አፋር!…
ጌታቸው አበራ
በዚህ ርዕስ ግጥም የጫርኩት ልክ የዛሬ 27 ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ፣ በዚያ ቀውጢ የወያኔ ዘመን፣ የአገር ክብርና ፍቅር መገለጫ የሆነችውንና በስሟ ስንትና ስንት መስዋዕትነት የተከፈለባትን ክቡሯን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ፣ የወያኔው መሪ መለስ ዜናዊ “ጨርቅ” ብሎ በማንኳሰስ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አእምሯችን ፈጽሞ ያልተዘጋጀበትን ጸያፍ ነገር ውስጣችን ከቶ ለህመም የዳረገን ወቅት ስለነበረ፤ በዚያ የንዴትና የቁጭት ስሜት ውስጥ እያለን፣ የአፋሩ ሱልጣን አሊሚራህ በአንድ መጽሔት ላይ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ “የኢትዮጵያን ባንዲራ እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቁታል” በማለት ታሪካዊውን ጥቅስ እንደ መድሐኒት አቅምሰውን ከህመማችን ፈወሱን። በዚያ መንፈስ ነበር “አፋር” የምትለዋን ግጥም ለ ሱልጣን አሊሚራህ መታሰቢያነት በመስጠት የጻፍኩት (በወቅቱ ያገር ቤት ጎጆዬ በምትለዋ የግጥም መድበል ስብስብ ውስጥ ተካታ የታተመች ናት)። ዛሬ ከሃያ ሰባት ዓመታት በኋላ ካለችበት ያነሳኋት ደግሞ፣ በቅርቡ የአፋር ወገናችን ላይ የተፈጥሮ አደጋ ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት፣ ወገን ተረባርቦ የድጋፍ ምላሽ እንዲሰጥ የበኩሌን ጥሪ ለማስተላለፍና የአፋር ወገኖቻችንን በክብር በማሰብ ነው።
አፋር!
(ለሱልጣን አሊሚራህ)
ያገር አፈር ያገር ድንበር
የተፈጥሮ የባሕር በር..
አስከባሪ ባለአደራ
የቃል ባለውል፣ የሐቅ አውራ!
አፋር!
ልበ-ኩሩው ቆራጥ ደፋር!
የኢትዮጵያን መታወቂያ
ያንድነቷን ህያው መኩሪያ፣
ደማቅ ዓርማ ባንዲራዋን
አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን፣
..አጉል ጊዜ ያፈራቸው
ሲያናንቁት፣ ሲያጣጥሉት፣
“ጨርቅ” ብለው ሲኮንኑት..፣
አፋር ጀግናው..!
አይቶ፣ ሰምቶ፤ ዐይኑ ቀልቶ፣
በእልህ ሲቃ ተቆጥቶ፣
እምቢኝ አለ! አፋር ኩሩ፣
ተቆርቋሪው ለአገሩ!
ባፋር በረሃ በንዳዱ
በጀግናው ምድር በዚያው ባንዱ፣
ባንዲራችን ለመለመች
ኢትዮጵያ በአፋር ኮራች፤
እረፍት የለሽ ዘላን ዟሪ
ካገር አገር ተሽከርካሪ፣
የኢትዮጵያ ድንበር ቃፊር
ላንድነቷ የዘብ አጥር፣
ባለግመል ባለካራ
ልበ-ሙሉ የጀግና አውራ!
የጭንቅ ዘመን ልጅ የኢትዮጵያ
የአዲስ ታሪክ ሃሌ ሉያ
አፋር!
ልበ-ኩሩው ቆራጥ ደፋር!