>
5:28 pm - Wednesday October 9, 8599

"በወልቃይት፣ ጠገዴ እና ራያ አካባቢ እየደረሰ ነው የተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል...!!!" የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ 

“በወልቃይት፣ ጠገዴ እና ራያ አካባቢ እየደረሰ ነው የተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል…!!!”

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ 
* ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል

በወልቃይት አካባቢ እየደረሰ ነው የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከወልቃይት ጠገዴ አስመላሽ ኮሚቴ በአካባቢው የተለያየ አይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰ መሆኑን በመግለጽ እንዲጣራልን በሚል ለኮሚሽኑ ጥቆማ ማድረሳቸውን የሰብዓዊ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በራያ አካባቢ እየደረሰ ነው የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተም ራያ ራዩማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በአካባቢው ተከስቷል በሚል ያወጣውን የአቋም መግለጫ ለኮሚሽኑ እንደላከ ኮሚሽነሩ አክለው ገልጸዋል።
ዶ/ር ዳንኤል እንደሚሉት በአካባቢዎቹ እየተከሰቱ ነው የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ኮሚሽኑ በመታዘቡ ትኩረት እንደሰጠውና ወደፊት አስፈላጊውን ማጣራት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። በተጠቀሱት አካባቢዎች እየደረሰ ነው የተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኮሚሽኑ እንደሚያሳስበው ኮሚሽነሩ ገልጽዋል።
ኮሚሽኑ በአካባቢው ተከስተዋል የተባሉትን ማንነትን መሰረት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለማጣት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ጉዳዩ ስፋት ያለው የኖረ የማንነት ጥያቄ ስለሆነ ዘላቂ መፍትሔ ያሻዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል። በተለያዩ ቦታዎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው አሳሳቢ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም ከማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች በመንግስት በኩል ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚገቡ ቢሆንም በዋናነት በአገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ግድያ፣ አፈናና እስር ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተከሰቱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የማጣራትና የመመርምር አቅም ጋር የማይመጣጠንበት ደረጃ ላይ መድረሱን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
 በመሆኑም ኮሚሽኑ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሙሉ በሙሉ የማጣራትና የመከታተል አቅም እንደሌለው ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ያለው አቅምና የአገሪቱ ችግር ስለማይመጣጠን ከኮሚሽኑ አቅም በመዝለሉ በውስን አቅም በየቦታው የተከሰቱ ችግሮችን ለማጣራት እንቅፋት እንደሆነበት ከዚህ ቀደምም መገለጹ ይታወሳል። ነገር ግን እስካሁንም ድረስ ችግሩ እንዳለ መሆኑ አዲስ ማለዳ ከኮሚሽኑ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
በኢትዮጽያ በተለያዩ ጊዜ እና ስፍራዎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ክስተት እየተበራከት በሚሄዱ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነበት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
 በመሆኑም ኮሚሽኑ የማንነት ጉዳይ ላይ መሰረት ያደረጉ ሰፊ አገራዊ ጥናት ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ዶ/ር ዳንኤል ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። ጥናቱ የማንነት ጥያቄዎችን ለመመለስና በአገሪቱ ያለውን የሰብዊ መብት ጥያቄ በተገቢው ለመመለስ በሚሰራው ስራ ላይ ግብዓት እንዲሆን ነው ተብሏል።
ጥናቱና ለማካሄድ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እንደሚሰሩ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ የጥናቱ ጭብጭ በዋናነት ከሰብዓዊ መብት አንደምታ ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ተመላክቷል።
ምንጭ :- አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
Filed in: Amharic