>

“ጠብቁ በሃይማኖት ነው የሚመጣብን...!!!” ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

“ጠብቁ በሃይማኖት ነው የሚመጣብን…!!!” ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

* ክቡርነትዎ እንደዚህ ያለ ሰቅጣጭ አደጋ እንደሚመጣ ካወቁ ለመከላከሉ ምን አሰነፈዎ? ወይስ ለቤተክርስቲያኒቷ ያለዎት ጥላቻ …?!?
አባይነህ ካሴ

 


 

ሰሞኑን በኦርቶዶክሳውያን ላይ እየደረሰ ስላለው የተቀናጀ የተጠና እና የታቀደ ጥቃት በተመለከተ (በእመቤታችን ተአምር መኾኑን ያዙልኝ) ጥብቅ የኾኑ ምስጢሮች እያፈተለኩ እየወጡ መኾኑን በዘመኑ ያለን ሁሉ በዐይናችን ሥር እያለፈ ነውና ምሥክሮች ነን፡፡ ፊታቸውን ጸፍቶ አፋቸውን ከፍቶ መንፈስ ቅዱስ ከሚያናግራቸው ሰዎች መካከል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አንዱ ናቸው፡፡ ደጋግሞ ያዳልጣቸዋል፡፡ እያመለጣቸው መኾኑን ልብ እንበል፡፡ ለምን ያመልጣቸዋል? ከተባለ ወድደው ሳይኾን ተገድደው እንደኾነ እንመን፡፡ ይህን ያደረገ እግዚአብሔር ነውና፡፡
እንግዳ ባይኾንም ዛሬም ለማስታወስ የተገደድነው ከዚህ ቀደም ካነሣናቸው በተጨማሪ አሁንም የሚከተለውን ቃል ከአንደበታቸው ስለሰማነው እንጅ ተንብየን አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችን (መያድ) ተወካዮች ሲያወያዩ፡-
“ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ከኦሮሚያ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በዚያኛው አዳራሽ ስብሰባ ነበረን፡፡ ጠብቁ በሃይማኖት ነው የሚመጣብን ብዬ ነግሬአቸዋለሁ፡፡ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ቪድዮው አለ፡፡ አይ ኖው በሃይማኖት እንደሚመጣ ዐቀዋለሁ፡፡ ግን በሃይማኖት እያንዳንዱ ቦታ ገብቼ ይህን ልከላከል አልችልም፡፡” ብለዋል፡፡
እውን ጥቃት እንደሚመጣ ያወቀ መንግሥት እንዲህ ነበር የሚያደርገው?
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከአምስት በላይ ጥቃቶች ሲሠነዘሩ የት ነበር?
ዝምታው ይበለው ከማለት የመነጨ መኾኑ ነውን?
 በወርኀ ጥቅምት እና በሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. ኹለት ሰፋፊ ጥቃቶች በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ተፈጽመዋል፡፡ በኦሮሚያ፣ በሐረሪ እና በድሬዳዋ የታለፈው መከራ እንዴት ይረሳል?
 የመስቀልን እና የጥምቀትን በዓልን ለማክበር የታለፈው መከራ እና የጥይት ሩምታ በቀላሉ የሚታይ ነበርን? ይህ ደግሞ በሰበብ አስባቡ ከአዲስ አበባ ከተማ ይጀምራል፡፡
 በሰሜን ኦሞ አካባቢ በተደጋጋሚ የተፈጸመው ከፕሮቴስታንታውያን የመንግሥት ባለሥልጣናት የደረሰው ጥቃት መቼም ሊዘነጋ የማይችል መከራ ነው፡፡
 በሆሳዕና አሁንም በፕሮቴስታንታውያን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቤተ ክርስቲያን የደረሰባት መገፋት በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡
 በስልጤ ዞን በጽንፈኞች የተፈጸመው ጥቃት፡፡ ከሚጠቀሱት ናቸው፡፡
እርሳቸው ከጠቀሱት አንድ ዓመት ተኩል በላይ የሔድን እንደኾነ ደግሞ ከሶማሌ እስከ ሲዳማ ከዚያም እስከ ጅማ ወደኾነው ዘግናኝ የስቃይ ውቅያኖስ እንገባለን፡፡
የሞቱት ክርስቲያኖች የተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት ተቋምን የማጥፋት ፕሮጀከት አካላት መኾናቸውን አሳይተውን አልፈዋል፡፡ ጥያቄው መንግሥት እንደዚህ ያለ ሰቅጣጭ አደጋ እንደሚመጣ ካወቀ ለመከላከሉ ምን አሰነፈው?
“መንግሥታችን” በማያወላዳ ቃል የደረሰውን ሁሉ ጥቃት እንደሚመጣ አስቀድሞ እንደሚያውቅ ነግሮናል፡፡ እያወቀ አለመከላከሉ  ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ጥልቅ ጥላቻ ያመለክታል፡፡
Filed in: Amharic