>

የዜጎች መገደልና መፈናቀል እንዲቀጥል እያደረጉ ያሉ የባለስልጣናት መርዝ ቃላት.. !!! (ብርሀኑ ተክለያሬድ)

የዜጎች መገደልና መፈናቀል እንዲቀጥል እያደረጉ ያሉ የባለስልጣናት መርዝ ቃላት.. !!!

ብርሀኑ ተክለያሬድ

1. “ሚሊዮኖች ቢሞቱም ኢትዮጵያ አትፈርስም”
ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን መፈክር ተከትሎ ብዙ ባለስልጣናት “ኢትዮጵያ አትፈርስም” እያሉ ሲደጋግሙት የሚውሉት መፈክር ነው በእርግጥ ሀገር እየመራን ነው የሚሉ ግለሰቦች ሀገራችን አትፈርስም ቢሉ ክፋት የለውም። ይሁንና ዜጎች ራሳቸው ባቀኑት ሀገርና ዋጋ በከፈሉባት ሀገር በአሰቃቂ ሁኔታ  እየተከታተፉ ሲሞቱና ሀብታቸው ሲወድም በዝምታ እየተመለከቱ አንዳንዴም በእሳቱ ላይ ቤንዚን እየጨመሩ “ይህ ሁሉ ቢሆንም ኢትዮጵያ አትፈርስም” ማለት ግን ከፌዝም በላይ ፌዝ ነው።
ለመሆኑ አትፈርስም የተባለችው ኢትዮጵያ ቤታቸው ለፈረሰባቸውና መሄጃ አጥተው ለሚቅበዘበዙ ግፉአን ምናቸው ናት? አትፈርስም ብለው ፎካሪዎቹስ ለመፍረሷ ከነሱ በላይ አስተዋፅኦ እያደረገ ያለ ሰው አለመኖሩን ተረድተው ይሆን? የ”ሰባበርናቸው” ትርክት ባለቤቱ ሽመልስ አብዲሳ “ኢትዮጵያ ኢያሪኮ አይደለችም በጩኸት አትፈርስም” ሲል ከመስማት በላይ ፌዝስ ከወዴት ይመጣል? ኢትዮጵያ አትፈርስም እየተባለ ስንት አማራዎች ይገደሉ?ስንት ኦርቶዶክሳውያንስ ይጨፍጨፉ? ስንት አብያተክርስቲያናትስ ይንደዱ?
2.ኦሮሞ ኦሮሞን አይገልም
የኦሮሞ ፖለቲከኞች(ስልጣን ላይ ያሉትን ጨምሮ) በተለያዩ አጋጣሚዎች በንግግራቸው ደጋግመው የሚያነሱት ከወንድማቸው ጋር’መታረቂያ’ ቃል ነው። ይህ ቃል በየቦታው እየተደነቀረ ብዙዎችን አሳርዷል፤ ወዲህ መግደል መሸነፍ ነው ወዲህ ደሞ ኦሮሞ ኦሮሞን አይገልም ማለት እርስ በእርሱ ከመጣረሱም በላይ ትርጉሙ ግድያን ይጠራል።
ለመሆኑ ኦሮሞ ኦሮሞን አይገልም ማለት ሌላውን መግደል ይችላል ነው? ኦሮሞን አትግደል የተባለውስ ሌላውን እንዲገድል ልዩ ፈቃድ እየተሰጠው ይሆን?
 
3.”ቶሎ ባናስቆመው ኖሮ…..”
ሁልጊዜም እጅግ ዘግናኝ የሆነ እልቂት ከተፈፀመ በኋላ የመንግስት ባለስልጣናት በሚዲያ መጥተው ይቅርታ ይጠይቃሉ ተጎጂዎችንም ያፅናናሉ ተብሎ ሲጠበቅ  አይናቸውን በጨው አጥበው”ቶሎ ባናቆመው ኖሮ ብዙ ጉዳት ይደርስ ነበር” ብለው በተጎጂዎች ቁስል እንጨት ይሰዳሉ።
ከሌሊቱ 6:00 የተጀመረ ማቃጠልና መግደል እስከ ቀኑ 11 ሰአት ድረስ ቆይቶ፣ ገዳዮቹ አስከሬን እንኳን ለማንሳት ሳይፈቅዱ እስኪደክማቸው ድረስ ሲገድሉና ሲያቃጥሉ ቆይተው “ባንከላከለው ኖሮ….” ማለት ፌዝ አይሆንም?
…………………………………………………………
እንደ መንግስት ምሩን!!!
አልያም ተዉን!!!
Filed in: Amharic