>

የኦሮሞ ልጃገረዶች በዓል - አላዱ ቡቂሳ..!!! (ከባላምባራስ ጀቤሣ ኤጄታ)

የኦሮሞ ልጃገረዶች በዓል – አላዱ ቡቂሳ..!!!

ከባላምባራስ ጀቤሣ ኤጄታ

ይህ በዓል የአበባ በዓል ይባላል። በኦሮሞዎች ዘመን መለወጫ ቀን ጥቂት ቀደም ብሎ በየቤቱ ድግስ ይደገሳል። በዋዜማው አላዱ ቡቂሳ ( ቄጤማ ነቀላ ) ይባላል። ወደ ማታ የአንድ አካባቢ መንደርተኛ ልጃገረዶች ተሰብስበው ጥሩ ጥሩ ዜማ እያዜሙ ቄጤማ ወዳለበት ቦታ ይሄዳሉ። ቄጤማውን አጭደው አበባ ለቅመው በሚያምር ዜማቸው እርስ በርሳቸው፣ ለሚዎቻቸውንና ጎሳዎቻቸውን እያሞገሱ በሄዱበት አኳኋን ይመለሳሉ። … ማታ ወንዶች ወጣቶች እህቶቻቸውን እየረዱ ቄጤማውን ሲጎነጉኑላቸው ያመሻሉ።
የበዓሉ እለት ማለዳ ልጃገረዶቹ በተቃጠሩበት ቦታ ተገናኝተው “ፋጋ” የሚሉት እንደ ጥሩምባ ያለ ከቀርክሃ የተበጀ አየነፉ ይገናኛሉ። እንደልማዳቸውም ዜማቸውን እያዜሙ ፤ ወደ እያንዳንዱ መንደርተኛ ቤት ሄደው ጉንጉኑን ቄጤማ ኡቱባ ዲባዩ በሚሉት (ምሰሶ) ላይ ያስራሉ። በቤት ውስጥ አበባ ይበትናሉ። ባለቤቶቹም ግብዣ ያደርጉላቸዋል። የሴቶቹን ፀጉራቸውን ቅቤ ይቀቡላቸዋል። … እኩለ ቀን ሲሆን ተበታትነው ወደ ቤታቸው ይገባሉ። በዚህ ቀን ወንዶች ወጣቶች ከልጃገረዶቹ ጋር አይሄዱም። እነሱ ባሉበትም አይደርሱም። …
ምንጭየኦሮሞ ብሔር ባህልና አጭር ታሪክ
Filed in: Amharic