>

አለቃ አያሌው ታምሩ- ደማቁ ፀሐይ (አባይ ነህ ካሴ)

አለቃ አያሌው ታምሩ- ደማቁ ፀሐይ

አባይ ነህ ካሴ

* …ወጣቱን ትውልድ አዳሪ ትምህርት ቤት ሰብስበው እያስተማሩ ነው፡፡ እነዚህ ነገ ሲወጡ ጉድጓድ ውስጥ ያደገ የውሻ ግልገል መሆናቸው ነው፡፡ አንዳች ክፉ ነገር ቢመጣ እንኳን ደሙን የሚያፈስልዎ ውኃ የሚረጭልዎ አያገኙም!!!” 
ዛሬ ነሐሴ ፲፬ ሊቁ ሐዋርያ አለቃ አያሌው ታምሩ ካረፉ ፲፫ኛ ዓመት ኾነ። ሊተካቸው ቀርቶ ሊከተላቸው የቻለ እስካሁን አልተገኘም። በጥቁር ካባቸው ኾነው በቤተ ክህነቱ ቅጽር ብቅ ሲሉ የግል ብርቱ ወግ የያዘው ሁሉ አፉን ይለጉማል። ጸጥታው ኃይለኛ ዐውሎ ነፋስ ያለፈ ይመስላል። የተቀመጠው ተነሥቶ የቆመው እጅ ነሥቶ የቀረበው ጉልበት ስሞ መስቀላቸውን ተሳልሞ በረከታቸውን ይቀበላል። አቤት አለቃ ልካቸው ወደ ደመና ከፍ ያለ ነበር።
ለቤተ ክርስቲያን ያወጡላት ልዩ የቁልምጫ ስም አላቸው። ስንዱ እመቤት ይሏታል። ዛሬ ሁሉ ተቀብሎላቸዋል። በእሷ እና በኢትዮጵያ ድርድር መግደርደር የለም። አጼ ኃይለ ሥላሴን እንኳን መገሰጽ ቀርቶ ቀና ብሎ ማየት በማይቻልበት ጊዜ የተናገሩት (ቃለ ትንቢትም ነው) ይህን ያሳያል። ወንድማችን መልካሙ በየነ እንደጻፈው።
“…ጃንሆይ! ሃይማኖት እየጠፋ ነው፡፡ ጀሰዊቶች በገቡበት አገር ሁሉ ያልተገለበጠ መንግሥት፥ ያልተናወጠ አገር…ያልተለወጠ ሥርዓት ያለመኖሩን ከእኔ የበለጠ ጃንሆይ ያውቃሉ፡፡ ሁሉ እየተነሳ ኃይለ ሥላሴ ይሙት…ኃይለ ሥላሴ ይሙት እያለ የአባቱ ማሳረፊያ ቢያደርግዎ ምንም የሚጠቅም ነገር የለውም፡፡
ወጣቱን ትውልድ አዳሪ ትምህርት ቤት ሰብስበው እያስተማሩ ነው፡፡ አስተማሪዎች ደግሞ የሌላ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ የራሳቸውን ታሪክ፥ እምነትና ባህል ከሚነግሩት በቀር የራሱን ታሪክ የሚያስተምረው የለም፡፡ እነዚህ ነገ ሲወጡ ጉድጓድ ውስጥ ያደገ የውሻ ግልገል መሆናቸው ነው፡፡ አንዳች ክፉ ነገር ቢመጣ እንኳን ደሙን የሚያፈስልዎ ውኃ የሚረጭልዎ አያገኙም።”
በ፲፱፻፵፰ ዓ.ም. መስከረም ፲ ቀን በተከበረው የተቀጸል ጽጌ በዓል ላይ በንጉሠ ነገሥቱ ፊት የተናገሩት፡፡
Filed in: Amharic