>

እባብ ነደፈኝ ብዬ አልበሳጭም ...!!! (ዳንኤል ሽበሺ)

እባብ ነደፈኝ ብዬ አልበሳጭም …!!!

ዳንኤል ሽበሺ
 “… በሰበሩበት ሰበርናቸው”
የቱለማው ኦቦ ሽመልስ አብዲሣ ፦
ከአቶ መለስ ዜናዊ የከፋ የሀገር ጥላቻ

ዕድሜ ለኦቦ ሽመልስ አብዲሣ! ድሮም ፈራተባ እያልን፤ በጥርጣሬ እያየናቸው ነበር ። አሁን በነጭ በጥቁር ነገሩን እናመሰግናለን።
ፍጥረታት በሙሉ የየራሳቸው ባሕሪያት እና ከባሕሪያቸው የሚመነጭ ሀሳብ/አሰተሳሰብ እንዳለው ሁሉ እባብም፥ብሄርተኛም እንዲሁ የየራሳቸው የታደሉት ባሕሪያት/ሀሳብ/አሰተሳሰብ አሏቸው ። በነፍስም ሆነ በደመነፍስ … ቢሆንም ።
… እባብ በምላሱ እንድናደፍ ተፈጥሮ የለገሰው ባሕሪው ሲሆን፤ ባሕሪውን አውቀን መጠራጠርና መላ ማበጀት ለእኛ የተተወ ሰው’አዊ ችሮታ ነው ። <እባብ ነደፈኝ ብዬ ባልበሳጭም> ወደ ውስጤ የገባው መርዝ ለጤናም ሕይወትም አያሰጋኝም፤ መርዙ ጥሎ የሚያልፈው ወይም ይዞ የሚሄደው ዘላቂና ጊዜያዊ ውጤት የለም ማለት አይቻልም ።
“… በሰበሩበት ሰበርናቸው”
የቱለማው ኦቦ ሽመልስ አብዲሣ ፦
ከአቶ መለስ ዜናዊ የከፋ የሀገር ጥላቻ!
ሰሞኑን የኦሮሚያው ኦቦ ሽመልስ አብዲሣ የተናገረውን አነበብኩ አዳመጥኩ ። ስለ ሰው ልጅ ስናስብ ሁሌም ሀሳብ ይቀድማል፤ ድርጊት ይከተላል። የሆነውም እየሆነ ያለውም ይሄ ነው ። ድርጊታችን የሀሳባችን ውጤት ነው። ከአንዱ ወዳጄ ጋር ሳወራ የሰውየውን ንግግር ከሰማሁ በኋላ “መብረቅ የመታኝ ያህል አስደነገጠኝ” አለኝ። እኔም መልሼ ምን የሚያስደነግጥ ነገር ተፈጠረ? መደንገጥ የለብህም አልኩት ። የምንደነግጥ ከሆነ ሲጀመር ባሕርያቸውን አላወቅንም ማለት ነው ። የሰውየውን ንግግር ሁሉም የኦሮሞ ልህቃን የሚጋሩት ነው ባይባልም ግን #የሚናቅም እንደ ዋዛ የሚተው አይደለም ። ይልቁንም በሰውየው ድንፋታ ብዙም ሳንገረም ሀገራችንን ለማዳን ቀበቷችንን ጠበቅ እንዲናደርግ ከፍንጭ ዘለግ ያለ ማስረጃ አቀብለውልናል በማለት አከልኩት ።
ከየትኛውም ክልል እና አህጉር ቢሆን ብሄርተኛ (በተለይ አክራሪ ብሄርተኛ) የስልት ወይም የማስፈፀሚያ መንገድ ልዩነት እንጂ አቋማቸው ወይም ውስጣዊ ሥሪታቸው ተመሳሳይ መሆኑን በቅጡ ልንረዳ ይገባል ። ምንም ቢማርና ቢሰለጠን ወይም ምንም በሰለጠነው ዓለም ቢኖር የሚቀያየሩት ባሕርያቸውንና ግባቸውን ሳይሆን ሥልታቸውን ወይም የማስፈፀሚያ መንገዳቸውን ነው ። ባሕሪይ ካልተለወጠ ሀሳብ አይለወጥም፤ ሀሳብ ካልተለወጠ ድርጊት አይለወጥም ። እንዲሁ መተግበሪያው ካልተለወጠ ውጤትም አይለወጥም ። ነገር ነገርን ያነሳል እንዲሉ፦ በደንብ ፈልፍለን ስናይ የወንድማችን የአርቲስት #ሀጫሉ ሁንዴሣ ሞት መንሥዔውኮ የዚህ አስተሳሰብ፤ የዚህ ባሕሪይ ውጤት መሆኑን እንደት መጠራጠር ይቻላል? በአስተሳሰባቸው የገደሉትን በለቅሶ ማሽሞነሞን ልዩ ድራማ መጫወት፤ አዛኝ መስለው ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ማንን ለማሞኘት ነው?? የሚል ጥያቄ ቢጭር ስህተት አይሆንም ።
