>
5:14 pm - Wednesday April 20, 8129

አዲስ አበቤ አለሁ ብለሻል፤ ተበልተሽ አልቀሻል!!! (አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

አዲስ አበቤ አለሁ ብለሻል፤ ተበልተሽ አልቀሻል!!!

አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

*… እነ ዐቢይም ብልጭልጭ ነገር እያሳዩ የአዲስ አበባን ሕዝብ አፍዝዘውና አደንዝዘው ጥሬ ቆርጥሞ ለዘመናት በመቆጠብ የገነባውን ኮንደሚንየም ቤቱንና የከተማውን መሬት እየዘረፉት እንዲሁም ቤቱን እያፈረሱ እንደቆሻሻ እየጠረጉት ይገኛሉ.. !!!
 
እነኝህ ሰዎችማ እውነትም እንዳሉት ቁማሩን ተክነውበት የለም እንዴ??? የኦሕዴድ ጎጋዎች እንኳ ሰው ሆነው እንዲህ አፍዝዘውና አደንዝዘው ጭራሽ ከፊሉን ሕዝባችንንም ደጋፊያቸው አድርገው እንዲህ በነፍስ በሥጋችን ይጫወቱብን??? እጅግ በጣም ያሳዝናል!!!
“እችም የኔ እችም የኔ!” የሚባል በካርታ የሚጫወቱት የቁማር ጨዋታ ታውቃላቹህ አይደል? ልጁ ሦስት ካርታዎች አንዷን ያሳያቹህና ዓይናቹህ ላይ እንዴት አድርጎ እንደቀየራት ሳታውቁት “እሷ ናት!” ብላቹህ ገንዘባቹህን ስታስቀምጡ እሷ ሳትሆን ትቀርና ገንዘባቹህን ትበላላቹህ፡፡ ገንዘባቹህን ተሞልጫቹህ እያረራቹህ ትሔዳላቹህ!!!
እነ ዐቢይም ብልጭልጭ ነገር እያሳዩ የአዲስ አበባን ሕዝብ አፍዝዘውና አደንዝዘው ጥሬ ቆርጥሞ ለዘመናት በመቆጠብ የገነባውን ኮንደሚንየም ቤቱንና የከተማውን መሬት እየዘረፉት እንዲሁም ቤቱን እያፈረሱ እንደቆሻሻ እየጠረጉት ይገኛሉ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን የአዲስ አበባ ሕዝብ ፈጽሞ ሊነቃና በህልውናው እንደመጡበት ተረድቶ የግድ ወደ የሞት ሽረት ትግል መግባት እንዳለበት፤ ይህ ካልሆነ በስተቀር ግን ፈጽሞ ሊያስቆማቸው እንደማይችል ሊረዳ አልቻለም!!!
እነ አቶ በቅዠት አሻግሬ (አቶ ዐቢይ አሕመድ) ባዶ ስፍራ ላይ መብራት አብለጭልጨውና ድንጋይ አንጥፈው “ቢሊዮን ብር ጨረሰ!” እያሉ ሲያጭበረብሩትና ሲዘርፉት እየተታለለ አብሮ ሲጨፍርና ሲያደንቅ እነሱ ግን አሁንም የአዲስ አበባ ሕዝብ በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ ለዓመታት ቆጥቦ የገነባውንና ከዛሬ ነገ ይሰጡኛል ብሎ በተስፋ ሲጠብቀው የኖረውን 21 ሽህ የኮንደሚኒየም ቤቱን ለሦስተኛ ጊዜ ከባለቤቱ ከአዲስ አበባ ሕዝብ ዘርፎ ወይም ነጥቆ በልማት በተነሡ ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው ስም ከተለያየ ስፍራ ላስመጣቸው በሽዎች ለሚቆጠሩ ካድሬዎቹ አድሎታል፡፡ ይሄንንም አቶ ታከለ ኡማ በቀደም ለታ በግልጽ “21 ሽህ የኮንደሚኒየም ቤቶችን በልማት ለተነሡ ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው ሰጥተናል!” ሲል ሰምታቹህታል!!!
“ለልማት ተነሡ!” የተባሉ ገበሬዎች ግን ከወሬ ውጭ ምንም የደረሳቸው ነገር እንደሌለና በስማቸው እየተነገደ መሆኑን ከሰሞኑና ቀደም ብሎም በተደጋጋሚ በኅብረት ተሰብስበው  በኢሳት አቤቱታቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እወቁልን ብለዋል!!!
ከዚህ አሁን ከወሰዱት 21ሽህ ኮንደሚኒየም በተጨማሪ ባለፈው ሀጫሉ ከመገደሉ አስቀድሞ ሌላ 20 ሽህ ኮንደሚንየም ቤቶችን ዘርፈው ከናዝሬትና ከተለያዩ ቦታዎች ላመጧቸው የኦሕዴድ አመራሮችና ካድሬዎች በማደላቸው ሕዝቡ ሲቆጣ የሕዝቡን ቁጣ ለማዳፈን ሀጫሉን ገደሉትና የሆነው ሁሉ እንዲሆን አደረጉ፡፡ እንዳሰቡትም አዳፍነው አስቀሩት፡፡ ማንም ተመልሶ ይሄንን ለማንሣት የደፈረ አልነበረም!!!
አሁን ደግሞ የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ ለመቀየር ላላቸው ዓላማ ሽመልስ አብዲሳ  “በሕገወጥ መንገድም ሕዝባችንን እያስገባን እያሰፈርን ነው!” እንዳለው ሁሉ ይሄንን ሁሉ ቤት ዘርፈው ለካድሬዎቻቸውና ለወገኖቻቸው ሲሰጡ ሕዝቡ ቁጣውን እንዳያሰማ ገና ያልተጠናቀቀ ፕሮጀክት “የእንጦጦ፣ የሸገር መናፈሻ መዝናኛ!” እያለ በጩኸት በማደናቆር እንደምታዩት ሕዝቡን በነፍስ በሥጋው እየተጫወተበት ይገኛል!!!
ለነገሩ ሕዝቡስ ቢሆን የሚያስተባብረውና የሚያነቃንቀው አካል ሳይኖር እንዴት ብሎ የሚጠበቅበትን በማድረግ ይጋፈጣቸውና መብቱንና ጥቅሙን ያስከብር??? እንዴት ብሎ ይፋለማቸው??? እነ እስክንድርንስ ያሰሯቸው ለዚህ አይደል??? ሕዝቡን እንዳያስተባብሩትና ለተቃውሞ ወጥቶ መብቱንና ጥቅሙን እንዳያስጠብቅ ለማድረግ አይደል ያሰሯቸው??? ደግሞም እንዳሰቡት አዲስ አበባን በሕገወጥም በምንም ብለው በእጃቸው አስገብተው እስኪያረጋግጡ ድረስ አይፈቷቸውም!!! ሌላ ታዲያ ማን ያስተባብረው ማን ያነቃንቀው ሕዝቡን???
ሌሎቹንማ እያያቹሃቸው እኮነው ነገሩ ጋል ሲል ለማስመሰል የሆነ የሆነ ነገር አውርተው ሕዝቡ “በቃ ጉዳዩን ይዘውልናል!” አስብለው ያቀዘቅዙትና ከማግስቱ ጀምሮ ግን የሉም፡፡ ብትጠሯቸው እንኳ አይሰሙም፡፡ ኢዜማ ከሀጫሉ መገደል አስቀድሞ ለተዘረፈው ኮንዶሚኒየም መግለጫ በማውጣት ጭምር ኮንዶሚኒየም መዘረፉን በመግለጽና ተቃውሞውን በማሰማት ምን ያህል ቤቶችና የት ቦታ እንደተዘረፉ በሚገባ ካረጋገጠ በኋላ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚያደርግና ሕዝቡን አነቃንቆ የተፈጸመው ስሕተት እንዲስተካከል እንደሚያደርግ ቀባጥሮ እንደነበረ ታስታውሳላቹህ፡፡ አብንም እንደዚያው በተመሳሳይ ሰዓት ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ መግለጫ አውጥቶ ቀባጥሮ እንደነበረ ታስታውሳላቹ፡፡ ዛሬ ላይ አገዛዙ ሌላ ተጨማሪ ዝርፊያ ፈጽሟል እነሱ ግን የሉም!!! እነኝህ የአገዛዙን ጥቅም አስጠባቂ ቡችሎችና አጫዋቾች ኢዜማና አብን ያኔ እንዲያ ያሉትም ሕዝቡን “በቃ ጉዳዩን ይዘውልናል!” አሰኝተው ለማቀዝቀዝና ለማዘናጋት እንጅ ኢዜማም ሆነ አብን ለሕዝቡ በማሰብ፣ ከሕዝብ ጎን ቆመው የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ለመታገልና ዋጋ ለመክፈል እንዳልሆነ ይገባቹሃል ብየ አስባለሁ!!!
እንደምታዩት አሁን ባለው ሁኔታ እዚህ ሀገር ውስጥ ሆኖ ሕዝቡን በማስተባበርና በማነቃነቅ የአዲስ አበባ ሕዝብ ዝርፊያውንና ወረራውን በማስቆም ጥቅሙንና መብቱን እንዲያስከብር ለማስቻል ይሄንን ኃላፊነት መወጣት የሚችል አካል የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ከዳያስፖራው በአስቸኳይ የሆነ ግብረኃይል ተቋቁሞ ሕዝቡን መምራትና ማነቃነቅ እንዳለበት ለዳያስፖራው ጥብቅና አስቸኳይ ማሳሰቢያየን ማቅረብ እወዳለሁ!!!
አገዛዙ ይባስ ብሎ ከዚህ ዝርፊያውና ወረራው በተጨማሪም ከየካ እስከ ጉለሌ ያሉ ክፍለ ከተማዎችን ከፊል ከፊል ክፍላቸውን በመውሰድ ዙሪያዋን አዲስ አበባን ከሰላሣ በላይ ወረዳዎችን ኦሮሚያ ወደሚሉት ከልሏል፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ይሄ ምን ማለት እንደሆነና ምን ዓይነት አሳር መከራ እየጠበቀው እንደሆነ ፈጽሞ ሊገባው አልቻለም!!!
እባካቹህን ዳያስፖራዎች አድርባዩ፣ ቅጥረኛው፣ ተደማሪው፣ ተለጣፊው፣ ተነጣፊው፣ ተደጋፊውና ምናምንቴው ሁሉ እንዳይገባባቹህ ተጠንቅቃቹህ አስተዋዮቹ፣ ብልሆቹ፣ ጽኑዎቹ፣ እውነተኞቹ፣ ቆራጦቹ፣ ቁርጠኞቹ ብቻ ፈጥናቹህ ተመራርጣቹህ የሆነ ግብረ ኃይል አቋቁሙና ተንቀሳቀሱ አነቃንቁንም???
እዚያው ባላቹህበት የሰላማዊ ሰልፍና የአድማ ጥሪዎችን በማስተባበር ከዚህም በላይ ሁኔታው ባስገደደውና በጠየቀው ነገር ሁሉ ለመብታችንና ለጥቅማችን አንባገነኖችንና ዘራፊ ሌቦችን ታግለን በመሠዋት ጭምር የሞት ሽረት ትግል በማድረግ መብታችንንና ጥቅማችንን ለማስከበር አነቃንቁን??? ፍጠኑ አትዘግዩ!!! ከዚህ ውጭ ምንም አማራጭ የለንም!!!
እነሱ በሕገወጥና በውንብድና መንገድ እንደዚህ በሰፊው እየተንቀሳቀሱ እኛ በሕጋዊ መንገድ ሔደን ልናስጠብቀውና ልናስከብረው የምንችለው መብትና ጥቅም አይኖርም!!! ዳኞችም፣ ገዥዎችም፣ የጸጥታ አካሎችም ሁሉም እነሱው ናቸውና!!!
Filed in: Amharic