>

እናቱ ገበያ የሔደችበት እናቱ ከሞተችበት እኩል ያለቅሳልን...??? (ዲ/ን አባይ ነህ ካሴ)

እናቱ ገበያ የሔደችበት እናቱ ከሞተችበት እኩል ያለቅሳልን…???

ዲ/ን አባይ ነህ ካሴ

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ ደረሰ ከሚለው ጉዳት ይልቅ አነጋጋሪነቱ ይጎላል። ምስቅልቅል የበዛበት ጎርበጥባጣ መልእክት አዝሏል።
ይህንን መግለጫ እንደቀላል ተመልክተን እንዳናልፈው አጽንዖት ሰጥተን መናገር ይኖርብናል። በምሥራቅ ኦሮሚያ በተደራጁ ቡድኖች በደረሰብን ጭፍጨፋ እና ጄኖሳይድ ክርስቲያኑ ክፍል ደሙ እንደውኃ ፈስሷል። በዚህ መግለጫ መሠረት «እኛም እንዲህ ያለው በደል ደርሶብናል» እያሉ ነው።
* የት ነው በጅምላ የተጨፈጨፉት?
* የሙስሊሞች ንብረት እየተለየ የወደመው የት ነው?
* ሙስሊሞች ብቻ እየተለዩ ከቤታቸው የተፈናቀሉት የት ነው?
በመስጊድ ውስጥ የተፈጸመ ግድያ አለ የሚለው ጉዳይ እውነት እስከኾነ ድረስ ነውር ነውና ተቀባይነት የለውም። በተቋም ደረጃ ድርጊቱን ያወገዘ የመጀመሪያው አካል ኢሰመኮ ሲኾን ራሱ ጠቅላይ ም/ቤቱ ገና ብቅ ማለቱ ነው።
መግለጫ ለማውጣት መዘግየቱን ረስቶ በተቃራኒው ሌላ ለመውቀስ እና የተዛባ አስተያየት ለመሠንዘር መፍጠኑ ያስገርማል። ባለቤቱ ያቃለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም ይባል ነበር።
ዛሬ ደረሰ ለሚለው አደጋ ከሰኔ ፳፫ ተነሥቶ ያኔ ለተፈጸመው ፍጅት የተዛባ ብያኔ ሰጥቶ መንደርደር ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ ቢኾንም ግልጽ አይደለም። መግለጫው ሦስት መሠረታዊ አደገኛ አሳቦችን አንሥቷል።
፩. በዚያን ጊዜ ሙስሊሞችም የጥቃት ሰለባ ነበሩ ይላል:- ግን ሙስሊምን በሃይማኖቱ ምክንያት ለማጥቃት አስቦ የተፈጸመ አልነበረም። ክርስቲያኑ ሲጎዳ ዳፋው የደረሳቸው መኖራቸው እውነት ነው። በንግድ ሥራ ከክርስቲያን መጎራበታቸው ያመጣባቸው ጣጣ እንጅ እንደ አጥቂው ኃይል ፍላጎትስ ቢቻለው ነጥሎ ቢያተርፍላቸው አይጠላም ነበር። ዞሮ ዞሮ ሙስሊሞች በሰኔ ፳፫ቱ ፍጅት መጠኑ ለንጽጽር ባይበቃም መጠቃታቸው አልተካደም።
፪. የሰኔ ፳፫ቱን ፍጅት ሃይማኖታዊ ገጽታ ለማላበስ ተሞክሯል:- ሲል ጠ/ም/ቤቱ በመግለጫቸው ሊያሳብል ተገደርድሯል። ይህ አደገኛ ድምዳሜ በጥሞና ታይቶ ከኾነ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ለካ ድምፁን አጥፍቶ የከረመው ስላልተቀበለው ኖሯል? ዝምታው ሲገርመን የባሰውን በቁስላችን ላይ መርዝ ነሰነሰበት።
፫. ሙስሊሙን የማሸማቀቅ አደገኛ እንቅስቃሴ ተደርጎብኛል:- ብሎ መግለጫው ይከስሳል። ጽንፈኝነትን የሚያራምዱ በእስልምና እምነት የተደበቁትን ማውገዝ እኔን ማውገዝ ነው እያለን ነውን? እኛ ያንን ድርጊት ከክርስቲያኑ እኩል ሃይማኖታዊ ጥቃት መኾኑን አምነው ያወገዙ ሚሊዮን ሙስሊሞች  መኖራቸውን እናውቃለን። ይህ መግለጫ እነርሱን እንደማይወክልም በሙሉ ልብ አምናለሁ።
ሰሞኑን በአሳሳ ደረሰ የተባለው ጥቃት በመንግሥት ታጣቂዎች የተፈጸመ መኾኑ ተነግሯል። የሰኔ ፳፫ቱ ፍጅት ግን ሃይማኖታችሁ የእኛን ካልመሰለ አሰቃቂውን ግፍ እንካችሁ ባሉ ጽንፈኞች የተመራ እና የተፈጸመ ነው።
በአክራሪ ወሐቢያዎች ቁጥጥር ሥር ወድቋል እያሉ ሙስሊሞች የሚቃወሙት የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ መጅሊስ በደማችን እንዲቀልድ ልንፈቅድለት አይገባም። መሞታችን ካልቀረማ እውነቱን እየተናገርን እንሞታለን እንጂ ዝም ብለን አናልቅም። እውነትን እስከያዝን ድረስ ሐሰትን ድል እናደርገዋለን።
ይህ መግለጫ ይታረማል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ካልኾነ ግን የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤቱ አሰላለፍ ምን እንደኾነ ግልጽ ስለኾነልን እናመሰግናለን።
ይህንን ያደረገ ፊት ጸፍቶ አፍ ከፍቶ የሚያናግረውን መንፈስ ቅዱስ እልፍ ጊዜ እልፍ ምስጋና ይድረሰው።
————
*” 17ቱ የወሀቢይ መፍትሄ አፈላላጊዎች አይወክሉንም!” በሚል የማህበራዊ ሚድያ ገጽ ላይ ይህ እውነት ቁልጭ ያለ እውነት ሰፍሮ እናገኛለን…!
 
ያለ ምንም ሀፍረት የኛን የሙስሊሞችን 40 ሚሊዬን ብር ሰልቅጦ የበላው፣በርካታ ዑለማዎቻችንን በአሻጥር ገድሎ ያስገደለውና መጅሊስ ውስጥ ለመዝረፍ የተሰገሰገው የነ አህመዲን ጀበሉ አራጅ ቡድን መጅሊስን ተጠቅሞ አዛኝ ለመምሰል ሲዳዳው እያየን ነው።
ትናንት መሻይኾቻችንን ያስገደለ ማነው? ውሐብያ።
ትናንት መሻይኾቻችንን በአደባባይ የሰደበ፣የዘለፈና ክብራቸውን ያዋረደ ማነው? ውሐብያ።
“በእምነት ሊቃውንት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፍጹም ተገቢነት የለውም” እያላችሁ ስትለፋገዱ ቢያንስ ትንሽ ሀፍረት ብጤ አይሰማችሁምን??
መሻይኾቻችን ላይ ጥቃት ያደረሰ ከእናንተ ውጭ ማን አለ?
እስኪ ንገሩን ከእናንተ የባሰ ገዳይ አስገዳይ ማን አለ????
አንድ ነገር ብቻ እንንገራቸሁ!
እናንተ ፈጽሞ ልታታልሉን አትችሉም።ፈጽሞ!!!
መጀመሪያ በደም የተጨማለቀ ማንነታችሁን አጽዱ።
Filed in: Amharic