>

ጦርነታችን ከማን ጋር ነው? (አሳፍ ሀይሉ)

ጦርነታችን ከማን ጋር ነው?

አሳፍ ሀይሉ

የኢትዮጵያ ህዝብ ‹‹ሆ!›› ብሎ ለአንድ ወር ላልሞላ ጊዜ ተደራጅቶ፣ ራሱን አስታጥቆ ቢነሳ – ያለምንም አንጃ ግራንጃ – የወያኔን ፋሺስት ሽማግሌዎች የገቡበት ገብቶ ጆሮአቸውን አንጠልጥሎ ለፍርድ ለማቅረብ የሚችል ታላቅ ኃይል በእጁ እንዳለ ማንም ቢሆን መቼውኑም መርሣት የሌለበት እውነት ነው፡፡ የግድ ይህን በተግባር ሆኖ ካላየሁት አላምንም ብሎ መድረቅ – ሽጉጥ ጥይት ጎርሶ ሲተኮስ እንደሚገል ሰው ገድለህ ካላሳየኸኝ አላምንልህም እንደማለት ያለ የጅል ድርቅና ነው፡፡ ጥያቄው የመቻልና ያለመቻል ጉዳይ አይደለም፡፡ ጥያቄው የአቅም ጉዳይ በፍፁም አይደለም፡፡
ጥያቄው – ለፍርድ መቅረብ ያለባቸው ዘረኛ ፋሺስቶች የወያኔ ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው ወይ? የሚለው የፍትሃዊነት ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄው ማዕከላዊ መንግሥቱንስ የተቆጣጠሩት የተራቡ ጅቦች – ከወያኔ ዘረኛ ሽማግሌዎች ያነሰ ዘረኝነትን የተላበሱ ፋሺስቶች ናቸው ወይ? የሚለው የሚዛናዊነት ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄው – የወያኔዎቹ ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ – የየክልል ተብዬዎቹስ ባለ ሥልጣኖች አብዛኞቹ ይኼው የወያኔው የዘረኝነት ሥርዓት ያፈራቸው ታማኝ የፋሺስታዊው ሥርዓት ሎሌዎች አይደሉም ወይ? የሚለው የእውነታ ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄው ያለንበትስ አጠቃላይ ሥርዓት ዜጎቻችንን በዘር ልዩነት ሸንሽኖ አንዱ ወደሌላኛው ድርሽ እንዳይል በትልቅ የህግና የጥላቻ አጥር የከለለ የአፓርታይድ ፋሺስታዊ ሥርዓት አይደለም ወይ? የሚለው የሀቅ ጥያቄ ነው፡፡
እና ማን ደህና ሆኖ፣ ማንስ ከፋሺስታዊው የዘረኝነት ልክፍት ነፃ ሆኖ ነው – የወያኔዎቹን ሽማግሌዎች ለፍርድ ለማቅረብ የሞራል ልዕልና ያለው? መንግሥቱን፣ ጦርሠራዊቱንና ካዝናውን ተቆጣጥረው – ሁሉን ነገራችንን እጃቸው ካስገቡት ወፈሠማይ የፋሺስቱ ሥርዓት ተረኛ ጋሻጃግሬዎች ውስጥ – ማን በተለየ ንጹህ ሆኖ ነው – መርጦና ለይቶ የወያኔን መሪዎች ለማደን የሞራል ሥልጣኑ ያለው? በዘረኞቹ ስብስብ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብሎ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተሾመው የኦህዴዱ ሊቀመንበር አብይ አህመድ ራሱስ – ማን ሆኖ እርሱ – ሌሎቹን የወያኔ መሪዎች እነ አባይ ፀሐዬንና ስብሃት ነጋን አስራለሁ ብሎ የሚነሳው? ለመሆኑ የብአዴኑ የወያኔ አድርባይና ተላላኪው ደመቀ መኮንን ራሱ ማን ሆኖ ነው  – የህወኀቱን ደብረፅዮንን ለፍርድ አቅራቢና ፈራጅ ሆኖ ሊነሣ የሚችለው? የኦህዴዱ ብርሃኑ ጁላ ራሱ ማን ሆኖ – ከወያኔው ሣሞራ የኑስ ተሽሎ የሚገኘውና – አንዱ ሌላውን ለፍርድ አቅራቢ ሆኖ የሚነሳው?
