>

የጄነራል ኃየሎም አሟሟት እና የአቶ ሊላይ ‘አዲስ መረጃ’! (ዳዊት ከበደ)

የጄነራል ኃየሎም አሟሟት እና የአቶ ሊላይ ‘አዲስ መረጃ’!

ዳዊት ከበደ

በፋና ሚዲያ ላይ የቀረበውን፤ የአቶ ሊላይን ቃለ ምልልስ ያደመጠ ማንኛውም ሰው፤ በትርክቱ መማለሉ አይቀርም። ሆኖም ልብ አንጠልጣዩ ትርክት ስለጄነራል ኃየሎም አሟሟት ሊነግረን ሲታትር፤ አንድ ቦታ ላይ ስህተት እንዳለ – ያን ጊዜ ገባን። በሚቀጥለው ትርክት ደግሞ “አበበ ገላው ፕሮፌሰር አስራትን ሰልሎ አሳሰራቸው” ሲለን፤ ነገሩ እያሳቀ አስደመመን። ምክንያቱም በዚያን ወቅት አበበ ገላው ከፕሮፌሰር አስራት ጋር ሊያገናኘው የሚችል መስመር የለም። በእድሜም ቢሆን እሳቸው በአዛውንት ደረጃ፤ አቤ ደግሞ ገና አፍላ ወጣት ነበር።
 በዚያ ላይ አበበ ገላው እድሜውን የጨረሰው በሚዲያ ውስጥ ሲሰራ፤ ሃሳብን በነጻነት ስለመግለጽ መብት ሲታትር እንጂ በፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ገብቶ ሲያቧችር እንዳልሆነ የቅርብ ሙያ አጋሮቹ እናውቃለን። እናም በዚህ በአበበ ገላው እና በጄነራል ኃየሎም አሟሟት ጉዳይ ለመነጋገር ወደ ፋና ሚዲያ ስልክ መደወላችን አልቀረም።
—-
በፋና ቴሌቪዥን የቀረበውን ቃለ ምልልስ ከነግድፈቱ ሰምተን ማለፍ እንችላለን። ነገር ግን ስህተት የሆነ ትርክት ሲቀርብ፤ “የለም ተው!” ማለት ካልቻልን፤ እኛም የጥፋቱ አካል ወይም ተባባሪ የሆንን ስለሚያስመስልብን፤ ወደ ፋና ዋና መስሪያ ቤት ስልክ ለመደወል ተገደድን። ከአቶ ሊላይ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገውን ጋዜጠኛ ተስፋዬንም ለማግኘት ብዙ ታተርን።
“ሃሎ ጋዜጠኛ ተስፋዬን ፈልገን ነበር።” አልነ ለኦፕሬተሯ።
“ስቱዲዮ አየር ላይ ካልሆኑ እናቀርብልዎታለን።” አለችና የፕሮግራም ሃላፊው ጋር አገናኘችኝ። የፕሮግራም ሃላፊውም… ተስፋዬን በዚህ መስመር ማግኘት እንደማልችል በትህትና ገለጸልኝ።
“እንግዲያውስ…” አልኩና በፋና ውስጥ በሃላፊነት ደረጃ የሚገኝ፤ የማውቀውን ሰው ስም ጠርቼ፤ የሱን የእጅ ስልክ እንዲሰጠኝ ጠየኩት። ሳያመነታ የሃላፊውን ቁጥር ሰጠኝ።
ሃላፊው ጋር ደወልኩ።
ሃላፊው ስልኩን አነሳና… “አበበ በጣም ይቅርታ… ስብሰባ ላይ ስለሆንኩ ነው። አሁንም አላገኘኸውም? በኢሜይል ሞክርለት።” እያለ ሊቀጥል ሲል…
“ኧረ እኔ ዳዊት ነኝ። አበበ ገላውም ደውሎ ነበር እንዴ?” አልኩትና ትንሽ ተጨዋውተን፤ የፋናውን ጋዜጠኛ የተስፋዬን የእጅ ስልክ ቁጥር ሰጠኝ።
እንደ እውነቱ ከሆነ፤ በዚህን ያህል ብዛት ለማንም ስልክ ደውዬ የማውቅ አይመስለኝም። ያለመታከት፤ አንዳንዴ እያረፍኩ፤ ሌላ ጊዜም እያከታተልኩ ደወልኩ… ደወልኩ… ደወልኩ። የተስፋዬ ስልክ የመያዝ ምልክት ይሰጠኛል፤ አንዳንዴም ስልኩ መዘጋቱን ይነግረኛል። በፈለኩት መጠን ጋዜጠኛ ተስፋዬን ለማግኘት ስላልቻልኩ፤ ከሱ ጋር ላወራ የነበረውን እውነት ለመጻፍ እና ለህዝቡ ለማካፈል ወደድኩ።
እንደአብዛኛው አድማጭ… የመጀመሪያዎቹን የአቶ ሊላይን ቃለ ምልልስ በመገረም እና በመደነቅ ነበር የተከታተልኩት። ውስጤ ግን ብዙም ደስተኛ አልነበረም። በዚያን የደርግ ዘመን፤ ሂልተን ሆቴል እየሰሩ፤ በሂልተን ሆቴል ስልክ ወደ ውጭ እየደወሉ፤ “ለመለስ ዜናዊ እና ለስዩም መስፍን የስለላ ወሬ አቀብላቸው ነበር” በማለት በድፍረት እና በጀብደኝነት መልክ ሲነግሩን፤ ውስጤ አልተቀበለውም። “አሁን ያለውስ ትውልድ ከዚህ ምን ይማራል?” በመንግስት ሆቴል ውስጥ ተቀምጦ፤ በመንግስት ወጪ ስልክ ወደ ውጭ እየደወሉ፤ ‘የገዛ ወገንን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠትንስ ምን ይሉታል?’ በማለት ከራሴ ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ መግባቴ አልቀረም።
ቤተ መንግስት ውስጥ ከሶስት ግዜ በላይ ገብተው ኮ/ል መንግስቱ ወታደራዊ መግለጫ የሚቀበሉበትን ቢሮ፤ እንዴት እና በማን አማካኝነት ይህን እድል አገኙ? እርግጥ ነው፤ በዚያን ዘመን የፋክስ ማሽኖች ከሚገኙባቸው ውሱን ቦታዎች አንደኛው የሂልተን ሆቴል ስለነበር፤ ለጄ/ል ተስፋዬ የሚመጣው የፋክስ መልዕክት በሂልተን ሆቴል በኩል ከሆነ አንደኛውን ኮፒ አቶ ሊላይም ሊያገኙት ይችሉ ይሆናል። ለዚያውም ጄነራሉ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት የሆኑት ለሰባት ቀናት ብቻ ስለሆነ፤ በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ የሚገኘው ሚስጥር ብዙም የሚያጓጓ እና ውሃ የሚያነሳ አይሆንም።
ይህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ… ጨዋታችንን ከአንደኛው የደርግ ጄነራል ወደ ኢህአዴግ ጄነራል እንውሰደው። ስለጄነራል ኃየሎም አርአያ ጉዳይ እንነጋገር። በቃለ ምልልሱ ላይ… “ያሲን” የሚባል ሰው እንደገደላቸው ሲናገሩ፤ ጋዜጠኛው ያርማቸዋል ብለን ስጠብቅ፤ ሁለቱም እየተቀባበሉ… “ያሲን ያሲን” ሲሉ ሌላም ስህተት እንዳለ ግልጽ እየሆነ መጣልን። ምክንያቱም የጄነራል ኃየሎም ገዳይ ጀሚል እንጂ ያሲን አይደለም። ጀሚል ያሲን ይባላል – የጄነራል ኃየሎም አርአያ ገዳይ።
የስም አጠራሩን እንደመጠነኛ ስህተት በማየት ልናልፈው እንችላለን። ነገር ግን በስለላ ሙያ ብዙ እንደሰሩ የነገሩን አቶ ሊላይ እንዲህ አይነት ስህተት ሊሰሩ ባልተገባ ነበር። በዚያ ላይ… ‘በጣም የምወደው ጓደኛዬ የሚሉትን፤ የጄነራል ኃየሎም ገዳይ ሙሉ ስም እንዴት አያውቁትም?’ ጋዜጠኛውውስ ቢሆን… ግዴለም ጋዜጠኛውን እንተወው። አቶ ሊላይ ግን እዚህ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያ ጋር ተያይዞ የገለጹት ታሪክ እውነት እውነት ነው? በትርክታቸው መጨረሻ… “ጄነራል ኃየሎምን ወያኔ አስገደለው” የሚለው መደምደሚያስ አላዋቂን እንጂ፤ እኛን እንዴት ሊያሳምነን ይችላል?
