>
5:16 pm - Monday May 24, 4438

ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ መሻገር ስለምን ተሳናት ?!? [በፍቃዱ ኃይሉ]

ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ መሻገር ስለምን ተሳናት ?!?

[በፍቃዱ ኃይሉ]

በይቅርታ እና ምኅረት ማራኪ የድል ዜማ የጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ወደ ሐዘን እንጉርጉሮነት ተለውጧል። ብዙውን ጊዜ የሁለትዮሽ ጫወታ የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሦስት ማዕዘናዊ ሆኗል። ከ2010 ቀድሞ የነበረው የፖለቲካ ትግል በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚዎቹ ነበር።
በይቅርታ እና ምኅረት ማራኪ የድል ዜማ የጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ወደ ሐዘን እንጉርጉሮነት ተለውጧል። የለውጥ አምሮት በነውጥ ምሬት ተነጥቋል። ተስፋ የተጣለበት የሽግግር ጊዜ የችግር ጊዜ እየሆነ ነው። ለውጡ ለውጥ ያስፈልገዋል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ወደዚህ ውስብስብ ጉዳይ የገባችው ለምንድን ነው? ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገርስ ለምን ይህን ያክል ከበደ?
የኃይል_አሰላለፉ
ብዙውን ጊዜ የሁለትዮሽ ጫወታ የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሦስት ማዕዘናዊ ሆኗል። ከ2010 ቀድሞ የነበረው የፖለቲካ ትግል በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚዎቹ ነበር። ገዢው ፓርቲ ውስጣዊ አንድነት ነበረው። ተቃዋሚዎችም ከነልዩነታቸው ዋና ትኩረታቸው ገዢው ፓርቲ ላይ ነበር። ገዢውን ፓርቲ ለመጣል ሲባልም እርስ በርስ የሚደጋገፉበት አጋጣሚ ነበር። በ2010 የመጣው የፖለቲካ ለውጥ ግን አጨዋወቱን ለመተንበይ በሚያስቸግር ሁኔታ ቀይሮታል።
የፖለቲካ ተጫዋቾቹ ማሊያ ተቀያይረዋል፤ ደጋፊዎቻቸውም እንደዚያው።
 ከሁሉም በላይ አስቸጋሪ የሆነው ግን ጫወታው ከሁለትዮሽ ወደ ሦስትዮሽ ግጥሚያ መቀየሩ ነው። ይህንን ተከትሎ አጨዋወቱም ተቀይሯል።
ሦስቱ ዋነኛ የፖለቲካ ተዋናዮች ሥልጣን የተቆጣጠሩት፣ ሥልጣን የተቀሙት እና ሥልጣኑ ይገባናል የሚሉት አካላት ናቸው። ሁሉም የየራሳቸው ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች አሏቸው። ቀድሞ በተቃዋሚው ምድብ የነበሩት አሁን ሥልጣን በተቆጣጠሩት ወገን ሆነው የገዢው ቡድን አካል የሆኑ አሉ። በሌላ በኩል ቀድሞ የቀድሞ ገዢ የነበሩና አሁን ሥልጣን የተቃዋሚ አካል የሆኑ አሉ። ነገር ግን እያንዳንዳቸው ትንቅንቃቸው ከሁለት ቡድኖች ጋር ነው።
ስለዚህ የጫወታው ሕግ እና መመሪያ፣ የትኛው ቡድን የቱን መቼ አጋር እንደሚያደርገው፣ መቼ ተቀናቃኙ እንደሚያደርገው ግልጽ አይደለም። እንደሁኔታው እርስበርስ መተባበርም ይሁን መተናነቅ የጫወታው ሕግ ነው። በዚህ መሐል የትንቅንቅ መሣሪያው ነውጥ መሆኑ ደግሞ በውስብስብነቱ ላይ ተጨማሪ አደጋ እያስከተለ ያለው።
ለውጥ እና ነውጥ
የሽግግር ጊዜ የትም ይደረግ መቼ በባሕሪው ተስፋ እና ስጋት ማዘሉ የተለመደ ነገር ነው። በአንድ በኩል ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች (በተለይም ከተገፉት ወገን) ቀን ይወጣልኛል ብለው ያስባሉ፤ በሌላ በኩል ከሥልጣን በተገፉት እና ሥልጣን እየተቆጣጠሩ ባሉት ወገኖች መካከል ድርድር እና ሥምምነት ከሌለ አገር በጥፋት ሊታመስ ይችላል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ሁለቱንም በአንድ መድረክ ያሳየ ትያትር ይመስላል።
ከላይ የጠቀስናቸው ሦስቱም የፖለቲካ ተዋናዮች ተስፋም ስጋትም አላቸው። በአንድ በኩል ከለውጡ አተርፋለሁ የሚል ተስፋ፣ በሌላ በኩል  ተቀናቃኞቼ የለውጡን ትሩፋት በሙሉ አጥረግርገው ሊወስዱት ይችላሉ የሚል ስጋት። ስለሆነም ተስፋቸውን እውን ለማድረግ እና ስጋታቸውን ለማዳፈን ያላቸውን ኃይል በየፈረቃው ሲያሳዩ ከርመዋል።
መጀመሪያ የድጋፍ ሰልፎች ነበሩ። ከአዲስ አበባ እስከ መቐለ፣ ከግንቦት ሰባት እስከ ኦነግ አቀባበል፣ በየቦታው ብዙ የደጋፊ ማዕበሎች በተለያየ መልኩ ተስተናግደዋል። በመቀጠል የደቦ ፍርዶች፣ ማፈናቀሎች፣ አናሳ ቡድኖችን ማጥቃት፣ ስብሰባዎችን ማስተጓጎል፣ ወዘተ. በየክልሉ ታይተዋል።
ተቀናቃኝነቱ እና ድጋፍ ማሳየቱ ጎጂ አልነበረም። ችግሩ በመንግሥት የኃይል የበላይነት (Monopoly of Violence) ላይ መተማመን ላይ አለመደረሱ ነው። የኦ.ነ.ግ. ወታደራዊ ክንፍ ነኝ የሚል አካል ትጥቅ አልፈታም ብሎ ሲል፣ በወቅቱ የሲቪል ድርጅቱ መሪ ዳውድ ኢብሳ የሰጡት ምክንያት ‘የመንግሥት ወታደሮች ገለልተኞች ሳይሆኑ የገዢው ፓርቲ ናቸው፤ ስለዚህ እነርሱ የራሳቸው ሠራዊት ኖሯቸው እኛስ ለምን የራሳችን ሠራዊት አይኖረንም’ የሚል ነበር። የኋላ ኋላ ሲቪሉ እና ታጣቂው ቡድኖች ዕውቅና ተነፋፍገው የተለያዩ አካሎች ሆነው መንቀሳቀስ ቀጥለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን የለውጥ ጊዜ እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደው ትልልቅ መዋቅር ያላቸው ድርጅቶች በመመሥረት ፈንታ ማንቀሳቀስ በሚችሉት የነውጥ ኃይል ሲመኩ ቆይተዋል። በአማራ ክልል ሰኔ 2011 የተፈፀመው የአመራሮች ግድያ በክልሉ ገዢ ቡድን ውስጥ የተስተዋለው ነገር በሥልጣን የያዘው አካል ውስጥም የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ መኖሩን ነው። ይህም በኃይል ተቋጨ። በኦሮምያ የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ የተቀሰቀሰው ነውጥም የፖለቲካ ሽኩቻው አካል ነው። የፖሊስ ምርመራ ውጤትን ከተቀበልን፣ የአርቲስቱ አሟሟትም እንዲሁ የፖለቲካ ነውጥ ነው።
ነውጠኝነት ከዚህ በፊትም በኢትዮጵያ ለታዩ የለውጥ ዕድሎች መክሸፍ ምክንያት እንደሆነ ዶናልድ ሌቪን በሰፊው ጽፈዋል። እርሳቸው ‘የወንድነት’ ባሕል እያሉ ይጠቅሱታል። ፖለቲከኞቹ ይህ ‘የወንድነት’ ስሜት ያሉት ነውጠኝነት የተፀናወታቸው መሆኑ በመደራደር ፈንታ መፋለምን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል። በዚህ መሐል የለውጥ ፍላጎቶች ይዳፈናሉ። የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ የተቋቋመው ወታደራዊ ጊዜያዊ መንግሥት ለአምባገነንነት ዕድል ያገኘው የከተማ ነውጥን ለትግል ስልትነት የመረጡት ተቀናቃኞቹ የሰጡት ሰበብ ነው ይባላል።
የኃይል የበላይነት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆኑ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም፣ ተቀናቃኝ ድርጅቶች ይህንን የኃይል የበላይነት በተቀበሉ ቁጥር በሰላማዊ ውድድር ውስጥ ለመቆየት ቁርጠኝነት ይኖራቸዋል። ነገር ግን፣ የመንግሥትን የኃይል የበላይነት በተጠራጠሩ ቁጥር በኃይል ሥልጣን ለመንጠቅ ስለሚሞክሩ በፖሊሲ እና ሕዝብን በማደራጀት ለመመረጥ የመሞከር ዕድላቸው አነስተኛ ይሆናል። በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የታዘብነው ይህንኑ ነው። የፖለቲካ ድርጅቶች በኃይል የሚፈልጉትን ለማግኘት ሲፍጨረጨሩ ነው የቆዩት። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሥልጣን ላይ ያለውን አካል “ይዋጣልን” ሲሉት ከርመዋል። መጨረሻው ግን የሽግግሩን ተስፋ በከፍተኛ ሁኔታ ያዳፈነ ሁኔታ አምጥቷል።
በፖለቲካ ለውጡ ላይ ጨለማ ያጠላው የገዢው ፓርቲ ቁርጠኝነት ማነስ [ብቻ] አይደለም። ገዢው ፓርቲ የያዘው አቋም የተስማማውም ያልተስማማውም ለሰላማዊ ትግል ቁርጠኝነቱን ለማሳየት መቻል ነበረበት። ባለፈው ዓመትም ይሁን ዘንድሮ የተከሰቱትን ነውጦች ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች እንዲሁም ጋዜጠኞች ታስረዋል።
ለገለልተኛ ሰው ለነዚህ የፖለቲካ መሪዎች እና ጋዜጠኞች መሟገትም፣ አለመሟገትም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ነውጦችን የማበረታታት አዝማሚያዎች ሲስተዋሉ ነበር። ዝም ብሎ የመንግሥትን እርምጃ መመልከትም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም መንግሥት የገዢው ፓርቲ ታዛዥ ነው። ገዢው ፓርቲ የሥልጣን ሽኩቻው ባለድርሻ ነው። ገለልተኛ አይደለም፤ አልፎ ተርፎም የቀደመ ታሪኩ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎችን ለሥልጣን ማደላደያ ሊጠቀምበት እንደሚችል ያስጠረጥረዋል። በዚህ መሐል አጋጣሚው ለባለኃይሉ ተመችቷል።
ኢትዮጵያ ወደዴሞክራሲ ለመሻገር ስለምን ተሳናት ቢሉ፣ የፖለቲካ ተዋናዮቹ በሰላማዊ የጫዋታ ሕጉ ባለመገዛታቸው የሚለው ብዙ የሚያጣላ አይመስለኝም።
Filed in: Amharic