>

ወላይታ እና አጤምኒልክ...!!! (ሳሚ ዘብሔረ ኢትዮጵያ)

ወላይታ እና አጤምኒልክ…!!!

ሳሚ ዘብሔረ ኢትዮጵያ
ይድረስ ሰሞኑን ስለወላይታ ለሚያቀረሹ የወላይታ ተቆርቆሪ ነን ባይ ጽንፈኞች…..
የወላይታው ንጉሥ ጦና አልገብርም ብለው አስቸገሩ፤ እንዲያውም የገበረውን ሀገር ሁሉ እየወጉ እንደገና እንዲከዳ ያደርጉ ጀመር፤ በዚህም ምክንያት ራሳቸው አጤ ምኒልክ በ1887 ዓ.ም ኅዳር 7 ቀን ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ወላይታ ጉዞ ጀመሩ፤ ከወላይታ የግዛት ወሰን ሾሊ የሚባለው ቦታ ሲደርሱም መልዕክተኛ ለጦና ላኩባቸው።
“ሰውንም አታስፈጅ፣ ሀገርህንም አታስጠፋ፣ ግብርህን ይዘህ ግባ” አሉ።
ንጉሥ ጦናም ምኒልክ ለላኩባቸው መልዕክት፤ “…ባገሬ ክርስቲያን አይገባበትም፤ ገፍተውም ከመጡ እዋጋለሁ እንጂ ለክርስቲያን መንግሥት አልገብርም…” ብለው መለሱ።
ፈረሰኛው የምኒልክ ጦርም እንዳያልፍ መሬቱን በሙሉ ጉድጓድ ብቻ አድርገው አስቆፈሩት፤ የምኒልክን ሠራዊት እንዲያውክም ሠራዊታቸው እንጨት እያሾለ በሜዳው ሁሉ ተከለበት። አጤ ምኒልክም እሄንን ድርጊት እንደሰሙ ራስ ሚካኤልን፣ ደጃዝማች ኃይለማርያምን፣ ፊታውራሪ ገበየሁንና ሊቀ መኳስ አባተን ጠርተው ሠራዊታቸውን ይዘው ጉድባውን እንዲያስደለድሉና የተተከሉትን ሹል እንጨቶች እንዲያስነቅሉ አዘዟቸው። የታዘዙትም ሥራቸውን ከጨረሱ በኋላ ምኒልክም ሠራዊታቸውን እየመሩ ኅዳር 23 ቀን ቆንጦላ ሰፈሩ።
ምኒልክ ቆንጦላ እንደሰፈሩ እጅግ በጣም የበዛ የጦና ሠራዊት ሊዋጋ መጣ። ምኒልክ ጦሩን ከማዘዛቸው በፊት ጥቂት ሰዎች ወጥተው ጦርነት ገጠሙ። በዚያም ከምኒልክ ሠራዊት 75 ሰዎች ተገደሉ። ምኒልክ እሄን እንደሰሙም
 ሊቀ መኳስ አባተና በጅሮንድ ባልቻን ጠርተው ተዋጊውን አባረው የእነሱን ሠራዊት እንዲመልሱ አዘዟቸው።
አባተና ባልቻም የጦናን ሠራዊት አባርረው የምኒልክ ሠራዊትን ወደ ሰፈር መለሱ።
ይህ ከሆነ በኋላ ምኒልክ በሰላም ተጉዘው ከጦና ዋና ከተማ ደልቦ ላይ ኅዳር 27 ቀን ሰፈሩ። ጦና ግን ከዚያ ቦታ አልነበሩምና ካሉበት ድረስ መልእክተኛ ልከው “…ሀገር ከጠፋ በኋላ ሊያቀኑት ያስቸግራል፣ ገንዘብም በግድ ካልሆነ በቀር በፈቃድ የሰጡት አያልቅም፣ ሀገርህን አታስጠፋ፤ ግብርህን ይዘህ ግባ…” ብለው ላኩባቸው። እሳቸው ግን አልገባም ብለው ቀሩ።
አጤ ምኒልክ ዳሞት ተራራ ላይ ወጥተው ጦራቸውን ካሰለፉ በኋላ በለው ብለው አዘዙ። የታዘዘውም ሠራዊት በአንድ ጊዜ ወላይታን በሙሉ ያዘ። ጦናም ከወላይታ ወጥተው ወደ ቦረዳ ሸሹ። የምኒልክም ሠራዊት ተከታትሎ ጦናን በጥይት አቁስሎ ያዛቸው። ጦናም ተይዘው ምኒልክ ፊት ከቀረቡ በኋላ ምኒልክ “#አወይ #ወንድሜ #እንዲያው #በከንቱ #ሕዝብ #አስጨረስክ” ብለው ወቅሰው የቆሰለው ቁስል እንዲታጠብና እንዲታከም አደረጉ። ሠራዊቱም ብዙ ከብት ማርኮ ነበርና የተማረከው ከብት በሙሉ ለባላገሩ እንዲመለስ አዋጅ አስነገሩ። የባላገሩ ከብት እስቲመለስና ጦናም እስቲያገግሙ ጥቂት ቀናት ከርመው ጦናም ካገገሙ በኋላ የወላይታን ሕዝብ ሰብስበው “#እንግዲህ #ወዲያ #የሚያስተዳድርህ #ልጄ #ወዳጄ #ጦና #ነውና #ተገዛለት #አውቆ #ሳይሆን #ሳያውቅ #እኔን #የበደለ #መስሎት #ሰው #አስጨረሰ #እንጂ #ከድሮም #ከአያቶቻችን #ቂም #የለንምና #መልሼ #እሱኑ #ሾሚያለሁ ከእንግዲህ ወዲያ ብታምፅ በራስህ እወቅ ግብሬን አግባ…” የሚል አዋጅ አስነግረው የወጓቸውን ጦናን ሾመው ጥር 11 ቀን አዲስ አበባ ገቡ።
ምኒልክ ከነበራቸው ጠባይ ዋና የዲፕሎማሲ ዘዴ ስለነበር አልገብርም ያለውን ዋናውን ባላባት ሲማርኩ በቦታው ላይ የሚሾሙት ተማራኪውን ባላባት ወይም የተማራኪውን ልጅ ነበር ፤ ያለዚያም ሕዝቡን ሰብስበው ሕዝቡ የመረጠውን ይሾሙታል፤ ምኒልክ የሀገሩን ተወላጅ በሀገሩ ላይ ቢሾሙም ተሿሚው የሚሾመው ለውስጥ አስተዳደር ብቻ ነው፤ ጠቅላላ የጦሩ ኃይል በምኒልክ እጅ በመሆኑ ሌላም የቀኝ ገዥ እንዳይገፋ ለሀገሩ ጥበቃ የጦርን ኃይል ለማዘዝ የሚሾመው ከመሀከለኛው መንግሥት ነበር። ምኒልክ ለአስተዳደር ከሾሙት ባላባት ላይ በየዓመቱ የሚገብረውን ግብር ይፈልጋሉ እንጂ ተሿሚው ሕዝብ ካልበደለ በስተቀር በውስጥ አስተዳደሩ አይገቡበትም ነበር።
እስከ ሩዶልፍ ሐይቅ ድረስ የተጓዘው ዊልቤ በ1893 ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፉ “…በጠረፍ ያሉት ሰዎች ምኒልክ ጥሩ ሰው እንደሆነ ያውቃሉ፤ ምኒልክ ሁሉም ሰው በኃይማኖቱ ይደር ስላለና በሕዝቡ መሀል አድሎና የሀይል ሥራ ስለማይሠራ ይወዱታል፤ “….ሲያወሩም እንደሌሎቹ ንጉሦች መስሎን ሸሽተን ነበር በኋላ ይቅርታ እየጠየቅን ተመለስን ያኔ ተታለን ነበር…” ይላሉ። አሁን ግብራቸውን እየገበሩ በሰላም ይኖራሉ…” በማለት ስለ ወላይታ ሕዝብ ጽፏል።
በጅሮንድ ተክለሐዋርያትም በሕገ መንግሥት ንግግራቸው
“አጤ ምኒልክ በቅድመ አያቶቻቸው መንግሥት በሙሉ ኢትዮጵያ ለመግባት በቁ፤ ገብተውም ኦሮሞ ቀምቶን የነበረውን የጥንት ግዛቶቻችንን መልሰው እጅ አደረጉና ኦሮሞውንም ከሸዋው ጋር አስማተው አዛምደው በትዳር አንድ ሕዝብ አደረጉ” ብለዋል።
ጸሐፊ ትእዛዝ ገብረስላሴም ሲተርኩ “…ከጥንት የኖረ በሸዋ ብርቱ ሥርዓት ነበረ፤ ጥፋት የተገኘበት ሰው ገንዘቡን ተወርሶ እጁን ታስሮ መሬቱ ይሸጥ ነበር፤  ሰው የገደለም እራሱ ቢያመልጥ ዘመዱ እስተ ሦስት ትውልዱ ከመሬቱ ይነቀል ነበር፤ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ግን የፍትሃ ነገሥት ሥርዓት ተመልክተው በ1883 በጥር 23 ቀን ከዋያት በመለስ አዋሽ ድረስ ያለውን የጋሻ መሬት ሁሉ እንደመንዝ ርስት አድርጌልሃለሁ፤ ምንም ብታጠፋ ገንዘብህ ይወረስ እንጂ መሬትህ አይነቀል፤ ብለው አዋጅ ነገሩ፤ ካሉ በኋላ በሌላ ምዕራፍ ደግሞ… ” በሸዋ የኦሮሞ ባላባት የተነቀለበትስ ምክንያት እንደምነው ቢሉ ከአጤ ሣህለሥላሴ ጀምሮ ሀገር ሲቀና የክርስቲያኑን ሀገር እየወረረ ቤተክርስቲያን እያቃጠለ በኦሮሞው ሀገር የተሾመውን አላስገዛ እያለ እየተዋጋ ክርስቲያኑን እየተዋጋ ርስቱን ተነቅሎ ነበር፤ ደግሞም ሀገሩ መቅናት ከጀመረ በኋላ የኦሮሞው ባላባት ጉልበት እያነሰው የአባቱን መሬት ለአማራው እያወረሰ ይኖር ነበር።
 አጤ ምኒልክ ግን ልጁ ተነቅሎ መቅረቱ አሳዝኗቸው “እኔ  የአባቴን ሀገር ስገዛ ባላባትም ልጁም ተነቅሎ አይቅር” ብለው ከአባቱ መሬት ከአባቱ መሬት ከአማራ ተካፍሎ አዘዙለት” ብለዋል።
ካዎ ጦና በአዲስ አበባ ካረፉ በኋላ በባለወልድ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሞ እቴጌ ጣይቱ ሀውልት አሠሩላቸው፤ መካነ መቃብሩም በአዲስ አበባ ከሚገኙ 440 አንዱ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ለጎብኚዎቹም ክፍት ነው።
ምንጭ:-
ጳውሎስ ኞኞ – አጤ ምኒልክ
*********************//*****************
እንግዲህ እኚህን ንጉሥ ነው ከሲቪል ኮሌጅ ከአስረኛ ክፍል እየተመረቀ ዶክተር ነኝ የሚል የሀሰት ምሁር ነኝ ባይ ጽንፈኛ ግማሹ በሆዱ እየተደለለ ግማሹ ያለበትን የበታችነት ስሜት በሰፊው ሕዝብ ላይ ለማስተላለፍ እየተነሳ የውሸት ትርክት ሲያስተገባ የምንሰማው ምንም አርቀህ ብትቀብረው ታሪክ ታሪክ ነው።
ታላቁ ጥቁር እኛ ታሪክህና ሥራህ የገባን እናከብርሃለን!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic