>
5:18 pm - Sunday June 15, 6797

በአንድ ጊዜ 8ሺ ሰው - በአንድ ቀን ደግሞ እስከ 40ሺ ሰው የሚስተናገድበት ታላቁ የግብር አዳራሽ ፣ (ሲሳይ ተፈራ መኮንን)

በአንድ ጊዜ 8ሺ ሰው – በአንድ ቀን ደግሞ እስከ 40ሺ ሰው የሚስተናገድበት ታላቁ የግብር አዳራሽ ፣

ሲሳይ ተፈራ መኮንን

* የእምዬ ሚኒሊክ የተራበን ማጉረሻ የተጠማን ማጠጫ – ግብር ቤት፤ 
 
* ከ120 አመት በፊት የተሰራው የምኒልክ የግብር አዳራሽ ምህንድስና፣ ቅርጽና ይዘት፣
 
* የመንግሥታዊ ድግሡ ታዳሚዎች ማንነትና የግብሩ ሥርአት፣
 
* “ቀድሞም ጠቢብ ነበር ሰለሞን አባቱ
ምኒልክ ይበልጣል ሰው ይዞ መብላቱ” 
ዳግማዊ ምኒልክ ሰዉ ሁሉ አንድ ጊዜ ተሰብስቦ የሚበላበትን ትልቅ አዳራሽ ለመስራት በመወሰን፣ በ1889 ዓ.ም ክረምቱን መናገሻ ወርደው እንጨት ሲያስጠርቡ ከረሙ፡፡ ወታደሩም በድግስ ጊዜ ሜዳ ላይ ሆነን ጸሀይና ዝናብ እንዳይመታን ለኛ ብለው አይደለምን በማለት ደስ ተሰኘ፡፡ ላዳራሹ የሚያስፈልገውን 4 ማዕዘን፣ ሳንቃና እንጨትም ላሊ እየወጣና እየዘፈነ ማመላለስ ጀመረ፡፡
በ1890 ዓ.ም በዘመነ ማርቆስ ዳግማዊ ምኒልክ ከአውሮፓ መሀንዲሶችን በማስመጣት ውስጡ 1፣ ውቅሩ 3፣ ቁመቱ 120 ክንድ፣ ጎኑ ደግሞ 60 ክንድ የሆነ አዳራሽ አሰሩ፡፡ ይህም የሚበላበት ብቻ ነው፡፡ ለእንጀራ ለጠጅና ለስጋ ማቅረቢያ ደግሞ ለየብቻው ተሰራ፡፡ የእንጀራ ማቅረቢያው በስተደቡብ በኩል ቁመቱ 37 ክንድ ጎኑ 7 ክንድ፣ በሰሜን በኩል ያለውም እንደዚሁ ቁመቱ 37 ክንድ፣ ጎኑ ደግሞ 7 ክንድ ሆኖ ተሰራ፡፡
የሥጋውም ማቅረቢያ ቁመቱ 24 ክንድ ጎኑ 7 ክንድ ነው፡፡ የጠጁም ማቅረቢያ ጋንና ገንዳ ተተክሎበት አሳላፊዎች የሚቆሙበት በሰሜንና በደቡብ ቁመቱ እኩል 59፤59 ክንድ፣ ጎኑም እኩል 7፤7 ክንድ ሆኖ ተሰራ፡፡ ጠጅ የሚመላለስበት ገንዳም ቁመቱ እኩል በሰሜንና በደቡብ 7፤7 ክንድ ቁመቱም 2፤2 ክንድ ሆኖ ተሰራ፡፡ እያንዳንዱ የብረት ገንቦም 20፡20 ብርሌ የሚይዝ ሆኖ የብረቱ ገንቦ ባጠቃላይ በአንድ ጊዜ 700 ገንቦ/14000 ብርሌ ይይዛል፡፡
