>

"ኬኛ!" - የአንዱ ስጋት የሌላው ተስፋ ...!!! (መስከረም አበራ)

“ኬኛ!” – የአንዱ ስጋት የሌላው ተስፋ …!!!

መስከረም አበራ
የአባይ ግድብም ቢሆን በቤኒሻንጉል ክልል ነው እየተገነባ ያለው፡፡ እናም እነዚህ ሰዎች በሃገራቸው ቋንቋ “ኬኛ” የማይሉበት ምን ምክንያት አላቸው? ሃይል መንጭቶ ሲሸጥም ልዩ ጥቅም ይገባናል ቢሉስ ህገ-መንግስት የሰጣቸውን መብት ማን ይከለክላቸዋል?
 
“የአማራ ሲሆን የአማሮ ሲሆን ነው የሚታይሽ? ” ለምትሉኝ ወገኖቼ ዘረኝነትን የትም ቦታ ሳየው ያስጠላኛል፣ እንዳስጠላኝ ደግሞ ብቸኛዋን ጉልበቴን -ብዕሬን አነሳለሁ! ዘረኝነት ሁሌም፣ የትም ፣ማንም ላይ ሳየው ያስጠላኛል። ችግሩ  “አቅልለው ሲሉት አምጥቶ ቆለለው” መሆኑ ነው። የዘር ፓርቲ ያስጠላኛል ስል የዘር በተስኪያን ፣የዘር የኳስ ቡድን ፣የዘር ባንክ፣የዘር ሚዲያ፣የዘር እድር እቁብ ፣የዘር የፈተና ውጤት እየተግተለተሉ መግባታቸው ነው። የዘር ባንክ ድሮም ዛሬም ያስጠላኛል፣የዘር ሚዲያ የሩዋንዳውን መተራረድ ያስታውሰኛል ይቀፈኛል! ይሄው ነው……
ከትናንት በስቲያ አንድ ወዳጄ በውስጥ መስመር ስናወራ “ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ needየን  limite አድርጌ የቆጠብኳት ትንሽ ገንዘብ ነበረችኝ ‘ኬኛ’ ይሉኝ ይሆን?” ሲል መልዕክት ላከልኝ፡፡ትንሽ ከሳቅኩ በኋላ “አንተ ይህን ሳታረጋግጥ ነው እንዴ
ገንዘብህን የምትሰጠው? እምነት በሌለበት አደራ አለ እንዴ?” አልኩት፡፡ “ኧረ እኔ ለቤቴ ቅርብ ስለሆነ፣ደሞም ወረፋ ስለማይበዛበት ነበር ያስቀመኩት፤አሁንኮ “ኬኛ” ሲበዛ ሄጄ ለማውጣትም ስጋት ያዘኝ” ሲለኝ፡፡ “ሂድና ቁርጥህን እወቅ ፈጠሪ ይረዳሃል፤ባይሆን ስትጠይቅ ደገፍ ብለህ ቁም መልሱ ካዞረህ እንኳን ገንዘብህንም ራስህንም እንዳታጣ” ብየው ተሳስቀን ተለያየን፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋልና ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክን ሳስብ ራሴም አንድ ጉዳይ ገጥሞኛል፡፡ባፈው ወር ከአንድ ወዳጃችን ጋር የሆነ ነገር ተገበያይተን ገንዘቡን ባንክ እንደሚያስገባልን ተስማማን የባንኩን ስም ግን አልነገረንም፡፡ ከዛ በአካል ተገናኝነት ብሩን ሊያስረክበን ስንሄድ ገዣችን ወስዶ ወስዶ እዚሁ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ ዶለን፡፡የመሰለኝ ብሩን አውጥቶ በካሽ ሊሰጠን እና እኛ ደግሞ ወደ ምንገለገልበት ባንክ ወስደን የምናስገባ ነበር፡፡ይንኑ ለልጁ ስንነግረው “ግንኮ እዚህም አካውን አውጥታችሁ ብታስቀምጡ ችግር የለውም ጥሩ ባንክ ነው” አልን፡፡”አይ አይ እኛ የራሳችን ደምበኛ ባንክ ነው ማስቀመጥ የምንፍለገው አለ” ትዳሬ ፈጠን እና ቆፍጠን ብሎ! ልጁ ሲደነግጥ አየሁና(ደሞ ጥሩ ጓደኛችን ነው) እኔ በቀልድ ወደማለዘቡ ገባሁ፡፡
“አይ ምልህ እዚ ባንክ ኮ እናውጣ ስንል ማነው አውጭ ማነው አስወጭ እንዳንባል ስጋት ስላለን ነው” ብየ አሳቅኩትና፤እዚህ ማስቀመጥ እንደማንፈልግ ረጋ ብየ ነገርኩት፡፡”ካልፈለጋችሁማ ችግር የለም” አለ ቀናው እና ጨዋው ደምበኛችን፡፡በዚህ ተስማምተን ገንዘቡን አውጥቶ ሊሰጥን ሲል “ሞቼ ነው ቆሜ የእኛ ደምበኛ የማትሆኑት!” አለች መልከ መልካሟ የባንክ ሰራተኛ እየሳቀች፡፡ “ኧረ ተይ እኛ ሌላ ደምበኛ ባንክ አለን እባክሽ” አልኩኝ፡፡ “እኛን ስላላያችሁ ነው፤ ሌላ ቦታ የሄዳችሁት” ብላ ድርቅ፡፡ባለቤቴ ብስጭት! “አንፈልግም ካልን መብታችን እኮ ነው; ለምን እንገደዳለን?”አለ ከገባን ጀምሮ ብስጭት ብስጭት ብሎታል፡፡ “ተው እንጅ! እሷኮ ስራዋን ነው የምትሰራው፤ በቃ እኔ ላናግራት አንተ አረፍ በል” ብየ የምለውን አልኳት::ልትሰማኝ አልፈለገችም::
 ድርቅናዋ እርድና ነገር ስላለው እኔ ወደድኳትና “የበላይ አካል” እየተናደደም ቢሆን አካውንት ከፍቼ ብሩ አንድ ሁለት ቀን እንዲያድር አደረግኩ:: ለእሷ ስል እንጅ በሆነ ዘር የሚጠራ የቢዝነስ ተቋም ውስጥ ገንዘቤን የማስቀመጥ ፍላጎቱ የለኝም፡፡ ሶስት ቀን ሲሞላ ሄጄ ብሬን አወጣሁ፡፡ “ዋናው አካውንት መክፈትሽ ነው” አለችኝ ያች ደስ የምትል ደረቅ ልጅ ! “ግን ለምንድን ነው እንዲህ የጠላችሁን” አለችኝ፡፡ አይ ጥላቻ ሳይሆን ስጋት ነው-የ”ኬኛ ስጋት” አልኳት፡፡ “እንደምታስቡት ግን አይደለም” ስትለኝ፡፡ “ስም ብዙ ይናገራል-ይገፋል ይጠራል፤ የባንካችሁ ስም የሚጠራውም የሚገፋውም አለ” አልኳት፡፡ ዝም አለችኝ ፤ቻው ብያት ወጣሁ፡፡
ይህ የኬኛ ስጋት ብዙ ነው፡፡ በነጃዋር መንደር ተወስኖ የሚቀር ካሆነ በተለይ አሳሳቢም ነው፡፡በሃገራችን ግልገል እንትን አንድ፣ ግልገል እንትን ሁለት እየተባሉ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ግልገል አራት ነው አምስት ደርሰዋል፡፡ እነዚህ ማመንጫዎች የተገነቡት ሰዎች ተፈናቅለው፣ ህገ-መንግሰታችን በሸለማቸው የሆኑ ብሄረሰቦች የግል ግዛት ላይ ነው፡፡ የአባይ ግድብም ቢሆን በቤኒሻንጉል ክልል ነው እየተገነባ ያለው፡፡ እናም እነዚህ ሰዎች በሃገራቸው ቋንቋ “ኬኛ” የማይሉበት ምን ምክንያት አላቸው? የእጣኑን ዜና ሰምተው እዚህም ሰዎች “ማንህም እኛ ሳንፈቅድ በእኛ ሃገር ተገድቦ የመነጨ መብራት አብርተህ ራትህን መብላት ቀርቶ ሽንትህን አትሸናም” ያሉ ጊዜ ምን ሊውጠን ነው?ሃይል መንጭቶ ሲሸጥም ልዩ ትቅም ይገባናል ቢሉስ ህገመንግስት የሰጣቸውን መብት ማን ይከለክላቸዋል? የሃገር ሰው ሁሉ ደሞዝ ተቆርጦ የተሰራ ግድብ ዋናው ባለቤቱ ባለመሬቱ ብሄረሰብ ነው ከተባለ ስለመዋጮህ ብታወራ ማን ይሰማሃል!
ጊደር ከአህያ እንዳትውል መፀለይ ብቻነው አማራጫችን
Filed in: Amharic