የብሄርተኛነት ግንዱ የጥቅም፣ የውግንናና የጠላትነት ፍረጃ እንደሆነ ብዙ ብዙ ተብሏል ። በጥቅሉ ብሄርተኛነት እና ጎሰኝነት የመገበያያ ማዕከላቸው <የጠላትነት እና የወዳጅነት> መስመር ነው ። ብሄርተኛነት ከፍ ስል የዘረኝነት፤ ዝቅ ስል የጎሰኝነት ውሃ ልክ ነው። ድምር ውጤቱ የበታችነት ስሜት የሚዘራበት ለም አፈር ነው ። የበታችነት ስሜት ሀሳብ አይደለም። የድሮ ቁስል ማከክ፣ እንደ ዶሮ የተቀበረ አጥንት መጫር ነው ። የሰው ልጅ እንደት በዚህ ልክ ልወርድ ይችላል? ይህ የእኔ ጥያቄ ነው ። ትህነግ/ህወሓት ከሩብ(25) ዓመት በላይ ፈጅቶ ያሳካውንና ማሳካት ያልቻለውን በሶስት ዓመታት ለማሳካት መሞከር ምን አይነት እብደት ነው? እንደት ለሀገር ማሰብ፣ የፖለቲካ ሀሁ ሊሆን ይችላል?
ኦቦ ፕሬዘዳንቱ!
በኦቦ ፕሬዘዳንቱ የተተፋው መርዝ እንዲያው በግምገማ እና “ይቅር ተባባሉ” በመጽሐፉ ምክር የሚታለፍ ነው ወይ? አላውቅም ። ለምጣዱ ሲባል ይሞከር ይሆናል ። ምን እያልኩ ነው መሰላችሁ፦ በአንድ በኩል በባለጊዜነት ትዕቢት እየተዋጥን፤ በሌላ በኩል ሀገራችን በየአቅጣጫው ቀስፎ በያዛት ውጋት፣ ህግና ሥርዓት የሰፈነባት ሀገር ቢትሆን ኖሮ ሰውየው ከኃላፊነት በአንድ ሽርፍራፍ ሴከንድ ተነስቶ በሀገር ክህደት (ሀገር ማፍረስ) ወንጀል ከመስከሰስም ባሻገር ንግግሩ ለፍርድ ቅጣት ማክበጃ ይሆንለት ነበር ። ጊዜው የባለጊዜዎች ነውና … ፍርዱን ለጊዜው ጌታ መተው አዋጪ ይመስለኛል ።
በአንድ ወቅት በእሥራት ቴቪ ባደረኩት ቆይታዬ  <ባለጊዜነት እያቆጠቆጠ ነው> ብዬ ነበር ። ያነም ልክ ነበርኩ ። ዛሬም የሆነውና እየሆነም ያለው ይህ ነው ። እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና እንደ ኦሮሚያ ክልል አስተዳደር አካሄድና ድርጊት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያዬ ቻው! ያስብላል፤ ነገር ግን ፈጽሞ እንደማይሳካላቸው ልንረዳም ሊረዱትም ይገባል ። ይህ መንገድ <ሀገርን በዘዴ በዕቅድ ማፍረሻ እንጂ እየገነባን ነን> ካሉን ፈገግ ከማስባል በዘለለ ጠብ የሚል ነገር የለም። በጥቅሉ ይህ መንገድ ለጣሊያን ወራሪዎችም፣ ለህወሓት ገዠዎችም አልጠቀማቸውም። አላዛለቃቸውም4.
በመጨረሻም፦ ታምራየሁ ተክሌ የሚባል የፌስቡክ ጓደኛዬ በገጹ ላይ ያሰፈረውን አጭር መለዕክት ላጋራችሁና እንሰነባበት ። “ከአቶ ሽመልስ ንግግር የተረዳነው ሌላው ነገር <በጥድፍያ የደቡብን ክልል በማፈራረስ ከኦሮሚያ ክልል የማይወዳደር ትናንሽ ክልሎችን የመፍጠርና ሥልጣንን በህዝብ ብዛት የማስቀጠል የብልጽግና ስትራቴጂ መሆኑን በግልጽ  ያመላከተ ሆኗል።> ይላል ።
ተክደናል። ክህደት!!!
ቸር ያሰማን!
እባብ ነደፈኝ ብዬ አልበሳጭም፤ ባሕሪዩ ነውና ።
Filed in: Amharic