ግብር የሚበላበት አዳራሽ ጠጅ ቤትም ቁመቱ 92 ክንድ፣ ቁመቱ ደግሞ 20 ክንድ ነው፡፡ የማለፊያው ጠጅ ቤት ቁመት ደግሞ 50 ክንድ ሲሆን ጎኑም 14 ክንድ ነው፡፡ በገንዳው ግራና ቀኝ ባለመዘውር የብረት አሸንዳ የተተከለበት ሲሆን ግብር በሚበላበት ቀን ግራና ቀኝ ያለው አሸንዳ ካዳራሹ መካከል በትልቁ የብረት ድስት መዘውሩ እየተዘወረ ከድስቱ ላይ ሲፈስ፣ ከገደል የሚፈስ ትልቅ ውሃ ይመስላል፡፡
ባለ 3 ውቅር በሆነው አንድ ትልቅ አዳራሽ 3 ውቅር ቤቶች እያንዳንዱ ቤት ላይ 50፤50 ጉልላት አለበት፡፡ በእያንዳንዱ ውቅር ላይም የሰጎን እንቁላል ተደርጎበታል፡፡ በአዳራሹ ውስጥ የተሰቀለው ባለኤልክትሪክ ፋኖስ በበራ ጊዜ እንደ ጸሐይ ብርሀን አይን ይበዘብዛል፡፡ በምስራቅ በኩል በአረንጓዴ ብጫ ቀይ ሰማያዊና ብዙ ህብረ ቀለማት የተሸለመ ብርሀን የሚያስገባ ሶስት ባለመስታወት መስኮት ተሰርቶለታል፡፡
በምስራቅ፣ በምዕራብና በሰሜን ባሉት ታላቅ በሮች ላይም 2፡2 ባለመስታወት መስኮት አለው፡፡ በደቡብ በስጋ ማቅረቢያና ጠጅ ማሳለፊያ በኩልም 3 መስኮት አለው፡፡ በጓዳው በኩልም እጅግ ያማረ 5 ባለመስታወት መስኮት እንዲሁም ከማጠፊያና ማጠፊያው ላይ ደግሞ 4 ባለመስታወት መስኮት ተሰርቶለታል፡፡
መሃል ላይ 3ቱን ውቅሮች የሚደግፉ 34 አምዶች ቆመዋል፡፡ የአዳራሹ ግንብም ከውስጥና ከውጭ እንደ አምደ ወርቅ ሆኖ ተሰርቶ በብዙ ህብረ ቀለም በዕብነ በረድ እየተሸለመ ልዩ ልዩ በሆነ የወይን ሐረግ ተቀርጹዋል፡፡ ቅርጹም እጅግ ያማረ ነው፡፡
የአዳራሹ ስራ ሲጠናቀቅም ከባህር ማዶ የመጣ እንደወርቅ የሚያንጸባርቅ እጅግ ያማረ መንበረ ዳዊት ተተከለበት፣ በውስጡም ዘውድ ክዋክብትና ብዙ ያማሩ ነገሮች ተሰሩበት፡፡ ወርቅ በሚመስሉ አምዶች ላይም የእሳት ልሳን የመሰለ ባለወርቅ ዘርፍ ያለው መጋረጃ ተጋርዶበታል፡፡
ከጃንሆይ ምኒልክ ፊት ለፊት፣ ግራና ቀኝ፣ በአንዴ በግብር አዳራሹ በየማእረጉ የሚቀመጠውና በየጥጉ የሚቆመው ሰው 7987 ይሆናል፡፡ ይህም ሥጋ እንጀራና ጠጅ አሳላፊውን ሳይጨምር ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ 380 ይሆናሉ፡፡ ፊት የገባው በልቶ ሲወጣ ቀጣዩ ደግሞ ምሽቱ እስኪያቋርጠው ድረስ ለ5 እና 6 ዙር እየገባ ይበላል፡፡
ጠጅ የሚመጣጠበት ኩባያ 3 ብርሌ ያክላል፡፡ ለግብር የሚመጣው ሰው ግብሩ እስኪዘጋጅ ድረስ ካዳራሹ በስተምዕራብ 200 ክንድ ርቆ ባለው ሜዳ ይሰበሰባል፡፡ ሰዉ ጨርሶ ከገባ በኋላ የገባው እንዳይወጣ፣ በልቶ የሚወጣውም ድጋሚ እንዳይደባለቅ አጋፋሪዎች ይቆልፉበታል፡፡ የገባው በልቶ ጠጥቶ ሲጨርስ በሰሜን በኩል ባለው ትልቅ በር ከሚገባው ጋር ሳይተያይ ይወጣል፡፡
ከአውሮፓ የመጣ 400 የሚሆን ታላላቅ የብረት መሶብ ከግብሩ አዳራሽ ከእንጀራ ማቅረቢያው ላይ ሳይነሳ ይቀመጣል፡፡ በግብር ቀን በአዳራሹ እየገባ የሚበላና የሚጠጣው ወታደር ብቻ አይደለም፡፡ ለጩኸት የመጣ ባላገር፣ እረኛ፣ የወታደር አሽከር፣ ባደባባይ የተገኘ ሁሉም ሰው እየገባ ያለከልካይ ይበላል ይጠጣል፡፡ አጋፋሪዎችም የማነህ አይሉትም፡፡
የምኒልክ ድግስ ሁል ጊዜ እንደጸና ተዘርግቶ የሚኖር በመሆኑ ለመግለጽ ያስቸግራል፡፡ አዛዦች በቀጭን ድርብ በአብደላከኒ ቀሚስ ባለወርቅ ጫማ ጎራዴ እየታጠቁ፣ አጋፋሪዎችና ዙፋን ቤቶችም እንደዚሁ እያጌጡ የእሳት ልሳን መስለው በአዳራሹ ይመላለሳሉ፡፡ የማር ጠጅ፣ የወይን ጠጅ፣ አረቄ፣ ሻምፓኝና ከውጭ አገር የመጡ ልዩ ልዩ መጠጦች ይቀርባሉ፡፡
በምኒልክ አዳራሻ ሁሉም ይጠግብበታል እንጂ ሰው አይመረጥበትም፡፡ ጠጅ፣ እንጀራና ሥጋ አሳላፊዎችም አፈጣጠናቸውና አካሄዳቸው አስገራሚ ነው፡፡ አንዱ ባንዱ ሲተላለፍ ሥጋ የያዘው ብርሌ የያዘውን፣ ዋንጫም የያዘው ሥጋ የያዘውን አይገፋውም፡፡ አስተናጋጆቹ ሳይገፋፉ እየተላለፉ ሲሾልኩ መላዕክት ይመስላሉ፡፡
በዚህ የተደነቀው አዝማሪም በአንዱ ቀን እንካ ተቀበል አለ፣
ቀድሞም ጠቢብ ነበር ሰለሞን አባቱ
ምኒልክ ይበልጣል ሰው ይዞ መብላቱ
ታሪክ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፣ ከጸሓፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ (ከ1837-1905 ዓ.ም ድረስ የኖሩ)፣ አርቲስቲክ  ማተሚያ ሊሚትድ 1959 ዓ.ም፣ ገጽ 278-284፣ 206-207
የፎቶ መግለጫ
– የተያያዘው ምስል የምኒልክ አዳራሽ አሁን ያለውን ይዘት የሚያሳይ ነው፡፡ ዶ/ር አብይም የ5ሚ ብር እራት እያበሉበት ነው፡፡
–  የምኒልክ የግብር አዳራሻ ከ110 አመት በፊት በ1900ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ የነበረውን ገጽታ የሚያሳይ ተጨማሪ ፎቶግራፍ በአስተያየት መስጫው ላይ መመልከት ይቻላል፡፡
Filed in: Amharic