
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃገርን ያበለጸገች ባለውለታ ለመሆኗ ሃገርን የገነባችበት አሻራ እማኝ ምስክር ነው!!!

መምህር ታሪኩ አበራ
† የኢትዮጵያ ውበቷ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መገንባቷ †
† ኢትዮጵያ ስትገለጥ የውስጥ ውበቷ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ዕንቁ ያሻበረቀ ነው።†
† ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃገርን ያበለጸገች ባለውለታ እንጂ የብልጽግና እንቅፋት ሃይማኖት ተብላ በጠባቦች የማትወቀስ አለመሆኗን ሃገርን የገነባችበት አሻራ እማኝ ምስክር ነው።†

ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ሰርታ ያቆመቻት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ናት።ሕዝብን በባህልና በሥነ ምግባር በማስተጋበር ቋንቋውን፣ታሪኩን፣ባህላዊ ዕሴቱን ጠብቆ እንዲኖርና አንዱ ከሌላው እንዲዋረስ የፍቅርን መስመር የዘረጋችው ቅድሥት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ነች።

አንዳንድ ጨለምተኛ የብሔር ፓለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች የኢትዮጵያን ታሪክ በቅጡ ሳይረዱና ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን እውነተኛ ጥልቅ የታሪክ ትንታኔዎችን ሳያነቡ በግልብ ንባብና በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ኦርቶዶክስን ለመስደብ አንደበታቸውን እንደ መቃብር ሲከፍቱ እናያለን።አለመታደላቸው እንጂ እነርሱ ዛሬ የሚጽፋበትንና የሚናገሩበትን ፊደል ቀርጻ የሰጠቻቸው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነች።ማሰብ ተስኗቸው እንጂ እነርሱ ዛሬ በቅኝ ግዛት ባለተገዛ የነጻነት ምድር ላይ በሕይወት እንዲመላለሱ ያደረገቻቸው ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ነች።
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነጻነትን ከነክብሩ፣ሃገርን ከነዳር ድንበሩ ጠብቃ ያቆየች የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ነች።በኪነ ህንጻ፣ በሥነ ጽሑፍ፣በሕዝብ አስተዳደር፣ በዜማና ቅኔ በአጠቃላይ ሃገር እንደ ሃገር የምትሰራበትን ማገርና ምሰሶ ያቆመች ጠንካራ መሰረት በጽኑ ዓለት ላይ የጣለች ቅድሥት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ነች።

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለዘለዓለም በትውልድ ልብ ውስጥ እያበራች ትኖራለች።