ማን ከማን ተሽሎ – እና ማን ከማን የተሻለ ንፁህ ሆኖ ነው – ማን ማንን ለህግ የሚያቀርበው? ማን ነውስ አሁን ‹‹ህግ›› እየተባሉ የሚጠሩትን የዘረኛው ሥርዓት መተዳደሪያ ደንቦች የሚያወጣው የህግ አውጪው? ሁሉስ አንድ አይደሉ ወይ? ሁሉስ አንድ የዘረኛ ሥርዓት የፈጠራቸው፣ የዘረኛው ሥርዓት አስጠባቂዎችና ደላላዎች አይደሉም ወይ? ሁሉ ነገራችን – የምናየው መንግሥታዊ ትያትርና ድራማ ሁሉ – እዚያው ሞቀ፣ እዚያው ፈላ – አይደለም ወይ? ሁሉም ያው – ሁሉም ስሙ ቢቀያየርም ያው አንድ – አይደለም ወይ?
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት በኩል – በትግራዮቹ ፋሺስቶች ላይ የሚቃጣን ማንኛውንም ዓይነት የኃይል እርምጃ አጥብቀን የምናወግዘውም እኮ – ‹‹ጦርነት›› በምንም መልኩ መወገዝ ያለበት አጥፊ ተግባር ስለሆነ ብቻ አይደለም! ጦርነትን የምንቃወመው – ጦርነት ሊያውጁ የሚሰናዱትም፣ ጦርነት የሚታወጅባቸውም – ሁለቱም በአካልም፣ በአምሳልም – ከአንድ ወንዝ የተቀዱ – እና ወደ መጨረሻው የመጠፋፋት እንጦረጦስ በቁማችን እየነዱ እየወሰዱን ያሉ – ሁሉም ዘረኞች፣ ሁሉም ፋሺስቶች፣ ሁሉም የወያኔ የአፓርታይድ ሥርዓት ተከታዮችና አራማጆች ስለሆኑ ነው፡፡ የምናየው ነገር ሁሉ – ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል? የሆነበት ዘመን ላይ ስለተገኘን ነው፡፡ ገሞራው እንዳለው – ሁሉም ነገራችን ያው! አንዱ ከአንዱ የማይሻልም የማይለይም – ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ሥልቻ! – ስለሆነብን ጭምር ነው፡፡
‹‹ቀልቀሎ ስልቻ፣ ስልቻ ቀልቀሎ
ማንን ይመርጡታል፣ ማን ከማን ተሽሎ፡፡
ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ
ምን ደህና አለበት፣ ሁሉም አራሙቻ፡፡
ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ
ዝም ብለሽ ተቀበይ፣ የሰጡሽን ብቻ፡፡››
    ( – ገሞራው /ኃይሉ ገ/ዮሐንስ/፣ 1967)
አንዳቸው ከሌላኛቸው የተሻለ – ከዘረኝነት የተሻገረ ሥርዓት አቁመው – ለዚህች በዘረኞች ክንድ ተደጋግማ ተደቁሳ ለተኮሳመነች ምስኪን ሀገርና፣ ለፈረደበት ሕዝባችን ጠብ ላያደርጉልን ነገር – በዘረኛ ዝሆኖች መካከል ጦርነት ቢነሳ – ማነው ተጠቃሚው? ምንድነው ጥቅማችን? የፈረደበትን የድሃውን ልጅ ለሞት ከመዳረግ ውጪስ – ያም ያው፣ ያኛውም ያው፣ ይሄም ያው በሆነበት ሀገር – በእነርሱ ጦርነት የሚመጣ ምን የተለየ ለውጥ ይኖራል?!  ‹‹ባየው ባየው፣ ባየው ባየው – አመልሽ – ያው ያው ያው ነው!