>

አማሮምኛና ኦሮማራ (መስፍን አረጋ)

አማሮምኛና ኦሮማራ

 

መስፍን አረጋ


አማርኛ ማናቸውንም ነገር በቀላሉ ለመገለጽ የሚያስችል እጅግ በጣም ቀና፣ ቅን፣ ተጣጣፊና፣ በዚያ ላይ ደግሞ ውብ ቋንቋ ነው፡፡  እንግሊዘኛን ጨምሮ፣ ዐበይት ከሚባሉት ከማናቸው የዓለም ቋንቋወች ጋር አቻ ለመሆን ብቻ ሳይሆን በብዙ እጥፍ በልጦ ለማስከንዳት የሚያስፈልገው የቆሸሸውን አጽድቶ፣ የተሳሳተውን አርሞ፣ የተዘበራረቀውን አደራጅቶ ቋንቋውን ስርዓት ማስያዝና አስፈላጊወቹን አዳዲስ ቃሎች መፍጠር ብቻና ብቻ ነው፡፡  

እነዚህን ለማከናወን ደግሞ በቀላሉ የሚያስችሉን ከሰባ ስምንት የማያንሱ አገራዊ ቋንቋወች፣ ተቀድተው የማይልቁ የቃላት ምንጮች አሉን፡፡  ሁሉ በጃችን በደጃችን ነው፡፡  በነዚህ አገራዊ ቋንቃወች ላይ አማረኛ እንደ ልብ ለመተጣጠፍ ያለውን ወደር የለሽ ችሎታ ስንጨምርበት ወሰናችን ሰማይ ሳይሆን ህዋ ይሆናል፡፡  አማረኛን በባዕዳን ቃሎች ከማኩሰስ በወገኖቹ ቃሎች ስናገዝፈው ደግሞ ሕዝባችን የበለጠ ላማፋቀርና ለማስተሳሰር የበኩሉን ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል፣ ቋንቋው የሁሉም ጦቢያውያን ገንዘብ ይሆናልና፡፡  

እንደዚህ ያለውን፣ ከወንድሞቹ አገራዊ ቋንቋወች ጋር የተወራሰሰ፣ የተጋባና፣ የተዋለደ ቋንቋ  አማረኛ ማለት ትቸ፣ አማረኛንና ኦሮምኛን በማጣመር አማሮምኛ ብየዋለሁ፡፡  አማሮምኛ በተለይም ለሰገል (science) የሚያገለግል ሰገላዊ (scientific) ቋንቋ ስለሆነ ደግሞ፣ ሞክሸ ስሙን ሰገላዊ አማረኛ ብየዋለሁ፡፡  

እኔ መስፍን አረጋ የአማሮምኛን ፅንሳብ (concept) ካሠርት ዓመታት በፊት ፀንስቤ (conceptualize) ሰገላዊ አማረኛ (አማሮምኛ) በሚል ርዕስ ያሳተምኩት፣ የዚህ ዓይነት አገራዊ እሳቤ ቀንደኛ ፀር የነበረው ጎጠኛው ወያኔ አለቅጥ በገነነበት በ 2000 ዓ.ም (ካሥራ ሁለት ዓመታት በፊት) ነበር፡፡  

እኔ እስከማውቀው ድረስ አሞሮምኛ በታሰበበት ጊዜ ይቅርና በታተመበት ግዜ እንኳን ኦሮማራ የሚል ቃል ከናካቴው አልነበረም፡፡  ለዚህ ነበር የመጽሐፉን አታሚ ጨምሮ አያሌ ሰወች የመጽሐፉ ርዕስ ግራ ስላጋባቸው ወይም ደግሞ ስላልጣማቸው አያሌ ጥያቄወችን ይጠየቁኝ የነበሩት፡፡ 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የወያኔ ቀንደኛ ሎሌ የነበረው ጎጠኛው ለማ መገርሳና ቢጤወቹ ካማሮምኛ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ኦሮማራ የሚሰኝ ቃል ፈጥረው (ወይም ደግሞ ካማሮምኛ ኮርጀው)፣ ካማሮምኛ የተቀደሰ ዓላማ ገማዘንጋዊ ተቃራኒ (diametrically opposite) ለሆነ እርኩስ ዓላማ ተጠቀሙበት፡፡   

የአማሮምኛ ዓላማ የአማርኛን እንዳበጁት መበጀትነት በግእዝ፣ በትግርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በወላይትኛና በቀሩት የጦቢያ ቋንቋወች በማዳበር፣ የጦቢያን ሰገላዊ ፍየሳ (scientific progress) በእጅጉ የሚያፋጥን፣ በተጨማሪም ደግሞ ከሁሉም የጦቢያ ቋንቋወች የተውጣጣ በመሆኑ ምክኒያት የጋራ ቋንቋነት ስሜት አስፍኖ ጦቢያውያንን ይበልጥ ለማስተሳሰር ጉልህ  አስተዋጽኦ የሚኖረው ሰገላዊ ቋንቋ (scientific language) መፍጠር ነው፡፡  

ለማ መገርሳና ቢጤወቹ ኦሮማራን የተጠቀሙበት ግን በጦቢያዊነት መቃብር ላይ ኦሮሙማን የመገንባት ትልማቸውን (strategy) የማሳኪያ ጊዜያዊ ስልት (temporary tactic) እንዲሆናቸው ብቻና ብቻ ነበር፡፡  አሁን፣ አሁን ደግሞ ኦሮማራ ሥራውን የጨረሰ ስለመሰላቸው፣ እሱን አሽቀንጥረው ጥለው ኦሮትግሬ ማለት ጀምረዋል፡፡

የሐበሻ ጠላ በጋን እሚነሳ 

አይበጅም በማለት ለኦሮሞ ጎሳ

ላይቀምሰው የማለው ለሚቾ መገርሳ፣

ጋኑን ሊሰባብር ማጀት እስኪገባ

ጦቢያ ሱሴ እያለ ጦቢያን ግራ አጋባ፡፡

ስለዚህም አማሮምኛና ኦሮማራ ባጠቃቀማቸው ተቃራኒ ብቻ ሳይሆኑ አጥፊና ጠፊ ናቸው፡፡  በመሆናቸውም፣ የኦሮሙማ ሽፋን የሆነውን አሮማራን ሽንጥን ገትሮ በመቃወም፣ የጦቢያዊነት መግለጫ ለሆነው ለአማሮምኛ ቀበቶን አጥብቆ መትጋት ይቻላል፡፡  እኔም መስፍን አረጋ ባለኝ አቅምና ጊዜ ለማድረግ እየሞከርኩ ያለሁት ይህንኑ ነው፡፡  ዋናው የአማሮምኛ ጠላት ደግሞ ባንደበቱ አማሮምኛዊ ሆኖ በምግባሩ ኦሮማራዊ የሆነው ሳሙናው ዐብይ አህመድ ነው፡፡  

ዐብይ አህመድ ዐሊ የኦነጉ ኦቦ

አፉና ምግባሩ ሐራምባና ቆቦ፡፡   

 mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic