>

የአማራ ሕዝብ በልዩ ሁኔታ ስለመበደሉ በአሥራት ጋዜጠኞች ላይ እየተፈፀመ ያለው በደል ጉልህ ምስክር ነው...!!! (የአሥራት ሚድያ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ)

የአማራ ሕዝብ በልዩ ሁኔታ ስለመበደሉ በአሥራት ጋዜጠኞች ላይ እየተፈፀመ ያለው በደል ጉልህ ምስክር ነው…!!!

(የአሥራት ሚድያ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ)

* …. ለአብነት ያህል ከሀጫሉ ግድያ ማግስት የወቅቱ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የነበሩት ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት አሥራት ከሀጫሉ ግድያ በኋላ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ፕሮግራም አስተላልፏል ብለው ወንጅለውታል። ይሁንና አሥራት ሚዲያ ከሀጫሉ ግድያ ቀደም ብሎ ሰኔ 17/2012 ዓ/ም ስርጭት ማቆሙ ይታወቃል….!
 
የአማራ ሕዝብ ለዘመናት በሀሰት ትርክት ሲጠቃ ኖሯል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተፈፀሙ ታሪኮች በልብ ወለድ ተዘጋጅተው ላልተፈፀመ ወንጀል የአማራ ሕዝብ በቀል ሲፈፀምበት ኖሯል። አሥራት ሚዲያ ይህን የተሳሳተ ትርክት ለማረምና በአማራ ሕዝብ የሚፈፀመውን ዘርፈ ብዙ ጥቃት በማጋለጥ ለአማራ ሕዝብ ድምፅ ለመሆን የተመሰረተ  የሕዝብ ሚዲያ ነው። ይሁንና የአማራን ሕዝብ በደል በማሳወቅ፣ የተሳሳቱ ትርክቶችን በማስተካከል በአማራ ላይ ሲፈፀም ኢትዮጵያን እያፈረሰ ያለውን መርገምት ለማስተካከል የተቋቋመው ሚዲያም የአማራ ሕዝብ የሀሰት ውንጀላ ሰለባ ከመሆን አልዳነም።
አሥራት ሚዲያ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል በመረጃ አስደግፎ ለሕዝብ ከማሳወቅ፣ ሕዝብን ከማስተማርና ከማንቃት ያለፈ  አንድም ቀን ይህ ነው የሚባል ስህተት አልፈፀምም። ይሁንና ብአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሱትን በደሎች በማጋለጡ፣ ሕዝብን በማስተማሩ ጥርስ ተነክሶበት ቆይቷል።  ለአብነት ያህል ከሀጫሉ ግድያ ማግስት የወቅቱ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የነበሩት ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት አሥራት ከሀጫሉ ግድያ በኋላ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ፕሮግራም አስተላልፏል ብለው ወንጅለውታል። ይሁንና አሥራት ሚዲያ ከሀጫሉ ግድያ ቀደም ብሎ ሰኔ 17/2012 ዓ/ም ስርጭት ማቆሙ ይታወቃል።  ይህ የሀሰት ውንጀላ ከምንም የመጣ አልነበረም። በሌላ ወንጀል የማይገኘውን የአማራን ድምፅ ሰበብ ፈልጎ ለማጥቃት የተደረገ ስለመሆኑ ግልፅ ነው።
አሥራት ሚዲያ ከሀጫሉ ግድያ በኋላ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ መልዕክቶችን አሰራጭቷል ብለው ባልነበረበት የወነጀሉ የመንግስት ኃላፊዎች  ሚዲያውን በመውቀስ አላበቁም። ሀምሌ 29/2012 ዓ/ም አራት የአሥራት ጋዜኞች (በላይ ማናዬ፣ ሙሉጌታ አንበርብር፣ ምስጋናው ከፈለኝና ዮናታን ሙሉጌታ) እንዲታሰሩ ተደርጓል። ከእነዚህ መካከል  ዮናታን ሙሉጌታ ከአሥራት የለቀቀው በሕዳር ወር 2012 ዓ/ም በመሆኑ ታሳሪዎቹን ከአርቲስት ሀጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ ለመክሰስ ምቹ አልነበረም። በመሆኑም አንደኛው ታሳሪ ከአሥራት ወደለቀቀበት ኅዳር ወር በመመለስ  ከኅዳር ወር 2012  ዓ/ም  እስከ ሰኔ 2012   ዓ/ም በኦሮሚያ ክልል አመፅ በማስነሳት በሚል ጠርጥሬያቸዋለሁ ተብለው ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ቆይተዋል። በመሰረቱ አሥራት አመፅ የሚያስነሱ ፕሮግራምና ዜናዎችን የሰራበት ጊዜ የለም። በተለይም አሥራት በሰራው ፕሮግራምና ዜና ኦሮሚያ ውስጥ አመፅ ተቀሰቀሰ ብሎ ሰራተኞቹን ማንገላታት ለማጥቃት ሰበብ ከመፈለግ ውጭ ሌላ ምክንያት ሊሰጠው አይችልም። ከምንም በላይ አማራዎች ሊያምፁ ቀርቶ  በማንነታቸው ሰለባ በሆኑበት ክልል ውስጥ የአማራ ድምፅ የሆነ ሚዲያ አመፅ አስነስቷል ማለት በሚዲያው ላይ  ብቻ የተደረገ ጥቃት ተደርጎ ሊወሰድ አይቻልም።
የአሥራት ጋዜጠኞች ኦሮሚያ ውስጥ አመፅና  ብጥብጥ አስነስተዋል ብሎ መዝገብ ያስከፈተባቸው ፖሊስ በተደጋጋሚ ቀጠሮ መረጃ ማቅረብ ሲያቅተው ጳጉሜ 2/2012 ዓ/ም የአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲወጡ ወስኗል።  በሕጉ መሰረት  ከእስር መውጣት ሲገባቸው ፍርድ ቤት የጠየቀውን ዋስትና ከከፈሉ  በኋላ በሕገወጥ መንገድ በእስር ቆይተው ይግባኝ ተጠይቆባቸዋል። ጳጉሜ 3/2012 ዓ/ም የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የይግባኝ ወንጀል ችሎት፤ የፖሊስን ይግባኝ ውድቅ አድርጎ እንዲፈቱ በወሰነው መሰረት በኅዳር ወር ከአሥራት የለቀቀው ዮናታን ሙሉጌታ ሲፈታ ቀሪዎቹ በላይ ማናዬ፣ ሙሉጌታ አንበርብርና ምስጋናው ከፈለኝ ከእስር ቤቱ እንደወጡ ሲቪል ለባሽ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሰዎች ትፈለጋላችሁ ተብለው እንደገና በሕገወጥ መንገድ ታስረዋል። በሕገወጥ መንገድ በእስር የቆዩት የአሥራት ጋዜጠኞች ጳጉሜ 4 2012 ዓ/ም “ከአርቲስት ሀጫሉ ግድያ በኋላ ሁከትና ብጥብጥ አስነስታችኋል” በሚል ሌላ የክስ መዝገብ ተከፍቶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ። ይህ ውንጀላ አሥራት ሚዲያ በአየር ላይ ባልነበረበት ወቅትም በሀሰት የተፈፀመበት ሲሆን በጋዜጠኞች ላይም ሕግ ተጥሶ በሕገወጥ መንገድ ለተጨማሪ እስር እንዲዳረጉ ሆኗል።
ፖሊስ በመጀመርያ የአሥራት ጋዜጠኞች “የአማራ ሕዝብ በልዩ ሁኔታ ተበደለ” ብለው አመፅ  አስነስተዋል ሲል በእስር ላይ አቆይቷቸዋል። ምንም እንኳ ይህ ውንጀላ ሀሰት መሆኑን ራሱ ፖሊስ በማስረጃ ማረጋገጥ ተስኖት ፍርድ ቤት ከእስር እንዲፈቱ ከአንድም ሁለት ጊዜ የፈቀደላቸው ቢሆንም የአማራ ሕዝብ በልዩ ሁኔታ ስለመበደሉ ግን በአሥራት ሚዲያና በአሥራት ጋዜጠኞች ላይ በሀሰት እየተፈፀመ ያለው ወንጀላ፣ እስርና እንግልት ትክክለኛ ማስረጃ ነው።
የአሥራት ጋዜጠኞች የአማራ ሕዝብ ሲበደል መንግስት አይደርስለትም ብለው አመፅ አስነስተዋል ብሎ ጋዜጠኞቹን ሲያንገላታ የነበረው ፖሊስ ለውንጀላው መረጃ ማቅረብ ባይችልም የአሥራት ጋዜጠኞች በሕገወጥ መንገድ ሲታሰሩ፣ ሲንገላቱ  የዜጎችን መብትና ደኅንነት አስጠብቃለሁ የሚለው መንግሥት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር በአማራ ሕዝብ ላይ ለሚፈፀመው ከልክ ያለፈ በደል ጉልኅ ማሳያ ነው።
አሥራት ስርጭት ላይ ባልነበረበት ወቅት በሀሰት የወነጀሉ አካላት፤ በአሥራት ጋዜጠኞች ላይ እየፈፀሙ ያሉትን በደል ሕዝብ እየታዘበ ይገኛል። የአሥራት ሚደያ ቦርድ መንግስት በአሥራት ጋዜጠኞች ላይ የሚያደርገውን በደል እያወገዘ:_
1) በሀሰት አመፅ አስነስታችኋል ተብለው በተጠረጠሩበት ጉዳይ በዋስትና  እንዲወጡ በተወሰነው መሰረት የሕግ የበላይነት ተከብሮ እንዲፈቱ፣
2) በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት ከእስር ሲወጡ ጋዜጠኞቹን በሕገወጥ መንገድ አግተው ያሰሩ አካላት በጥፋታቸው እንዲጠየቁ፣
3) የአሥራት ጋዜጠኞች በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት መርማሪዎች ያልታሰሩና ሊያዙ የሚገባቸው የአሥራት ሰራተኞች እንዳሉ እንደገለፁ መረጃው የደረሰን ሲሆን ይህ የአሥራት ጋዜጠኞችን ማዋከብ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ እንዲሁም
4) ፍርድ ቤቶች እስካሁን ያደረጉትን እያደነቅን ፖሊስ የአሥራትን ጋዜጠኞች ጠረጠርኳቸው ያለበትና  ዋስትና የተሰጠበት “የሁከትና ብጥብጥ” ጉዳይ በመሆኑና በአንድ ጉዳይ ከአንድ ጊዜ በላይ ሊጠየቁና ሊሰቃዩ ስለማይገባ፤ በሕገወጥ አሠራር የታሰሩት የአሥራት ጋዜጠኞችን ጉዳይ በተመለከተ እየተጣሰ የሚገኘውን  ውሳኔውን እንዲያስከብር እንጠይቃለን።
የአሥራት ሚድያ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ
ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ/ም
Filed in: Amharic