>

ሽው ሽው አራዳ… ! ሸገር… ሚን ኢዳ ኖ?!? (አሣፍ ሃይሉ)

ሽው ሽው አራዳ… ! ሸገር… ሚን ኢዳ ኖ?!?

አሣፍ ሃይሉ

(በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ አጭር ልብወለድ)
“አሁን ግን የወላይታ ወጣቶች የአዲሳባን ወጣቶችን ከገቡበት ያለመንቀሳቀስ ሰመመን የሚያነቃ- ታሪክ ሠርተዋል፡፡  . . .”
የአዲስ አበባ ወጣት በተወለደበት፣ ባደገበት፣ በኖረበት ሀገሩ፣ በኖረባት ከተማ ላይ መብት የለውም፡፡ የአዲስ አበባ ወጣት አንድም ሁለትም ሆኖ አደባባይ ቢወጣ የሚጠብቀው ስናይፐር የደገነ አጋዚ ነው፡፡ የአዲሳባ ወጣት ክልል የለውም፡፡ የአዲስ አበባ ወጣት በገዛ ከተማው ላይ መሰብሰብ አይችልም፡፡ አዲስ አበቤው መደራጀት አይችልም፡፡ የፖለቲካ መሪዎች ማፍራት አይችልም፡፡ የአዲሳባ ልጅ ባንዲራ መያዝ አይችልም፡፡ ኮሽ ባለ ቁጥር በሺህዎች እየታፈሰ ሰበታና ዝዋይ በግዞት የሚጫነው የአዲስ አበባ ልጅ ነው፡፡
ህገመንግሥቱ አዲስ አበባን በአረንጓዴ ጽፎ፣ በቀይ ሰርዟታል፡፡ ህገመንግሥቱ አዲስ አበቤን አያውቀውም፡፡  የአዲሳባ ልጅ የቤርቤረሰቧ ኢጦቢያ የእንጀራ ልጅ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ወጣት ከአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኘው በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ የሚደርሰው ሽራፊ ሶልዲ የለም፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሚያ የግል ንብረት ተደርጋለች፡፡ የአዲስ አበባ ወጣት ደግሞ የቄሮ የጉዲፈቻ አሽከር እንዲሆን እየተሠራ ነው፡፡ አምኖ እስኪቀበል ድረስ የአዲሳባ ወጣት በብዙ አፈሙዞች ሥር ነው፡፡
አሁን ግን የወላይታ ወጣቶች የአዲሳባን ወጣቶችን ከገቡበት ያለመንቀሳቀስ ሰመመን የሚያነቃ- ታሪክ ሠርተዋል፡፡  . . . የአዲሳባ ወጣት ዓይኑ እያየ፣ ጆሮው እየሰማ – የወላይታ ልጆች – በወላይታ ላይ አሪፍ የፖለቲካ ተጫውተው – ቁማርተኞቹን በልተው – ጨዋታቸውን አጠናቀዋል! ብዙ ትምህርት የሚገኝበት ጨዋታ ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ይሄ ወላይታ ላይ ሽው ሽው ያለው ነፋስ አዲስ አበባ ላይስ – መቼ ይሆን የሚደርሰው? ከወላይታ ዲንቻ አጨዋወት – የአዱ ገነቶቹ ቡናና ሳንጅዬስ ምን ይማሩ ይሆን?
ነገሩ ለቀባሪው አረዱት ነው፡፡ ‹ለአንበሣ አይመትሩም – ለአራዳ ልጅ ሁሉን አይነግሩም!›፡፡ ግን የሆኑ ብንኖዎች የማይቀሩ ናቸው! ለምሳሌ ማንንም – ቄሮንም ቢሆን – ከቦ ማናገር አይኖርም! ግልብጥ ብሎ መውጣት ሊኖር ይችላል! መሪውን ማስፈታት ሊኖር ይችላል! መብቱን ማስከበር ሊኖር ይችላል! ክልሉን የራሱ ማድረግን – ይሄም ሊደረግ ይችላል! የአዲሳባ ወጣት የኢትዮጵያ ህዝብ መዲና፣ የአፍሪካ መዲና የሆነችው የአዱ ተረካቢና ጠባቂ ነውና – አደራውን እየተወጣ – መብቱንም መጠየቅ ያለበት ጊዜ ሩቅ እንዳይደለ ይገመታል! የትም ሂድ – የትም እደግ – አዱ ላይ ተወለድ!
ሽው ሽው አራዳ… ! ሸገር… ሚን ኢዳ ኖ!? …. ወዘተ. ወዘተ. ወዘተ. ወዘተ. ወዘተ.ወዘተ. ወዘተ. …
እያልኩ የመጣልኝን ሀሳብ እንደወረደ መጻፍ አሰብኩ፡፡ ደግሜ ደጋግሜ አሰብኩት፡፡ ምክረ ሀሳቡ ውሃ አላነሳልህ አለኝ፡፡ ስሜት ነው ይሄ፡፡ ሌላ የዘረኝነት እንድርድሮሽ፡፡ ውበትን ፍለጋ – እንደሚለው የጌትነት ትያትር፡፡ ይሄም ቀውስን ፍለጋ መሰለኝ፡፡ እና በመጨረሻ ተውኩት፡፡
የጀመርኩትን ትቼ በምትኩ “አዲሳባ ከወላይታ የምትማረው ሃባ ነገር የለም!” በሚል አዲስ ርዕስ ሥር መጻፍ ጀመርኩ፡፡ “ሽው ሽው አራዳ! ሽው ሽው ፒያሳ…!” የሚለውም ዜማ አልጣመኝም፡፡ ቀየርኩት እሱንም፡፡ “ጂሚ፣ ጂሚ! ሃጃ፣ ሃጃ…!” በሚለው ቀየርኩት፡፡ አልኸካሁም – እንዳለው ሼኽ አላሙዲ – እኔም አልኸካሁም፡፡ ነፍሴ ልትረካልኝ አልቻለችም! ቀየርኩት ዜማውን፡፡
አሀት፣ ሰስት፣ ሄሽት… ዥው ዥም ዥም… ነፍሱ የካዛንቺሲ! እኔ ስል ቴዲ – እናንተ በሉ ዮ! ቴዲ – ዮ! ቴዲ… ዮ፡፡ ይሄ ይልቅ ለጭሰት አሪፍ ነው፡፡ ብዬ አሰብኩ፡፡ በመውደድ ክብሩ የካርቱን ዳንስም አጀብኩት፡፡ ጽሑፌን፡፡ ቆንጂት ሚን ኢዳ ኖ! አልማዝ ሚን ኢዳ ኖ! ሸገር… ሚን ኢዳ ኖ!? የሚኒገናኞ… ቤዬቲኛው ቄንኖ!? ሼጌር ሚን ኢዳ ኖ?!፡፡ የሚል ሚክስ ጨመርኩበት፡፡ ፊቸሪንግ – ጆኒ ራጋ! ሺፍታው ልቡ! ሹካው ልቡ….!!!
አበቃሁ፡፡
አሣፍ ነኝ፡፡
ከቀጨኔ! ከሽሮሜዳ! ከኮልፌ! ኢና … ከካዛ – ኢን – ጂሩ!!!!
Filed in: Amharic