>

ስለወላይታ ሕዝብ ጨዋነት! በትውስታ 17 ዓመት ወደ ኋላ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ስለወላይታ ሕዝብ ጨዋነት! በትውስታ 17 ዓመት ወደ ኋላ…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ሰሞኑን የክልል ጥያቄን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ቁጣ በወላይታ ሕዝብ ላይ የመንግስት የጸጥታ ጏይሎች ያደረሰቱ ጉዳት እጅግ የሚያሳዝን ነው። የመንግስት የጸጥታ ጏይል ለቀናት በተላያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ዜጎች ሲታረዱና ንብረታቸው ሲወድም አልታዘዝንም በሚል አሳፋሪ ምክንያት እዳር ቆመው ተመልካች እንዳልነበሩ ሰላማዊ በሆነው የወላይታ ሕዝቡ ላይ ይሄን ሁሉ ውርጅብኝ ማድረስ ባለስልጣናቱ የት እና በምን ሁኔታ ጏይላቸውን መጠቀም እንዳለባቸው የተረዱ አይመስልም። ይህን የምለው ነገርየው እየተደጋገመ ሲከሰት ስላየሁ ነው።
ዋናው እርዕሴ የወላይታ ሕዝብ ምን ያህል ስልጡን፣ ሰላማዊ እና ጨዋ መሆኑን ከማውቀው ለመመስከር ነው። የኢሰመጉ መርማሪ በነበርኩበት ወቅት ለምርመራ ሥራ በስፋት የተንቀሳቀስኩት በደቡብ ክልል ውስጥ ነው። በተለይም ወላይ፤ ሶዶን እና ሌሎች ወረዳዎቿን ደጋግሜ ጎብኝቻለሁ። ከሕዝቡ ጋር ለመቀራረብ እና ከአገር ሽማግሌዎቻቸውም ጋር ቁጭ ብዬ ብዙ ሰዓታት ለማውጋት እድል ገጥሞኛል። አውርተው የማይጠገቡት እና እርጋታ የማይለያቸው አዛውንቶች ትልቅ ኮሌጆች ናቸው። ላወቀበት ከነሱ ብዙ መማር ይቻላል። የዘመኑ የወላይታ ወጣቶች ያ ዕድል የገጠማቸው እና ከአዛውንቱ ብዙ የተማሩ ይመስላል። በመንግስት ጏይሎች ወገኖቻቸው በተገደሉበት ማግስት ስልጡን እና ሰላማዊ ተቃውሞ አሰምተው መመለሳቸውም ጥሩ ማሳያ ነው።
የዛሬ 17 ዓመት ግድም በ1995 ዓ/ም መለስ ዜናዊ ሲያቀብጠው አራት የአካባቢውን ቋንቋዎች ጨፍልቄ አንድ አዲስ ወጋጎዳ (ወላይታ፣ ጋሙ፣ ጎፋ እና ዳውሮ) የሚባል ቋንቋ ፈጥሬያለሁ እና ትምህርት በአማርኛ ሳይሆን በዚህ ቋንቋ ይሰጥ ብሎ ባወጀ ጊዜ በሶዶ ትልቅ ተቃውሞ ተነሳ። መምህራንን ጨምሮ ብዙ ተማሪዎች ታሰሩ። የተወሰኑ ሰዎችም ተገደሉ። ውጥረቱ በተነሳበት ጊዜ በአገር ሽማግሌዎች ጥሪ ተደርጎልን እዛው ሶዶ ከተማ ስለነበርኩ ለአራት ቀናት ሂደቱን ለመከታተል፣ የተጎዱ ሰዎችን ሆስፒታል ሂዶ ለመጎብኘት እና መረጃውን በትኩሱ ለመሰብሰብ አስችሎኛ።
ከሁሉም የማረሳዉን ሁለት ገጠመኞቼን አንስቼ ላቁም። የመጀመሪያው ከተማው በወታደር ተጥለቅልቆ ውጥረት በነገሰ ጊዜ የአገር ሽማግሌዎች ከየወረዳው የመጡ የሕዝብ ተወካዬችን ሰብስበው በአንደኛው ሽማግሌ ቤት በጥንቃቄ እንድመጣ ሰው ልከው አስጠሩኝና ሄደኩ። ቁጥራቸው ወደ ሃያ የሚጠጉ አዛውንቶች ተሰብስበው ጠበቁኝ። ጠዋት ሁለት ሰዓት የጀመርን እስከ ቀኑ አሥር ሰዓት ድረስ እያንዳንዳቸው ሽማግሌዎች የሕዝቡን ብሶት በዝርዝር ታሪክ እያጣቀስ በሚመስጥ መልኩ አወጉኝ። እኔም በጥያቄ ላይ ጥያቄ እያከልኩ ለስምንት ሰዓታት ውይይታችንን በድምጽ መቅጃ ቀዳሁት። ወደመጨረሻ ሰዓት የድምጽ መቅጃውን የያዘው እጄ ይንቀጠቀጥ ነበር።
ሁለተኛው የማይረሳው ትውስታ የወላይታ ሕዝብ መንግስት አዳቅሎ በፈጠረው ቋንቋ ልጆቻችን አይማሩም። ትምህርቱ በአማሪኛ መሰጠቱ መቀጠል አለበት የሚል ነበር። ግጭቱን ተከትሎ ወጥረቱ ሲከር አንድ ምሽት መለስ እራሱ መጥቶ የአካባቢውን ሹማምንት እና የአገር ሽማግሌዎችን ሰብስቦ እረዥም ውይይት አደረገ። ሕዝቡ ከአቋሙ ስንዝር ፍኔክች እንደማይል ሲያውቅ ወጋጎዳ ቋንቋ እንዲወገድ እኩለ ሌሊት አካባቢ ከሽማግሌዎቹ ጋር ተስማሙ። ይህ ብስራት ሂደቱን በጉጉት ሲጠባበቀ ላመሸው የወላይታ ሕዝብ ይፉ ተደረገ። በዚህ ወቅት እንደገና ከተማዋ በእልልታ፣ በጭፈራ፣ በደስታ ለቅሶ ተናወጠች። መንገዶች በድል አድራጊነት በሚጨፍሩ ወጣትች ተሞላ። የአገር ሽማግሌዎቹ በአንድ ሆቴል ተሰብስበው ፌሽታ ሆነ። እኔም እነሱ ያሉበት ሆቴል ተጠርቼ ሌሊቱን ሙሉ በደስታ አብረን ጨፈርን፣ በላን ጠጣን። ወጋጎዳ ቋንቋም፤ የሃሳቡ አፍላቂዎችም በየተራ አፈር ለበሱ። የወላይታ ሕዝብ ከነ ጨዋነቱ እና ጸጋው አለ። ይኖራልም።
Filed in: Amharic