>

ሽግግሩ ወደ ህሊና ቁስልነት እየተለወጠ ነው!!! (ያሬድ ጥበቡ)

ሽግግሩ ወደ ህሊና ቁስልነት እየተለወጠ ነው!!!

ያሬድ ጥበቡ

* ከመጥበሻው ወደ እሳቱ መወርወራችንም የማይታበል ሃቅ  ነው!!!
ከታች የተያያዘው ፅሁፍ፣ በዛሬው ዕለት ከ4 ዓመታት በፊት ለወያኔ መሪዎች የተላለፈ ተማፅኖ ነበር። ዛሬም ለኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ይሠራ ይመስለኛል። ቢያንስ ወያኔ በፊትለፊት “ለትግሬ የበላይነት እሠራለሁ” ብሎ ካድሬዎቹንና ባለሃብቶቹን ሲያናግር አልተያዘም። ቢያንስ ወያኔ የገጠር ወንጀለኞች ቆመጥ ይዘው ሲገቡ እያጀበ፣ ልጆቹንና ንብረቱን ለመታደግ የወጣው የአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ አልተኮሰም። ቢያንስ ወያኔ ከልጆቻቸው አፍ እየነጠቁ ለቤት መግዣ ያስቀመጡ  እናቶችን ኮንዶ እየነጠቀ በነፃ ለደጋፊዎቹና ለብሄረሰቡ ውላጆቹ ያለክፍያ አላከፋፈለም። ይሉኝታ ቢስነትና መስገብገብም ወሰን አለው። ዘረኝነትም ገደብ አለው። የዘንድሮው ግን እጅግ መረን የለቀቀ ነው። ያሳፍራል፣ ያሳዝናል፣ ያስለቅሳል። ለማንኛውም ከ4 ዓመታት በፊት የፃፍኩትን ተማፅኖ አንብቡና ከዛሬው ብካይ ጋር አነፃፅሩት።
ከመጥበሻው ወደ እሳቱ መወርወራችን ሃቅ እንጂ ነው። ሽግግሩ ወደ ህሊና ቁስልነት እየተለወጠ ነው። የኦሮሚያ ብልፅግና ጥጋቡንና እኩይ እምነቱን ትቶ ወደ ኢትዮጵያዊ ፍትህና እኩልነት እንዲመለስ እንማፀናለን። የአዲስ አበባም ህዝብ ለሰብአዊ ክብሩና ህልውናው እንዲቆምና እያንዳንዱ በግሉ ከራሱ ጋር ተነጋግሮ ሰብእናውን ከወደቀበት ረመጥ እንዲፈልግ እንማፀናለን። በፍርሃትና በለቅሶ መኖር ያክተም። በክብርና እንደዜጋ ተቆጥሮ መኖር ይስፈን። የ5 ሚሊዮኖች መኖሪያ የሆነች አዲስ አበባ በዙሪያዋ ያለውን ገጠርና በነዚህ ገጠሮች ያሉ ወሮበሎችን ፈርታ የምትኖርበት ህይወት መቆም አለበት። ለዚህም የመጀመርያው እርምጃ ከቀበሌ ጀምሮ ከነዚህ ወሮበሎች ጋር የሚመክሩትን ዘረኞች፣ ፖሊሶች፣ የአገዛዙ ካድሬዎችና ገዢዎች ከወንጀለኞች ጋር ትብብራቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ ነው። ትብብራቸውን ለማስቆምም ቀናው መንገድ ከአብራኬ ባልወጡ የቀበሌ፣ የወረዳ፣ የክፍለ ከተማ፣ የከተማ እስተዳደርና ፖሊስ እንዲሁም ዳኛ አልተዳደርም ብሎ እምቢተኛ መሆን ነው። ይህንንም እምቢተኝነት ለዓለሙ ይፋ ማድረግ ነው። አቢይ ያድነናል ብሎ በአንድ ሰው ላይ ተስፋን ጥሎ መብትን አሳልፎ መቀመጥ ያደረሰውን ብካይ የምታውቁት በመሆኑ ለቀባሪ አላረዳም። መብቱን የተረዳና የተደራጀ ከተማ በዙርያው ያሉ ገጠሮችን የሚፈራበት ምንም ምክንያት የለም። በእውቀትም፣ በክሀሎትም፣ በሃብትም፣ በጀግንነትም ገጠሩ ከተማውን ሊበልጥ አይችልም። በተጨማሪ ግን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው ገጠር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማናውያን ቀዬ ነው። እነርሱም እንደ አዲስአበባ የአርሲና ባሌ አክራሪ የሙስሊም ብሄርተኞች ብካይ ናቸው። ከአዲስ አበባ ጎን መቆም ይችላሉ። በውስጣቸው ያሉ የተሳሳቱ ልጆቻቸውን መምከርና መመለስ ይችላሉ። በምንደኝነት የተገዙትንም አሳልፈው ለህግ እንዲሰጡ መተባበር ይችላሉ።
አዲስ አበባ ለቅሶና ፍርሃትህ ይብቃ። በቁምህ አትሙት። እናቴ አዘውትራ “ፈሪ 10 ጊዜ ነው የሚሞተው” ትል ነበር። በቁምህ አስር ጊዜ አትሙት። ለህልውናህ፣ ለክብርህ፣ ለስምህ፣ ለልጆችህ፣ ለንብረትህ፣ ለዜግነትህ፣ ለኢትዮጵያህ ቁም። ጌታዋን አምና ላትዋን ውጪ እንዳሳደረችው በግ አትሁን። በራስህ፣ በጎረቤትህ፣ በአጥቢያህ፣ በደብርህ ተማመን። ምከር፣ ተወያይ፣ ህገወጥነትን፣ ሙስናንና ዘረኝነትን ተጠየፍ። በሃገርህ ላይ በፍርሃት አትኑር፣ ለምን ብለህ! ይሄው ነው፣ በቃ!
ከ4 ዓመታት በፊት ለወያኔ መሪዎች የተላለፈ ተማፅኖ…!!!
 
ህዝባዊ እምቢተኝነትና የሽምቅ ስልት
ንጋት ላይ ከአዲስ አበባ የደረሰኝ የመጀመሪያው መልእክት ከሥርአቱ ደጋፊ ከሆነው ከዳንኤል ብርሀኔ ነበር ። ሰልፉ አለመሳካቱን የሚገልፅ መልእክት ። ዳንኤል ያልተረዳው ነገር ፣ የአዲስ አበባ ሰው ተኝቶ ሲያድር የሥርአቱ አጋፋሪዎች ቁጭ ብለው ማደራቸውን ነው ። ሥርአቱ በከፍተኛ ደረጃ ፍጅት ለማካሄድ መዘጋጀቱ ሲታወቅ በአስተባባሪዎቹ ውሳኔ ሰልፉን ላለማድረግ ውሳኔ መደረጉን ነው ስርአቱ ያልተረዳው ። የስርአቱ ቁንጮዎች ግን የመኝታ ቦታቸውን ሲለዋውጡና፣ ምን ይፈጠር ይሆን በሚል ስጋት ማደራቸውን ሰምተናል ።
ወደፊትም ተመሳሳይ ጥሪዎች እየተደረጉ ሊደርስ የሚችለው ጥፋት ይገመገማል ። አስፈላጊም ሲሆን ሰልፉ ይሰረዛል ። የስርአቱ ቁንጮዎች በተዘናጉበት እለት ግን ይህ ህዘባዊ እምቢተኝነት የማይቀር ነው ። ሰላማዊ የሽምቅ ስልት ነው ። ባልጠበቁት ጊዜ ግን  ከች የሚል ። እስከዚያ ስርአቱ እንደተረበሸ፣ እንቅልፍ እንደናፈቀው፣ በለጋሽ መንግስታቱ የሰላም መፍትሄ  እንዲሻ ጫናው እየበዛበትም ይሄዳል ።
በአንድ ወቅት ግን ያቺ ቀን ግን ትደርሳለች ። የከተማው ነዋሪም ብቻ ሳይሆን፣ በአካባቢው ካሉ የኦሮሞና አማራ የገጠር ቀበሌዎች በመጣ ህዝብ የታጀበ፣ የሁለቱን ታላለቅ ሀይማኖት አባቶች ግንባር ቀደም ተሳትፎ ባካተተ፣ ቢያስፈልግ በ44ቱ ታቦቶች የታጀበ ሰልፍ ይደረጋል ። ያኔ በታቦት ላይ የሚተኩሰው ሰራዊታችሁ ምን አይነት ጀግንነት እንዳለው ይታያል ። የፍፃሜውም ፍፃሜ ይሂናል ። አርበኛው ከእስር ቤት “የፈራ ይመለስ” ብሎ የህሊና ደውል አሰምቷልና ።
ሆኖም አሁንም እዚህ ምሬት ላይ መድረስ የለብንም ብለን እናስባለን ። የፃፋችሁትን ህገመንግስት በግንባር ቀደምነት እያፈረሳችሁ መቀጠል አትችሉም ። ከዘረኝነትና መድልኦ የመታቀብ ምርጫ አላችሁ ። የፖለቲካ ምህዳሩን መልሳችሁ ከግንቦት 97 ምርጫ በፊት ወደነበረበት ቦታ መመለስ ትችላላችሁ ። የህሊና እስረኞችን፣ የፖለቲካ እስረኞችን፣ የነፃ ፕሬስ እስረኞችን ሁሉ መፍታትና፣ ወደ ሃገራዊ እርቅ የሚወስድ መንገድ መክፈት አማራጭ በእጃችሁ ነው ። ተጨነቁበት፣ አስቡበት ። እናንተም ከዛፍ ላይ መኝታ ነፃ ሁኑ ። እንዴት በገዛ ሃገራችሁ እየባነናችሁ ትኖራላችሁ? በ17 አመታት የትጥቅ ትግል እንግልትና በ25 አመታት የመንግስታዊ አስተዳደር ውጣውረድ የደከመው ሰውነታችሁ ሰላማዊ እረፍትን ይሻል ። ለምን ለራሳችሁ ማዘን አትችሉም? ለምንስ በንፁሀን ደም እጃችሁ ይበከላል? ያወጣችሁትን ህገመንግስት አክብሩና፣ የህዝቡን ነፃነት መልሱ ። ለ25 አመታት የተጓዛችሁበት የሀይልና እብሪት መንገድ ያደረሳችሁ የገደል አፋፍ እንዴት አይታያችሁም ።  እባካችሁ ተለመኑ ።
Filed in: Amharic