›› እንዳለው ዘፋኙ – ቢቦካ ቢጋገር – ቢሰለቅ ቢወቀጥ – ያው ራሱኑ ነው፡፡ አረም ተዘርቶ ስንዴ አይታጨድም፡፡ የእንቧይ ተክል – የወይን ፍሬን አያፈራም፡፡ በዘረኛ ሥርዓት ላይ ቆመው፣ የዘረኛው ሥርዓት አስጠባቂ፣ የዘረኛው ህገመንግሥት ጥሰት ፈራጅና አስፈራጅ ከሆኑ የዘረኛው ሥርዓት ተረፈ ምርቶች ጋር በመወገን – የሚገኝ አንዳች ለውጥ የለም! በዘረኝነት እርሻ ውስጥ፣ ዘረኝነት እያጨዱ፣ ዘረኝነትን ከምረው ከሚያመነዥኩ ሰብዓዊ እንስሳት የሚጠበቅ አንዳች የተሻለ ነገ የለም፡፡ አንዳች ፋይዳ ያለው ለውጥ የለም፡፡ ከዘረኛ ቆንጆ ምን ይመራርጡ – ነው፡፡
እውነተኛ ለውጥ ይመጣ ዘንድ – አንድ ቀን ዘረኝነቱ ተጠራቅሞ፣ በዝቶ፣ እንደ ተራራ ገዝፎ፣ የኢትዮጵያ ሀዝብ የማይወጣው ደረጃ ላይ ሲደረስ፣ የዘረኝነቱ ጠንቅ የሁሉንም ቤት ጫን አድርጎ ሲያንኳኳ፣ ዘረኛው ሥርዓት ሁሉንም በየፊናው ሲያንገፈግፍ፣ በላያችን ላይ እንደ ሸረሪት ድር የተዘረጋው የአፓርታይዱ የዘረኝነት አጥር ሀገሪቱንና ህዝቦቿን አላላውስ፣ አላንቀሳቅስ ብሎ ማፈናፈኛ ሲያሳጣ – አንድ ቀን ምናልባት – የኢትዮጵያ ህዝብ ምርር ብሎት – ‹‹ሆ!›› ብሎ ተነስቶ – ይሄን ወያኔ የገነባችውን እኩይ የአፓርታይድ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገርሠስ ይኖርበት ይሆናል! አንድ ቀን ላይ ይሄ እንደማይሆን ማረጋገጫ የለንም፡፡ እንደሚሆንም ማረጋገጫ የለንም፡፡
የማይሆነውን ማለምም መፅናኛ ነው፡፡ ማን ያውቃል? አንድ ቀን ላይ – ትናንትናና ዛሬ ላይ በዘረኝነታቸው ደርቀው የቀሩት የሥርዓቱ ጭፍሮች ሁሉ – አንድ ቀን እግዜሩ ድንገት ይቀርባቸውና – የሩሲያ የፔሬስትሮይካ አብዮተኞች እነ ጎርቫቼቭ ድንገት ተነስተው – ይሄ ኮሙኒዝም ለእኛ አያስፈልገንም ብለው እንደተነሱት ሁሉ – የእኛም ዘረኞች አንድ ቀን እግዜሩ የቀረባቸው ዕለት – አንድ የወደፊት ዘመን ላይ – ድንገት ተነስተው – ሁሉም ነገር ስህተት ነበር – ከዛሬ ጀምሮ የዘረኝነት ሥርዓቱ አብቅቷል – ብለው የሚያውጁበት ቀን ይመጣ ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል? – ‹‹ማን ያውቃል፣ የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ፣ ማን ያውቃል?›› እንዳለው መንግሥቱ ለማ፡፡ ማን ያውቃል? ምናልባት አንድ ቀን – የፋሺስቶቹን አዕምሮ እግዜሩ ተጠግቶት – የክፉ ሥራቸውን መጨረሻ ወለል አድርጎ እንዲያሣያቸውና ከተቆጣጠራቸው ክፉ የዘረኝነት አጋንንት ነፃ እንዲያወጣቸው፣ እና ሃሳባቸውን በገዛ ፍቃዳቸው እንዲቀይሩልን – በርትተን መፀለይ ነው!
የመጨረሻው አማራጫችን – ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገን ትተን – እጃችንን አጣጥፈን – ወደ ሠማያታችን እያንጋጠጥን – የሚሆነውን እየታዘብን – ሀገሩ የሆነውን እየሆንን መቀጠል ነው፡፡ መቀጠል እስከቻልን ድረስ መቀጠል፡፡ ካልሆነም ሌላው የሆነው ይኮናል – ከሌላው ሰው የተለየ ምናባቱ ሊመጣብን!? እና ሀገር በላያችን እስክትፈርስ – እንደ ሩዋንዳና ቡሩንዲያውያን እርስ በርሳችን እስክንባላ ድረስ – እንደ ሶቭየቶች፣ እንደ ዩጎዝላቪያኖች፣ እንደ ሱዳኖች፣ እንደ ሶማሊያዎች፣ እንደ ኮንጎዎች፣ እንደ ሊቢያዎች፣ እንደ ቢያፍራዎች፣ እንደ የመኖች፣ ወይም እንደ ሌሎች የዘረኝነት መቅሰፍት እንደጎበኛቸው ሀገራትና ህዝቦች – እኛንም በተራው የዘረኝነት መቅሰፍቱ ደህና አድርጎ እስኪመታንና እርስ በርስ ስኪያፋጀን ድረስ – እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ ማለት የተገደድንበትም ጊዜ ሊሆን ይችላል! ይህም አንደ ራሱን የቻለ ጊዜ መግፊያ መንገድ ነው፡፡ የማትታገለውን ባላጋራ – የሚሠራውን አሻግረህ ከማየት ሌላ – ምናልባት ምንም የምታደርገው ነገር የለህም ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለጊዜው እንዲህ የሆነ ይመስላል፡፡ እንዲህ ሆኖ የተቸገረ ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መርከቢቷ በዘረኝነት ማዕበሉ እየተላጋች ከወዲያ ወዲህ በምትዋዥቅበት በዚህ ሰዓት እጁን አጣጥፎ ቆሞ እየተመለከተ ነው፡፡ ፈጣሪ ይርዳው፡፡
ከነዚህ አማራጮች ሌላ ምንም አማራጭ የለንም! አንዱን ዘረኛ ወግኖ ሌላኛውን ዘረኛ ለመውጋት መሰለፍ – የመጨረሻው የነፈዞች አማራጭ የሚሆነው ለዚህ ነው! በዚህ መልኩ በተፃራሪ ዘረኛ ካምፖች መካከል የሚለኮስ ጦርነት ለሀገራችን የማይበጃት – ይልቁንም ይህን ዓይነቱን ሀገርን የሚያልፈሰፍስ አውዳሚ አጋጣሚን አሰፍስፈው ለሚጠባበቁ – የዘመኑ ጠባብ ዘረኞች መንገዳቸውን አልጋ በአልጋ የሚያደርግላቸው – ካልሆነ በቀር ለህዝባችን ጠብ የሚጠቅም ነገር የለውም፡፡ አሁን ላይ ዘረኞቹ ሀገርምድሩን ተቆጣጥረውታል፡፡ ‹‹መንግሥት›› የምንለው እና ‹‹ህግ›› እያልን የምንጠራቸው የተከበሩ ነገሮች ሁሉ በዘረኞቹ እጅ ውስጥ የገቡ የዘረኞቹ መማቻና መጫወቻዎች ከሆኑ እጅግ ብዙ ሰነባበቱ፡፡ ህጋዊ ነኝ የሚለውም፣ ህገወጥ የተባለውም – ሁሉም ዘረኛ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ በዘረኞች መካከል የሚካሄድ ጦርነት በፍፁም ለኢትዮጵያ መፍትሄ አይሆንም የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
አንድ የማይታበል እውነት ግን አለ፡፡ በዓለም ላይ ዘረኝነት በሰዎች ምግባርና ልብ ውስጥ በሽበሽ ሆኖ ሊገኝ ይችል ይሆናል እንጂ – በሀገር ደረጃ ግን – ዓይን ያወጣ በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት መሥርቶ እስከመጨረሻው ፀንቶ የቀረ ሥርዓት ግን በዓለም ላይ የለም! የእኛም ዘረኛ ሥርዓት አንድ ቀን ቢያንስ መንግሥታዊ ሥርዓት ሆኖ የመቀጠሉ ጉዳይ ማብቃቱ፣ መፈራረሱም፣ አይቀርም፡፡ እና በዚህ ከተማመንን አንድ ቀን በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር በላያችን መንግሥታዊ ሥርዓት ሆኖ የነገሠብንን ዘረኝነት የሚያከትም ነገር መከሰቱ እንደማይቀር ሳይታለም የተፈታ ነው! ወይ አንድ ቀን ዘረኞቹ ነገርዓለሙን ከሸበበባቸው አዚም ድንገት የሚነቁበት አንድ ወሣኝ የለውጥ ቀን ይመጣል፡፡ አሊያ ደሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘረኝነትን ለማጥፋት ‹‹ሆ!›› ብሎ የሚነሳበት አንድ የፍፃሜው ጦርነት ቀን ይመጣል፡፡ አሊያ ግን ዘረኝነት ልክ በትላልቅ የዓለማችን ሜትሮፖሊታን ከተማዎች ውስጥ እንደሟሟው – በእኛም ሀገር አንድ ቀን ዘረኝነት በሂደት በራሱ ጊዜ እንደ ጨው ሟሙቶ ከስሞ የምናገኝበት ጊዜ መምጣቱ የማይቀር ይሆናል፡፡
በአሁን ወቅት እኮ – የዘረኛው ሥርዓት ጭፍሮች – በመጨረሻ እንጥፍጣፊ ኃይላቸው እየታገሉ ያሉት – ከዚህ የማይቀር የሜትሮፖሊታን ሲቲ የዝግመተ ለውጥ ሂደት ጋር ነው፡፡ አዲስ አበባን የመሰለች የብዙ ሚሊየን ሰዎች መግቢያ መውጫ እና ማደሪያ የሆነች አፍሪካዊት ከተማ – በአንድ ወይም በሌላ ዘር እና በዘረኝነት አፓርታይዳዊ ፖሊሲው አንጻር ለመገንባት የሚደረገው ግብግብ – የቱንም ያህል ሥርዓቱ ቢሟሟትለት እውን ሆኖ የማይሰምረውም ለዚህ ነው! ቢያንስ በአዲስ አበባ ላይ የዘረኝነት ሥርዓቱ ዘረኝነቱን ከሚያራምድበት ቤተመንግሥት አንድ ጋት እንኳ ሳይርቅ የዘረኝነት ሥርዓቱን ክሽፈት በሂደት የሚያይባት ወሳኝ የለውጥ ማስፈንጠሪያ ሜዳ እንደምትሆን – አንዳችም ጥርጥር የለውም፡፡ እየሆነችም ነው፡፡ እና ዘረኞቹ ወደዱም ጠሉ – ይዘገይ ይሆናል እንጂ – ጊዜ በልቶም – ዘረኝነቱ በጊዜ ሂደት መክሰሙ አይቀርም፡፡ አንድ ቀን – ይሄ የማይቀር የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡
እስከዚያው – በዘረኞች መሐል ለሚነሳ ጦርነትና የሥልጣን ግብግብ ግን – እጃችን የለበትም፣ ልባችን የለበትም፣ ትብብራችን የለበትም! ዘረኛ ገዢዎቻችን – ጊዜያችሁ እስኪያልቅ – ሀገሩን ህዝቡን እንደፍጥርጥራችሁ ተጫወቱበት! ተጫወቱብን! ያሻችሁን ሁኑ! ስትሻሩ እንዳይቆጫችሁ – ሹመታችሁን ብሉበት! ያገኘውን አመንዥኮ፣ ቆሻሻውን በህዝብ ላይ ተፀዳድቶ፣ ጊዜውን ጠብቆ ከመሞት ሌላ ከዘረኞች መንጋ ምን የተለየ ነገር ይጠበቃል? ምንም አይጠበቅም፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ አንድ ቀን ግን የደሃው አምላክ ቅጣቱን እስኪሰጣችሁ ድረስ – ዕድሜውን ይስጣችሁ! እያልን እንፀልይላችኋለን፡፡ ዕድሜ መስታወት – አቆይቷችሁ – የሚሆነውን እንዲያሳያችሁ ጥልቅ ምኞታችን ነው፡፡ ብትኖሩም ክስመታችሁን አታመልጡትም፡፡ የሚገርመው ብትሞቱም ክስመታችሁን አለማምለታችሁ ነው፡፡
‹‹ከሞታችን ወዲያ፣ እፊታችን ያለው
ከዘር በላይ ያለ፣ አንድ መንግሥት ነው!››
    (- ኤሚሊ ዲኪንሰን)
ፈጣሪ ከተጣባን የዘረኝነት መቅሰፍት ጨርሶ ይማረን!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic