>

ህወሃት የነበረ ሰው ከህወሃት ይወጣ ይሆናል እንጅ ህወሃት ከውስጡ እንደማትወጣ አይነተኛ ማሳያ - አቶ ሊላይ..!!! (መስከረም አበራ)

ህወሃት የነበረ ሰው ከህወሃት ይወጣ ይሆናል እንጅ ህወሃት ከውስጡ እንደማትወጣ አይነተኛ ማሳያ – አቶ ሊላይ..!!!

መስከረም አበራ 

አቶ ስየ አበርሃን፣ሜ/ጄ/ፃድቃንን፣ሜ/ጄ አበበ ተ/ሃይማኖት(ጆቤ)ን ያየ ሰው ህወሃት የነበረ ሰው ከህወሃት ይወጣ ይሆናል እንጅ ህወሃት ከውስጡ እንደማትወጣ መረዳት አይከብደውም፡፡እነዚህን ሰዎች ካየሁ በኋላ ህወሃት ነበርኩ የሚል ሰው ከህወሃት ወጣሁ ሲል በህወሃት ላይ ጊዜያዊ ተናዳጅ እንጅ እውነተኛ ኮብላይ ነው ብሎ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ ስለዚህ አቶ ሊላይ የተባሉ ሰው ወደ ፋና ተመላልሰው የተናገሯቸውን ነገሮች ሳደምጥ በብዙ ትዝብት እና ጥርጣሬ ነበር፡፡ትዝብቴ መንግስትንም፣ፋናንም ይጨምራል፡፡ ከትዝብቶቼ/ጥርታሬዎቼ ዋነኞቹ
አቶ ሊላይ ውይይታቸውን ሲጀምሩ ስለ ቀዳማይ ወያኔ የትግል ምክንያቶች ሲያነሱ ዋናውን የትግል ምክንያት ሳይነኩ ዳርዳሩን ያሉበትና አባታቸውን መለዓክ ለማድረግ ሲሉ ያስቀመጡት ነጭ ውሸት ነው፡፡ የቀዳማይ ወያኔ ዋነኛ የትግል ምክንያት ከወጀራትና ራያ እየገሰገስን አፋር ላይ የምናደርገውን ዝርፊያ የንጉሱ አስተዳደር ለምን ከለከለን የሚልና ከጣሊያን መምጣት በኋላ ደግሞ በማይጨው ጦርነት በነዚህ አካባቢዎች ከጣሊያን ጋር አብረው አርበኞችን  የመውጋት ታሪክ ስለነበረ ይህ ደግሞ ከነፃነት በኃላ ምን እንደሚያመጣ ስለሚያውቁ ለምን በጣሊያን መገዛታችን አልቀጠለም የሚል ምክንያትም አለበት፡፡ምንጭ የሚፈልግ እነሆነ
1. Gebru Tareke, “Peasant Resistance in Ethiopia: the Case of the Weyane,” Journal of African History,25(1984), pp 71-80
2. Tewodros Hailemariam ,”The history of Nationalism in Ethiopia 1941-2012″, pp 150-162
 ይህን ዋነኛ ምክንያት ቢያወሩት ስለማያምር አቶ ሊላይ ሊያወሩት አልፈለጉም፡፡ አቶ ሊላይ ቀዳማይ ወያኔን የተሻለ ለማድረግ ሲሟሟቱ ህወሃት የቀዳማይ ወያኔ ወራሽ አይደለም ብለዋል፡፡ ሆኖም የነ አቶ መለስ  ህወሃት የቀዳማይ ወያኔ የመንፈስ ልጅ ለመሆኑ ምስክሩ አቶ መለስ በአንድ ወቅት በአንደበታቸው “በኤርትራ የጣሊያን ባንዲራ ተነቅሎ የኢትዮጵያ ባንዲራ የተተከለበትን ታሪክ ሳስብ ልቤ ይደማል” ያሉት ንግግር ነው፡፡
ሁለተኛው ትዝብቴ ስለ ፕሮፌሰር አስራት ሞት የተናገሩት ነው፡፡የፕሮፌሰር አስራትን ሞት ምክንያት ከህወሃት አንስተው ወደ አበበ ገላው ሊያጠጋጉ የሞከሩበት ጭራሽ አቶ መለስ ለፕሮፌሰር አስራት ያዝንላቸው እንደነበር ሊነግሩን የሞከሩበት ፌዝ ነው፡፡ ይህ ነገር ትልቅ ህወሃታዊ እኩይነት ያለበት ነው፡፡ እንደሚታወቀው የፕሮፌሰር አስራት ሞት ምክንያታዊ የሆነን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በተለይ ደግሞ ለሞቱ ጠበቃ የሆኑለት የአማራን ህዝብ በእጅጉ በህወሃት ላይ እንዲያቄም ያደረገ ነው፡፡ አቶ ሊላይ የፕሮፌሰሩን ሞት በተመለከተ የነገሩን ነገር ታዲያ በህወሃት ላይ የተያዘውን ክፉ ቂም ወደ ግለሰቦች በማዞር በተለይ ፕሮፌሰር አስራትን ያስገደሉት ራሳቸው አማሮች እንጅ ህወሃት እንዳልሆነ በማድረግ ዕዳን ከእናት ፓርቲያቸው ላይ የማንሳት መሰሪ አካሄድ ነው፡፡
ሶስተኛው እና እጅግ አደገኛው መርዝ ደግሞ የራያን ጥያቄ ከእንደርታ ጥያቄ ጋር አገናኝተው ሁለቱ አካባቢዎች ወይ ከትግራይ ተለያይተው  ራሳቸውን የቻሉ ክልለሎች እንዲሆኑ ወይ ደግሞ ከአፋር ጋር እንዲዳበሉ ያወሩት ነገር ነው፡፡ ይህ ነገር ራያ ወደ አማራ ክልል ከሚቀላቀል ይልቅ ወደ አፋር ወይም ወደ ሌላ  እንዲሄድ የሚፈልግ ነው፡፡የዚህ ምንጩ ደግሞ የአማራ ክልልን የግዛት ግዝፈት ሸራርፎ የትግራይ ጓደኛ የማድረግ የህወሃት ዘፍጥረታዊ ምኞት ነው፡፡ህወሃቶች ራያ ወደ አማራ ክልል ከገባ የአማራ ክልልን የሚጠናከር ይመስላቸዋል፡፡ ህወሃቶች ቢጣሉም የሚስማሙበት ዋነኛው ነገር በአማራ ዘውግ /ክልል ላይ ያላቸው አቋም ነው፡፡
የመጨረሻው ትዝብቴ “ትግርኛ ከተናገረ ጅብም ቢሆን ወንድምህ ነው” እያሉ ያሳደጓቸው የአቶ ሊላይ አባት ፍፁም ኢትዮጵያዊነትም አብሮ ሊነገር የተሞከረበት ነገር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ንግግር ዘውገኝነት እንዴት ከቤት ወጥቶ ገበያ እንደሚውል የሚያሳይ ነው፡፡ አቶ ሊላይንም ከሃመር ባኮ አብርሮ አይተዋት ወደማያውቁት ትግራይ፣ህወሃትን ፍለጋ ያባዘናቸው ይሄው ከአባት ወደ ልጅ የተላለፈ ጥብቅ ዘውገኝነት ነው………
የመጨረሻው ትዝብቴ መንግስትን  ይመለከታል፡፡ ለውጥ ለውጥ ሲባል አንድ ተስፋየ የነበረው ሚዲያዎች እንዲህ ካለ የፕሮፖጋንዳ ስራ ወጥተው ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚያስችሉ ይሆናሉ የሚል ነበር:: አሁን የተያዘው ግን ወያኔ ሞላ አስገዶምን አምጥታ ታስቀባጥር የነበረውን የመድገም ነገር ነው፡፡ መጥፎውን አዙሪት የመዞር ትልቅ እርግማን!
Filed in: Amharic