እንግዲያውስ ታሪኩን ለማያውቁ በአጭሩ ማስታወስ ሊኖርብን ነው። ጀሚል ያሲን በምን ምክንያት ጄነራሉን እንደገደላቸው፤ የት እና እንዴት እንደሞቱ በዝርዝር ይታወቃል። የካቲት 6 ቀን፣ 1986 ዓ.ም ሜጀር ጄነራል ኃየሎም አርኣያ ሲገደሉ፤ ከዚያም ጋር ተያይዞ ዜናው ለህዝብ ሲሰማ፤ ህዝቡ በከፍተኛ የድንጋጤ ውርጭ ተመትቶ እንደነበር በዚያን ጊዜ ለአቅመ አዳም የደረሰ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚያስታውሰው ይመስለናል። ጄነራል ኃየሎም እንደሃጫሉ ሁንዴሳ በተጠና ሁኔታ፤ በእቅድ አልተገደሉም። የጄነራሉ እና የጀሚል ያሲን ጸብ በድንገት የተፈጠረና በፍጥነት የተቋጨ አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
 በዚያን ወቅት አብዛኛው ሰው ጀሚል ያሲንን ከጄነራል ኃየሎም ባልተናነሰ ያውቀዋል። “ጀሚያስ” የሚባለው አስመጪ ድርጅቱ በቴሌቪዥን በጣም ይተዋወቅ ነበር። የኪነ ጥበብ ስራዎችን ስፖንሰር በማድረግ ይታወቃል። በመሆኑም ከጄነራል ኃየሎም አርአያ የሞት መርዶ በኋላ በቀጣዮቹ ቀናት ገዳዩ ማን እንደሆነ ሲነገረን ብዙዎች መገረማችን አልቀረም። ምክንያቱም ጀሚል ያሲን፤ ጉራ እና ቸበርቻቻ ይወዳል እንጂ፤ ሰውን የመግደል ፍላጎት እና አቅም ሊኖረው ይችላል የሚል ግምት ብዙዎች አልነበረንም። ነገር ግን ይህ ግድያ የተፈጸመው ከመጠጥ በኋላ፤ በመጠጥ ቤት መሆኑን ስንሰማ፤ ጀሚል ያሲንም ሲጠጣ አቅሉን እንደሚስት ለምናውቅ ሰዎች ነገሩ አሳማኝ ሆነብን።
አቶ ሊላይ ስለህወሃት እና በታሪካቸው ውስጥ ስለፈጸሟቸው አስከፊ ተግባራት ሲነግሩን የምናምናቸውን ያህል፤ ስህተታቸውን የመንገር ሃላፊነት ስላለብን፤ ይህንንም በመግቢያችን ላይ ስለገለጽነው፤ ደጋግመን ማሳሰቢያ መስጠት አይኖርብንም። ለምሳሌ የህወሃት ወይም የወያኔ ባለስልጣናት የነበሩት ሰዎች፤ በአቶ ሊላይ እና በትግራይ ላይ ከፈጸሙት ግፍ በሚበልጥ ሁኔታ፤ በእኔ እና በአገሬ ላይ የሰሩት በደል እጅግ የበዛ ነው። ህወሃቶች ያደረጉት መጥፎ ነገር… ሃጢያት እና ጥፋታቸውን ዘርዝረን ልናበቃው አንችልም። ቢሆንም ግን ባደረጉት እንጂ ባላደረጉት ነገር እነሱን መክሰስ ፈጽሞ ትክክል አይደለም። አሁንም በሜጀር ጄነራል ኃየሎም አርአያ ሞት የሚጠየቀው ጀሚል ያሲን እንጂ ወያኔ አይደለም። ይህን የምንለው ደግሞ በግምት ወይም በመላምት ሳይሆን፤ በተጨበጠ እውነት እና መረጃ ነው።
ጄነራል ኃየሎም መሞታቸው እንደተሰማ፤ እሮብ እለት በምትታተመው ፊያሜታ ጋዜጣችን ላይ፤ የመጀመሪያውን ዜና ዘገባ የሰራነው እኛ ነበርን። ይህ ብቻ አይደለም። በጄነራል ኃየሎም አርአያ ምክንያት ከታሰሩት ሰዎች መካከል አንደኛው አሁንም ድረስ በህይወት የሚገኝ የቅርብ ጓደኛዬ ስለነበር፤ የሆነውን ነገር ሁሉ እንደትላንት የማስታወስ ብቃት ያለው ሰው በመሆኑ፤ ዛሬም የህይወት ምስክርነቱን ሊሰጥ ይችላል። እኔም ገዳዩን ጀሚል ያሲንን በግል ማወቅ ብቻ ሳይሆን፤ እያንዳንዱን የፍርድ ቤት ውሎ እየተከታተልኩ በጋዜጣችን ላይ አቀርብ ስለነበር፤ በዚያ ላይ ጀሚል ያሲን ሞት ከተፈረደበት በኋላ የመጨረሻውን የኑዛዜ ቃል በጽሁፍ የሰጠኝ ለኔ ስለነበር፤ ከሞተም በኋላ በቃሉ መሰረት ሙሉውን የኑዛዜ ቃል ለህዝብ ስላቀረብኩት፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከአቶ ሊላይ ይልቅ እኔ እና በወቅቱ የነበሩ ጋዜጠኞች ጉዳዩን በቅርበት ብቻ ሳይሆን፤ በተሻለ ሁኔታ የምናውቀው ይመስለኛል።
ከዚያ ጋር ተያይዞ፤ በአቶ ሊላይ የተገለጸው… የወጣቶቹ ደህንነቶች ጉዳይ ለማመን ቢያስቸግርም፤ ከሳቸው በተሻለ ስለማላውቀው ነገር ብዙም መከራከር አልፈልግም። ሆኖም የደህንነት ሃላፊው አቶ ክንፈ እና ኃየሎም አርአያ የቅርብ ጓደኛሞች ሆነው ሳለ፤ በጄነራሉ ላይ የደህንነት ሰራተኞች መላኩ በግሌ አላሳመነኝም። “ደግሞስ እነዚያ ወጣቶች ኃየሎምን አግኝተውት ቢሆን ኖሮ ምን ሊያደርጉት ይችሉ ነበር?” መቼም ‘የኃየሎምን እጅ አስረው… ይወስዱታል’ ብሎ ማሰብ ራሱ፤ ኃየሎምን የመስደብ ያህል የሚቆጠር ነው። ደግሞስ በመጨረሻው ወታደራዊ የስልጣን እርከን ላይ የነበረውን፤ ብዙ ሺህ ጦር የሚያዘውን፤ የብዙ ሚሊዮን ህዝብ ድጋፍ ያለውን፤ የራሳቸው አባል የነበረውን ብቸኛ ጄነራል፤ በደህንነት አሳፍነው እስር ቤት ሊወረውሩት ነበር’ የሚል ትርክት ማንን ያሳምናል? ምናልባት ያንን ዘመን እና ኃየሎምን የማያውቅ አዲስ ትውልድ ካልሆነ በስተቀር፤ የኃየሎምን ጀግንነት ለምናውቅ ሰዎች ይህ ትርክት ፈጽሞ አያሳምነንም።
በዚያ ላይ… ህወሃት ጄነራል ኃየሎምን መግደል ከፈለገ፤ እንደተለመደው ወደጦር ግዳጅ ልኮ ከጀርባው ሊያስመታው ይችል አልነበረምን? የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር የነበረው አራንሺም ቢሆን፤ ጀሚል ያሲን ሽጉጥ እንዲያገኝ የፈቀደለት… ኃየሎምን ለማስገደል ነው ብሎ ማለት ምን የሚሉት ጨዋታ ነው? ጀሚል ያሲን ሽጉጥ የወሰደው ህጋዊ በሆነ መንገድ ሲሆን፤ አራንሺ ተገምግመው ከሃላፊነት የተነሳው ግን፤ “ጀሚል ያሲን ኤርትራዊ መሆኑን እያወቅክ፤ ለሌላ አገር ዜጋ ሽጉጥ እንዲሰጠው ለምን ፈቀድክ?” በሚል ጠንከር ያለ ግምገማ መሆኑን በወቅቱ በሰፊው ጽፈንበታል።
በዚያም ተባለ በዚህ የሜጀር ጄነራል ኃየሎም አርአያ ግድያም ሆነ፤ የጀሚል ያሲን መጨረሻ አሳዛኝ ነበር። ይህንንም ቢሆን… ከዚህ በፊት በተከታታይ የጻፍኩት ነገር ስለሆነ ወደኋላ ተመልሼ ማብራሪያ ልሰጥበት አልፈልግም። ነገር ግን አቶ ሊላይን ስለማላገኛቸው፤ ጋዜጠኛ ተስፋዬንም በስልክ ፈልጌ ስላጣኋቸው… ስህተት የሆነ ነገር ተናግረን ትውልድ እንዳይደናገር፤ ከሚል ቅን ሃሳብ በመነሳት፤ ይህን አጭር ማስታወሻ ለመተው ወደድኩ። ደህና ክረሙልኝ።
Filed in: Amharic