሸመኔም ቢሆን ማን ይሁኑ ማን አናውቃቸውም ከመቶ በላይ ሰዎች ናቸው፡፡ እናቃጥላለን አታቃጥሉም በሚል የተቀጠቀጡም ነዋሪዎች አሉ፡፡ ሀጂ ጀማል ራሳቸውን አታልፉም ብለው ሲከለክሏቸው፡ ገፍተረው ጥለዋቸው እጃቸውም ላይ ጉዳት አድርሰውባቸውም ነበር፡፡የሰፈራችን ሙስሊም ወጣቶች ላይ ራሱ በያዙት ስለት ማስፈራራት ነበር፡፡ ሰይጣን ነው ምን አይነት ሠይጣን  እንደሆነ ነው የማናውቀው፡፡ ድርጅቴ ከቀን ሰራተኞች ጋር በትንሹ ከመቶ ሰው በላይ ይተዳደርበታል፡፡ ” ብለውናል፡፡
ሐጂ ጀማል
የመልካ ኦዳ፡ ኑር መስኪድ አስተዳዳሪ ናቸው፡፡በአካባቢያቸው የነበሩትን ትልልቅ ተቋማትና ቤቶች እንዳተረፉ ገልጸውልናል፡፡ለምሳሌ ተወልደ ጋራዥን፣ ሰለሞን የግንድና ጣውላ መሰንጠቅያ፡ ትልቅ ድርጅት ነው፡፡
“በኔ ቅርብ ያሉ የተቃጠለ ቤት የለም አልሀምዱሊላህ፡፡ ብዙ ግብ ግብ እና እንግልት ነበር፡፡ የነበረውን ስቃይ ተወው” ብለውናል፡፡
የሪፖርቱ  ምንጮች
በቦታው በመገኘት የታዘብን ሲሆን የተንቀሳቃሽ ምስል፣ የምስል እና የድምጽ ማስረጃዎችን ለማስቀረት ተችሏል፡፡በተጨማሪም የነበሩንን መረጃዎች ለማጥራትና ለማመሳከር ለተከታታይ አራት ቀናት በስልክ ቃለ መጠይቅ የማረጋገጥ ስራ ተሰርቷል፡፡
አቶ አብነት ገለታው (በ አዳሚ ቱሉ ጥቃት 5 የቤተሰብ አባላትን ያጡ)
አቶ ሚክያስ ገለታው(በ አዳሚ ቱሉ ጥቃት 5 የቤተሰብ አባላትን ያጡ)
አቶ አንዳልካቸው ጥጋቡ (ተጠቂ)
አቶ ብዙአየሁ ጥጋቡ (ተጠቂ)
ወ/ሮ ቆንጂት በላይ (በጥቃቱ ባለቤታቸው የተገደሉባቸው)
አቶ ይንጋልኝ ወንደሰን ( በጥቃቱ ወላጅ አባቱን ያጣ)
መምህር አስናቀ ደቻሳ ( በባቱ ለተጎዱት በቤተክርስቲያን አስተባባሪ)
አቶ መሳፍንት ተስፋዬ (ሻሸመኔ ኪዳነምህረት ለተጠቁ በቤተክርስትያን ላሉ አስተባባሪ)
ወ/ሮ አስናቀች ዘውዴ ( ተጠቂ)
አቶ ጌቱ ተመለሰው ( ተጠቂ)
አቶ መንበሩ አድገህ (ተጠቂ)
አቶ ሳብር ሀምዛ ( ተጠቂ )
አቶ ፋሪስ ሲራጅ (ተጠቂ)
ወ/ሮ ፀሐይ እልፋይ (ተጠቂ)
ወ/ሮ ስላስ አባዲ  (ተጠቂ)
ወ/ሮ መብሪት አያሌው (ተጠቂ)
አቶ ሰለሞን መኮንን (ሻሸመኔ የግንድ መሰንጠቅያ ድርጅታቸው የሙስሊም ማህበረሰቡ አትርፎላቸው አርሲ ነገሌ የተቃጠለባቸው)
አቶ መኮንን ወ/ገብርዔል ( የሙስሊም ማህበረሰቡ ንብረታቸውንና ሕይወታቸውን ያተረፈላቸው)
ሐጂ ጀማል ( የሻሸመኔ መልካ ኦዳ ኑር መስኪድ አስተዳዳሪ)
* ይህ ሪፖርት በሁለቱ ቀናት ከጎበኘናቸው ቦታዎችና አግኝተን ካነጋገርናቸው ተጎጅዎች መካከል የተወሰኑትን የያዘ እንጂ በአጠቃላይ በከተማዎቹ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት የሚያሳይ አይደለም፡፡
ማጠቃለያ
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ሪፖርቱን ገምግሞ በተጠቀሱት ስፍራዎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ማለትም
ሀ. በዘር
 
ለ. በሐይማኖት
ሐ. በዘር እና በሐይማኖት መፈፀማቸውን ተገንዝቧል፡፡
በየደረጃው ያለው የፀጥታ እና የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ እነዚህን ጥቃቶች ለማስቆም ከፍተኛ ዳተኝነት ታይቶ እንደነበር ተረድቷል፡፡
ይህንን ወንጀል ፈፃሚዎችም ሆኑ አስፈፃሚዎች ቀድሞ የታቀደ እና ዝግጅት የተደረገበት እንደነበር በሚያሳይ መልኩ በተወሰኑ ስፍራዎች ላይ፡ የስም ዝርዝር በመያዝ ጭምር ቤታቸውና የስራ ቦታቸው በመሄድ በሕይወት እና ንብረታቸው ላይ ጉዳት እንዳደረሱ ተረድቷል፡፡
ተጎጂዎችም ሆነ ከአሁኑ ጥቃት የተረፉ ዜጎች
ሀ. አሁንም ዛቻና  ማስፈራርያ እንደሚደርስባቸው
ለ. ለደህንነታቸው በክልል የፀጥታ ኃይል እምነት እንዳጡ እና
ሐ. ዳግም ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ተረድቷል፡፡
እንደ ማህበረሰቡ ፤ በነበረው አቅም፡ ወገኑን መከላከል፣ መደበቅ፣ ማሸሽ እና ተማፅኖ ባይሆን ኖሮ የደረሰው ጥፋት ከዚህም የከፋ ይሆን እንደነበር ተገንዝቧል፡፡
ማሳሰብያ
መንግስት የዜጎችን ደህንነት ከመጠበቅ የቀደመ አጀንዳ ሊኖረው አይገባም!
የዜጎች ሰው በመሆናቸው ብቻ በሕይወት የመኖር፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልሎች መኖር፣ተንቀሳቅሰው የመስራትና ንብረት የማፍራት መብት አላቸው፡፡ በማንኛውም የማንነት መገለጫቸው፤ በመረጡትም ቢሆን ባልመረጡት፤ በየትኛውም አካል ፡ በምንም አይነት መልኩ፤ እንኳን ጥቃት፡ አድልዎ ሳይደረግባቸው፡ በነፃነት፡ የመኖር መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ከዚህ የሚቀድም ምንም አጀንዳ ሊኖር አይገባም፡፡ ሌላው ችግር እና ፈተና ሁሉ ዜጎች በሰላም ሲኖሩ እና በህብረት ሲቆሙ፡ በአንድነት፡ ፊት ቀላል ነው፡፡
በዓለም ላይ ማንነትን በዘርም ይሁን በሐይማኖት መሰረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች ድንገት የሚከሰቱ አይደሉም፡፡ የሩዋንዳው ፍጅት የረጅም ጊዜ የጥላቻ ንግግር፣ የሚድያ ቅስቀሳ፣ ማንቋሸሽ እና ዝግጅት የተደረገበት በኃላ ለተፈጠረው ዕልቂትም  የተለያዩ ምልክቶች እየሰጠ ቆይቶ የተፈፀመ ነው፡፡
በሀገራችንም ከፍተኛ የጥላቻ ንግግሮች፡ የሚድያ ቅስቀሳዎች፡ የተዛቡ የታሪክ ትርክቶች፡ ያላግባብ የተለጠጡ  እና ጥላቻን መሰረት ያደረጉ የማንነት ግንዛቤዎች፡ፍረጃዎች፡ ከዘመኑ ጋር ያልዘመነ በሃሳብ ላይ ያልተመሰረተ የፖለቲካ አካሔድ የፈጠረው ውጥረትና ትኩሳት፡ ተደጋጋሚ ግጭቶችን እየፈጠረ፡ የንፁሃንን ደም በተደጋጋሚ እያፈሰሰ፡ ንብረታቸውን እያወደመ፣ እያፈናቀለ፣  የቆየ አብሮ የመኖር እሴታቸውን እና ማሕበራዊ መሰረታቸውን ቀስ በቀስ በመሸርሸር መቃቃርን እያመጣ ነውና፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ወደ ለየለት፡ በዓለም፡ የዘርና የሐይማኖት ጭፍጨፋ፡ ጥቁር መዝገብ ላይ የሀገራችን እና የሕዝቦቿን ስም እንዲሰፍር ሊያደርግ የሚችልን አደገኛ ልምምድ መንግስትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመተባበር ማስቆም ይገባናል፡፡ አንዳችን ሰላም ካልሆንን ሁላችንም ሰላም አይደለንም፡፡
በመሆኑም የጥቃቱን አይነትና ስያሜ ላይ ጊዜ ማጥፋቱን ትተን የአንድም ሰው እንኳን ሕይወት ቢሆን ክቡር እና ታላቅ ነው፤ በየትኛውም ምክንያት ሊያልፍ አይገባም! በማለት ጠንካራ አቋም በመያዝ መንግስት
አሁንም ስጋት ላይ ያሉ ወገኖችን ከሌላ ጥቃት እና ዛቻ በዘላቂነት እንዲታደግ
የሕግ የበላይነት እንዲከበር፡ የዜጎች በየትኛውም የሀገራቸው ክልሎች በእኩልነት የመኖር መብት እንዲረጋገጥ
በቶሎ ጥፋተኞችን ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ በማድረግ ለተጎጂዎች ፍትህ እንዲሰጥ
ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ተሰይሞ ጥቃቱ እንዲጣራና ውጤቱ በቶሎ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ
ቤተሰቦቻቸውን እና ንብረታቸውን ያጡ ዜጎች ካሳ እና መልሰው የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች
አንድ አንድ የፀጥታ እና የአስተዳደር ተቋማት በማህበረሰቡ እምነት እየታጣባቸው ያለበት ሁኔታ ስር ሳይሰድና ወደ ለየለት ስርዓት አልበኝነት ሳይመራን መንግስት ከላይ እስከታች የጀመረውን መዋቅሩን የመፈተሸ ስራ በማጠናከር ዜጎች፡ ተቋማትን ”የኔ” የሚሉበትን ስርዓት እንዲፈጠር አበክሮ እንዲሰራ
የፌደራል መንግስት፣ የክልል መንግስታት፣ እንዲሁም ፖለቲከኞችና የሚመለከታችሁ በሙሉ፡ አሁንም በተከበረው ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን፡ ማህበራዊ ሰላም እና የማይበጠሱ ተፈጥሯዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ስነልቦናዊ እና የደም ትስስሮችን መሰረት ያደረገ፣ መሬት ላይ በዜጎች መካከል ያለውን ውህደት፣ የማይክድ፣ ሰው መሆናችን አንድ ያደረገን ታላቅ ማንነት መሆኑን፡ በማጉላት ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚከበርበት፤ በሌሎች ማንነቶቹ ደግሞ በብዝኃነት በሕብረት የሚደምቅበት፡ የመንግስት የአስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት ለዘላቂ ሰላም እና ዕድገት በቅንነት እና በዕውነት በመቆም ታሪክ ሰርተን እንድናልፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
ቁ.047/SMNE/20
ነሐሴ 4 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic