>

ከአምስት መቶ አመት በፊት በበራራ (አዲስ አበባ) ዙሪያ  ከ "ክብረ አምሓራ" መጽሐፍ፣ ምዕራፍ ሦስት - "ታሪካችን ማንነታችን"  (ልጅ ተድላ መላኩ)

ከአምስት መቶ አመት በፊት በበራራ (አዲስ አበባ) ዙሪያ  ከ “ክብረ አምሓራ” መጽሐፍ፣ ምዕራፍ ሦስት – “ታሪካችን ማንነታችን” 

 ልጅ ተድላ መላኩ
. . .  ግራኝ አህመድ የአዋሽን ወንዝ ተሻግሮ በነበርች ከተማ ላይ ዝርፊያን እና ቃጠሎን–ንጉሰ ነገስቱ ከሰራዊታቸዉ ጋር ከመድረሳቸዉ በፊት–አካሄዶ ሸሸ። የግራኝ አህመድ ሰራዊቶች ከብዙ ብሔሮች (ዐረብ፣ ቱርክ፣ ሶማሌ፣ ወዘተ) የተውጣጡና ወግቶ የመሸሽ ጥቃትን እንጂ ስትራቴጃዊ ጦርነትን አያውቁም ነበር። አንድን ከተማ ገብተው በማውደምና ቃጠሎ በማካሄድ ንጉሠ ነገሥቱና ሠራዊቱ ሳይደርሱ ይሸሹ ነበር . . . ። በአፍሪቃ ቀንድ በኢትዮጵያ ምድር ላይ የመጀመሪያዉን መድፍ ግራኝ በ16ኛዉ ክፍለ ዘመን አስተኮሰ።
ልብነ ድንግልም ምስራቅና ደቡብ ያሉትን አጠቃላይ ስር ግዛቶች ለጄኔራላቸዉ ለራስ ወሰን ሰገድ ትተዉ ወደ ቤተ አምሐራ ሰራዊታቸዉን ለማጠናከር አመሩ። ወሰን ሰገድ ደብረ ቡሳት አጠገብ ከኡራኢ ኡትማን ጋር ሲዋጉ ጦርነት ላይ ሞቱ፤  ሰራዊታቸዉም ተበተኑ። አልፎም ግራኝ ልብነ ደንግልን የአምባሰል ዉጊያ ላይ በዘመናዊ መሳሪያና ታላቅ ውጫዊ ድጋፍ አማካኝነት ጠነከረባቸው። የግራኝ ሰራዊትም ቤተ አምሐራ ዉስጥ ለመግባት ችሎ ያገኙአቸዉን ቤተክርስቲያኖች ሁሉ እየዘረፉና እያቃጠሉ አወደሙ። ካቃጠሉአቸዉ አቢያተ-ክርስቲያናት ዐፄ ናኦድ ሙሉ በሙሉ በወርቅ ያሰሩአት ድንቂቱ መካነ ሥላሴ፣ አትሮንሰማሪያም ደብረ-ነጎድጓድና ገነተ-ጊዮርጊስ ይገኙበታል። በነዚህም የግራኝ ዘመቻዎች ብዙ ገዳማትና አቢያተክርስቲያናት ጠፉ ክርስቲያኖችም በጦር ግዳጅ ሃይማኖታቸዉን እንዲለውጡ ተገደዱ። በዚህ ጥቃት ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናና ስቃይን አሳለፈች። የአፄ ዳዊት የበኩር ልጅም በግራኝ ጦር ተገደለ። ሜናስ የተባለዉም ልጃቸዉ ተይዞ ወደ የመን እንዲወሰድ ተደረገ (በኋላ ይመለሳል)።
አምባ ጊሸንም ተወሮ ንጉሳዊ ግምጃቤቱ ተዘረፈ። በዚያን ጊዜም ልብነ ድንግል ሳይሸሹ እስከ መጨረሻው “ወደ ንጉሣዊ ሥልጣናችን መገኛ፣ ወደ አባቶቻችንና አያቶቻችን አምሓራ ነገሥታት ምድር ቤተ አምሓራን እስከ ሞት እንከላከል ዘንድ ወደ አምሓራ በሮች ሄደን እንሙት” ብለው ለሠራዊታቸው ትእዛዝ ሰጥተው እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ተዋጉ። በዚህ ዘመን . . . የቤተ አምሐራ መንግስት በግራኝ ወረራ  በጠላት እጅ ላይ ወድቆ 20 አመታትም እንኳ ባይቆይ የደረሰበት ጉዳት ግን በብዙ መቶ ክፍለ ዘመናትም እንኳ ሊተመን እንድማይችል የታሪክ ጠቢባን ያሳውቁናል። ከዳግማዊ አፄ ዳዊት  (ልብነ ድንግል) ልጆች አንዱ፣ ያዕቆብ፣ ሽዋ ላይ መንዝ ውስጥ ተሸሽጎ ቆየ። የያዕቆብም ልጅ ሱሶንዮስ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ተብሎ  የጎንደርን ሰሎሞናዊ ንጉሳዊ የዘር ሐረግ ይጀምራል።
የዐፄ ልብነ ድንግል ልጅ ገላውዲዮስ የአባቶቹን ሃላፊነት ተረከበ። ገላውዲዮስ ሽዋ ሆኖ — ግራኝ የቱርክ የሶማሌና የዐረብ ሠራዊት ድጋፍ እንዳለው — የኢትዮጵያን መንግሥት ጦርነቱ ላይ እንዲደግፉ ጥሪ ቀርቦላቸው የመጡ በሃያ ስድስት ዓመት ወጣት  የሚመሩ አራት መቶ ያህል የፖርቱጋል ወታደሮች ስምንት መድፎች፣ መቶ ጠብመንጃዎች እና ብዙ ሌሎች የጦር መሣሪያዎች ይዘው በትግሬ ምድር በኩል ንጉሠ ነገሥት ገላውዲዮስ ወዳለበት ወደ ሽዋ አመሩ። መንገዳቸውን እየተዋጉና ጥቃቶችን እየተከላከሉ በሚሄዱ ጊዜ ከነሱ ውስጥ የሃያ ስድስት ዓመቱ ወጣት መሪአቸው — የቫስኮ ደጋማ ልጅ ፣ ክሪስቶፍ ደ ጋማ — ቆስሎ ወደ ኋላ ቀርቶ ስለነበር  የግራኝ ጭፍሮች ይዘው አሰቃይተውና ሰውነቱን ቆራርጠው ገደሉት። ግራኝ ካለው ሠራዊትና ትጥቅ ላይ አስር መድፎችና ዘጠኝ መቶ ባለ ሙስኬት ጠብመንጃ ወታደሮች ዐረብ ምድር ላይ ካሉ ዜቢድ ቱርክ ፓሻዎች ተልኮለት ውጊያውን ቀጥሎ፣ በመጨረሻ ድል ያደረገ መስሎት፣ ዐፄ ገላውዲዮስ ሠራዊቱን ሰብስቦና የተረፈውን የፖርቱጋሎች ሠራዊት ከሠራዊቱ ጋ አዋህዶ ወይና ደጋ ላይ ግራኝን እና የቱርክና የዐረብ ሠራዊቱን እያሳደደ ገድሎ ጨረሳቸው። ግራኝ በገላውዲዮስ በጠብመንጃ ጥይት ተመትቶ ተገደለ፣ ወታደሮቹም ተሸንፈው አለቁ።
የግራኝ ወረራ በአማራ ምድር ላይና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ታላቅ የሥልጣኔ መጥፋትና መውደምን አስከተለ። በሐብትም በሞራልም ሕዝቡ ተጎዳ። የህ በሚሆን ጊዜ ኦሮሞ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ከዋቢና ጁባ ሸለቆ መፍለስ ጀመረ። የግራኝን ገዳዮች ለመበቀልና ሚስቱን ለማስደነቅ ኑር ኢብን አል ዋዚር የሚባል ጥቃት መፈጽም ጀመረ። ሃረር ከተማ ዙሪያ ያለውን ግምብ የገነባው እሱ ነው። የሱን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ለምላሽ ሃረር ላይ ጥቃት ፈጸመ። ከዚያም ኑር ኢብን አል ዋዚር ከብዙ ዓመታት በኋላ ጠብቆ ሊበቀል ፈጠገርን ወረረ። ወረራው ላይ በአብዛኛው መነኩሴዎች የሠራዊት ኃይሉን ተቀላቅለው ወረራውን ሊከላኩ ግድ ሆነ። ገላውዲዮስ ዜና መዋዕሉ እንደሚለው በአንዲት ሴት ፍቅር ምክኒያት — ውጊያው ውስጥ እንዳይገባ ልታስቀረው ብትሞክርም — ቄስ ከነበረ ባሏ ወስዶአት ስለነበር ባደረገው ነገር ተቆጭቶ ራሱን ውጊያው መሃል ወርውሮ እንዳስገባና ውጊያው ላይ እንደ ሞተ ተጽፎአል።
ለሕዝብ መዳንና ከጠላት ወረራ ባርነት መትረፍ ራሱን የሰዋው ገላውዲዮስ ጭንቅላቱን ቆርጠው ለግራኝ ሚስት ሊያሳዩ ወሰዱ። ገላውዲዮስ ትድባበ ማሪያም ቤተ ክርስቲያንን የገነባ እሱ ነው። የገላውዲዮስ ኑዛዜን የጻፈም እሱ ነው። ከአስራ አምስት መቶዎቹ ማጋመሻ በኋላ ኦሮሞዎች ከዋቢና ጁባ ሸለቆዎች ፈልሰው በምስራቅ በኩል ወደ ኣንጎት፣ አምሓራ፣ በጌምድር እና ምዕራብ ጎጃም – ወለጋ ያለው ምድር ላይ – ገቡ። ገላውዲዮስን ተከትሎ የነገሠው ሚናስ በአንድ በኩል ቱርኮች በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮሞዎች ምድሩን ወረው ፈተኑት። እሱም ሞተ። ይህ አልበቃ ብሎ በሰሜን ሚናስ ላይ አምጾ የነበረ የትግሬ መሪ ከምጽዋ ቱርኮች ጋ ትብብር ፈጥሮ ካደ። ደቡብ እስከ መሃል አገር የኢትዮጵያ መንግሥት በሚስፋፉ ኦሮሞ ጎሳዎች ተወረረ። በሃምሳ ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ ላይ ታይቶ ያልነበረ አይነት ወረራ ተካሄደ። የኢትዮጵያን መንግሥት ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሐብት የያዙ የትምህርት ስፍራዎችና ገዳሞች ከነሙሉ የብዙ ዘመን የእውቀት፣ የማንነታችንና የከፍታችን መገልጫ መጻሕፍትና ንብረቶች ላይመለሱ ጠፉ።
 በዚህ ታላቅ የጥፋት ዘመን ታላቁ ሠርፀ ድንግል ተነሳ [አባ ባህርይም ሠርፀ ድንግልን በዜና መዋዕላቸው “መሲሕ” ይሉታል፤ ሕዝብን ለማዳን የተቀባ፣ ሰሎሞናዊ ንጉሠ ነገሥት ነበርና]።  በእሱ ዘመን ወራሪ ኃይሎች ቀስ በቀስ መሸሽ ጀመሩ። ይህ ንጉሥ ታላቅ አርበኛ ነበር። ፍርሐትን የማያውቅ ታላቅና ኃይለኛ ተዋጊ ነበር። ስለ እሱ ብዙ የምስጋና ድርሠቶች በረዥም ዜና መዋዕል ተጽፈዋል። ሠርጸ ድንግል ከተሞችን ባጠፉና ሕዝብን በስደት በሚያንከራትቱና በጭፍጨፋ በሚጨርሱ ወራሪ ኃይሎች ተፈተነ። ሠርጸ ድንግል ረፍት አልነበረውም። በሰሜን በኩል የቱርክ ወራሪዎችን፣ በደቡብ በኩልም እየወጋ አስጣለ። አማራን እና የኢትዮጵያን መንግሥት ከመጥፋት አተረፈ። ዘመኑን ሁሉ ሕዝብን በታላላቅ ዉጊያዎች ከጥቃት ሲከልል እና ወራሪውን ኃይል ከአማራ ምድር ላይ እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ለማስወጣት፣ እንደ መዥገር የተጣበቀውን አጥፊና ገዳይ ነቅሎ ለመጣል ተጋደለ። የአባ ባሕርይ ድርሰቶች የሠርጸ ድንግል ተጋድሎ ይዘክራሉ።
Filed in: Amharic